“ጉባኤው” (ልብወለድ)

ጉባኤው

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

[በደራሲውመልካምፈቃድለአንድምታየቀረበ]

.

(በበዕውቀቱ ድምፅ ሲተረክ ለማዳመጥ)

መሳፍንት እየተፈራረቁ በነገሡበት ዘመን ንጉሥ አሊጋዝም የድርሻቸውን ገዙ። በዘመናቸውም ብዙ እኩይና ሠናይ ክስተቶች ታዩ። እኔ ትሑት ጸሐፌ ትእዛዛቸው ከሰማሁትና ከአየሁት መካከል የመረጥኩትን ተረክሁ።

በዚያን ዘመንም ሀገራችን በድርቅ ተመታች።

የሰማይ ግት ነጠፈ።

መሬት ፍሬ ነፈገች።

ሕይወት ያለ ፍሬ፣ ያለ ቅጠል ቆመች።

አልጋዎች ቃሬዛ ሆኑ።

ግርማዊ ጃንሆይም መፍትሔ ፍለጋ ሊቃውንትን በአዋጅ ጠርተው በየዕለቱ ጉባኤ ያደርጉ ጀመር። በዘመኑም ሰዎችን የሚያሰባስባቸው ጉባኤና ቀብር ሆነ።

ከዕለታት በአንዱ ቀን የተመረጡ ሊቃውንት የንጉሡን አዳራሽ ሞልተውት ነበር።

ግርማዊ ጃንሆይ የፀሐይ ሽራፊ በመሰለ ዙፋናቸው ላይ ተቀምጠው ተደምጦ በማይጠገብ ድምፃቸው ይናገሩ ጀመር።

“ወገኖቼ! ሊቃውንት! ጠቢባን!

“… እንደምታዩት በአገራችን በየጊዜው አስፈሪ መአት እየተላከብን ነው። የዚህ ምክንያት ምንድነው? ራብን እንዳይመለስ አድርገን ለማባረር በምን አኳኋን መሥራት አለብን? ይሄ የሕይወት የህልውና ጉዳይ ነው … እስካሁን አስራ ሁለት ጊዜ ተሰብስበናል … አስራ ሁለት ጊዜ ሊቃውንት! … ዛሬ ግን ጉዳዩ እልባት ማግኘት አለበት። ይሄን ጥያቄ ሳንመልስ ከዚህ አዳራሽ ንቅንቅ ማለት አንችልም። ሊቃውንት ናችሁ! … መላችሁን ወዲህ በሉ!”

ፀጥታ የእያንዳንዱን አንደበት ሸበበው።

“በሉዋ ሊቃውንት! … የምን መለጎም ነው?” ከማለታቸው ከፊት ከተኮለኮሉት አንዱ ተነሳ። ወገቡን ቆልምሞ እጅ ነስቶ ሲያበቃ “ጃንሆይ እኔ …” ብሎ ሊቀጥል ሲል ድምጡ በፍርሀት ደከመበት።

ጃንሆይ ለማበረታታት ራሳቸውን ሲወዘውዙለት “እህህ!” ብሎ ጉሮሮውን አፅድቶ ገባበት።

“እሺ እንግዲህ እኔ ነጋድራስ የትምጌታ ነው ስሜ … የእናቴና የእናቴ ዘመዶች መሸሻ ብለው ይጠሩኛል። ወላጅ አባቴ ዋልድባ ተመግባቱ በፊት የፈጻሜ መንግሥት ተክለ ጊዮርጊስ አማካሪ ነበር። የሱ ታናሽ ወንድም ደሞ …”

የሊቃውንቱ ዝምታ ወደ ጉርምርምታ ተለወጠ …

“እንግዲህ ስለ ራሴ ይህንን ታልሁ … ወደ ዋናው አሳቤ እገባለሁ። እንግዲህ ተዚህ ቀደም በእርስዎና በአባቶቻችን ፍቃድ ለንግድ በተለያዩ አገሮች ተመላልሻለሁ። ለመሆኑ የት የት ሄደሃል የሚለኝ ታለ የሄድሁባቸው ሀገሮች የሚከተሉት ናቸው። ታምስት ዓመት በፊት ሰማይን የሚታከኩ፣ ዓለምን የማረኩ ቢራሚዶች ባሉባት ግብጥ ነበርሁ። ተዚያም አስከትዬ የነውጠኛው እስክንድር አገር በሆነችው መቄዶንያ ከራርሜ ወደ ፋርስ ተሻገርሁ! … ተፋርስ ወደ ኑብያ ተኑብያም …”

“ማነህ ነጋድራስ?” አሉ ጃንሆይ ትዕግሥታቸው አልቆ …

“ነጋድራስ ነው ያልከኝ? አዎ ነጋድራስ … እኛ እዚህ ወርቅ ጊዜያችንን ቆጥበን የምንሰበሰበው ያንተን የዙረት ታሪክ ለማድመጥ አይደለም። እኛ ያስጨነቀን ጉዳይ ራብ ነው፤ በራብ ጉዳይ ላይ መላ ካለህ መላህን ወዲህ በል! … አለበለዚያ ላሁኑ ይቅር ብለንሃል። ወደ ጥግህ ተመለስ …”

“ጃ! … ጃንሆይ …” አለ ነጋድራስ የወረዛ ግንባሩን ባይበሉባው እየፈተገ …

“እንግዲህ መንገዴን ስቼ ንግግሬን እንደ ባልቴት አስረዝሜ ተሆነ በውነቱ ግሣፄ የሚገባኝ ግም ሰው ነኝ። በውነቱ እኒያን ትልልቅ ሀገሮች መጥቀሴ ለከንቱ ውዳሴ ብዬ አልነበረም። ዘላንነት እጣ ፈንታ እንጂ ክብር እንዳልሆነ አውቃለሁ … ይህን ስል ጉዳዩን ረስቼ ሳይሆን በእኝህ ሀገሮች በነበርኩበት ግዜ የቀሰምኩትን ጥበብ ለማካፈል አስቤ ነው …”

በጃንሆይ ፊት ላይ ወገግታ ታዬ።

“እንዲያ አትለኝም?!” አሉ በደስታ በተቃኘ ድምፅ …

“እንዲህ ያለውን ሊቅ ነው በመብራት ስንፈልግ የቆየን … በል እስቲ የምታውቀውን ንገረን! …”

“ጃንሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!”

እንደገና ታጥፎ እጅ ነሳ።

“እንግዲህ አስቀድሜ ወንዞቻችን ስለምን አገር አቋርጠው እንደሚነጉዱ እገልጣለሁ። ለጥቄ እንዴት አድርገን አናሳ ወንዞችን መገደብ እንደምንችል አብራራለሁ። ያንን አንድ ባንድ ታስረዳሁ በኋላ መስኖ በምን አኳኋን እንደምናበጅና …”

“ምን ሆናችኋል?” አሉ ጃንሆይ “መሪጌታ ስነ ኢየሱስ! … ምንድር ነው ነገሩ? ቅር ያለህ ትመስላለህ!”

በገፈጅ የሚያክል አዳፋ ጥምጣም አናታቸው ላይ የደፉት መሪጌታ ስነ ኢየሱስ ብድግ ብለው እጅ ነሱ። ከዚያም ጣዝማ ያበጀችው ሽንቁር በመሰለው አንድ ዓይናቸው ጃንሆይን ሽቅብ እየተመለከቱ፣

“እኔ እንኳን ቅር ያለኝ የነጋድራስ ነኝ ባዩ የቋንቋ አጠቃቀም ነው!” ከማለታቸው

“እንዴት?” ጃንሆይ ተቀበሏቸው።

“እንዴት ማለት ጥሩ ነው፤ ሊቁ አባታችን ጃንሆይ!” አሉ መሪጌታ

“ወንድሜ ነጋድራስ አውቆ በድፍረት ይሁን ሳያውቅ በስሕተት እንጃ የታፈረውን የተከበረውን ቋንቋችንን ሲዘነጣጥለው ባይ እንባዬ መጣ! ሆድ ባሰኝ! ቁጭት ልቤን መዘመዘው! … አላስችል አለኝ …” እንደ ማልቀስ ቃጣቸው።

“… በመዠመሪያ ጅረት ማለት ሲገባው አናሳ ወንዝ አለን። ዝም አልነው። እሱ ግን ይህንን ሳያርም ሌላ ገደፈ። ቀጥዬ ማለት ሲገባው ለጥቄ ብሎ ተናገረ። በዚህ መች አብቅቶ! መስኖ ለመጥለፍ እል ብሎ መስኖ ማበጀት ብሎ አረፈ። እንግዲህ ይህን ዝም ብሎ ማለፍ እንደምን ይቻላል?”

ግራ ቀኙን ባይናቸው ገመገሙት።

ዝምታውን “አበጀህ” በሚል ተረጐሙት።

“ጃንሆይ! … አሳምረው እንደሚያውቁት የህዝብ አንድነት መሠረት ቋንቋ ነው። የሰናዖር ሥልጣኔ የፈራረሰችው በቋንቋ ቅየጣ ምህኛት ነው! የቋንቋ ቅየጣስ ሰዋስውን ባልባሌ ሁኔታ ከመጠቀም የሚመጣ አይደለምን? … መቸም የቋንቋ ሊቅ ለመሆን የግድ ሰዋስው ጥበብ መማር አለብን እያልኩ አይደለም። አስተዋይ አድማጭ ለሆነ ቢያንስ የጃንሆይን ንግግር ለሁለት ሰዓት ያህል ማድመጥ የተባ አንደበተኛ አያረግም? … አያረግም ወይ ሊቃውንት? …”

“እስቲ ይሁንልህ” በሚል ምልክት ሊቃውንት ራሳቸውን ወዘወዙ።

“ስለዚህ እንደኔ እንደኔ የቋንቋ ችግር አለብን። ይሄንን የቋንቋ ችግር ታልፈታን እንደ ሰብአ ባቢሎን እንደምንፈታ ጥርጥር የለውም! …”

“እህ! … እህ! …… እህ! …….”

አሉና ጃንሆይ ራሳቸውን ናጡ።

“ማነህ? … ነጋድራስ … ነጋድራስ ነኝ ነው ያልከኝ? … አዎ ነጋድራስ ተቀመጥ እስቲ!”

(ለካ ነጋድራስ ያንን ሁሉ በትር የተቀበለው በቁሙ ነው)

“እስቲ መሪጌታም ይቀመጡ … ለነገሩ እኔም በቋንቋችን ውስጥ ያለውን ጉድለት ጉዳይ ሲከነክነኝ ነው የቆየ! … መሪጌታ እንዳሉት የቋንቋ ችግር ጊዜ የሚሰጠው አይደለም። የቋንቋችን ችግር ተየት የመነጨ ነው? በምንስ አኳኋን ሊታረም ይችላል? ሊቃውንት በሞሉባት አገር ይሄንን ሳንመልስ ተዚህ አዳራሽ ብንወጣ የሚያፍረው መከረኛው ህዝባችን ነው … በሉዋ ሊቃውንት! መሪጌታ ተርስዎ ልጀምር መሰል?!”

“ጥሩ እንግዲህ ……..” አሉ መሪጌታ

“በርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ ባውጠነጥን ብዙ በተናገርሁ! … ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የቋንቋን ችግር የምንፈታው እንደ ተክለ አልፋ ያሉትን የሰዋስው መምህራን ከፍልሰት ስንታደግ ነው ባይ ነኝ …”

“ተክለ አልፋ ምን ሆነ?”

“አዬ ጃንሆይ ተሚያስተምርበት ደብር አሳደዱትኮ!”

“ተክለ አልፋን?”

“እንዴት ያለውን ሊቅ ጃንሆይ!”

“እኮ ለምን?!”

“ምን አውቃለሁ ጃንሆይ ምህኛቱማ ዝምታ ነው!”

“ነው?” አሉ ጃንሆይ ነገር በገባው ሰው ቋንቋ …

“ለነገሩስ የሊቃውንትን የፍልሰት ወሬ ታንድም ሁለት ጊዜ መስማቴን እኔም አልሸሽግም። ጉዳዩ እንዲህ ስር የሰደደ መሆኑ ግን አሁን ነው የተገለጠልኝ። መቼም የጅሎች ሁሉ በኩር ታልሆን በቀር በነግ እናቆየዋለን ብዬ አላስብም። ሊቃውንቶቻችን የሚፈልሱበት ምህኛት ምንድነው …? ማነው የሚያፈልሳቸው? … ነገሩን ተስር መሠረቱ ለማድረቅ ምን ማድረግ ይገባናል …? መልሱልኝ ሊቃውንት! …”

“ጃንሆይ” አሉ መሪጌታ …

“በኛ አገር ጠቢብ መሆን አብሪ ትል መሆን ማለት ነው። አብሪ ትል ከሌሎች ትሎች የሚለየው ገላው እንደ ፍም ማብራቱ ነው። ታዲያ ብላቴኖች በጨለማ ሲያበራ ሲያዩት በገዛ ብርሃኑ ተመርተው ይመጡና አንስተው ይጨፈልቁታል። ለጠላቶቹ መንገድ ከማሳየት አልፎ የገዛ ብርሃኑ ለምንም አይጠቅመውም።”

“ተክለ አልፋ የተባረረው ንዋየ ቅዱሳት መዝብሮ ነው! … ጃንሆይ!”

አለ አንድ ከግራ ጥግ ተወርውሮ የመጣ ሻካራ ድምፅ

“ምን?”

ጃንሆይ ገነፈሉ።

“ጃንሆይ በደካማው ሥጋዬና በጠልጣላዋ ነፍሴ እምላለሁ። ተክለ አልፋ የሳር ውስጥ እባብ ነው። የሥነ ፍጥረትን መጽሐፍ ሸሽጎ ሊወጣ ሲል እኮ ነው ለቀም ያረግነው!!”

“እኮ ተክለ አልፋ?!”

“ማን ያምናል ጃንሆይ! …”

“ተነአህያው ሞተልሽ!” አሉ ጃንሆይ ተስፋ መቁረጥ በቃኘው ድምፅ …

“አልቀናል በሉኛ! እንግዲህ ንዋየ ቅዱሳቱ ተዘርፈው ከወጡ ምን ቀረን? እኛስ አለን ወይ? … ህልውናችንንኮ ነው የመዘበሩት … እኛስ ተንግዲህ ማን ተብለን ልንጠራ ነው? በምን በኩል ኢትዮጵያውያን ነን እንበል? … ጎበዝ እዚህ ላይማ ዋዛ የለም …!

“ተቀመጥ መሪጌታ … በሉ ሊቃውንት ይህን ጉዳይ መልሱልኝ። ይህንን ሳንፈታ ብንወጣ ያባቶቻችን ዐፅም እሾህ ሆኖ ይወጋናል! … በሉ እንጂ ምሁራን!”

እዚህ ላይ እኩሌቶች ሊቃውንት አዛጉ።

አንጎላጁ።

ይኼኔ ነው ከኋላ ከተቀመጡት አረጋውያን ሊቃውንት መካከል አንደኛው የተነሱ።

እኒህ ሊቅ እድሜም ጥበብም የጠገቡ እንደሆነ ስለተመሰከረላቸው ሲነሱ ዓይን ሁሉ ወደሳቸው መጣ።

“ግርማዊነትዎ ፍቃድዎ ከሆነ ብናገር …”

“ቀጥሉ” አሉ ጃንሆይ።

“የተከበሩት ጃንሆይ! …” አሉ የአቡየ ገብሬን የመሰለ ረዥም ፂማቸውን እየላጉ።

“አያሌ ሀያላን በሀገሬ ላይ ተፈራርቀው ሲነግሱ አይቻለሁ። በዚች እፍኝ በማትሞላ እድሜዬ የብዙዎች አማካሪ የመሆን እድልም አጋጥሞኛል! እኔ እንደታዘብኩት ከድርቅና ከቸነፈር በላይ ይችን አገር ያደቀቃት ጉባኤ ነው። ጉባኤ ምን አተረፈልን? ተሰብስበን እንወጥናለን። ወጥተን እንበተናለን። ስለዚህ ከሁሉ አስቀድሞ የዚህ ቢታይ ደግ ነው ባይ ነኝ …”

ጃንሆይ ለጊዜው ምንም አላሉም። አርምሟቸው ግን ጊዜ አልፈጀም።

“አዬ ጉድ …” አሉ በመዳፋቸው ጭናቸውን እየጠበጠቡ …

“እንዲህ ልክ ልካችንን ንገሩን እንጂ … ለነገሩስ አገሩ በጠቢብ እንደማይታማ አውቃለሁ … ግና በእድሜ ያልተፈተነ ጥበብ የገደል ማሚቶ ነው! ለመናገርማ ብዙዎች ሲናገሩ ቆይተው የለምን?

“እንዲህ የንስር ዓይን የታደሉ ብስል ሊቅ ግን ተሰውሮብን የነበረውን ጥበብ ገላለጡት! ልክ ነው! ትልቁ የኛ ራስ ምታት ጉባኤ ነው። ጉባኤያችን ለምን ፍሬ አጣ? እንዴት ፍሬ ይኑረው? ይህንን ነው መነጋገር! ይህንን ተነጋግረን ታልፈታን ከዚህ ጉባኤ ንቅንቅ አንልም! ነቃ በሉ እንጂ ሊቃውንት!”

ተፈጸመ ዝንቱ መጽሐፍ።

ጉባኤው ግን ቀጠለ።

.

.

በዕውቀቱ ሥዩም

.

[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

[ምንጭ] – “በራሪቅጠሎች” (፲፱፻፺፮)፤ ገጽ 65-72።

6 thoughts on ““ጉባኤው” (ልብወለድ)

  1. ”GUBAEAW”

    A shinning example of a twilight of hope still gliming in the murky waters of cultural confusion and ephemeral melange, kitsch art of the multi-ethnic land of today. It is indeed endearing to experience such a beauty of literary gem coming out of a unique quill of this generation, laced with a historical theme..

    The very subject of ‘language and Babylonian confusion’ and the existential inertia of ‘meetings’ and ‘conferences’, and the permanent issue of hunger; being treated with a time-honoured golden Amharic prose, and with an integrated style too.

    We hope your ”Goobaea” of cultural dialogue will continue to help solve our phenomenal ‘Rehab’ { hunger } problems as well as create a broader consensus for a life enhancing more original artistic products.

    Thank you and Blessings !!.Bewqetu Seyoum !!.

    Jamoki.

    London
    UK

    Like

Leave a Reply to shumet asmare Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s