“ከአድማስ ባሻገር” (ልብወለድ)

“ከአድማስ ባሻገር”

በአሉ ግርማ

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ] 

.

ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል። ከዚያ ዝምታ በዝምታ የሚመነጨው የሙዚቃ ቃና መጨረሻ የለውም። ነፍስን በሀሴት ሊያወራጭ አእምሮን ኮርኩሮ ሀሳብን በስልት ሊያስደንስ ይችላል።

አበራ ወርቁ፣ በዚያ መጨረሻ በሌለው ዝምታ ተውጦ ሙሉ የሌሊት ልብሱን ለብሶ እንደልማዱ የጣት ጥፍሩን በጥርሱ እየከረከመ ወዲህና ወዲያ በመንጐራደድ ለገላው ያሞቀው ውሀ ወደ ገንዳው እስኪወርድለት ድረስ የወትሮው ባልሆነ ትእግስት ይጠባበቃል።

ቧንቧው እንፋሎት ብቻ ስለሚተፋ ወደገንዳው የሚወርደው ውሀ ዝናብ ዘንቦ ካባራ በኋላ ከሰንበሌጥ ላይ ኮለል ኮለል እያለ እንደሚወርድ ጠፈጠፍ ስልት እየጠበቀ አንድ ባንድ ይንጠባጠባል።

“ትኩስ የህይወት ጠብታ፣ ትኩስ፣ ወፍራም የህይወት ጠብታ” የሚል ሀሳብ ላንዳፍታ አእምሮው ውስጥ እንደመብረቅ ብልጭ ብሎ መልሶ ድርግም አለ። የአበራ አእምሮ ካንድ ሀሳብ ወደሌላ ሀሳብ ስለሚጋልብ አንድ ነገር በተለይ ወስዶ እስከ መጨረሻው ድረስ ሊያስብበት አይችልም። ለዚህ ነበር ባለቅኔ፣ ወይም ደራሲ፣ ወይም ሰአሊ የመሆን ተስፋውን ውስጡ ቀብሮ ያስቀረው። ነፍሱ ግን ራሷን ባንድ ነገር ለመግለጥ ዘለአለም እንደዋተተች፣ እንደቃተተች ትኖራለች። አእምሮው ወዲያና ወዲህ እንደሚባክን ስለሚያውቅ አዘውትሮ፣ “ሀሳብ መጨረሻ የለውም፤ ቁም ነገሩ መኖር ነው፤ የኑሮን ጣእም ማወቅ። ሀሳብ የፈጠረው ግብ ካልደረሰ ውጤቱ ያው ነው፤ ምሬትና ብስጭት። አዎን፣ ሌላ ምናለና!” ይላል።

አንድ ትልቅ ወፍራም ጥቁር ዝንብ ከየት መጣ ሳይባል እንግዳ ቤት ገብቶ ጥዝዝ – እያለ አንዴ ከኮርኒሱ ጋር፣ አብዛኛውን ጊዜ ከመስኮቱ መስተዋት ጋር፣ አንዳንዴ ደግሞ ከተንጠለጠሉት ባለአራት ጡት መብራቶች ጋር እየተጋጨ ክፍሉን ውጦት የነበረውን ከባድ ዝምታ ባንዳፍታ አደፈረሰው። የዝምታው ሙዚቃ ስልቱን አጣ። አበራ መንጐራደዱን ትቶ ዝንቡን ለመግደል ይሯሯጥ ጀመር። የጧት ካቦርቱን አውልቆ፣ ዝንቡ መስኮትና ኮርኒሱ ላይ ሲያርፍ ለመግደል አንድ ሁለት ጊዜ ከሞከረ በኋላ ጥዝዝ … እያለ ሂዶ መብራቱ ላይ በማረፉ የሚያደርገው ነገር ጠፍቶት ወደላይ አንጋጦ ለጥቂት ጊዜ ተመለከተውና ተስፋ እንደመቁረጥ ብሎ ራሱን ነቀነቀ። “አሀ!” አለና ሂዶ መስኮቱን ከፍቶ ይጠብቀው ጀመር። እሱም እንዳሰበው፣ ዝንቡም በበኩሉ ይጠብቅ የነበረውን መውጫ ቀዳዳ ያገኘ ይመስል ጥዝዝ … እያለ ሹልክ ብሎ ወጣ። ከውጭ የሚመጣው ሁካታ ተወርውሮ ጆሮውን መታው። የመኪና ጋጋታ፣ ጡሩምባ፣ የበጎች ጩኸትና የሰዎች ድምጽ ባንድነት ሲሰማ የአማኑኤል ሆስፒታል እብዶች ተሰብስበው ያቋቋሙት የሙዚቃ ጓድ ይመስል ጆሮ ይጠልዛል። ቶሎ መስኮቱን ዘጋ። “እኔ ግን መውጫ ቀዳዳ የለኝም!” አለ ዝንቡን አስታውሶ።

አበራ ለጊዜው የሚኖርበት ሰፈር በየበአላቱ ቀን የበግ ገበያ ሆኖ ይውላል። የሚኖረው በመስፍነ ሀረር መንገድ ከሾላው በላይ ተስፋዬ ቀጄላ ቤት ፊትለፊት ሲሆን፣ ይሄኛው ቤት በአምስት አመት ውስጥ ዘጠነኛ ቤቱ መሆኑ ነው። ከወንድሙ ምክር መሀል አበራ ልብ ውስጥ በመጠኑ የሚገባው የቤት መስራት ጉዳይ ነው። አበራ ወርቁ ቤት አጠገብ ወይም ፊትለፊት የሚባልበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? ጊዜው ሩቅ መስሎ ታየው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በኩራት አይን የቤቱን እቃ አንድ ባንድ ይመለከት ገባ። ውጭ የደመቀ የጸሀይ ብርሀን ቢኖርም የዝምታው አዘቅትና ጽላሎት በስውር መንገድ ተዋህደው የእንግዳ ቤቱን ብርሀን ደበብ አድርገውታል። በብርሀን አይን የሚያሞቀው የምንጣፉና የሶፋዎቹ ደማቅ ቀይ ቀለም አሁን የረጋ ደም መስሏል። ወርቅማ ሆነው በጥቁር ጥለት ያጌጡት የመስኮት መጋረጃዎች በብርሀን ያላቸውን ድምቀት አጥተው ፈዝዘዋል። ከውጭ ወደ ውስጥ ሲገቡ በስተቀኝ ካለው ግድግዳ ላይ የተሰቀለው በህብረ ቀለማት ስለቀለማት የተሰራው ስእል ብርሀን በማጣቱ የቅኔው ውበት ጠፍቷል። ትኩር ብሎ ተመለከተው። ፍዝዝ ብሎ በተመሰጠ አእምሮ አየው። ስእሉን ሳይሆን በስእሉ ውስጥ አልፎ የሚመለከተው ራሱን ነበር። በከንቱ ያሳለፈውን ህይወቱን ነበር – ያለፈውንና ወደፊትም ቢሆን ሊያገኘው የሚችለው መስሎት የማይታየውን ህይወት።

“ማን ነኝ? ምንስ ነኝ? እቃ። ለዚያውም ዋጋ የሌለው የበሰበሰ እቃ። እቃ ሆኜ እንድቀር ያደረገኝ ማንነው? እኔው ራሴ? ወይስ ያፈራኝ ህብረተሰብ? ወይስ አልፌው የመጣሁት የትምህርት አቋም? የምን የትምህርት አቋም! የአቋሙ አላማስ ምን ይሆን? ላይ ላዩን የሽምጥ ለማስጋለብ! ለምን አላማ! የትምህርት አላማው እያንዳንዱ ሰው ራሱን፣ ማንነቱን፣ የተፈጥሮ ችሎታውን እንዲያውቅ ማድረግ ነበር። እኔ ግን ማንነኝ?” እያለ፣ አይኖቹን ስእሉ ላይ ተክሎ ሲያስብ ፍዝዝ ብሎ ቀርቶ ነበር። ደንዝዞ ነበር።

በስተግራ ያለው ግድግዳ ጽላሎቱን አሳርፎበት ተንጣሎ የሚታየው ራዲዮግራም የሬሳ ሳጥን መስሏል። ሱዛን ሮስ የተባለችው የሰላም ጓድ ልኡካን ባልደረባ ህይወቱ ውስጥ በድንገት ለጥቂት ወራት ባትገባ ኖሮ አበራ ይህን ራዲዮግራም ለመግዛት ሀሳብ አልነበረውም። ነገር ግን፣ ከገዛ ላይቀር የሚገዛው ነገር ሁሉ ከባድና ዋጋ ያለው መሆን አለበት። “የምቆጥበው ለነገ የሚሆነኝ መሆኑን ወይም አለመሆኑን በርግጥ ስለማላውቅ ለምን ርካሽ ነገር እገዛለሁ? በርግጥ የማውቀው ዛሬን ብቻ ነው!” በማለት ሁልጊዜ ውድ እቃዎችን ይገዛል። ቤቱ ርካሽ እቃ አይገኝም።

ሱዛን ሮስ፣ “ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል፤ ምክንያቱም ለውድና ለከፍተኛ ነገሮች የሚጣጣሩ ወንዶች ሲያጋጥሙኝ እኔ ስለራሴ ያለኝ አስተያየት ውሀ እንዳገኘ ጽጌረዳ ይለመልማል” እያለች ደጋግማ ትነግረው ነበር። ሆኖም አልጋ ውስጥ ገብታ ያለሙዚቃ መንቀሳቀስ ፈጽሞ እንደማትችል አስታወሰ። ያለሙዚቃ ሰውነቷ አይፍታታም። ያለሙዚቃ ፍቅር ሰጥታ ፍቅር መውሰድ ጨርሶ አይሆንላትም። ከስንት ማግባባት በኋላ ቤቱ የወሰዳትን ወንድ አስቀድማ የምትሰጠው ምርጫ “ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ” የሚል ነበር። ታዲያ፣ አበራ ቤቱ ባመጣት ምሽት እንደዚያ ያለውን ምርጫ ስታቀርብለት አላመናትም። ውርጭ ውስጥ እንዳደረ ብረት የሚቀዘቅዘውን ጭኗን እየደባበሰ፣ ረጅም ጠጉሯ ስር ውሎ እንደዝሆን ጥርስ የነጣውን ማጅራቷን አንዴ በጥፍሩ እየቧጠጠ፣ አንዴ በጥርሱ እየነከሰ፣ ከንፈሯን አሁንም እየሳመ፣ ካሁን አሁን ተሸነፈችልኝ በማለት ልቡ ድው ድው፣ የደም ስሮቹ ትር ትር እያሉ ሲጠብቅ ከላዪዋ ላይ ገፍትራው ተነሳች።

የታጠፈውን ቀሚሷን እያስተካከለች፣ “ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ!” አለችው በቁጣ ቃል፣ ሲቃ በያዘው ድምጽ። ጉንጮቿ ላይ የነበረው ደም ቁልቁል ወረደ። ባንዳፍታ ጸሀይ ያልነካው በሽተኛ ይመስል ገረጣች። ከሩቅ ሲመለከቱት ነጭ፣ ከቅርብ ሲያዩት ሽሮ የሚመስለውን ጥርሷን ታፋጭ ጀመር።

“ስለግዜር ብለሽ አሁን ሙዚቃ ምን ያደርግልሻል? ልባችንን አንድ ብናደርገው እኛው ራሳችን ውብ ሙዚቃ ልንፈጥር እንችላለን – የተፈጥሮ ዳንኪራ እየረገጥን።”

“እውር ነህ፤ ለማየት አትችልም!” አለችው፤ በረጅሙ ተንፍሳ፣ ረጅም ጠጉሯን በሁለት እጆቿ ጭምድድ አድርጋ ይዛለች። እጆቿ ላይ ያሉት የደም ስሮች እንደሽምጥ አጥር ተገትረዋል። እና ከቀሉት ትናንሽ ውብ አይኖቿ እንባ እየፈለቀ የገረጡትን ጉንጮቿን ያርሰው ነበር።

“ምን!”

“ያለሙዚቃ አይሆንልኝም፤ ፍጹም አይሆንልኝም። ፍቅሬን ለወንድ አሳልፌ ከመስጠቴ በፊት ነፍሴ ወደ ሙዚቃ አለም መግባት አለባት። ከዚያ በኋላ ነጻነት ይሰማኛል፤ ውስጤ እንደጽጌረዳ እምቡጥ ይከፈታል፤ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዝግጁ እሆናለሁ።”

“እሱን ተይው! ፍቅርሽን ለመስጠት ነፍስሽን አስቀድመሽ ለሙዚቃ መለወጥ የምትፈልጊው ለጥቁሮች ብቻ ነው? ወይስ ከብጤዎችሽም ጋር እንዲሁ ነሽ?”

“አበራ፣ ለምን እንዲህ ትላለህ? ለቀለም ደንታ እንደሌለኝ እዚህ መምጣቴ ሊያረጋግጥልህ አይችልም?”

አበራ ጊዜ አላጠፋም። በሚቀጥለው ቀን ሂዶ ራዲዮግራም ገዛ። ከዚያ በኋላ ሱዛን የየሙዚቃውን ስልት በግለት፣ በስሜት እስከተለየችው ቀን ድረስ ትጠብቅ ነበር። ጸሀይ እንዳየች የጽጌረዳ እምቡጥ ወከክ፣ ትርክክ ትልለት ነበር።

ከኒውዮርክ፣ ከሱዛን ዘንድ ትናንት የደረሰው ካርድ “መልካም ፋሲካ፣ ስኳር ወለላዬ፣ የትም ብሆን አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል። የማዝነው አንተ ለጋብቻ ፍጹም ደንታ ስለሌለህና ብዙ ሙዚቃዎችን አብረን ሳናዳምጥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በመለያየታችን ነው። ሆኖም ቅሬታ የለኝም፤ እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች” የሚል ነበር። ራዲዮግራሙ ላይ አስቀምጦታል። “እሳቱ አልፎ ረመጥ፣ ረመጡ በርዶ አመድ የሆነ ትዝታ ነው” ሲል አሰበና የጧት ካቦርታውን ትከሻው ላይ ጣል አድርጐ ወደ መታጠቢያ ቤት ሄደ።

መታጠቢያ ቤቱን ያጥለቀለቀው እንፋሎት ያፍናል። የፊት መስተዋቱም፣ የመስኮት መስተዋቱም፣ ግድግዳውን ያለበሱት ነጭ ሸክላዎችም በሙሉ በላብ ደፍቀው ወርዝተዋል። ገንዳው ውስጥ የወረደው ውሀ ግን ይህን ያህል አይፋጅም። እንደፍላጐቱ ቢሆን ውሀው መፋጀት አለበት። አበራ ገላውን አሽቶ ለመታጠብ ስለሚሰንፍ ገንዳው ውስጥ በጀርባው ተንጋሎ መቀቀልን ይወዳል። በተለይ የጀርባው ነገር ጭንቁ ነው። ጀርባውን አሽቶ የሚታጠብበት ዘዴ ሊገባው አልቻለም። ለሌላ ሳይሆን ለዚህ ብቻ ሚስት ቢያገኝ አይጠላም።

የሌሊት ልብሱን አውልቆ እርቃነ ስጋውን አንድ ሁለት ጊዜ ከተንጐራደደ በኋላ በእንፋሎት ወርዝቶ የጧት ጭጋግ የመሰለውን የፊት መስተዋት በፎጣው ወለወለና ላንዳፍታ ፊቱን ተመለከተ። የቀይ ዳማ ቢሆንም ጸሀይ ያልመታው ፊቱ ገርጥቷል። የአበራ መልክ ቁንጅና ትላልቅ አይኖቹ ላይ ነው። ችርችም ያሉት ቅንድቦቹ ከኮፈናቸው ወጣ ወጣ ላሉት አይኖቹ ልዩ ውበት ይለግሷቸዋል። ሽፋሎቹ በምላጭ የተስተካከለ ይመስላሉ። በራው በመጠኑ ገለጥ ባያደርገው ኖሮ የግንባሩ ማጠር ጐልቶ በታየ ነበር። አፍንጫው ሰልከክ ብሎ ወርዶ ቀዳዳዎቹ በመጠኑ ሰፋ ሰፋ ያሉ ናቸው።

መቀስ አንስቶ ካፍንጫው ውስጥ እንደ ራዲዮ አንቴና ረዘም ብለው የወጡትን አንዳንድ ጠጉር ከርክሞ ሲያበቃ፣ አፉን በመክፈት ምላሱን ወደ ውስጥ ቀልሶ፣ ተዋጊ በሬ ይመስል ያንገት ስሮቹ እስኪያብጡ ድረስ ወደታች አቀርቅሮ፣ የታችኛዎቹ ጥርሶቹን ከውስጥ በኩል ሲጃራ ምን ያህል እንዳበለዛቸው ተመለከተ። የዛገ ቆርቆሮ መስለዋል። ሽንት እንዳሸተተ በግ ስስ ከንፈሮቹን ብልጥጥ አድርጐ ተመለከተ። ጥርሶቹ እንደወተት ባይነጡም ጸአዳ ናቸው።

ጢሙ አድጐ እንደሆን ለማየት በሁለት እጆቹ ጉንጮቹን ከታች ወደላይ መላልሶ ደባበሰ። ጢሙ አላደገም፤ ጉንጮቹ እንደህጻን ልጅ ገላ ለስልሰዋል። ብብቶቹ ውስጥና ጉያው መካከል ያለው ጠጉር ግን እንደባህታዊ ጠጉር አድጐ ተገማምዷል። የእግሩ ጥፍሮች አድገው ገሚሶቹ ተጣጥፈው ገሚሶቹ ደግሞ ተሰባብረዋል። ሱዛን የብብቱንና የጉያውን ጠጉርም ሆነ የእግር ጥፍሮቹን በየጊዜው ታስተካክልለት ነበር። እርሱ ለራሱ ሊያደርግ የማይችለውን ስታደርግለት ልዩ ደስታ ይሰማት ነበር።

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል። እንዳንተ ያሉ የእግር ጥፍራቸውን መቁረጥና የብብት ጠጉራቸውን መላጨት የማይችሉ ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል” የምትለው ሁሉ ትዝ አለውና፣ “ምንነው አሁን በተገኘሽ!” ብሎ በመመኘት ገንዳው ውስጥ ገብቶ በጀርባው እንደልማዱ ተንጋለለ።

የገንዳው ርዝመት ለአበራ መካከለኛ ቁመት ይህን ያህል አስቸጋሪ ሁኖ አልተገኘም። የስፖርትን ነገር እርግፍ አድርጐ የተወው ከሰባት አመት በፊት ካዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እንደወጣ ቢሆንም፣ የትከሻው ስፋት፣ የወገቡ ቅጥነትና የዳሌው ስልክክ ማለት ከስፖርት አለም ተለይቶ የኖረ ሰው አያስመስሉትም።

ሰውነቱን በስንፍና ለማሸት ሲሞክር ደረቱ ላይ በቀኝ በኩል ያለውን ለሀያ አምስት አመታት አብሮት የኖረውን ትልቅ ጠባሳ ነካ። ትርንጐ ትዝ አለችው። በነፍስ ትኖር ይሆን? ሞታ ይሆን? አያውቅም። የሚያውቀው አንድ ነገር ብቻ ነው።

እድሜዋ ከእርሱ እድሜ ገፋ ያለ ነበር። ፊቷ እንደውድቅት ጨለማ ጠቁሮ በወዝ የተንጨፈጨፈ ነበር። ጠጉሯ አንድ ባንድ የሚቆጠር፣ ፍርጥምጥም ያለች ጉጭማ ነበረች። እናቱ ወይዘሮ ባፈና ሞልቶት ቡና ለመጠጣት የግል ሲኒአቸውን ይዘው መንደር ሲሄዱ፣ ትርንጐ አበራን ትጠራውና መደብ ላይ ተጋድማ፣ “ና እንጫወት” ትለው ነበር።

“ምን አይነት ጨዋታ?”

“ና ምን ቸገረህ፣ እኔ አሳይሀለሁ”

ታጫውተዋለች። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከጨዋታው የሚያገኘው ደስታ እየጣመው ስለሄደ የእናቱን ከቤት መውጣት በናፍቆት ይጠባበቅ ነበር። እንዲያውም አንዳንዴ ትርንጐ ስራ ይዛ አላጫውትህም ስትለው ምርር እያለ ያለቅስ ነበር። በተለይ ከባይከዳኝ ጋራ ስትዳራ ያየ እንደሆነ ትንሿ ልቡ እርር፣ ድብን ትል ነበር። ቆየት ብለው እሱን አስወጥተው በር ሲዘጉበትማ አይጣል – ትርጉሙን ለይቶ የማያውቀው ስሜት በሰራ አካላቱ እየተሰራጨ ያብከነክነው ነበር … ያብሰለስለው ነበር።

ታዲያ አንድ ቀን ጧት እናቱ ቡና ለመጠጣት ከቤት እንደወጡ አበራና ትርንጐ መደብ ላይ ወጥተው ጨዋታቸውን ቀጠሉ። ወይዘሮ ባፈና አንዴ ከቤት ከወጡ በየቤቱ ቡና አክትመው ቤት እስኪመለሱ ድረስ ጥላው ቤት ስር ክትት እንደሚል ያውቃሉ። ነገር ግን፣ ያን ቀን ለካ ስኒአቸውን ረስተው ሂደው ኖሮ ወዲያውኑ ተመልሰው መጥተው የአጥረ ግቢውን በር “ትርንጐ፣ ትርንጐ” እያሉ ሲያንኳኩ፣ ትርንጐ ደንግጣ አንዴ ከላዪዋ ላይ ስትወረውረው ጊዜ ሽንኩርት ለመክተፍ ያስቀመጠችው ቢላዋ ላይ ሂዶ በደረቱ ወደቀ። ጠባሳው አብሮት ይኖራል – ማስታወሻ ሆኖ። አሁን የት ትሆን?

የትርንጐ ትዝታና የውሀው ሙቀት ሰውነቱን አዝናንቶት ኖሮ ፍትወት አደረበት። አበራ አንድ ስሜት ካደረበት ያንን ስሜት ሳያረካ ለመቆየት አይችልም … ከዚያ በኋላ ራሱን እየጠላ አይኖቹን ከድኖ ከህሊናው ጋር ሲሟገት የመታጠቢያው ቤት በር ተንኳኳ።

“ማንነው?” ሲል ጠየቀ፣ በጐረና ድምጽ። አድሮበት የነበረው ምትሀት ከመቅጽበት አለፈ። በፍትወት ስሜት አብጦ የነበረው ሰውነቱ ባንዳፍታ ሙሽሽ አለ።

“ከእቁባቶችህ አንዷ መስዬህ ደነገጥክ እንዴ?” ሲል ውጭ የቆመው ሰው መልሶ ጠየቀው። ከፍ ዝቅም ሳይል አንድ አቅጣጫ ይዞ የሚሄድ፣ ለአበራ ጆሮ እንግዳ ያልሆነ ወፍራም ድምጽ ነበር …

.

በአሉ ግርማ

(1962 ዓ.ም)

.

(በበአሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “ከአድማስ ባሻገር”። ፲፱፻፷፪። ገጽ 5-14።

 

 

6 thoughts on ““ከአድማስ ባሻገር” (ልብወለድ)

  1. እሚገርም ድርሰት። ለመጀመሪያ ጊዜ የጄነራል ዊንጌት ተማሪ እያለሁ ለአማርኛ ትምህርት በአስተማሪያችን ተመርጦ ካነበብኩት በሗላ ድርሰቱ አእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ቀረ። ድንቅ የአማርኛ ቋንቋ ቅንብር።

    Like

Leave a Reply to ሰመረ ተክሉ Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s