“ባንዶቹ” (ራስ ባንድ)

“ባንዶቹ”

(ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቡድኖች)

.

በሳይም ኦስማን

.

(ራስ ባንድ)

.

ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘ወርቃማ ዘመን’ ስናወራ እነዚያን መሳጭ ሙዚቃዎች ከዘፋኞች ኋላ ሆነው ስላቀነባበሩት ስለ ባንዶቹ ሳናነሳ አናልፍም።  በዚህ ጽሑፍ (እና በቀጣዮቹ ክፍሎች) የዋና ዋናዎቹን ዘመናዊ ባንዶች ታሪክ እና ባንዶቹን ስላቋቋሙት ሙዚቀኞች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ።

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በጣም ተወዳጅ የነበሩት የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ባንድ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኦርኬስትራ፣ እና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም የታህሳሱ ግርግር የኃይለሥላሴን መንግስት ለመገልበጥ የተሞከረበት ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሁለተኛ ምዕራፍን ከፈተ። በዚህም ወቅት የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ ለበርካታ ወራት ለመበተን በቃ። ብዙዎቹ አባላቶቹም ከኦኬስትራው እየለቀቁ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖችን (ፖሊስ፣ ምድር ጦር እና ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ቴያትር) መቀላቀል ጀመሩ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ኦኬስትራዎች ቀስ በቀስ ወደ ብዙ ትናንሽ ባንዶች እየተቀየሩ መጡ።

እነዚህም ትናንሽ ባንዶች መጀመሪያ ስራ የጀመሩት በተለያዩ የአዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ለዚህም ይመስላል የባንድ ስማቸውን በሆቴሎቹ ስም ያደረጉት … እንደ “ራስ ባንድ”፣ “ግዮን ባንድ”፣ “ሸበሌ ባንድ” የመሳሰሉት። ብዙም ሳይቆይ ሆቴሎቹ በጣም ታዋቂ መዝናኛ ቦታዎች እየሆኑ መጡ። በተለይም አርብ ማታ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶች ለመታደም የማይቀርበት ቦታ ሆኑ።

ras hotel 1950s
ራስ ሆቴል በ1950ዎቹ መባቻ።

.

ራስ ባንድ

.

የመጀመሪያው ራስ ባንድ የተቋቋመው በ1953 ዓ. ም ነበር። ባንዱንም የመሠረቱት ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክስፎን)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) በመሆን ነበር። በዛሬ ዘመን በሕይወት በመሀከላችን የሚገኙት ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ባህታ ገብረሕይወት እና ግርማ በየነ ናቸው።

Ras Band 3
ራስ ባንድ በራስ ሆቴል (1953-1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 1|

የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።

“አርብ ማታ በራስ ሆቴል የሚያስደስት ጊዜ ነበር” ይላል ባህታ ገብረሕይወት – Addis Live ራዲዮ ኢንተርቪው ላይ፣ ባህታ የሆቴሉን ድባብ ሲያስታውስ ሁሉም የባንዱ አባላት በሚገባ ዘንጠው መገኘት ነበረባቸው። እያንዳንዱም የሆቴል ተጠቃሚ አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት የሆቴሉ ህግ ነበር። በሚገባ አለባበሱ አልተስተካከለም ብለው ለሚያስቡት ተጠቃሚ ክራቫት ይሰጠው ነበር። ብቻቸውን የሚመጡ ተስተናጋጆች እምብዛም ናቸው። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ይደንስ ነበር።

Ras Band
ራስ ባንድ በአክሱም አዳራሽ መክፈቻ በዓል (ታኅሣስ 4፣ 1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ባህታ ገብረሕይወት (ድምፅ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 2|

ራስ ባንድ ውስጥ እያለ ነበር ባህታ ብዙዎቹን ስራዎቹን ያበረከተልን። እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን።

[“ካላጣሽው አካል”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

ባህታ የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፈው እራሱ ሲሆን፣ ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የሚጽፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር። ባህታም በዚህ ዘመን ከጻፋቸው ሙዚቃዎች ዜማ አንዱ እና ግርማ በየነን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታዋቂ ያደረገው ዘፈን ‘ይበቃኛል’ የተሰኘው ነበር።

AE690c Bahta

በዚሁ ራስ ባንድ በሚሰራበት ጊዜም ነበር ባህታ በትርፍ ጊዜው ተምሮ አካውንቲንግ ያጠናው። በ1964 ዓ.ም ከሙዚቃ ዓለም ሲርቅ ለግዮን ሆቴል እና ለፊልም ኮርፖሬሽን የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ባህታ እንደሚለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አካሄድ አላምር ብሎት ነበር ከሙዚቃ አለም የራቀው። በታህሳስ 1996 ዓ.ም ከብዙ አመታት በኋላ ባህታ ገብረሕይወት ‘አንቺም እንደሌላ’ን Either Orchestra ከሚባል ቦስተን ከሚገኝ የጃዝ ቡድን ጋር አቅርቦ ነበር።

[“አንቺም እንደሌላ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን/ራስ ባንድ)። 1957-1960 ዓ.ም።]

የመጀመሪያው የራስ ባንድ የተመሰረተው ከ1953 ዓ.ም ነበር። ታዲያ በ1956 ዓ.ም አጋማሽ ሁለቱ የባንዱ አባላት (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) በሌሎች ሙዚቀኛች የተተኩ ይመስላል። ወዳጄነህ ፍልፍሉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ሳክሰፎን በመያዝ፣ አሰፋ ባይሳ ደግሞ ትራምፔት በመጫወት ራስ ባንድን ተቀላቀሉ። በሐምሌ 1956 ዓ.ም አካባቢም እንግሊዘኛ ድምፃዊው ግርማ በየነ ራስ ባንድን ለቀቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1957 ዓ.ም የባንዱ አባላት ከራስ ሆቴል ወጥተው በግዮን ሆቴል ለተወሰኑ ዓመታት “ግዮን ባንድ” ተሰኝተው ተጫውተዋል።

Ras Band 2
ራስ ባንድ በነሐሴ 1956 ዓ.ም። [ከግራ ወደ ቀኝ] ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ አሰፋ ባይሳ (ትራምፔት)፣ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባሕታ ገብረሕይወት (ድምፃዊ)፣ እና ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ሳክሰፎን)። |ምስል 3|

በድምፃዊነት እና በፐርከሽን ከሦስት ዓመት በላይ “ራስ ባንድ” ከተጫወተ በኋላ ግን ወጣቱ ግርማ በየነ በተራው የራሱን ባንድ ለማቋቋም ወሰነ።

Girma Beyene (old)
ግርማ በየነ በ1956 ዓ.ም መገባደጃ። |ምስል 4|

.

.

(ይቀጥላል)

.

ሳይም ኦስማን

.

[ትርጉም] – ሕይወት ከተማ

.

[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com

ትምክሕት ተፈራ መኰንን። የግል ምስሎች ስብስብ። [ምስል 1]

 “የአዲስ አበባ ትዝታ”። vintageaddis.com [ምስል 2]

ሰለሞን ተሰማ። “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም። [ምስል 3፣ 4]

Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”. http://www.funkfidelity.de

Francis Falceto. “Abyssinie Swing – Pictorial History of Modern Ethiopian Music.” 2001.

.

.

ተጨማሪ

የራስ ባንድ ሥራዎች

.

[“ወደ ሐረር ጉዞ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

[“ወደ ሐረር ጉዞ – 2”። ባሕታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ። 1957-1960 ዓ.ም።]

“ፍቅር እና ሆሄ” (ልብወለድ)

“ፍቅር እና ሆሄ”

በአዳም ረታ

.

[ይሄ ጽሑፍ በ1999 ዓ.ም አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች (በመስፋቱም ጭምር) በመጀመሪያ ንድፍ ላይ ከደረሰ ‘ፍቅርና ሆሄ’ ከተባለ ግን ሳይታተም ከቀረ የ2500 ገጽ ልብወለድ መጽሐፍ ላይ የተወሰደ ነው። ጽሑፉ የተቆረሰው አርባ ገጾች አካባቢ ብዛት ካለው ‘ዑር እናት’ ከተባለ የመጽሐፉ መግቢያ ምዕራፍ ነው።]

.

Adam Inside Photo

.

(አገሪቱ በፀሐይ ሙቀት ለነደደች ጊዜ፣ በከተማውና በከተማው ዙሪያ ያሉ ባሕር ዛፎች በጠል መጥፋት ቢጫ ለነበሩ ጊዜ፣ የሚቀመስ እህል ጠፍቶ ለነበረ ጊዜ፣ በተለይ የአገሪቷ ተወዳጅ ምግብ ዱባ የተባለው ፍሬ ዘር ማንዘሩ ለጠፋ ጊዜ፣ ብቻ ከዛሬ ልጅ ለነበረ ጊዜ ……… አያቱ እናኑ የተመቻቸው ቦታ ተቀምጠው ሲያያቸው ገላው ለመታቀፍ ይቁነጠነጥ ነበር። እቅፋቸው ውስጥ በረዶ በመሰለ ጋቢያቸው ሲጠቀለል የሚያደርገው ዓይኖቹን ጨፍኖ ለማይቆም ጊዜ መተኛት ነው። ‘እናና!’ ብሎ ሲጠራቸው ለሌሎች ሰዎች ጎምዛዛ የሚሆኑት ሴትዮ እንደ አበባ ይከፈታሉ። ጉንጭና አፉን ሲስሙ ሁለመናቸው ወተት ይሆናል። አንዳንዴም አላዛር እንደሚወደው ጋቢያቸውን ድንኳን አስመስለው በላያቸው ላይ ይዘረጉና እንደ ልጅ ይላፉታል ……… ከረሜላ ይወዱ ነበር። ሲያውቃቸው ጀምሮ ከአፋቸው የማይጠፋው ከረሜላ ነበር። የሳምንቱን ቅዳሜ ጠብቆ አባቱ በሚሰጠው ገንዘብ ብዙ ማር ከረሜላና ደስታ ከረሜላ ገዝቶላቸው ይሄዳል። ለእሱ የሚፈልገውን በሱሪ ኪሱ፣ ለእሳቸው የመደበውን ደሞ በእጁ ጨብጦ ይቀርባቸውና ‘ትልቋ እማማ ከረሜላ አመጣሁልሽ’ ይላቸዋል። ከረሜላ የያዘበት እጁን በሁለት እጆቻቸው ያቅፉና በምራቃቸው ረጥቦ እስኪያብረቀርቅ ቡጢውን ይስሙለታል።)

… ለምን ትልቅዋ አያቴ ትለኛለህ? ማን አስተማረህ? እኔ ተአያትህ ተሰብለ ብዙ አላረጅም እኮ … ግን ኑሮ ቀደም ብሎ በጥቁር እጁ ሲነካኝ ምን ይሁን? ነካ ነካ ያደርግሃል ኑሮ። ይነጅስሃል። እስዋ የፊታውራሪ ልጅ ነበረች። እኔ በጉዲፈቻ ሞጆ ያደግሁ አባትና እናቴ በስልቱ የማይታወቁ። በእናትህ በኩል ቅድመ አያትህ ፊታውራሪ መሸሻ የሚባሉ የጎጃም ሰው ስማቸው የተጠራ ነበሩ በዋላ ስሰማ። ሰብለ ዲማ ነው እንግዲህ የወለደችው። ለአቅመ ሔዋን የደረሰችው እዛ ነው። የሚገርም ታሪክ ነበራት በዋላ ስትነግረኝ … እሱማ ሰሚ ካገኘ የማንም ታሪክ አይገርምም? እንደው እየመረጥነ እንጂ። ሀሁ ተሚያስተምራት ዲያቆን ይሁን ደብተራ የትኛው እንደሆነ እንጃ በዛብህ ተሚባል ጎረምሳ … ጎረምሳ ነው … ፍቅር ይይዛታል። አባትዋ ሲቀብጡና ሲኮሩ ባል ሲመርጡ ትልቅ እስትትሆን ቤት ዘግተውባት ይኖራሉ … እና አልኩህ እንዳለችኝ ይሄ በዛብህን ወደደች። ታዲያ ያኔ እንደ ዛሬ ዘመን ማንም ከማንም አይጋባም። ዘር አለ ምን አለ … ጦረኛ የጦረኛ ልጅ ነው የሚያገባ … ባለመሬት ባለመሬትን። ፍቅር ማን ያውቃል? ፍቅር አብረው ሲኖሩ ነው … እስቲ አትደብቀኝ አላዘር ዓለምዬ እንደው ያቺ የጎረቤታችሁ ልጅ ማን ነበር ስምዋ? እ? …

(ሊመልስላት አልፈለገም። ገና ቅልስልስነቱን ባልጨረሰ ልጅነቱ ጊዜ ለምን እንዲህ እንደምትጠይቀው ግራ ይገባዋል። እየሳቀች በአፏ ከተባረኪ ጋር ባልና ሚስት ስታጫውተው ትወዳለች። እየተሽኮረመመ አያት። አታየውም። ሊመልስላት አልፈለገም። ድምፁ ውስጥ የመሽኮርመም ዜማ እንዲሰማበት አልፈለገም። ወደ እሱ ያዞረችው ፊቷ ሳያቋርጥ ያሳዝነዋል። ልመልስላት አልመልስላት ሲያስብ …)

ተባረኪ? ወይ ስም እቴ አይ የስም ማማር … ለመሆኑ አባትዋ ይመጣል? … አይመጣም … አይ እቴ ያልሸገረኝን። እና ሰብለ ዲያቆን ለምዳ በዋላ መሰማቱ ይቀራል እግዜር ሲያቅደው። አባት ‘ካልገደልኩት ይሄን ቅማላም ደሃ’ ሲሉ ይፈራና ነፍሱን ሊያድን አምልጦ ወደ ሸዋ ይመጣል። መሄዱን ስትሰማ እስዋ ተከትላ እግሬ አውጭኝ … ወደ ሸዋ እግሩን ተከትላ። መንገድ ላይ ሽፍቶች ደብድበውት … መቼም የሰማሁትን መደበቅ ምን ያደርግልኛል? … ብዙ ነበር የምትለው ሊሞት ሲል የባላገር ቤት አርፎ በጠና ቆስሎ ትደርሳለች። ግጥጥሙ አይገርምም? ምን ይደረጋል እግዜር ያቀደውን … አይታገሉት። ክንድዋ ላይ ደም መቶት ይሞታል። አያሳዝንም? እንዲህ ስታወራኝ በጉንጭዋ ዕንባ እየወረደ። የሰማት ሁሉ ነው የሚያለቅስ … እስቲ ያን ውሃ አቀብለኝ … ያቺ ልጅ አልመጣችም? መድሃኒቴን የት ነው ያስቀመጠችው? ጊዜው ተላለፈ እኮ። ሰዓት ስንት ሆነ? አምስት? ያ አባትህ እኮ ገና በልጅነትህ ሰዓት መስጠቱ ለእኔ ሳይጠቅመኝ አልቀረም። ለመሆኑ አያድርግና ስትጫወት ብትሰብረውስ? እ? አምስት አልከኝ? አንድ ሰዓት አለኝ። አምስት ተሩብ? ያው ነው … ስለ አያትህ ስለ ሰብለ ልቀጥልልህ። ሰብለ መሸሻ። የእኔ እህት… የእኔ እመቤት። አራዳው ካገኘሁዋት ጀምሮ ለአስራ አምስት ቀን አለቀሰች። ተዚያ ተሁለት ሰንበት በዋላ ተሻላት። መብላት ጀመረች መጠጣት ጀመረች። አልፎ አልፎ እንደው ቢደብታትም። እኔ ምን ነበረኝ ያኔ? ምንም። ሴት ነኝ የሁለታችንንም ሆድ መሙላት አልችል። በደህናው ጊዜማ የንግሥት ጣይቱ ወጥ ቤት ነበርኩ። አይ ጣይቱ እናቴ። አንቺም አፈር ይበላሻል። ንግሥት ገና ጠዋት ብቅ ሲሉ ‘የት ናት እናኑ? የእኔ ጎራዳ’ ይላሉ። ‘ያቺ አገጫም የታለች?’ እንደ እኔ ጎረድረድ ያሉ ሴትዩ ነበሩ። ‘ለእሳቸው’ ለሚኒሊክ ማለታቸው ነው ‘ቁርሳቸውን አድርሺ መመለሻቸው ነው’ ይሉኛል። ሁልጊዜ ፊቴን ያዩና ወደ ማታ ተሆነ ‘ደክሞሻል?’ ይሉኛል። አልደከመኝም ካልኳቸው ‘በይ ትንሽ ንፍሮ ቢጤ ይዘሽለኝ ነይ ተብርዝ ጋር’ ይሉኛል። እመቤት እኮ ናቸው። ምላሳቸው ግን አይጣል ነው ተከፉ። መኝታ ቤታቸው ይዤላቸው እሄዳለሁ … ንፍሮውን በቁልቢጥ ብርዙንም በቀንድ አድርጌ። ገና እሱን መሬት እንዳስቀመጥኩ ይጠቅሱኝና ጋቢያቸውን ወረድ ያደርጋሉ። ድንቡሽ ያሉ ናቸው። ተዛ ጀርባቸውን አክላቸዋለሁ። … ምግብ አቅራቢያቸውና አካኪያቸው ነበርኩ። አንገታችው ትዝ ትለኛለች። አንገታቸው በመወፈራቸው የተጣጠፈች ሥጋ ነበረች። ‘ማከኩን ተወት አድርጊና እሱን እሺኝ ሳይጣምነኝ አልቀረም’ ይሉና እሱን ሳሽላቸው በቀስታ ያንጎራጉራሉ። ‘ልጅ እያለሁ እዘፍነው ነበር’ ይሉኛል። ወረሂመኑ ለነበሩ ጊዜ … ለመሆኑ ወረሂመኑ የሚባል ቦታ ሰምተሃል?

(አልመለሰላትም። እንደሚያይ ሁሉ ወደ ተቀመጠበት ዞር ትልና ‘ታየዋለች’ … ወደ ተጋደመችበት ሄዶ ከአፏ ዳርና ዳር ቆበር በኩታዋ ጠርጎ ያነሳላታል … አሁንም አሁንም)

አላልኩም አላልኩም አገራችሁን ትንቁዋታላችሁ እንጂ የት ታውቁዋታላችሁ። ወረሂመኑን የመሰለ አገር አታውቅም … አውሮባ ምናምን ቢሏቸሁ ይሄኔ ታታታታ ታደርጋላችሁ። የዚህን የጣይቱን ነገር ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ወሬ ምን ይታወቃል ማን ጋ እንደሚደርስ። እስተ ዛሬ ንጉሡ እኮ አለቀቁኝም። ንግሥት ጣይቱ ጀርባቸውን ያሳክኩ ነበር ተብሎ ቢጣፍስ? ሁሉ በየቤትዋ ታሳክካለች እኮ። ተፈሪ ጣይቱን ያሸነፋቸው እኮ ስም በማጥፋት ነው። እንደ ወንድ መቸ ችሎበት። ወንድ ቢሆን ኖሮ እዝህ ለሰላቶ ለፋሺስት ትቶን ይሄድ ነበር? ወንድ ሆኖ ክንድ የለውም። ክንድ ተፈረንጅ ሊበደር ይሄዳል። ለአንተ ብቻ ነው የምነግርህ። ጣይቱ አምባላጌ ሲያዋጉ ባዶ እግራቸውን ወንዶች ፊት ፊት ሲሮጡ ተሩቅ ጥልያን አይቶ መትረየስ ቢያዘንብባቸው ይህቺ የግራ እግራቸው ትንሽ ጣት ተቆረጠች። በቃ የለችም። አራት ጣት ነው ያላቸው። አንድ ጎበዝ እላያቸው ላይ ወድቆ ነው ያዳናቸው። ጎናቸውን ደሞ ሲወድቁ ጫንቃቸው ላይ የተሸከሙት የዓላማ ሰንደቅ ወግቶአቸው አሁን ድረስ እስቲሞቱ ያማቸው ነበር። እዚህ ከብብታችው ዝቅ ብሎ። ገና ብርድ ሲሆን ውሃ አሙቄ ጨርቅ ይዤ ማደሪያቸው እሄዳለሁ። አንዳንዴ ‘እሱን ተይ’ ይሉኝና በጋቢ ተከናንበው ይቀመጡና እኔም ተከናንቤ አቅፋቸዋለሁ። ‘የሰው ሙቀት ይሻላል’ ይላሉ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ? … አድዋ ዘመቻ ጊዜ ከተማ ጠባቂና ፀሎተኛ ነበርኩ። በቀን ሶስቴ እንፀልያለን። አሸነፍን ሲባል ልጄ ተንጦጦ ባቡር ጣቢያ በእልልታ ቀለጠ። ዛፍ ተቃጠለ። ደን አለቀ ልበልህ። ምን ላይ ነበርኩ ዓለምዬ?…

(እምን ላይ እንዳቆመች ሊነግራት አልፈለገም። በዝምታ በተመስጦ ግርማው ያልጠፋ ረዥም ፊቷን ማየት ብቻ ነው የሚፈልገው። ጨዋታዋን ያቆመችበት ጠፍቷት “በል ሂድልኝ የሚቀጥለው ሳምንት ና” ብትለውም ይወዳል። የቆመችበት እንደጠፋው ሁሉ ዝም አላት)

… አዎ የጀመርኩልህ? ምን ነበር? አዎ። ስለ ዱባ ወጥ። ስለ መሐሌ ወለላ። ሚኒሊክ አያውቁም። ንግሥትነታቸውን እስቲነጠቁ ድረስ እስከ ሺህ አስር እስከ ሺህ ዘጠኝ መቶ አስር ድረስ ዱባ ወጥ ለጣይቱ መስራቴን ወጥ ቤት እንኳን አያውቅም። አየህ አላዛር ሞጆ በነበርኩ ጊዜ እንዲህ ሆነ። እረሳለሁ እንጂ የማይረሳ እረሳለሁ። የማይረሳ። ነሲቡ አሳዳጊዬ ሞተው እሳቸውን ቀብሬ ስመለስ ደብረዘይት ቢሾፍቱ ከመድረሴ በፊት ዝናብ ጣለ። የሚገርም የሚገርም ዝናብ። ምን? በለኝ። ምን? በለኝ። የተሰባበረ ዱባና የዱባ ዘር። እንደውልህ ከሰማይ እየመጣ የተፈናጠጥናቸው ከብቶች ላይ አናታችን ላይ አይለጠፍብን። ቀና ብዬ ሳይ ወርቅ የመሰለ ቢጫቴ ደመና። የዛ ዓይነት ደመና አይቼ አላውቅ ከተወለድኩ። ‘ሚካኤል ከዚህ ካወጣኸን በየወሩ ጠበል አደርግለሃለሁ’ አልኩት። ቁጥቁዋጦ ግራር ነገር ፈልገን ተጋረድን። የዘነበው ብዙ ቦታ አልነበረም። እንደው እኛ ጉድ ሊያሳየን ይሁን እንጃ። እንደው እኮ ሶስት ቀበሌ ቢዘንብ ነው፣ ቢሾፍቱ ስንደርስ ‘እህ’ አልን የዛን አገር ሰዎች። ‘በሉ አትቀልዱ’ አሉን። ‘እንዴ ከሰማይ ዱባ ዘነበ’ ስንላቸው እብድ አደረጉን። አብረውኝ የነበሩ መንገደኞች ነበሩ አንድዋ ጣይቱ ቤት ልትወስደኝ አንድዋ ዘመድ ጥየቃ ሞጆ ደርሳ የዓመቱ አቦ መሰለኝ ትዝ አይለኝም ስገምት ማለቴ ነው፣ እንደው እምቢ ሲሉ እኔ በመቀነቴ ርጥቡን የዱባ ፍሬ ሰብስቤ አዲስ አባ ገባሁ። አንድ ቀን መቀነቴን ላጥብ ስል ረስቼው ኖሮ … የቤተመንግስት ሥራ ጊዜ መች ይሰጣል? ማስተዳደር በለው፣ የመኩዋንንቱ ሆድ አያርፍም። ሁልጊዜ የሚበላ ያስፈልጋል መቆያም ይሁን። ጠዋት መስራት ማታ መስራት፣ እና በመቀነቴ እንደያዝኩት ዘሩ ሳይበላሽ ወር ከርሞ አገኘሁት። ያኔ እንደ ዛሬው ልብስ በየቀኑ አይታጠብም፣ ሳጥብ ደርቆ ልፋጩ መቀነቴ ቋጠሮ ውስጥ ተገፎ ረግፎ አገኘሁት። ሲሸት ነበር አንድ ሰሞን መተኛዬ ስገባ ይሸተኛል። ግን ልብ ሳልል እንጂ። እሱን ዘር ወሰድኩና ቤቴ ግቢ ሰፊ ቦታ ነበር፣ እዛ አጥር ሥር ፎገል ፎገል አድርጌ ቀበርኩት። ዝናብ ነበር ትዝ ይለኛል፣ ወሩን እንጃ … ምን ትዝ ይለኛል ወሩ። ዝናብ ነበር። ‘ያ ዱባ ከሰማይ የወረደ ዱባ ነው’ ብዬ ስናገር የሚያምነኝ አልነበረም። ተጫዋች ነበርኩ፣ እና ጨዋታ ይመስላቸዋል። ቀምሰው ዱባዬን … ቀምሰው እንኩዋን አያምኑኝም ነበር። ልጄ ሕዝባችን የተለየ ሕዝብ ነው። የማያዩትን የሚያምኑ፣ ያዩትን የማያምኑ ሕዝቦች ነን። ትደርስበታለህ። የማወርስህ ብችል እሱን የዱባ ዘር ነበር። ጥልያን ሲመጣ ትቸው ሄድኩ። ቤቴ የተሰጣቸው ባንዶች ቆፍረው ሌላ ነገር ሎሚና ወይን አብቅለውበት ደረስኩ። እቴጌ ጣይቱ ‘ዘር ስጪኝ’ ብለው እሳቸው ብቻ ያመኑኝ ወሰዱ። ያኔ እንጦጦ በቁም እስር እያሉ። ቁም እስር ታውቃለህ? ቁም እስር ማለት እንግዲህ አሳሪዎችህ እነሱ ዳገት ላይ ተቀምጠው አንተን ሜዳ ላይ ይለቁሃል እና ‘እንዳሻው ለቀቅነው’ ይሉሃል እሱ ቁም እስር ነው። ግሼን አምባም አይደለ። ማጣት ነው ያለበት። አውቆ ማጣት ነው። የዱባ ዘሬን በወሰዱ በሳምንቱ ጣይቱ እናቴ ከእንጦጦ ጠፉ። የተባለው ሞቱ ነው … እና ብፈልግ ብፈልግ መጠጫቸው ካቦና ያቺ የዱባ ቋጠሮ ለመሆኑ ካቦ ታውቃለህ? መጠጫ ጥዋ ነገር … የት ነበር ያቆምኩት ልጄ? የተነሳሁበት ይጠፋኛል። ለምን ይሄን አወራሃለሁ? የተነሳህበት እንዳይጠፋህ ነው ልጄ … እናልህ እስኪጠፉ እንደተባለው እስኪሞቱ ድረስ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ አብረን ከንግሥት ጋር ዱባ እንበላ ነበር። ዛሬ የተረፉ ወጥ ቤቶች አይጠፉም ቢጠየቁ ይህቺን የእኔንና የጣይቱን ሚስጢር አያውቁም። ማታ ማታ ወጥ ቤት ሁሉ ሲተኛ ቀን ደብቄ ያመጣሁትን ዱባ እልጥና አሳምሬ እሰራላቸዋለሁ። ጣታቸውን የሚልሱት ተእኔ ጋር ነበር። ምግብ ሲበሉ ‘ለመሆኑ የእናኑ እጅዋ አለበት?’ ይላሉ። የለበትም ተተባሉ ‘በሉ አስቀምጡትና ሂዱ ተራበኝ እበላለሁ’። አይበሉትም። ንክች። ‘ለመሆኑ የት ሄደች’ ይሉና መታመሜን ያውቁ የለ ይነገራቸውና መድሃኒት የሚያቅ ቤቴ ይልካሉ። አንድ ጊዜ ቅቤ ሳነጥር ከባድ ምች መቶኝ ሁለት ቀን ተኛሁ። በሁለተኛው ቀን ቤቴ መጡና እዝሁ ጎላ የደሃ ጎጆዬ ግማሽ ቀን ውለው ዳማ ከሴ ቆርጠው፣ አጥሚት ሰርተው አልጋዬ ጎን የተኛሁበትን ቁርበት ወርውረው ጨርቅ አንጥፈው … ዛሬ ድረስ አለ ያ ጨርቅ … ትንሽ ሲሻለኝ በበነጋታው መጥተው ገላዬን አጥበው … ማን ነበረኝ? ማን? ይሄ ሁሉ ልጄ በንግሥት እጅ። ዛሬ እንዲያ የሚያደርግ ንግሥት ቀርቶ እንደው ተራ ሰውስ አለ? ችሎታ ብላችሁት … የክፋት ችሎታ …

(ፈገግ አለ። የሚያስፈግግ ነገር አልነበረም። ስለ ንግሥት ቀባጢሶ ማውራት ወይም መስማት አይፈልግም። አሁን ወደ ውጭ መሄድ ይፈልጋል። ስታወራው ሳይቋርጥ የሚያየው ነገር ጠይም ፊቷን፣ ትልቅ አፏንና መውጫ በሩን ነው። ሲኒማ መግቢያው ጊዜ ደርሷል። ትንሽ ከቆየ ሊዘጋ ይችላል። ሊሞላ ይችላል። ፒያሳን ያስባል … አምፒር፣ የቡና በወተት ጠረን፣ የባቅላባ ጠረን፣ የእርጎ ጠረን፣ በቁንጅናቸው የሚያማልሉት ትናንሽ የጂንስ ቤልቦተም ሱሪዎች ያደረጉ ያኮረኮሩ ልጃገረዶች)

… አንድ ጊዜ ተአድዋ ዘመቻ በዋላ ትልቅ ግብር ያዘጋጃሉ። የእኛ መኩዋንንት ጦር ስላሸነፈ ብቻ ሁሉን ነገር ያወቀ ይመስለዋል። ‘መኩዋንንቱን ሁሉ እስቲ የሃበሻ ሴትን ሙያ እናሳየው’ ብለው ጣይቱ ምን የመሰለ ድግስ ያዘጋጃሉ። ከብት አለቀ ልበልህ። ተአምስት ሺህ በላይ ከብት። ብዙው መጋበዝ የሚመስለው ሥጋ ብቻ ነው። በመጨረሻ ዕለት ንግሥት ጠጋ አሉኝና ‘ለመሆኑ ያንን ዱባሽን በትልቁ ለብዙ ሰው መስራት ትችያለሽ?’ ይሉኛል። ተጠራጠርኩ። ‘እንዴ አንቺ ጎራዳ እናደርገውና እምቢ ካለን ዝም ነው’ አሉ … ሂሂሂሂ …

(ሳል ስላጣደፋት ከተኛችበት በክርኗ ደገፍ ብላ ተነሳችና ባዶ አየር ውስጥ በጭንቀት አፈጠጠች። ተረጋግቶ የነበረው ፊቷ ቁጣ እንደነካው ሁሉ ተኮማተረ። የምትስል ሳይሆን ብስጭት የሚሰማት ትመስላለች። እንደ አጋጣሚ በእጁ የያዘውን የኩታ ጫፍ ወደ አፏ ወሰደና ከአፏ ወደ ውጭ እየተገፋ የሚፈናጠቀውን ምራቅ መቅለብ ጀመረ። ከመሃል ትንፋሽ ስላጠራትና ዓይኖቿ ስለፈጠጡ ደንግጦ ለእርዳታ ሠራተኛዋን ሊጠራት ሲል መሳልዋን አቁማ ዝም አለች። የሚፈራው ይሄን ነው … )

…. ሲያምር ተንግሥት ጋር መዶለት። ዱባ ወጥ ሰራነ። አስቸገረ። አይ ሲጣፍጥ እቴ … አስቸጋሪው ደሞ በሰታቴ የተሰራ ያ ሁሉ ዱባ እንዴት ሳይፈርስ ተምድጃ ይወጣል ነው። ቀላል ይመስላል። እኔ እናትህ ማማሰያ ሳላስገባ እተጌን አስደሰትኩዋ። ጠረኑ ራሱ ‘የዛሬስ ወጥ ምን ቅመም ቢገባበት ነው?’ ተባለ። እኔና ንግሥት እንተዋወቃለን። ተራራው ላይ እንጦጦ ሳትወጣ ታች እዛ አሁን ሰፈራችሁ ያለበት ገደል ጋ ይሸትሃል … ስዋሽህ አይደለም። መኩዋንንት ተሰብስቦ ሲበላ ‘ምንድነው’ አለ? ‘የምን ሥጋ ነው? በምን ሰራችሁት?’ ሁሉ ተበልቶ አልቆ ‘ዱባ ነው’ ተብሎ ቢነገራቸው ‘አሁን ተሥጋው የበለጠ ጥሞአችሁ የበላችሁት እሱ ዱባ ነው’ ሲባሉ አላመኑም። አላዛር ሙት አላመኑም። እተጌ ሲናገሩአቸው አላመኑም። አምነናል ያሉትም ‘እንዴ ታዲያ መኩዋንንቱን ዱባ ታበያለሽ እንዴ? የሚበላ ጠፋ?’ አሏቸው። ብቻ ዱባ መሆኑ ሲነገራቸው ስለበሉት ነገር ማውራት አቆሙ። በዋላ ሲያስሩአቸው ‘ይህቺ እኮ ትንቀናለች ያ ዱባ ትዝ ይላችሁዋል?’ እያሉ ነበር። ‘መኩዋንንቱን ንቃ ዱባ ደብቃ የምታበላ’ እያሉ። እኔ እናኑ እውነቴን ነው የምልህ የዚያ ወጥ ጠረን ተማድቤት ቀርቶ ተራራው ራሱ ላይ ‘ስንት ጊዜ ምን የሚያምር ነገር ይሸተናል’ እየተባለ። ያን ሰሞን ቢበሽቁ እተጌ መኩዋንንቱን አዘፈኑባቸው።

አገሬን ወዳለሁ ሕዝቤን እወዳለሁ

አፈርዋን ዱባዋን ጠብሼ እበላለሁ

ደም አፍሰው ሥጋ ቢነጩት ቢነጩት

ልብ ይደፍናል እንጂ አይሆን ለሰው አንጀት

የጦብያ ሴቶች ሙያቸው ትላልቅ

በጦር ሜዳ ይሁን በማድ ቤት እናስንቅ

እናልህ እሳቸው በተፈሪ ሲታሰሩ ማድ ቤት የነበርነውም ተበተንን። እኔ በዋላ በዋላ ታዘነልኝና ባሌም ስለ ሞተ ዘውዲቱም ስለምትወደኝ ትንሽ መሬት ተቆርጦልኝ … አንድ መኩዋንንት ናቸው አሉ ‘ሴት ልጅ አትበድሉ’ ብለው ተከራክረውልኝ … ጣይቱ የቁም እስር ባሉበት ተዚህች ዓለም እስቲያልፉ ድረስ ተእኔ እንዳይገናኙ ቢከለከሉም አንዳንዴ እየጠሩኝ በአቅራቢ በአቅራቢ … እንግዲህ እኔ ተፈርቼ መሆኑ ነው … ከጓሮዬ ቀንጥሼ ዱባ ወጥ ሰርቼ እወስድላቸዋለሁ ወይ እልክላቸዋለሁ … ‘አረፉ’ ሲባል አለቀስኩ ልጄ … አሁን እኔ ኖሬ እሳቸው ይሞታሉ? የእግዜርን ነገር አየህ። አሁን ዘጠና አለፈሽ እባላለሁ ግን እመቤቴ እሳትዋ በአጭር ተጠለፈች። እግዜር ሚስጢሩ አይገባም …

(ብዙ ነገር ቢረሳም ይሄን አይረሳም። አባቱ ብርሃነመስቀል እናኑ ጋ አድርሶት ወደ ሚሄድበት ሊሄድ ታኑስ መኪናውን ግቢ አቁሞ፣ ዝናቡን እያማረረ፣ ሐምሌን እየረገመ፣ በጫማው የሰበሰበውን ጭቃ ድንጋይ ላይ ለመጥረግ ሲለፋ፣ አላዛር አባቱን ትቶት እየሮጠ ወደ ቤት ውስጥ ይገባል ……… ከፊት ለፊቱ ትራስ ተደግፈው ሶፋ ላይ ጋደም ያሉት እናኑ ላይ ወደቀ። እናኑ አላዛር ከረሜላ ያመጣልኛል ብለው የመጨረሻዋን የማር ከረሜላ አፋቸው ከተው እየመጠጡ ነበር። ያን ቀን ከረሜላ አልገዛም። ጭናቸው ላይ ተቀምጦ እንደ እንቦሳ እየተገላበጠ፣ አባቱ ገንዘብ አልሰጥህም ብሎት ከረሜላ ስላልገዛ ከሚበሉት ከረሜላ እንዲሰጡት ይጠይቃቸዋል። ‘እምቢ አፌ ከገባ አልሰጥህም’ ይሉታል። አልሰማም። ጣቶቹን አፋቸው ውስጥ ከቶ ከረሜላውን ለማውጣት ብዙ ለፋ። እምቢ ቢሉትም ጭናቸው ላይ በጀርባው ተኝቶ ካልሰጠሽኝ እያለ መነዝነዙን ቀጠለ ……… አላዛር ጭናቸው ላይ እንደ ቡችላ ሲሆን ሲያዩት፣ የወርቅ ሐብሉ ከነመስቀሏ የሚያምር አንገቱ ላይ ተልፈስፍሳ ሲያዩት፣ ወተት የመሰሉ ትናንሽ ጥርሶቹና እህል ገብቶበት የማያውቅ የመሰለ የአፉን ጽዳት ደሞ የቆዳውን ልስላሴ ሲያዩት … ብቻ ሁሉ ነገሩ ስቧቸው፣ የወለዱት ሁሉ መስሏቸው፣ ወደ አፉ እንደሚስሙት ሁሉ ቀርበው በምራቃቸው የመለገውን ከረሜላ በተከፈተ ለፍላፊ አፉ ጠብ አደረጉለት። ዓይኖቻቸውን በእርካታ ጨፈኑ። ልባቸው የምትቆም መሰላቸው። አላዛር በአፉ የገባው ከረሜላ አስደስቶት ያሉበትን ክፍል በትንሽ ልጅ ሳቁ ሞላው ……… አላዛር ይሄ ሲታወሰው ለእናኑ የዱባ ተረትና አይቶትም ይሁን ቀምሶት የማያውቀው የዱባ ወጥ ጣዕም አፉ ውስጥ ይሰማዋል። ከረሜላ አይደለም ምንም አይደለም ራሱንም ይጠይቃል እንዴት ያልቀመስኩት ትዝ ይለኛል? እንዴትስ ይጣፍጠኛል?)

.

አዳም ረታ

.

መሰንቆ እና ብትር (ወግ)

“መሰንቆ እና ብትር”

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ …”

አዝማሪ ጣፋጭ [1845 ዓ.ም]

.

የዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ጎሹ እና የቋራው ፋኖ ደጃዝማች ካሳ በኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም ጉራምባ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ካሳ፣ ከጥቂት ታማኝ ጭፍሮቻቸው ፊት ተሰልፈዋል። ጎሹም፣ በተለመደው የጀብድ መንገድ ከሰራዊታቸው ፊት ለፊት ቀድመው፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ ውለዋል። ውጊያው እንደተፋፋመ፣ ደጃች ጎሹ በጥይት ተመትተው ወደቁ። የመሪውን መውደቅ እንደተረዳ የዳሞት ጦር ፀንቶ መመከት ተሳነው። ወዲያው የንቧይ ፒራሚድ ሆነ። ያለቀው አልቆ ቀሪው ተማረከ።

ከምርኮኞች አንዱ፣ አዝማሪው ጣፋጭ ነበር።

ጣፋጭ፣ የደጃች ጎሹ አዝማሪ ስለነበር በብዙ ጦር ሜዳ ላይ ውሏል። በጌታው ጠላት እጅ ሲወድቅም የመጀመሪያው አይደለም። በራስ ይማም ዘመንም እንዲሁ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ የተባለ መስፍን ደጃዝማች ጎሹን ድል በነሳ ጊዜ፣ ከጌታው ጋር ተማርኮ ነበር።

ይሁን እንጂ ያኔ ዝንቡን እሽ ያለው አልነበረም። ጣፋጭ፣ የደጃች ማጠንቱ ምርኮኛ ቢሆንም፣ የእግር ብረት አልገባበትም። እንዲያውም፣ በድል አድራጊው አዳራሽ ውስጥ ያሻውን ከማንጎራጎር አልተከለከለም ነበር። በወቅቱም፣ አዝማሪው ጣፋጭ ይህንን ገላጋይ ዝማሬ አቅርቦ ነበር፤

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

ጣፋጭ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ በጦር ሜዳ ላይ ስምንት ወታደር መግደሉን አስታውሶ፣ አሁን ተማራኪውን ቢገድል የሚጨመርለት ክብር እንደሌለ አስታወሰው። በሁለት መስመር ግጥም ለድል አድራጊው የሚገባውን መወድስ ሳይነፍግ፣ የጌታውን ሕይወት ለመታደግ ጥሯል። ድል አድራጊው ደጃች ማጠንቱም ጎሹን ሳይገድለው ቀረ።

በዚህ በኅዳር ዕለት ጦርነት ግን፣ አዝማሪው ጣፋጭ በቋረኛው ካሳ ጦር ተማርኳል። ተስፋና ፍርሀት ከፊቱ ተደቅነዋል። ባንድ በኩል፣ አዝማሪን መግደል ነውር የሚያደርገው ባህል ጋሻ ሁኖት ከክፉ እንደሚታደገው ተስፋ ያደርጋል። በሌላ በኩል፣ ደጃዝማች ካሳ ይህን ደምብ ለማክበራቸው ርግጠኛ አይደለም።

እነሆ፣ አዝማሪው በካሳና በጭፍሮቻቸው ፊት ቆሟል። ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ የሚተርኩልን ለዘመኑ ቅርብ የነበሩት አለቃ ወልደማርያም ናቸው፤

“አዝማሪ ጣፋጭ … ተይዞ በቀረበ ጊዜ ባደባባይ አቁመው ደጃች ካሳ ‘እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ’ ቢሉት እጅግ ተጨነቀ፤ እንዴህም አለ፤

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

እንዲህም ቢል ሞት አልቀረለትም፤ በሽመል ገደሉት።”

አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ከሁለት ትውልድ በኋላ በጣፉት የጎጃም ታሪክ ውስጥ ደግሞ የሚከተለውን ተጨማሪ መስመር እናገኛለን፤

“አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

ከመቶ አመት በኋላ ታዋቂው ዘመናይ የታሪክ ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ በጻፉት ጥናትም “ብትር” የሚለውን “ሽመል” በሚል ቃል ከመተካት በስተቀር ያለቃ ተክለየሱስን ቅጂ ማስተጋባት መርጠዋል፣

“እወይ ያምላክ ቁጣ

ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

.

ጣፋጭ፣ የደጃች ካሳን ምሕረት አጥብቆ የሚፈልግ ምርኮኛ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ተሽቀዳድሞ በራሱ ይፈርዳል? እንዴት “ሽመል/ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ” ብሎስ ራሱን ለቅጥቀጣ ያቀርባል?

የጣፋጭን ፍርድ በመመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም ታሪክ ውስጥ መደምደሚያው ስንኝ አለመጠቀሱ አንድ ነገር የሚጠቁም ይመስለኛል። ስንኙ ምናልባት ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ይሆናል።

የኔ ግምት እንዲህ ነው … አዝማሪ ጣፋጭ በደጃዝማች ካሳና አጃቢዎቻቸው ፊት ይቀርባል፤

ደጃች ካሳ፤   እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ?

ጣፋጭ፣ በጦርነቱ ዋዜማ በደጃች ካሳ ላይ ያወረደውን ዘለፋ እዚህ ቢደግም፣ የድል አድራጊውን ቁጣ ከማቀጣጠል ውጭ የሚፈይድለት ነገር የለም። ስለዚህ የመጨረሻ መሳሪያውን ለመጠቀም ወሰነ። ቧልት! …. ካሳና ጣፋጭ በጎሹ ቤት በሎሌነት ሲኖሩ፣ ካሳ ቀልድና ፈሊጥ እንደሚወድ ያውቃል። ጣፋጭ መሰንቆውን ቃኝቶ ይህን በግለ ሂስ የተሞላ የቧልት ዘፈን ዘፈነ፤

ጣፋጭ፤   ህምም …

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ሥራ ሲያጣ።

ካሳ አልሳቀም። አዝማሪው የከፈተውን ተውኔት እንዴት መቀጠል እንዳለበት እያሰበ ይሆናል። ደጃዝማች ካሳ፣ ራሱን የመለኮት ተውኔት ፍሬ አድርጎ ስለሚቆጥር ፍርዱን ሳይቀር ተውኔታዊ ማድረግ ይወድ ነበር። የራስ አሊን እናት በማረከም ጊዜ “ገረድ ትሰለጥናለች እመቤት ትፈጫለች” የሚለውን የፍካሬ የሱስ ትንቢት ለማስፈጸም ወይዘሮ መነን ባቄላ እንድትፈጭ ፈርዶባት ነበር። “የኮሶ ሻጭ ልጅ” ብሎ የሰደበው ቀኛዝማች ወንድይራድን ደግሞ “እናቴ ከገበያ ሳይሸጥላት የቀረ ኮሶ ስላለ እሱን ተጋበዝ” ብሎ፣ ከመጠን ያለፈ ኮሶ አስግቶ ለመቅጣት የሆነ የተውኔት ስጦታ ያስፈልጋል። ያገራችን ጸሐፌ ተውኔቶች በፍቅሩ የነሆለሉት ብጤያቸው ስለሆነ መሆን አለበት።

ደጃች ካሳ፤   (ወደ አጃቢዎቹ ዞሮ)

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ።

.

ጣፋጭ በቧልት የጀመረውን … ካሳ በትራጀዲ ደመደመው።

.

* * *

ጣፋጭን ለድብደባ የዳረገው ዝማሬ ግጥም ይሄ ነበር …

አያችሁት ብያ፥ የኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞ፥ ጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ፥ መች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት፥ በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ ፥ በነ ጉንጭት ለምዶ።”

* * *

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ” [መስመር ፩]

ብያ” ዛሬ ለመረሳት ከደረሱት ያማርኛ ጥንታዊ ቃላት አንዱ ሲሆን “እኮ፣ አይደል” ማለት ነበር። “አያችሁት ብያ” ሲልም “አይታችሁታል አይደል?” ማለት ነው። ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሱን ገድሎ በወደቀ ማግስት ከወረዱ የሙሾ ግጥሞች አንዱ፣ “አያችሁት ብያ ያንበሳውን ሞት” የሚል ስንኝ አለው። ይህም በጊዜው ቃሉ የተለመደ እንደነበር ያመለክታል።

“እብድ” ተብሎ ካሳ በይፋ ሲጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የምንሰማው ከአዝማሪ ጣፋጭ ሳይሆን አይቀርም። ጣፋጭ ይህን ሲል፤ የጊዜውን አስተያየት እያስተጋባ ነው? ወይስ በራሱ ምርመራ የደረሰበት ነበር? አላውቅም። አለቃ ተክለየሱስ ከግማሽ መቶ አመት በኋላ በጐንደር ሲወርድ የነበረውን ግፍ ዘግቦ፣ የሕዝቡን ምላሽ ምን እንደነበር ሲጽፍ፣ “ከዚህ በኋላ፣ የበጌምድር ሰው ‘ይህስ የደህንነትም አይደለ’ እያለ አመል አወጣ … ንጉሡንም ጠላው። ሌሊት በተራራ እየቆመ፣ እንደ ሳሚ ወልደ ጌራ ‘እብዱ ገብረኪዳን’ እያለ ተሳደበ” ይላል። (“ገብረኪዳን” የአፄ ቴዎድሮስ የክርስትና ስም እንደነበረ ባልታወቀ ደራሲ ተጽፎ Fusella ባሳተመው ዜና መዋዕል ተጠቅሷል።)

.

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ [መስመር ፪]

ጋሞች” የሚላቸው ባለ አፍላ እድሜ ላይ ያሉትን ጋሜዎች ነው። ባዝማሪው አይን ሲመዘኑ የደጃዝማች ካሳ አጃቢዎች እድሜያቸው ለጋ፣ ቁጥራቸውም ጥቂት ነው። በርግጥም የካሳ ጭፍሮች ማነስ ለባላጋራዎች ግራ የሚያጋባ ነበር። ባነጋገር ፈሊጣቸው የታወቁት ራስ አሊ የቋራው ካሳን ሰራዊት ከሩቅ አይተው ከገመቱት በታች ቢሆንባቸው፣ “ጦረኛ እንዳንለው አነሰ፤ ሰርገኛ እንዳንለው በዛ” ብለው ነበር።

ጉራምባ” (ጉር አምባ) በዛሬው የደንቢያ ወረዳ፣ ጎርጎራ በተባለው ንኡስ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው። ደጃዝማች ካሳ ይህን ስፍራ የመረጡት ለመከታ የሚያመች አምባ ሆኖ ስላገኙት ሳይሆን አይቀርም። አዝማሪው ጣፋጭ በግጥሙ ውስጥ “ጉር አምባ” የሚለውን ነባር ስም “ጉራምባ” ብሎ አሸጋሽጎታል። ይህን ያደረገው ስፍራውን “ጉራ መንፊያ” ብሎ ለመተርጎም እንዲያመቸው ይመስላል። ጣፋጭም የቋራው ካሳን ለይስሙላ እንጂ የምር መዋጋት የማይሆንለት ጦረኛ አድርጎ ይገምተው እንደነበር ቀጣዩ መስመር ያሳያል።

.

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋ ካሳ” [መስመር ፫]

ያንጓብባል” የሚለው ቃል “አጊጦ በመልበስ ቄንጥ ባለው አካሄድ ይሄዳል፣ ዳር ዳር ይላል” ማለት ነው። ቃሉን የሚከተለው ከአለቃ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ” የተቀነጨበ አንቀጽ የበለጠ ያብራራዋል፣

“ሰማይ ከዚያ ላይ ሆኖ አንጓቦብን የሚኖር ከቶ ምንድር ነው? ቀን ፀሐይን ሌሊት ጨረቃንና ከዋክብትን ተሸልሞ ዘወትር እኔን እኔን እዩኝ እዩኝ እያለ ያደክመናል … እንደዚህ የኮራ እንደ ሰም ለመቅለጥ ነው እንጂ ፊቱን እንዴት ያየው ይሆን? ኩራቱም ምድር አስለቅቆታል። ምን ይሆናል እንደሚያልፍ አያውቅምን?”   [ክፍል 15፤ አንቀጽ 16]

ይህ ዳር ዳር ማለት የቋራው ካሳ ጠላቶቹን የሚያዘናጋበት ልዩ የጦር ስልት ነበር። በጠላቶቹ አይን ግን እንደ ፍርሀት ይቆጠር ነበር። ለአብነት ያክል፣ አለቃ ወልደማርያም በደጃች ካሳና በራስ አሊ መሐል የተደረገውን ውጊያ አስመልክተው ሲጽፉ፤ “ራስ አሊ አይሻል በሚባል ሜዳ ጦርዎን ሰርተው ተቀምጠው ሳሉ ደጃች ካሳም ዳር ዳሩን ይዞሩ ጀመሩ። ሰውም የፍርሀት መስሎት ‘ተመልሶ ሊሄድ ነው’ ይል ጀመረ።”

መች ይዋጋል …” የቋራው ካሳ ደፋርና ጽኑ ተዋጊ ቢሆንም ጉልበቱን መዝኖ መሸሽም ያውቅ ነበር። ደጃዝማች ጎሹ በ1840 ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሚካኤል አባዲ በጻፉት ደብዳቤ “ተካሳ ጋራ የተዋጋነ እንደሆነ ጎንደር እገባለሁ እንገናኛለን፤ ወደ ቆላ የሸሸ እንደሆነ …” ያሉት ይህን ስለሚያውቁ ይመስላል። እንደገመቱት፣ ካሳ ወደ ትውልድ ቦታው አፈግፍጎ ከርሟል። አዝማሪው ጣፋጭ “… መች ይዋጋል ካሳ” ያለው ይህን ሁኔታ በማጤን መሆን አለበት። ይሁን እንጂ፣ ካሳ ለጣፋጭ ያልተገለጠለት ጠንካራ ጎን ነበረው። ጠላቶቹ ሽሽቷል ብለው ሲዘናጉ እንደገና አፈር ልሶ ተነስቶ ማጥቃትና ማሸነፍ ይችል ነበር።

.

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ [መስመር ፬]

ወርደህ” የሚለውን ቃል አዝማሪው በዚህ ዝማሬ ውስጥ ሁለቴ ተጠቅሞበታል። መስመር 2 ላይ “ጉራምባ ሲወርድ” ብሎ ካሳን የገለጠውን ያክል “ወርድህ ጥመድበት” ብሎ ጎሹን ይጎተጉተዋል። የመፋለሚያውን ቦታ ቆላነት ያሳስባል፤ ወደ ቆላ ወረደ ይባላልና። “ጥመድ” በአማርኛ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከግጥሙ ዐውድ ጋር የሚሄደው “አሽክላን ዘረጋ፣ ወይም የጠፋ ሰውን አጥምዶ ሸምቆ ለመያዝ በጎደጎደ አደባ” የሚለውን ነው። ስለማይዋጋ ካሳን አድብቶ መያዝ እንደሚያዋጣ ጣፋጭ ሀሳብ እያቀረበ ነው።

በሽንብራው ማሳ” ሲል አዝማሪ ጣፋጭ ስለየትኛው ነው የሚያወራው? “ካሳ” ከሚለው ቃል ጋር እንዲገጥመለት ይሆን? የለም፤ እኔ እንደሚመስለኝ ቃሉ ታስቦበት የተመረጠ ነው። ደጃች ጎሹ የቋራውን ደጃች ካሳ አባርረው ደንቢያን በጃቸው ባስገቡበት ዘመን ከምግብ ሁሉ የሚወደውን የሽንብራ አዝመራ አውድመውበታል ይባላል። ጣፋጭ “ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ” ያለው ያንን አስታውሶ ይመስለኛል። አለቃ ዘነብ፣ “ያን ጊዜም ቋራ ሁሉ ጠፍ ሆኖ ነበር። ልጅ ካሳም ለባላገሩ ሁሉ ብዙ ብር ሰጡት። መቆፈርያ ግዛ ብለው … ከወታደሩ ጋር ብዙም ቆፍረው ዘሩ” ያሉት የሚታወስ ነው።

.

ወዶ ወዶ!” [መስመር ፭]

ወዶ ወዶ …” ጣፋጭ ይህን የተጠቀመው ለማሽሟጠጥ ነው፤ “ወድያ ወድያ” እንደማለት ነው። በዛሬ አማርኛ ብንመልሰው “ድንቄም ድንቄም” እንል ነበር።

.

በሴቶቹ በነ ጉንጭት ምዶ” [መስመር ፮]

ጉን” ለጉንጫም ሴት የሚሰጥ ቅጥል ነው። ጣፋጭ “በነ ጉንጭት” ሲል ደጃዝማች ካሳን በዘመኑ ያጅቡ ከነበሩት ቅሬዎች (ጋለሞቶች) አንዷን ጉንጫም አስታውሶ ይሆን?  “በነ ጉንጭት ምዶ …” ካሳ ከሴቶቹ ከነጉንጭት የለመደው ምንድነው? በጣፋጭ እይታ መሽቀርቀር፣ የእዩኝ እዩኝ ማለትን ተግባሮች ሁሉ ድምር የሆነው “ማንጓበብ” መሆኑ ነው።

ጣፋጭም ሆነ ካሳ፣ ወንድን እንደ መለኮት ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ሴትን እንደ ጉድፍ የሚያጣጥል ማኅበረሰብና ዘመን ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነቱ ዘመን አንድ ጦረኛ ጀብዱው ከከተሜ ቅሬዎች ተግባር ጋር መነጻጸሩን ሲሰማ ደም ብቻ እንደሚያጸዳው ውርደት አድርጎ ቢቆጥረው አይገርምም።

የጣፋጭን ፍጻሜ የወሰነችውም ይቺ የመጨረሻዋ መስመር ሳትሆን አትቀርም።

.

አዝማሪ ጣፋጭ (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም)

እና ድርሰቶቹ

*

“እወይ ያምላክ ቁጣ፣ እወይ የግዜር ቁጣ፤

አፍ ወዳጁን ያማል፣ ሥራ ሲያጣ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* *

“ክፉ የክፉለት፣ ይሆን የነበረ፤

ብሩን ‘ይሙት’ ብሎ፣ አለ የመከረ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * *

አያችሁት ብያየኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂመች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ  በነ ጉንጭት ለምዶ፤

(ሐሩ ቋዱ፣ ለውዙ ገውዙ አለ ቋራ፤

መንገዱ ቢጠፋ፣ እኔ ልምራ።)”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * * *

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ፤ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

[1820 ዓ.ም – ቋሚ ጨርቅ]

.

በዕውቀቱ ሥዩም

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

ምንጮች

ስለ አዝማሪ ጣፋጭ ሕይወት (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም) ያሉን ቀጥተኛ ምንጮች ሁለት ብቻ ናቸው። ቀዳሚው፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን (1875 ዓ.ም) የቴዎድሮስ ታሪክን የጻፈው አለቃ ወልደማርያም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን (1917 ዓ.ም) የጐጃምን ታሪክ የጻፈው አለቃ ተክለየሱስ ነው። ሁለቱም ስለ ጣፋጭ የጻፉት በጣም በጥቂቱ፣ ለዚያውም ባለፍ ገደም ነው። ጣፋጭም ለትውስታ የበቃው፣ አሳዛኝ እጣው ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ስለተቆራኘ መሆን አለበት።

ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሳቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 266፣ 821።

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)፤ ገጽ 94-102

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“፤ ገጽ 125-127።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

ደስታ ተክለወልድ። (፲፱፻፷፪)። “ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 169፣ 217።

Blanc, Henry (1868) “A Narrative of Captivity in Abyssinia“, p. 178.

Lejean, Guillaume (1865) “Théodore II: Le Nouvel Empire d’Abyssinie“.

አፈወርቅ ተክሌ እና “ቪላ አልፋ”

“ቪላ አልፋ” አዲሱ መልክ

ከበዓሉ ግርማ

(1961 ዓ.ም)

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገውን፣ በመደረግ ላይ ያለውንና ወደፊት የሚደረገውን ሁሉ እንደመጠጥ ብርጭቆ አንስተው የማስቀመጥ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ከተሜዎች አሉ። ሰሞኑንም ከሰላምታ በኋላ አርዕስተ ነገር አድርገው የያዙት ትችት ቢኖር ስለ አፈወርቅ ተክሌ (ወልደ ነጐድጓድ) አዲሱ የቪላ አልፋ መልክ ነው።

ትችቱ እንደተቺዎቹ የበዛ ቢሆንም አንዳንዶቹ፣

“ተርፎት፣ የሚሠራውን ቢያጣ ለመመጻደቅ ያደረገው ነገር ነው” ይላሉ።

ሌሎች ደግሞ (በተለይ የፍሮይድን ሳይኮሎጂ ከእጅ ጣታቸው እንደዋዛ የሚያንቆረቁሩት ተቺዎች) የዚህን ዓለም ጉዳይ ወደጎን ብለው፣

“አፈወርቅ ከአካባቢው ውጭ ወይም በላይ ሆኖ በራሱ የፈጠራ ዓለም ውስጥ ለመኖር የሚጥር ሰው በመሆኑ ነው እንዲህ ያለውን ቪላ የሠራው” በማለት ይናገራሉ።

“ግላዊ ልዩነቱን ለመግለጽ ያደረገው ነገር ነው” የሚሉም አሉ።

ያም ሆነ ይህ የነቀፌታዎቹ መነሾ ሠዓሊው አፈወርቅ ቪላ በመሥራቱ አይደለም። ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎችን የገነቡት በሰው አፍ አልገቡም። በግል መኖሪያቸው የሰማኒያና የመቶ ሺህ ብር ዘመናይ ቪላዎችን የሠሩት ዓይን አልበላቸውም።

“ታዲያ የአፈወርቅ ስም እንደ ትኩስ ድንች እያንዳንዱ አፍ ውስጥ የሚገላበጥበት ምክንያት ምን ይሆን?” ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።

ጐንደር የሚገኘውን የአፄ ፋሲልን ግንብ የሚመስል ባለአንድ ፎቅ መኖሪያ ቤት ባለንበት ክፍለ ዘመን በመሥራቱ ነው ልዩው ነገር። ሌላ ሰው ቢያስብም ሥራ ላይ የማያውለውን ነገር አፈወርቅ ግን በመሥራቱ ነው።

የዚህ አይነት ቤት (ወይም ካስል) በመሥራት አፈወርቅ በዘመናችን የመጀመሪያውና የመጨረሻው ሰው ሳይሆን አይቀርም። ምክንያቱም ቤቱን የቀየሰው መሐንዲስ G. Boscarino እንዳለው፤

“እንዲህ ያለው ቤት ውስጥ ከአፈወርቅ በስተቀር ሌላ ሰው ቢኖርበት፣ ቤቱ አሁን ያለውን ዋጋና ጥቅም ሊሰጥ አይችልም”።

አዎን፣ ከአፈወርቅ በስተቀር እንዲህ የመሰለውን ቤት አልሞ የሚሰራ የለም። የሚሰጠውን ጥቅምም በይበልጥ የሚያውቀው እሱው ብቻ ነው።

እንዲህ የመሰለውን መኖሪያ ቤት ለመሥራት ምን እንዳሳሰበው፣ ከተሰራ በኋላ የሚሰጠውንም ጥቅም እንዲነግረኝ ጠይቄው ነበር። ለማናገር ፈቃደኛ ቢሆንም ጊዜ አልነበረውም።

አናጢዎቹ በየደቂቃው ይጠሩታል።

በተመለሰ ቁጥር “የአገራችን አናጢዎች ለምን አንድ መስመር በትክክል ለመሥራት አይችሉም?” በማለት ይገረም ነበር።

እነሱም በበኩላቸው እሱ አሁን በቅርብ ጊዜ የሠራውን የእንሥራ ተሸካሚ ሥዕል፤ በተለይ ወተት መስሎ በጃኖ ጥለት የታጠረውን ቀሚሷን፣ አለንጋ የመሳሰሉትን ጣቶቿንና ሕልም መሳይ ውበቷን አይተው መገረማቸው አልቀረም።

ገና ተመልሶ ቁጭ ከማለቱም ቀለም ቀቢዎች ይጠሩታል።

አዎን፣ “የሰሜን ተራራ” የተባለውን ሥዕል (ኅብረ ቀለሙ ልብ መስጦ፣ ዓይን ማርኮ፣ የአእምሮ ሰላም የሚፈጥረውን) የሠራ ሰው ለተራ ቀለም ቀቢዎች ችሎታ ልዩ አድናቆት ሊኖረው አይችልም።

አሁንስ አፈወርቅን የሚጠራው ሰው የለም ብዬ በመተማመን ጥያቄዬን ወርውሬ፣ ብዕሬን ከወረቀት ለማገናኘት ስቃጣ፣ አንድ ጽጌረዳ አበባ የት እንደሚተክሉ የቸገራቸው፣ ወይም አበባ የያዘውን ሳጥን የት እንደሚያስቀምጡ ግራ የገባቸው ለምክር ይጠሩታል። ሳያማክሩት ያስቀመጡት፣ ወይም የተከሉት እንደሆነ ኋላ ማንሳታቸው አይቀርም።

አፈወርቅ ደጋግሞ እንደሚለው፣

“ማንኛውም ነገር ከተፈጥሮ ጋር በመዋሀድ በኅብረ ቀለሙና በአቀማመጥ አቅዱ ለአእምሮ ዕረፍትና ሰላምን ካልሰጠ አእምሯችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚመራ ነገር የመፍጠር ችሎታ ሊኖረው አይችልም። ከተፈጥሮ ኅብረት ጋር ሥራችንንና ኑሯችንን ለማስተባበር ካልሞከርን ውበትን ለመፍጠር አንችልም። ለኔ ከፍተኛው ምኞቴ ይህ ነው – ኅብረት ከተፈጥሮ ጋር። ይህንን ከፍተኛ ምኞት ለመግለፅ የምፈልገው በምሠራቸው ሥዕሎች ብቻ ሳይሆን በአኗኗሬም ጭምር ነው”።

ሠራተኞቹም ደከሙ። ከአንድ ሰዓት ጀምሮ ያራውጣቸው ነበር።

ጥሪው እያነሰ ሄደ። ቁጭ ለማለት ቻልን።

“ይህን ቤት መሥራት ከጀመርኩ ወዲህ የተማርኩት ነገር ቢኖር የቤት ሥራ ምን ያህል ብስጭትና ድካም እንደሚያስከትል ለማወቅ መቻሌን ነው። ወደ ሰላማዊው የሥዕል ሥራዬ የምመለስበት ጊዜ በመቃረቡ ደስ ይለኛል” አለና እግሩን ዘርግቶ ወለሉ ላይ ዘፍ አለ።

በሁለት ወር ያልቃል ተብሎ የታሰበው ቤት አሁን አራተኛ ወሩን ሊጨርስ ነው። በአራት ወር ውስጥ አፈወርቅ ሦስት ሥዕሎች ብቻ ነበር ለመሥራት የቻለው። የቀረውን ጊዜ ያዋለው በቤቱ ሥራ ላይ ነበር።

“ቪላ አልፋ” የተሠራው በአሥር ዓመት ፕላን መሠረት ሲሆን ቤቱን ለመሥራት አፈወርቅ ከሚሸጣቸው ሥዕሎች ዋጋ አንድ ሦስተኛውን ለዚህ ፕላን ቆጥቦ ነበር። ሆኖም የቆጠበው ገንዘብ ስላልበቃው የአዲስ አበባ ባንክ ብድር ሰጥቶታል።

ይሁንና በኔ በጠያቂው በኩል ሃያ ስድስት በሃያ ስድስት ሜትር ካሬ መሬት ላይ የተሠራው አዲሱ ቤት ይህን ያህል የሚያስደንቅ ወጭ የሚጠይቅ መስሎ አልታየኝም። አፈወርቅም ስንት ገንዘብ እንደጨረሰ ትክክለኛ ዋጋውን ሊገልጽልኝ አልፈቀደም።

ቤቱን የአፄ ፋሲልን ግንብ አስመስሎ ለመስራት ያነሳሳውን ነገር ሲገልጽልኝ እንዲህ አለ፣

“ስለ አፄ ፋሲል ግንብ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽና ይህ የጥንት ቅርሳችን ተሻሽሎ ለዘመናይ ኑሮ ለመዋል መቻሉን ለማሳወቅ ነው። አዎን የኮራና የከበረ ቅርስ እያለን የቤት ፕላን ከውጭ የምንቀዳበት ምክንያት አይታየኝም።”

አፈወርቅ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ምክንያት አለው።

በቤቱ ውስጥ ያለ ምክንያት የሚደረግ ነገር የለም። የአበባ ማስቀመጫው እሱ በፈለገበት ቦታ እንዲኖር የተደረገው ያለ ምክንያት አይደለም። የቤቱ ቆርቆሮ ቀይ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው። ቤቱ ነጭ ቀለም የተቀባበት ምክንያት አለው።

አንድ ሥዕል አንድ ግድግዳ ላይ በአንድ በኩል እንዲሰቀል የተደረገበት ያለ ምክንያት አይደለም። ቤቱ የተሠራው ለመኖሪያ ብቻ ሳይሆን ሌላ ምክንያት አለው። ቤቱም ቀለሙም አቀማመጡም – ሁሉም ባንድነት ተዋህደው ኅብረት መፍጠር አለባቸው።

“ይህን የመሰለ ቤት የሠራሁበት ምክንያት አለኝ። የሠራኋቸው ሥዕሎች በተሠሩበት አካባቢ እንዲታዩ ለማድረግ ሲሆን፣ እንዲሁም እንግሊዝ ሀገር ተማሪ ሳለሁና በታላላቅ አውሮፓ ከተማዎች እየተዘዋወርኩ ሥዕል በምሠራበት ወቅት፣ ብዙ ሠዓሊዎች ቤታቸው ይጋብዙኝ ነበር።”

“አሁንም በተራዬ እዚህ በመጋበዝ አንድ ኢትዮጵያዊ ሠዓሊ እንዴት እንደሚኖር ለማሳየትና ከዚህም አልፎ ከሀገራችን የታሪክ ቅርስ ጋር ለማስተዋወቅ ነው። እንግዶቼ በውብ ነገር ተከበው ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ ከማድረግ ሌላ የዕለት ኑሮዬን እንዴት እንደማሳልፍ እንዲያውቁም ጭምር ነው።”

“ከዚህ ቀደም ቤቴ በግንብ አጥር ተከቦ ታፍኜ ስኖር ነበር። አሁን ግን የቤቱ ሰገነት ወደ ውጭና ወደ እሩቅ ለመመልከት ያስችለኛል። ሰገነቱ ላይ ወጥቼ የአዲስ አበባ ተራራዎችን ለማየት እችላለሁ። ላንድ ሠዓሊ እንዲህ ያለው የመዝናናት ትዕይንት ጠቃሚው ነው።”

አዎን፣ ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

ቤቱ አንድ ሺህ ሜትር ካሬ ላይ መሠራቱ ምክንያት አለው። የመሬት ቁጠባን ለማስተማር ነው።

ሦስቱ መስኮቶች ሦስት አይነት ቀለማት የተቀቡበት ምክንያት አለው። የፀሐይዋን ዕለታዊ ጉዞ ተከትለው እንዲያንጸባርቁ ለማድረግ ነው።

የቤቱ ክፍሎች አቀያየስ ምክንያት አላቸው። ሃምሳ አራት ሥዕሎች ባንድ ጊዜ ለማሳየት እንዲቻል ታስቦ የተደረገ ነገር ነው። እንዲሁም እያንዳንዱ ክፍል ከየጠቅላይ ግዛቶች የሚገኙትን ጌጣጌጦች ማሳያ ሊሆን ይችላል።

የጸሎት ወይም የሀሳብ ማጠንጠኛ ክፍሉ የአክሱም ጽዮንን መልክ የያዘ ነው።

የምሥጢር በሩ ያለ ምክንያት አልተሠራም። አፈወርቅ ካንዱ ክፍል ወደ ሌላ ሳይታይ ለመዘዋወር እንዲችል ነው።

የጋራጁም ስፋትና ቀለም ያለ ምክንያት አልተደረገም። ሁለት መኪናዎች እንዲይዝ ከመሆኑም በላይ የጋራጁ ቀለም ከመኪናዎቹ ቀለም ጋር ተዋህዶ ኅብረትን ለመፍጠር እንዲችል ታስቦ ነው።

አዎን፣ በአፈወርቅ ቤት ያለ ምክንያት የተደረገ ነገር የለም።

በዓሉ ግርማ

በዓሉ ግርማ ፋውንዴሽን መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ

.

[ምንጭ] – መነን (ሚያዝያ ፳፱፣ ፲፱፻፷፩)፤ ገጽ ፲፮-፲፯።

የፒያሳው ኬዎርኮፍ ሕንጻ

የፒያሳው ኬዎርኮፍ ህንጻ

(ክፍል 2)

በሕይወት ከተማ

(… ከክፍል አንድ የቀጠለ)

 

በ1900ዎቹ መጨረሻ ማቲክ ኬዎርኮፍ በተባለ ነጋዴ ለሱቅነት የተገነባው ሕንጻ ለሃያ አመታት ያህል በዚሁ በመደብርነቱ ሲያገለግል ቆየ። ከስድስቱ የሕንጻ ክፍሎችም ሁለቱ (የዛሬዎቹ “ካስቴሊ” እና “አንበሳ ባንክ”) በዛን ዘመን የሕንጻው አካል አልነበሩም። ከ1928 ዓ.ም በኋላ ግን ይህ ታሪከኛ ሕንጻ ብዙ መሰናክል አጋጠመው። ሆኖም፣ ሕንጻውም በበኩሉ በርካታ አይነት ለውጦችን በማድረግ ከዘመኑ ጋር ለመሄድ ጥሯል።

Casa Littoria (1928-1933 ዓ.ም.)

በሚያዝያ 1928 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ (ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ በባቡር ሲሰደዱና ጣልያን ገስግሶ መዲናችን ሲገባ) የአዲስ አበባ ሕዝብ አራዳን መዝረፍ እና ማውደም ጀመረ። በሚቀጥሉት አራት ቀናት ውስጥ ብዙ ንብረት ጠፋ፤ እጅግ ብዙ ሱቆች፣ ሆቴሎችና ንግድ ቤቶችም ተቃጠሉ። የኬዎርኮፍ ሱቅም ይህ እጣ አልቀረለትምና ከአካባቢው ሕንጻዎች ጋር ተቃጥሎ በአጥንቱ ቀረ።

picture 08
ህንጻው በቃጠሎ ጊዜ  (ምንጭ – Fasil & Gerard – Plate 505)

ጣልያንም ወደ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የሕንጻ ባለሙያዎቹ የኬዎርኮፍን ሕንጻ ውበት ለማየት አልተቸገሩም። አፍርሰው በሌላ በመተካት ፋንታ እንዳለ ለማደስ ወሰኑ። አንዳንድ ለውጦችን ግን ማድረጋቸው አልቀረም።

Capture
የኬዎርኮፍ ሕንጻ ፕላን
picture 10
በጣልያን እድሳት ጊዜ  (ምንጭ – Cine ITTA` Luce Instituto)

ከጎን በምስሉ እንደሚታየው ፣ ዋነኛው ለውጥ “ሕ4” እና “ሕ5” ከህንጻው ጋር መቀላቀላቸው ነው። የሕንጻው አካል ለማድረግ የተጠቀሙበትም ዋነኛው መንገድ በቀኝ በኩል ላለው “ሕ5” (የዛሬው ካስቴሊ) የላይኛውን ፎቅ መስኮቶች ቅስት ማድረግ ነበር። በተጨማሪም ቀድሞ በ”ሕ1” እና “ሕ3” አናት እና ወገብ ላይ የነበረውን ተደራራቢ መስመር ወደ “ሕ5” እንዲቀጥል አደረጉ።

“ሕ2” እና “ሕ4” (ምንጭ – Cine ITTA` Luce Instituto)

በግራ በኩል ላለው “ሕ4” ግን እምብዛም ለማመሳሰል ጥረት የተደረገ አይመስልም። የውስጡ ፕላን እንዲገናኝና እንደ አንድ ወጥ ሕንጻ እንዲዋሐዱ ቢደረግም፣ ለአይን ግን እስካሁን ልዩነታቸው ጎልቶ ይታያል። “ሕ4” የሌላውን ሕንጻ ክፍሎች ዋነኛ ጸባይ (ከጥርብ ድንጋይ መሠራቱን) እንኳን አላሟላም።

በተጨማሪም፣ (ከእድሳት በኋላ) ጣራው ተነስቶ ወደውጭ ወጣ ብሎ የነበረው ገባ ተደርጎ የጣራው ተዳፋት በጣም አጭር ሆነ። እንዲሁም፣ የጣራው ቆርቆሮ እንዳይታይ ግድግዳው በትንሹ ወደላይ ከፍ ብሎ እንዲቀጥል ተደረገ።

የላይኛዋም ህንጣ (“ሕ6”) ከስሯ ጓደኛ ተፈጥሮላት አዲሲቷ እንጎቻ የራሷ ጣራና ትንንሽ መስኮቶች እንዲኖራት ተደረገ። የቀድሞዋ እንጎቻም ወደላይ ከፍ ብላ በአምስት ማእዘን ጎኖቿ ላይ የራሷ ቅስት መስኮቶች ተሰሩላት።

“ሕ6” ከእድሳት በኋላ
sketch 09
የመስኮቶች አቀማመጥ ከእድሳት በኋላ

እነዛ ትናንሽ አራት ማዕዘን መስኮቶችም ተደፍነው በግራ በኩል (“ሕ2” ክፍል) ያሉት በርና መስኮት ሁለቱም ዝቅ ብለው እንዲታዩ ተደረገ። በቀኝ በኩል (“ሕ3” ክፍል) ደግሞ አንደኛው መስኮት ከፍ ብሎ ከ“ሕ1” ጋር ሲቀላቀል፣ በሩ ግን ዝቅ እንዳለ በተዛነፈ ዲዛይን ተሠራ።(ምስል 21 – የመስኮቶች አቀማመጥ ከእድሳት በኋላ)

በመጨረሻም፣ መስኮቶቹ በሙሉ ያራት ማዕዘን ጠርዝ ባላቸው መስታወቶች ተቀይረው ከፎቁ ላይ “Casa Littoria” የሚል ጽሑፍ ካናቱ በትልቁ ተቀመጠበት። ህንጻውም በዚህ አዲሱ የፋሽስት ኢጣልያ አስተዳደር ቢሮነቱ ከ”ፒያሳ ሊቶሪዮ” አደባባይ ፊት ደረቱን ነፍቶ ቆሞ ካራት አመት በላይ አገለገለ።

kervekoff
ካዛ ሊቶሪያ  (ምንጭ – Berhanou Abebe Collection)

 

 የኢትዮጵያ የርሻ ባንክ (1930ዎቹ-1960ዎቹ)

 

ምንም እንኳን ጣልያን ወጥቶ ነፃነት ቢመለስም፣ ህንጻው ወደ ቀድሞው ባለቤት ወደ ኬዎርኮፍ ቤተሰቦች የተመለሰ አይመስልም። በኒህም ዓመታት፣ ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች (እርሻ ባንክ፣ ንግድ ምክር ቤት) በቢሮነት ማገልገል ጀመረ።

picture 14
የኢትዮጵያ የርሻ ባንክ  (ምንጭ – Postcards by “George Talanos, Addis Ababa”)

በ1950ዎቹ አካባቢ አሁንም አነስ ያለ እድሳት ተደረገበት። ይህም የሚታየው በተለይ ከላይኛዋ እንጎቻ ህንጣ ላይ ነው። አምስት ማዕዘኗ በጎባጣ መስኮቶች ፋንታ በአራት ማዕዘን መስኮቶች ተተኩ። ሶስቱ መግቢያ በሮችም የበር ፍሬም ለውጦች ተደርገውባቸዋል።

በእርሻ ባንክነቱ ዘመን
010-Haile-Selassie-Square
ህንጻው [በግራ] በእርሻ ባንክነቱ  ዘመን  (ምንጭ – Postcards by “George Talanos”)
043-Traffic-policeman
ሕንጻው  በርሻ ባንክነቱ ዘመን  (ምንጭ – Postcards by “Edit. National Photo Studio” )

 

ከኤልያስ ሆቴል እስከ ሮያል ኮሌጅ (1970ዎቹ-2000ዎቹ)

 

photo-1-5
ሕንጻው በቅርቡ ይዞታው  (ፎቶ በአንድምታ)
photo 2 (2)
ተመሳስሎ የተሰራው የመስኮት ድጋፍ  (ፎቶ በአንድምታ)

ከ1960ዎቹ በኋላ የተደረገው ዋነኛ ለውጥ “ሕ1” መሀል ላይ የነበሩት ሶስት ዋና መግቢያ በሮች ወደ ሁለት መስኮትና አንድ በር መቀየራቸው ነው። ይህንንም ለማድረግ ባለሙያዎች ከቀድሞው ሦስት በሮች ግራና ቀኝ የነበሩትን መስኮቶች አስመስለው በር 1 እና 3 ግርጌ የመስኮት ድጋፍና ጌጥ ከተመሳሳይ ድንጋይ አበጅተዋል።

ከመስኮት ወደ በር  (ፎቶ በአንድምታ)

በተጨማሪም፣ የ”ሕ1” አንዱን መስኮት (በግራ ያለውን) ወደ በር ለመቀየር ተወስኗል። ይህንንም ለማድረግ የቀድሞውን መስኮት ታችኛ ድጋፍ እና ጌጥ ጥርብ ድንጋዮች ሙሉ በሙሉ ነቅለው (ቆርጠው) ለማውጣት ተገደዋል። ከዚህም ሂደት የተረፈው የአሁኑ በር ጠርዝ በሊሾ ሲሚንቶ ለማስተካከል ሞክረዋል።

በህንጻው ሁለተኛ ፎቅ ወደ ባንኮኒ ያስወጡ የነበሩት ሰባት በሮች ከአንዱ በስተቀር (በቀኝ በኩል መጨረሻ ያለው) ሁሉም ወደ መስኮትነት ተቀይረዋል። የላይኛውም ህንጣ (“ሕ6”) እንደገና ሌላ እድሳት ተደርጎበት የመስኮቱ ማዕዘን በመጠኑ ሰፍቷል።

sketch 13
“ሕ6” በአሁኑ ይዞታ

በተጨማሪ ግን፣ ከግልጋሎትና አንዳንድ የቀለም ለውጥ ውጭ እምብዛም ለውጥ አይታይም። ከመጠቀም ብዛትና ከጥገና እጦትም እንደ ብዙዎቹ የሀገራችን ታሪካዊ ሕንጻዎች ጃጅቶ ይታያል።

በአሁኑ ጊዜ ይህ ህንጻ በቅርስነት ተመዝግቧል። በአሁኑም ይዞታው ህንጻው ሮያል ኮሌጅን፣ አቢሲኒያ ባንክን እና ካስቴሊ ሬስቶራንትን በውስጡ ያስተናግዳል። የካስቴሊ ቤተሰብ በጣልያን ወረራ ጊዜ በ1928 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደገቡ ይነገራል። ኋላም ጣልያን ካገር ሲወጣ አዲስ አበባ ቀርተው በ1940ዎቹ መጨረሻ ካስቴሊ ምግብ ቤትን ከፈቱ። ታዲያ ይህ ምግብ ቤት በምርጥ የጣልያን ምግብ አዘገጃጀቱ የአለም አቀፍ ተወዳጅነት አትርፏል። ብራድ ፒት እና ጂሚ ካርተርም ሳይቀሩ ስፓጌቲያቸውን በዚሁ ምግብ ቤት እንደጠቀለሉ ይወራል!

የኬዎርኮፍ ህንጻ ስልቶች

 

የኬዎርኮፍ ሕንጻ

discription-kevበመጀመሪያው የአሰራሩ ውጥን ብናየው የህንጻው ስልት (Architectural Style) በአጠቃላይ “እንዲህ ነው” ብሎ ለመፈረጅ ያስቸግራል። ነገር ግን ለያይተን ብንመለከት፤ (ሀ) ድርድር ቅስት መስኮቶች (Arched Windows)፣ (ለ) የጣራ ክፈፍ ስር ያለው ጌጥ (Entablature)፣ (ሐ) የህንጻው ወገብ እና ግርጌ ላይ የሚዞሩት ተደራራቢ መስመሮች (Stone Bands)፣ (መ) ቋሚ-መሳይ አምዶች (False Columns)፣ (ሠ) ሙሉ የጥርብ ድንጋይ ህንጻ ስራ፣ (ረ) ወጣ ገባ ማዕዘን ስራ (Quoins)፣ እንዲሁም (ሰ) የባንኮኒው አጋጌጥ መንገድ በአውሮፓ ከ1832-1911 በሰፊው ይሰራበት የነበረውን “Renaissance Revival” የተሰኘውን የሥነ ህንጻ ስልት ያስታውሰናል።

kev-descበተመሳሳይ መልኩ ደግሞ፤ (ሸ) የጣራው ክፈፍ ወጣ ብሎ አሰራር፣ (ቀ) የጣራው ተዳፋት ስፋት፣ (በ) የመስታዎቶቹ ፍሬም አሰራር፣ (ተ) የጣራው ክፈፍ ጌጥና ጉልላት (Fascia Board Ornamentation) (ቸ) የጣራ ስር ፎቅ (Dormer Floor)፣ እና (ኀ) ከአናት ያለችው ህንጣ አሰራር፤ የ “እስያ” የሥነ ህንጻ ጥበብ እና በተለይም ከ1829–1893 በአውሮፓ የነበረውን እስያ-ገረፉን “Victorian Architecture” ያስታውሰናል።

በአጭሩ ኬዎርኮፍ ህንጻ የተለያዩ የኪነ-ህንጻ ስልቶችን ያንጸባርቃል::

በጣልያን እድሳት ጊዜ ብዙዎቹን የ “Victorian Architecture” የሚያሳዩትን ስልቶች አስወግዶ ወደ  “Renaissance Revival” እንዲጠጋ ያደረገው ይመስላል። ማለትም (1) የጣራውን ክፈፍ ማስወገድ፣ (2) የጣራውን ተዳፋት አጭር አድርጎ ግድግዳውን ወደላይ በመቀጠል እንዳይታይ ማድረግ (3) የመስታወቶቹን ፍሬሞች በሙሉ በአራት መዓዘን መቀየር፣ (4) የጣራ ስር ፎቅን (Dormer Floor) ማስወገድ፤ ወደዚህ ስልት እንዲጠጋ ያደርገዋል። አሁንም ግን ሙሉ ለሙሉ ይህን የኪነ-ህንጻ ስልት ይከተላል ለማለት ያስቸግራል። በተጨማሪም ጣልያን ከህንጻው ፕላን ጋር ካቀላቀላቸው ህንጻዎች መካከል “ሕ4” ከጠቅላላው ስልት ጋር እንዲጣረስ አድርጎታል።

በአሁኑ ይዞታው ከጣልያን እድሳት እምብዛም የተለወጠ ነገር ባይኖርም፣ አንዳንድ በግዴለሽነት እንዲሁም ለግልጋሎት መመቸት ተብለው የተቀየሩ ነገሮች ከአጠቃላይ የህንጻው ቢጋር ጋር የማይሄዱ ሆነው እናገኛቸዋለን።

ለምሳሌ፣ አናት ላይ ያለችው እንጎቻ ህንጣ ከጎባጣ መስኮቶች ወደ አራት መአዘን መቀየሯ ከየትኛውም የህንጻው ቢጋር ጋር አይሄድም። እንዲሁም የግራና የቀኙ “ሕ2” እና “ሕ3” አለመመሳሰል የህንጻውን ሚዛናዊ እይታ ያዛባዋል። ወደ ባንኮኒው የሚያስወጡት በሮችም ወደ መስኮት መቀየር ባንኮኒውን ጥቅም ያሳጡታል።

በአጠቃላይ ይህ የመቶ አመት እድሜ ጠገብ ህንጻ ሂደታዊ ለውጥ ከሌሎች የአዲስ አበባ ህንጻዎች በልዩ መልኩ የሚታይ አይደለም። ማንኛውም ህንጻ ሕይወት ያለው ፍጡር ይመስል ያድጋል፣ ይጎረምሳል፣ ያረጃል፣ ይታደሳል፣ ይሞታል። የመዲናችንን ህንጻዎች በተመሳሳይ መልክ በቅርበት ብናስተውላቸው ተዘርዝሮ የማያልቅ የከተማችንን ታሪክ መልሰው ያንጸባርቁልናል።

(በክፍል ሶስት ይቀጥላል …)