ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ

ስለ ኢትዮጵያ ደራስያን

(ክፍል 4)

በተአምራት አማኑኤል

(… ከክፍል ሶስት የቀጠለ)

 

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ትውልዳቸው ሸዋ የሞቱበት አገር (+1931) በባት ከተማ በእንግሊዝ አገር ነው። በኢትዮጵያ ከፍተኛውን ትምህርት ፈጽመው በቤተ ክህነት ሲያገለግሉ ኑረው ሠላሳ ዓመት ያህል በቤተ መንግሥት ልዩ ልዩና ከፍ ያለ ሹመት ተቀብለው ከባድ የሆነ የኀላፊነት ሥራ የፈጸሙ ሰው ናቸው። የአሁኑ ማስታወሻ ስለ ደራሲነታቸው ብቻ የሚናገር በመሆኑ በሹመታቸው ስላስኬዱት ትላልቅ ሥራ ከዚህ ማንሣት የለብንም።

heruy-medal

ከጽሑፍ ሥራቸውም ዋና ሁነው የሚታዩን “ወዳጄ ልቤ”፣ “ጎሐ ጽባሕ” እና “ሀገረ ጃፓን” በመሆናቸው የቀሩት መጻሕፍቶቻቸው ግን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ስንኳ በብዙው ቢጠቅሙት፣ አሳባቸውንና ደራሲነታቸውን በሦስቱ መጻሕፍት ማግኘት ስለ ተቻለ ስለነርሱ ብቻ ባጭሩ እናመለክታለን።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ በጻፉት ሁሉ ዋና አሳባቸው፤

  1. በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ ሰው ሁሉ በፈጣሪውና በመንግሥት ዘንድ አኳያ መሆኑን ነው። የውነት ነው። ሲፈጠር ብልህና ሞኝ ሁንዋል፤ በሥራ ዕውቀትና ዕድለኛ በመሆን ከሰው የተሠራ አስፈላጊ የሆነ የመዓርግ ከፍተኝነትና ዝቅተኝነት ይህንንም የመሰለ ብዙ ልዩነት አለ። ነገር ግን በምንፈርድለትና በምንፈርድበት ጊዜ መሠረት ልናደርገው የሚገባን ሁሉም ትክክል መሆኑን ነው።
  2. በዘርና በሃይማኖት የመጣውን ልዩነትም እርስ በርሳችን ተቻችለን ከሌለ መቍጠር ይገባናል።
  3. የክርስቲያን ሃይማኖት በዓለም ከታወቁት ሃይማኖቶች ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ኑሮ የሚስማማ ነው።
  4. ሰው በማናቸውም ሰዓት ሞት እንደሚመጣበት ማሰብ ይገባዋል።
  5. ሰው የልማድ ባርያ ሳይሆን በነፃነት ሕጉንና ሥርዓቱን እያሻሻለ መሔድ አለበት።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ከጻፍዋቸው መጻሕፍት ከሁሉ ይልቅ ዕድለኛ ሁኖ ሕዝቡ አንብቦ የማይጠግበው “ወዳጄ ልቤ” ነው። እንዲህ ያለውን መጽሐፍ የሚጽፍ የእንግሊዙን ደራሲ የዮሐንስ ቡንያንን መጽሐፍ ያነበበ ሰው ብቻ መሆኑን የምንረዳው የዚሁኑ ደራሲ “የክርስቲያን መንገድ” የተባለውን መጽሐፉን ስናነብ ነው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ግን ንድፉን ስንኳ ከእንግሊዙ ደራሲ ቢቀበሉ፣ የጽሑፋቸውን ሕንፃ መልክና ጠባይ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ያውም የሚያምር ኢትዮጵያዊ አድርገውታል።

heruy-wedaje

ባሳባቸው የፈጠሩት “ወዳጄ ልቤ” የተባለው ሰው የርሳቸው ራሳቸው ወይም ክርስቲያን ሁኖ የክርስቲያንን ሕግ ለመጠበቅ የሚታገል ሰው ምሳሌ ነው። ወዳጄ ልቤ ለብቻው ሁኖ የእግዚአብሔርን ህላዌና የሕዝበ አዳምን፣ በተለየም የነፍስን ሁኔታ በሚያስብበት ጊዜ፣ ወይም እግር ጥሎት ከልዩ ልዩ ሰዎች ጋር ተገናኝቶ ክፋታቸውንና በጎነታቸውን በሚገልጥበት ጊዜ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ በተለየም በክርስቲያን ላይ የሚመጣበትን መከራ ሲያስታውስ፣ ተስፋ ሊቆርጥ ሲቃጣና፣ በርትቶ ሲታገል፣ ከባልንጀሮቹ ጋርና ለብቻው መሰንቆውን ይዞ ሲያንጐራጕር፣ በሠርግ አስመስሎ ስለ ክርስቲያን ሃይማኖት አጀማመርና፣ ድል እየነሣ በሔደበት፣ በሚሔድበትም ዘመን ሁሉ ያለበትን መከራ ሲተርክ፣ ፍጹም ክርስቲያናዊ ነው።

ወዳጄ ልቤ፣ “ሰው በየሱስ ክርስቶስ ካመነ በኋላ ከኃጢአት ላለመውደቅ ምን ቢሠራ ይሻላልን?” ብሎ የሚጠይቅ ወይም የዚህን አሳብ የሚያሳድር ሁኖ ይታያል። አንባቢው፣ ቁልፉን ወይንም መልሱን አገኘሁ! መጽሐፉ ሊነግረኝ ነው! ብሎ ሲጓጓ፣ “ብፁዓን እለ ተኃድገ ሎሙ ኃጢአቶሙ” ብሎ ያሰናብተዋል።

heruy-goh

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ስለ ሃይማኖትና ስለ ፖሊቲካ ስለ ልዩ ልዩ ጉዳይም ያሰቡትን ሁሉ ካንድ ላይ ሰብስበው ጽፈው ያወጡትን መጽሐፍ “ጎሐ ጽባሕ” ብለው ሰይመውታል። ጎሐ ጽባሕ ስለ ሃይማኖት የሚገልጠው አሳብ ንግግሩም ልዩ ቢሆን ከ”ወዳጄ ልቤ” አይለይም። ሕግንና ልማድን ማሻሻል ብላቴን ጌታ ኅሩይ፣ ሥራዬ ብለው የቆሙበት ዋና አሳብ በመሆኑ፣ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ቍጥር፣ ስለ ምንኵስናና ስለ ጋብቻ ሥርዓት፣ ስለ ጸሎትና ስለ ንስሐ ከጻፉት ክፍል፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ሥርዓት እየተሻሻለ የሚሔድበትን መንገድ መሠረት ባለው አካሔድ አስረድተዋል። ከቤተ ክህነት፣ ቤተ መንግሥትን መምራት ይገባኛል እያለ፣ በመንፈሳዊና በሥጋዊ ጕዳይ ሁሉ የበላይ አስተዳዳሪ ልሁን የሚል እንደማይጠፋ ስለ ተረዱት፣ የሁለቱንም ሥልጣን ወስነው ሁሉም በየክፍሉ፣ በየሥራው አላፊነት እንዳለበት፣ የሁሉ በላይ ግን መንግሥት መሆኑን አደላድለው ወስነዋል። ወገን ለሌለው፣ በዘር በሃይማኖት ለተለየ ሰውና ለእንስሳ ርኅራኄ እንዲገባ በብዙው ሰብከዋል። ለዛሬው ትውልድ ኢትዮጵያዊ አንዳንዱ ስንኳ የዚህ ዓይነት ምክር ባያስፈልገው፣ ካገራችን ሕዝብ ላብዛኛው አዲስ ነገር ሁኖ ታይቶት ከአሳባቸው አንዳንዱ ለመቀበል የሚያስቸግር ሁኖ ሳይታየው የማይቀር ነው፣ መጽሐፉ ለእንዲህ ያለው ክፍል ብርቱ አሳብ የሚያሳድርበትና ጥቅም ያለው ክርክር የሚያነሣ ነው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ገና ወደ ጃፓን አገር የመንግሥት መልእክተኛ ሁነው ሳይሔዱና ከዚያ በኋላ ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ስላይዋቸው አገሮች ሁነታ የጻፉዋቸው መጻሕፍት አሉ። በተስተካከለ አማርኛና ያላዩትን አገርና ሕዝብ ካዩት በሚያስቆጥር አነጋገር የመንገዳቸውን አካኋን የገለበጡበት መጽሐፍ ግን “ማኅደረ ብርሃን” (ሀገረ ጃፓን) ብለው የሰየሙት ነው።

heruy-japan

መጽሐፉ ከማያስፈልግና ከሚያታክት ዝርዝር ሳይገባ በወሬ የምናውቀው የጃፓን አገርና ሕዝቡ፣ ሃይማኖቱ፣ ያገሩ ልማድ፣ ሥልጣኔውና አስተዳደሩ ምን እንደሆነ ነግሮ የሚያጠግብ ነው። ደራሲው የተላኩበት ሥራ ከሕዝብና ከትላልቅ ሰው፣ ከንጉሠ ነገሥቱና ከንግሥቲቱ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የሆቴሉንና የባላገሩን፣ የሚኒስትሮችንና የቤተ መንግሥቱን እልፍኝ ታዳራሽ ወገኑንና ሥርዓቱን አይተዋል። ያዩትንም ላላየነው፣ ካየነው እንድንቆጥረው አድርገው ጽፈዋል። ከዚህም ሁሉ ጋራ ጃፓን ሕዝብ መሆን ከጀመረበት ዘመን አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን ታሪኩን እንድናውቀው ከሌላ ባለ ታሪክ እየጠቀሱ ባጭሩ ተርከውልናል። የባሕሩንና የመሬቱን፣ የጫካውንና ያትክልቱን ሁኔታ የሚነግረው ክፍል፣ ደኅና ሥዕል ሳይ፣ በሚስማማ ቀለም ነድፎ ያቀረበው ሰሌዳ ይመስላል። ክርስቲያኑ ኅሩይ፣ ክርስቲያን ያይደሉትን ወገኖች የአምልኮና ባህል የሚያዩት እጅግ ከፍ ባለ አስተያየት ነው። የጃፓን አምልኮም እንደ ሌላው አምልኮ፣ የእግዚአብሔርን ምስጢር ለማግኘት የሚጣጣር ሁኖ ስለታያቸው፣ ያገራችን ሕዝብ ደግሞ ባይቀበለውም በሰፊው እንዲመለከተው አድርገው ገልጠውታል።

ከዚያ በፊት ልዩ ልዩ መጻሕፍት በመጻፍ ብዙ ትግል ያየው የብላቴን ጌታ አእምሮና አማርኛ፣ “ሀገረ ጃፓን”ን በጻፈበት ጊዜ፣ ደርጅቶ ከፋ ካለ ደረጃ የደረሰ ሁኖ ይታያል።

አማርኛ ማሠሪያ አንቀጹን አርቆ፤ ከማህሉ ልዩ ልዩ አሳብ ጣልቃ ማግባት የተፈጥሮ ጠባዩ ነው ብለናል። ብላቴን ጌታ ኅሩይ አብዛኛውን ጊዜ ይህን ሳይከተሉ ንግግሩን ባጭር ባጭሩ ማሠር ልዩ ባሕርያቸው ነው። ከአማርኛ መርማሪዎች አንዳንድ ሰው ብላቴን ጌታ ኅሩይ አማርኛን በውጭ አገር (በኤውሮጳ) ንግግር ዓይነት እንጂ በተፈጥሮ ጠባዩ አያስኬዱትም ብሎ ጽፎባቸዋል። ነገሩም እውነት ይሆናል፤ ግን ደግሞ ደራሲ መከተልና ማሻሻል የሚገባው የሚጽፍበትን ቋንቋ ጠባይ ነው ስለ ተባለ፣ ይኸው ደራሲ የሚጽፈው፣ የንግግር ጣዕም ያለውና በፍጥነት የሚያስተውሉት ከሆነ፣ ከተራው ሕዝብ ተለይቶ መዓርግ ያለው ደራሲ ነው መባልን አያግደውም።

heruy-sikwarብላቴን ጌታ ኅሩይ ለሕፃናትና አእምሮ ለዋጭ የሚሆኑ ልዩ ልዩ መጻሕፍት ትተውልናል። እንዲያውም ከመጻሕፍት ዓይነት በጽሕፈት ለመግለጥ ያልሞከሩት ጥቂት ነው ለማለት ይቻላል። በሥራ የተፈተነው የተፈጥሮ ባሕርያቸው ትዕግሥተኛ ሲሆን፣ ጽሕፈት ሲልዋቸው ፍጥነታቸው የመኪና ያህል ስለ ነበረ፣ ካማርኛቸው በቀር በወጣቱ ኢትዮጵያዊ ላንዳንዱ የጻፉት ታሪክና ልብ ወለድ ታሪክ፣ ሌላውም ሁሉ አብዛኛውን ጊዜ ውዝፍ ሁኖ ይታየዋል።

ምክንያቱም በቤተ መንግሥት የነበረባቸው ከባድ ሥራ፣ ለሚጽፉት መጽሐፍ የተገባውን ምርመራ ለማጥለቅና ለማስፋፋት ፋታ አልሰጣቸው ስላለና ላገራቸው ሕዝብ በነበረባቸው ፍቅር፣ እርሳቸው ካወቁት ከብዙው ጥቂቱን ሳያስታውቁት ቢቀሩ “ዘደፈነ ወርቀ እግዚኡ” እንዳይሆኑ ሲሉ ይሆናል።

የሒሳብና የፍልስፍና የሕክምና የሥነ ፍጥረት ይህንንም የመሰለው ልዩ ልዩ ዕውቀት የተጻፈበትን ጽሑፍ ሥራ ቋንቋው የተጣራ ቢሆን፣ ያንኑ ዕውቀት የተማረ ሰው ካልሆነ በቀር፣ በሌላ ዕውቀትም ሊቅ የሆነ ሰው አያስተውለውም። የድርሰት ስጦታቸው አንዳንድ ሰዎች ግን፣ እንኳንስና የተማረ ሰው ተራው ሕዝብ ሳይቀር በሚያስተውለው ንግግር ልዩ ዕውቀታቸውን ለመጻፍ ተችልዋቸዋል። ቃለ እግዚአብሔር የሚያስተምሩና የሃይማኖትን መጻሕፍት የሚተረጕሙ፣ ስለ ሃይማኖትም የሚጽፉት ሊቃውንት፣ ምሥጢሩ ግድ እያላቸው ንግግራቸው ወይም አጻጻፋቸው አማርኛ አወቅሁ ለሚል ሁሉ የማይደፈር ሁኖ ይኖራል። ደግሞም ትምህርት ሲባል፣ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ያገር፣ የመንግሥት ወሰን የማያግደው አገሩና መንግሥቱም ቢለያዩ ሰንደቅ ዓላማው፣ ወይም ወገኑ አንድ የሆነ ነው። ለጊዜው ያገራችን ሊቃውንት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ያለው ትምህርትና ዕውቀት ባዕድ ሁኖባቸዋል።

 

(በክፍል አምስት ይቀጥላል …)

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s