አስኮ ጌታሁን እና ‘ዝምታ’
በአዳም ረታ
.
፩
“አስኮ ጌታሁን” የተባለው የጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል የአጭር ታሪኮች መድብል በውስጡ ሰባት ትረካዎችን ይዟል። በእነዚህም ትረካዎች ውስጥ ገኖ የሚታየው ሸካራ እውነታና እነዚህን ለመግለጽ የፈሰሰው አስገራሚ የገለጻ ቋንቋ ነው።
የጃርሶ ትረካዎች መቼት ከ1966 ዓ.ም በፊት ነው። በዚያን ጊዜ ወጣት ወይም ልጅ የነበረ ምን ያህል እነዚህ ታሪኮች ውበትና የዘመን ውክልናን እንዳቀፉ ሊሳተው አይችልም። ትረካዎቹ በሆነ መልክ የባህላችን ታሪክ፣ በሌላ መልክ ደግሞ የትዝታ እና የናፍቆታችን ሩካቤዎች (Communications of Nostalgia) ናቸው።
እነዚህ ውበትና ማህበራዊ ሀላፊነት የተመዘገበባቸው ትረካዎች ከተለያዩ የሥነጽሑፍ ሂስ ትወራ፣ የስነልቡናና የፍልስፍና መስመሮች አንጻር ሊታዩ ይችላሉ። ሆኖም ሁሉንም በዚህ መልክ ለማንበብ መሞከር ራሱን የቻለ ግዙፍ ስራ ነው። በከፊል ከጊዜ፣ በከፊል ከሀያሲነት ዕውቀት እጥረት ለማስታረቅ የመጽሐፉን “መሪ ታሪክ” (አስኮ ጌታሁን) ብቻ በመውሰድ፣ እንደገናም ከዚህ ትረካ ውስጥ አንድ ሴማ (Theme) ብቻ በማውጣት ንባብ ለማድረግ እሞክራለሁ።
ከሰባቱ ትረካዎች “አስኮ ጌታሁን”ን የመረጥኩበት ምክንያት የመጽሐፉ ማሰባሰቢያ አርእስት ስለሆነ ሳይሆን የ“አስኮ” ትረካ አጻጻፍ ከሌሎቹ የተለየ በመሆኑ ነው። በዚህም (ትረካ የተለየ መሆኑ) ደራሲው/ተራኪው ምን ሊነግረን ፈልጎ እንደሆነ ከመጠርጠር የመጣ ነው። አንድ የኪነት ስራ ከደራሲው እጅ ወጥቶ አንባቢ ዓይን ስር ሲያርፍ ባለው ማህበራዊ ዐውድ፣ በግለሰቦች የባህርይ ዝንባሌና አድልዎ የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። ይሄ ንባብ በመጠኑ የእኔም አድልዎ ነው።
“አስኮ ጌታሁን” 12 ገጾች ሲኖሩት በሰላሳ አንቀጾች የተከፋፈለ ነው። የትረካው አንጻር ገለልተኛ፣ ከፊል ሁሉን አወቅ ነው። አስጨናቂ የደይን ክስተቶችን ተራኪው ሲጽፋቸው ቋንቋው ውስጥ ሐዘን የለም። ራሱም ምን እንደሚሰማው አይገልጽም። ትረካው በስፋት ነገሮችን ከውጭ ስለሚገልጽ ተራኪው ስለአስኮ ስነልቦና ከእኛ የተለየ ብዙ ነገር አያውቅም ብለን እንድንጠረጥር ያደርገናል።
ታሪኩ እንዲህ ነው፤ ጌታሁን ፍቅረኢየሱስ (አስኮ ጌታሁን) ከገጠር አዲስ አበባ ይመጣሉ። አስተማሪነት ይቀጠሩና ወሎ ጠቅላይ ግዛት ደሴ ወ/ሮ ስህን ት/ቤት ይሄዳሉ። እዛ በአስተማሪነት ብቻ ሳይሆን በትርፍ ጊዜያቸው ጫማ ጠጋኝ በመሆን ራሳቸውን ይጠቅማሉ፤ ሕብረተሰቡንም ያገለግላሉ። ከሚሰሩበት የትምህርት አስተዳደር መዋቅር ወጥተው በሐሳብ ከሚመስሏቸው ወገኖቻቸው ጋር በመሆን በየገጠሩ ገበሬ ወገናቸውን ፊደል ያስቆጥራሉ። በተጨማሪም ስለ ትምህርት አስፈላጊነት የሚሰብክ ፍልስፍናቸውን በተመቻቸው ቦታ ያነሳሉ፣ ይከራከራሉ።
እኒህ ድርጊቶቻቸው ግን “አገር እናስተዳድራለን” በሚሉ ግለሰቦች አልተወደዱም። በሥርዓቱም ማሳደኛ ጥበብ አስኮ ጌታሁን በአካባቢው ነዋሪዎች እንዲጠሉ፣ እንዲጠረጠሩና እንዲሸሹ ይደረጋል። አልፎ ተርፎ በመገለል መቀጣቱ ሳይበቃቸው የአካልና የሕግ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። በአንድ ወቅት በተፈጠረ ቀላል አምባጓሮ መሀል ጣልቃ የገቡ እናታቸው ይሞታሉ። አስኮም ለአጭር ጊዜ ይታሰራሉ። ከዚህ አጭር እስር እንደወጡም ብዙ ሳይቆይ ሰበብ ተሰርቶ በሐሰት ተወንጅለው ሃያ ዓመት ተፈርዶባቸው አዲሳባ ከርቸሌ ይወርዳሉ።
ከአስራ ስምንት አመታት በኋላ ከከርቸሌ ነፍስ ይማር ይፈታሉ። የአስተማሪነት ነገር ተረስቶ፣ ጤንነታቸውም ተቃውሶ አዲሳባ ተክለሃይማኖት አደባባይ በጫማ ሠሪነት ‘እየተዳደሩ’ ይኖራሉ።
፪
አንድን አጭር ታሪክ አንብበን ስንጨርስ የተራኪውን ሃሳብ ወይም የታሪኩን መልእክት ለማወቅ “ተራኪው/ደራሲው ምን ለማለት ፈልጓል?” የሚል ጥያቄ መጠየቃችን አይቀርም። በእኔ ግምት ደራሲው ስለ ‘ዝምታ’ ለመጻፍ መሞከሩ ነው። ምንም እንኳን በራሴ አድልዎ የድርሰቱ መልእክት ዝምታ ነው ብዬ ብነሳም የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ትርጉም አስሰናል ሊሉ ይችላሉ።
ጥቂት ምሳሌዎች እነሆ፤ አንዳንድ አንባቢ “በጥቅሉ ስለ አንድ ሥርዓት ጭቆና ያሳያል” ብሎ ይደመድማል። አንዳንዱ “ባለታሪኩ የነበረበት የፊውዳል ሕብረተሰብ ብዙ ዜጎችን ምሕረት በሌለው ተመሳሳይ መንገድ በሚጨቁንበት ወቅት እምቢተኛ ግለሰቦች መኖራቸው አይቀርም። ግን እነዚህን እምቢተኞች ስለምን መሰል ተጨቋኞች ያገሏቸዋል? እኩል እየተጨቆኑ ለምን እኩል እምቢ አይሉም?” አይነት ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል።
ሌላው ደግሞ “አስኮ ጌታሁን ራሱን በነጠላ ለአደጋ በማጋለጡ ፍዳ ዘንቦበታል፣ ስለሆነ ይኼም ስለ ፖለቲካ ድርጅትና ስለ መሰሉ ድርጅቶች መኖር ጠቀሜታ ያሳየናል። አለበለዚያ ‘ብቻውን የታገለ ብቻውን ይሞታል’ አይነት ይሆናል፤ ትረካውም ስለዚህ አይነት ነጠላ መሥዋዕትነት ሊያሳየን የተነገረ ነው” ሊለን ይችላል።
አንዳንድ አንባቢዎች ደሞ “ለሚያምኑበት ዓላማ ፊት ለፊት ተጋፍጠው በዚህ ሰበብ የሚመጣባቸውን መሥዋዕትነት ስለሚቀበሉና ስለሚጠፉ ግለሰቦች አጢነናል” ሊሉ ይችላሉ። አንዳንዱ “ስለ ተዛባ ማህበራዊ ሩካቤና ሕብረተሰቡ ደካማ አሉባልተኛ በመሆኑ ለፍሬ የታገለለትን ግለሰብ ታሪክ የተዛባ መንገድ ተጠቅሞ መረዳት እንደሚሞክር (‘አስኮ ትልቅ የከሰረ ነጋዴ ነው’ ወይ ‘ሚስኪን’ ወይ ‘እብድ’ ነው) ለማሳየት የተጻፈ ነው” ሊሉ ይችላሉ።
እነዚህ ሁሉ አማራጭ አተረጓጎሞች ግን እንደሚመስለኝ ከሚፈለገው በላይ አድልዎ ባለበት ግፊት የሚነቃነቁና ጠባብ የሆኑ ናቸው። “ደራሲው ለምን ለአተረጓጎም እንዲቀለን እሱ ራሱ ልንረዳለት የሚፈልገውን አንድ ማዕከላዊ ሴማ በሚጎርፍ ቋንቋ አውጥቶ አያሳየንም ነበር?” ብለን ልንጠይቅም እንችላለን። ለምሳሌ፣ ድርሰቱ መጀመሪያ ላይ ጃርሶ ስለ አስኮ ተክለቁመና/መልክ በስፋት ገልጿል። ስለ ሥራው አካላዊ አካባቢ ብዙ የተብራራ ነገር አበጅቷል። “ለምን ታዲያ የዝምታን ጉዳይ በስፋት አልተናገረውም?” ብለን ልንጠይቅ እንችላለን።
ግን ሴማዎች የሚቀናበሩበት ደረጃ ይኖራል። በግልጽ እንዲህ ነው ከሚለው ጀምሮ በትንሽ ልፋት እስከሚገኝ ትርጉም ድረስ። የኋለኛውን ጥልቅ ሴማ (Deep Theme) እንበለው። የዝምታን ሴማ መዝዤ ሳወጣ “በአንተ ፍላጎት የመጣ አተረጓጎም ምኞት ነው” እንኳን ብባል (በተለያየ መልክ በደግግሞሽ ንባብ የሚከሰቱ) ደጋፊ ምልክቶችንና ይሄን ሴማ አጥረው የያዙ የመረጃ እብነ ወሰኖችን ድርሰቱ ውስጥ እናገኛለን።
ትረካው ውስጥ ወዳለው የዝምታ አወቃቀር ለመግባት ግን የሆነ ቀዳዳ ያስፈልገኛል። ዝምታን ተርትሬ ለመረዳትና የድርሰቱ “ዋና አጥንት” እሱ ነው ለማለት የሆነች ቁጢት ቆንጥጨ መያዝ ነበረብኝ። ይህቺ ቁጢት ‘ታስፈሩኛላችሁ’ የምትለዋ ቃል ናት።
የአስኮ ታሪክ በአስራ ሁለት ገጽ ብቻ መቅረቡ ‘አንዱ’ ምክንያት ንግግር ድርሰቱ ውስጥ አለመኖሩ ነው። ይሄ የተሰወረው ወይም ተሸርፎ የቀረበው ከፊል ንግግር የአስኮ ነው። የአስኮ ጌታሁን ዝምታ ወይም ጸጥታ የድምጽ አለመኖርን ወይም መሰወርን ይጠቁማል። ዝምታ ማለት (በሳይንሳዊ ትርጉሙ) በጆሮ የስሜት ሕዋሳት ልንቀበላቸው የሚቻሉ የድምፅ ሞገዶችን ከአፋችን አለማውጣት ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ ከሰፋና ከበረታ ከአፍ የወጣውን የራስ ድምፅ መስማት አለመቻል ወይም በሌላ የውጭ አካል ወይም የግል አቋም መከተርንም ይጨምራል። የዝምታን ትርጉም ትንሽ ለማብራራት አንዳንድ ጥያቄዎች በመጠየቅ እነሳለሁ።
አንደኛ እዚህ የምንነጋገረው ስለ ሰው ልጅ ነው። በዓለም ላይ ደሞ ድምፅ የሚያወጣው የሰው ልጅ ብቻ አይደለም። በራሳቸው የተፈጥሮ ግፊት ድምፅ ማውጣት የሚችሉና የማይችሉ አሉ። ሰው የሰራቸው ሜካኒካዊ ነገሮች ሁሉ ከራሳቸው ግፊት (Volition) ድምፅ አያወጡም። ይሄን ልዩነት የሚያሳይ የቃል አጠቃቀም ይኑረን አይኑረን አላውቅም። ምናልባት ሊኖር ይችል እንደሆነ በማለት ከቃላት ትርጉምና አጠቃቀም በመነሳት ልዩነት ለማበጀት ሞክሬ ነበር።
በመዝገበ ቃል ፍቺ ‘ዝምታ’ እና ‘ጸጥታ’ እንዲህ ይተረጐማሉ፤
- ዝም፤ – መጨረ (ቁጥር)
- ዝምታ፤ – ጭጭ፣ ቃል አለመስጠት፣ አለመናገር
- ዝም አለ፤ – አረመመ፣ ከመናገር ተከለከለ
- ጸጥታ፤ – መርጋት፣ ማረፍ፣ መቆም፣ መጨመት
(“ዐዲስ መዝገበ ቃላት” በደስታ ተክለወልድ ፲፱፻፷፪)
‘ደኑ ዝም ያለ ነው’ ማለት እንችላለን? ‘ደኑ ጸጥ ያለ ነው’ስ? አንድ በዕቃ የተሞላ ባዶ ክፍል ውስጥ ብንገባ የሚያጋጥመን ዝምታ ነው ጸጥታ?
ለምሳሌ፣ በአማርኛ ፊደል ጸጥታ የሚጻፈው በ‘ፀ’ አይደለም። ምክንያት ይኖረው ይሆን? በደስታ ተክለወልድ አባባል የጸጥታ ሥሩ ግዕዝ ነው። ከዛ ወደ አማርኛ የገባ የትርጉም ልዋጤ ይኖር? ብዙ የማይናገር ሰው ‘ዝምተኛ’ ይባላል (‘ጸጥተኛ ነው’ አይባልም)። ከአንደበት ጋር የተያያዘ ነው (ምላሳም፣ አፋም፣ አፈኛ እንደመሳሰሉ ቃላት)።
‘ዝም’ የሚለው ቃል ለሰው የሚቀርብ ነው። ምክንያቱም አብሮት ቋንቋ መናገርና ቁጥር ይጠቀሳሉ። ‘ጸጥታ’ የሚሰጠው ፍቺ በመጠኑ ሰፊ ነው ብለን ልንጠረጥር እንችላለን። ምንም እንኳን ይሄ ፅንሰ ሃሳብ የበረታ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም እኔ በመጠኑ አድልዎ ላስገባና እዚህ ንባብ ውስጥ የምጠቀመው ‘ዝምታ’ የሚለውን ቃል ይሆናል።
ዝምታን ከሰው ልጅ ካያያዝነው ባህላዊ እሴት ይሆናል። እንደማንኛውም ባህላዊ እሴት ይተረጎማል። ዝምታ በባህላችን አሻሚ ወይም አያኖአዊ ቦታ አለው። የአነጋገር ምሳሌዎች በመውሰድ ማረጋገጥ እንችላለን።
በደማሪ መልኩ፤ (“ካልተናገሩ ደጃዝማችነት ይቀራል”/ “መልካም ምላስ መልሕቅ ነው”/ “ዝም አይነቅዝም”)
በቀናሽ መልኩ፤ (“በለፈለፉ አፍ ይጠፉ”/ “አፍ ሲከዳ ከሎሌ ይብሳል”)
እዚህ ንባብ ውስጥ የምንነጋገርበት ዝምታ ሰዎች እየተወያዩ እያሉ ተራ ለመጠበቅ የሚወስዱትን እፎይታ አይደለም። በተጨማሪም በባህል አወዳዳሪ ጥናት እንደሚደረገው አንዱን ባህል ከሌላው ‘ዝምታ ያደንቃል’/‘ማውራት ያደንቃል’ በሚለው አፈራረድ ስር የሚገባም አይደለም።
እዚህ የማነሳው የዝምታ ፅንሰ ሃሳብ ልቀት ያለውን፣ ግለሰቦች በቋንቋ ከመሰል የሕብረተሰብ አባላት ለመገለል የወሰዱትን የጓነ መገንጠል (Radical Split) ለመጥቀስ ነው።