አስኮ ጌታሁን እና ዝምታ
(ክፍል ሦስት)
በአዳም ረታ
.
(ከክፍል 2 የቀጠለ)
፭
የፈጠራ ሥራ ከተጨባጭ ዓለም አንዳንድ እውነታዎች መውሰድ እና በነዚህ ላይ (የምናብ ችሎታና ቴክኒክ በሚፈቅደው መሠረት) አማራጭ ምትሀታዊ እውነታ ወረቀት ላይ በፊደላትና በቃላት መገንባት ነው። ይህ ማለት መጀመሪያ እውነታ ነበር፤ ወይም ተጨባጭ ዓለም የሚባለው። የመጻፍ ድርጊት አሰፋፉና አጠላለቁ ይለያይ እንጂ በስሜት ሕዋሶቻችን የመዘገብነው እውነታ ነው።
የፈጠራ ሥራዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕይወት ራሷ በድግግሞሽ የተሞላች ናት። እዚህ ጋ ተራራ አለ፣ ደሞ እዛጋም አለ። እዚህ ጋ አውቶቡስ ማቆሚያ አለ ደግሞ ፈቀቅ ብሎ ሌላ አለ ይቀጥላል። እዚህ ይዘፈናል እዚያም ይዘፈናል። አንዳንድ የፈጠራ ስራዎች እንደውም በድግግሞሽ የተናጡ ናቸው። ብዙ ጊዜ በተራኪው ችሎታ የመድገም ግዴታዎች ተቀናብረው ስልት ተበጅቶላቸው ትክክል እንዲሆኑ ይደረጋል፤ ይከየናሉ። ድግግሞሾች በቃላት ደረጃ፣ በሀረግ ደረጃ፣ በአንቀፅ ደረጃ፣ በኩነት ደረጃ ሊመጡ ይችላሉ።
“አስኮ ጌታሁን” ድርሰት ውስጥ የተቀናበረ ምት (Rhythm) አለ። ይህም የአጭር ታሪኩን አገነባብ ግጥማዊ ያደርገዋል። በኪነ አገነባብ ብቻ ሳይሆን በቦታ ደረጃ ሲሜትሪ እናያለን። ስለ ቦታ ሲሜትሪ ጥቂት ልበል።
የኢትዮጵያ ከተሞች አሰታተር በአንድ ትልቅ ከተማ (አዲስ አባ) ቁንጮነት ይጀምራል። የተቀሩት ከተሞች አነሰም በዛም በዚህ በቀዳማዊት ከተማ (Primate City) የሚደረገውን ኮፒ የሚያደርጉ ቀሽምነታቸውና እርፍናቸውን ከዚህ ዋና ከተማ እድገትና መበላሸት ጋር የሚያያይዙ ናቸው። በዚህ አገነባብ ውስጥ ጠቃሚ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕብረተሰብ ማፈኛ መሠረተ ልማቶች በተቀናበረ የተዋረድ መረብ ይሰራሉ።
ይሄ የመቆጣጠሪያ ተዋረድ በተብራራም ይሁን ባልተብራራ የስራ ክፍፍል መደጋገፍ ያለበት ነው። በትልቁ ከተማ የአገልግሎት ተቋሞች ከዝቅተኛው እስከ ከፍተኛው ድረስ ያሉበት ነው። ከክሊኒክ እስከ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል። ከቄስ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች። ከጠላ ቤት እንከ ታላላቅ ሆቴሎች። ትንንሽ የተባሉ ማዕከሎች (የጠቅላይ ግዛት ከተሞች፣ የአውራጃ ከተሞች፣ የወረዳ ከተሞች) ድርሻቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በስራ ክፍፍሉ መሰረትና የተለየ የቁጥጥር ስርዓት ወደሚያነቃንቀው ወደ አዲስ አባ ይሸጋግራሉ።
አለም በቃኝ ያለው አዲስ አባ ከርቸሌ ነው (ምንም እንኳን በዘወትር ቃል አጠቃቀም ‘እከሌ ከከርቸሌ ወጣ’ አንልም። ‘ወረደ’ ነው። አዘቅት ነው)። ከከርቸሌ በኋላ አስኮ የሰዎችን የአሰፋፈር ስልት ተከትሎ በየትም ደረጃ ባሉ ከተሞች ይኖራል ብለን በምንገመተው የቁጥጥር ጫማ ስር ያርፋል። በአጭሩ የጭቆና ሪትም ወይም ምት አለ።
አስኮ ጌታሁን “አንዳንዴ እንኳን ሳላስበው ዓለም ሰፊ አፍ፣ ሰዎች ሁሉ ጥርሶቿ ይመስሉኛል” (አንቀጽ 12) ሲል ዓለም ማለቱ አገሩን ነው። የልምዱ ስፋት ፕላኔታዊ አይደለም።
በተዋረድ በሚሰራ ዘመናዊ አስተዳደር ባለው አንድ ሉዓላዊ ክልል የተክለሃይማኖት አደባባይ የተለዋጭነት እሴት (Metaphorical Value) ሰፊ ነው። ተክለ ሃይማኖት ኢትዮጵያዊ ቅዱስ ናቸው። ከእስር ቤት ሲወጣ የተጠለለው እሳቸው በተሰየሙበት ደጀ ሰላም ነው። ህብረተሰቡ ከገነባቸው መንፈሳዊም ይሁን ዓለማዊ መሸሸጊያዎች ለአስኮ ያዳላ ወይም በሩን የከፈተ የለም። አላመለጠም። አስኮ ቦታ ቢለዋውጥም ያለበት የህልውና ስፍራ አንድ ነው። በሕይወት ጎዳና ሲጓዝ ተመልሶ የመጣው ወደነበረበት አዲስ አባ ነው። ክብ ነው።
ይሄ ስለ ጭቆና ሁሉ ቦታ መኖር (Omnipresence) ብቻ ሳይሆን ስለ ቦታ ምት ይነግረናል።
ከታሪኩ ጀርባና ፊት እየተወሰወሰ ከመጣው የጭቆና ስልት ጋር አብረው የሚነቃነቁ ድርጊቶች አሉ። አንዱ ጫማ ስራ ነው። ሁለተኛው የማይሳትና ቁልፍ የሆነው ‘ታስፈሩኛላችሁ’ የሚለው ቃል ነው። ይሄ ቃል ውይይት (Dialogue) ተከትሎ አልመጣም። ምክንያቱም ውይይት ሊደረግ የሚቻልበት ሁኔታ አይደለም። በዚያን ‘ነጠላ’ ወቅት ባየው ነገር ተገርሞም አይደለም። ከሃያ አመት ልምዱ ነጥሮ የወጣ ቃል ነው።
ይሄ ቃል ታሪኩ ውስጥ አራቴ አለ።
አንደኛው በክፍል አንድ (ሰሌዳ ሀ) ላይ (ሁለት ጊዜ)፣ ሁለተኛው ታሪኩ መዝጊያ ላይ (ሰሌዳ ሀ’) (ሁለት ጊዜ)። በዚህ ሂደት በሁለት ሰሌዳዎች (ሀ እና ለ) ላይ የሰፈረው ታሪክ ውህደት ያገኛል። ተራኪው ትረካውን በ ለ-ሀ-ሀ’ ሞዴል ቢሰራው ኖሮ በድርሰቱ ውስጥ ያለው ጥብቀትና ትስስር ይጠፋ ነበር።
ድግግሞሽ እዚህ የቋንቋና የኩነት ነው። ‘ታስፈሩኛላችሁ’ ቃል ነው። በተደራቢም በአካላዊ ንቅናቄ የሚሰራ በመሆኑም ኩነት ነው። አንዱ ምዕራፍ ወይም ሰሌዳ ከሌላ ሰሌዳ የመጣውን ድምጽ ተቀብሎ ማሚቶ እንደሰራም ይቆጠራል። ኤሚሌ ዞላ ‘ምት ለድርሰት አካልና ጠንካራ ትስስሮሽ ይሰጠዋል’ ይላል፤ ወይም አንድ ሀሳብን ወይም ስሜትን ያጠናክራል።
፮
ጫማ ስራ በሁለቱም ሰሌዳዎች (ሀ/ለ) ለአስኮ ችግር መቅረፊያ የኢኮኖሚ መሳሪያዎች ናቸው። ከሰሌዳ “ሀ” ላይ ግን የተለየ ሁኔታ ይከሰታል። ጫማ መስራቱን እንደ ሰሌዳ “ለ” ለራሱ መጠቀሚያ አያደርግም። ለሚሰራው ስራ የሚቀበለው ክፍያ ለምስማሮቹ መግዣ የሚበቃውን ያህል ብቻ ነው (አስኮ እንደሚለው)።
የሰው ልጅ ከዛፍ ወርዶ ቆሞ ለመሄድና ተፈጥሮን እያወቀና እየታገለ ለራሱ ጥቅም እያዋለ እንዲመጣ የረዳው አንዱ ብልቱ ወይም የአካሉ ክፍል እግር እንደነበረ ሳይንስ ይነግረናል። በአምልኮ ውስጥ እግርን ካሳከከ ‘ጉዞ አለብህ’ ይባላል።
ጫማ ከእግር ጋር የተያያዘ ነው። እግር ጉዞ ነው። ጫማ ምን ተምሳሌት እንዳለው በአገራችን በበቂ ባይታወቅም (በህልም አፈታትና በዘይቤ) ጌታሁን ሁሉን ነገር አጥቶ እስከ መጨረሻው ድረስ ግን የጫማ ነገር እየተከተለው መምጣቱ አንድ ፍቺ ቢኖረው ነው ብዬ እገምታለሁ።
አንዱ ፍቺ በቴክኒክ ደረጃ ታሪኩ እንዳይረግብ የያዘው ሞቲፍ ቢሆንም ከምንነጋገርበት የዝምታ ጉዳይ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማግኘት መጣሬ አልቀረም። አስኮ የግል ቦታ (Personal Space) አለው። ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ እዚህ ጠባብ የግል ስፍራ ውስጥ ቀዶ ለመግባት የሚፈልግ የለም። የጭቆና እና የማዋረድ መሳሪያው አካላዊ መሆኑ አንሶ (እስር ቤትና ከቦታ ቦታ መንከራተት) የድምጽና የቋንቋ ጉዳይ ይደረብበታል። የሚናገራቸውና የሚያናግሩት ሰዎች ጥቂት ስለሆኑ የግል ስፍራው ባብዛኛው ጸጥታ የወረሰው ነው። ጫማ ሰሪ በመሆኑ ምስማርና ቆዳ ሲቀጠቅጥ ድርጊቱ ከእሱ የበለጠ ድምጽ እንዲኖረው አያደርገውም?
ካለፈው ታሪኩ አብሮት የመጣው ጫማና ዝምታ ነው። ጫማ የሚሰራው ችላ ለሚሉት ያልፈለገውን፣ ያልተከመረበትን ቅጽል ለሚሰጡት በርቀት ንቀው ለሚያዩት ሰዎች ነው። አስኮ ከጫማው ጋር ሲነጋገር ይውላል ብለን እንኳን ማለት አንችልም።
አስኮ ለራሱ ጫማ እንደማይሰራ ለሚሰራላቸው ሰዎች ጉዞ አስቦ ነው? ወይስ በንግግር እንዳደረገው ሂሳብ ሲሰጡት በቋንቋው እንደሚያሽሟጥጣቸውን በኩነት ማሽሟጠጡ ነው? ወይስ የታሰረ ቋንቋውን ወደ ፊት ነጻ የሚያወጣበት አንድ ድርጊቱ? ማለት አብዶ ከጠፋ በኋላ “ይሄን ጫማ አስኮ ነው የሰራው። ጥሩ አልሰራውም?” ዓይነት ሲናገሩ አንደበታቸው ውስጥ ስሙን ለማስቀረት ነው? በእነሱ ድምፅ ውስጥ የመኖር።
ይሄ አፅናኝ ቢሆንም የአስኮ ድምፅ ጉዲፈቻ ከመሆን አያልፍም። በጊዜ እርዝመትም እሱ የሰራቸው ጫማዎች በማለቃቸው ወይም የሰራላቸው ሰዎች ትውስታ በመረበሹ (ስለሚረሱት ወይም የእሱን ስራ ከሌላ ጫማ ሰሪ ስራ ጋር ስለሚያምታቱት) ስሙ የሚጠፋ ይሆናል።
አስኮ ለሠፈረተኛው ደሃ ጫማ ይጠግናል። ያውም በዋጋ አይጎዳቸውም። ይሄ ለውለተኛነት ቦታ ቢከፍትም የአካባቢው ነዋሪዎች ግን አገልግሎቱን በርካሽ እየተጠቀሙ አይቀርቡትም። ሥርዓቱ የሰጠውን ጠባሳ አያዩለትም። እንደውም ሰዎቹና ስርዓቱ የመጠቃቀም ግንኙነት አላቸው። ስርዓቱ የህልውናውን ጣዕም አጎምዝዟል። ይሄ ሁኔታ በቀላሉ የሚታለል ወይም ግድ የማይሰጠው አስኮን ወልዷል። ይሄ ሙያውን ርካሽ ያደርገዋል። ምንም እንኳን አስኮ የወደቀለት አላማ በቦታ ደረጃ ሌላ ስፍራ ቢሆንም (ወሎ ስህን ት/ቤት) ሁሉም ዜጎች ግን የሚሹት ነው። ኑዋሪዎቹ ይማራሉ፣ ይሰራሉ ከእነዛም ውስጥ ለአገር የሚያስቡ ይኖሩ ይሆናል።
ግን የተጣመመው ስርዓት የተስተካከለ እንዲሆን ሲዋጋ የነበረውን ወንድማቸውን ያጣጥሉታል። ከአሁን በኋላ መንግስታዊ የሆኑ ቀጥተኛ የጭቆና መሰረተ ልማቶች አያስፈልጉም። ሕዝቡ ራሱ ያካሂደዋል። በመንግስት እስር ቤት መከተት ግድ አይልም። ሕዝቡ ራሱ አስኮን እንደ ጠላት በወሬውና በአገልግሎት ጥበቡ ያስረዋል። ከላይ የጠቀስነው ከአዲስ አባ እስከ ጭቃ ሹሞች የተዘረጋው የመንግስት መቆጣጠሪያ መዋቅር መሬት ላይ (ታች) ገንዘብ የማይከፍለው ስራ አስፈጻሚ አግኝቷል።
አስኮ የሲጋራ ፓኮ ሲለቃቅም አንዲት ሴትና ባሏ የሚለቃቅማቸው ወረቀቶቹን በጫማዎቻቸው ይረግጡበታል። ለመጀመሪያ ጊዜ የአስኮ ርዕዮት በቀጥታ ንግግር የሚገለጸው እዚህ ነው። ዝምታው በኮስታራ ቋንቋ የሚገሰሰው አሁን ነው። የተናገረው ሃይለ ቃል ልቧን ያራራበት ዘመናይ (ዘመናይ ፓ-ፓ-ፓ- ባለዘመን፣ የጊዜው ሰው) ወይዘሮ ልትክሰው እርጥባን ውራጅ ቀይ ካፖርት ትሰጠዋለች (ለምን ቀይ ካፖርት? ለምን ሌላ ቀለም አልሆነም? ለአዲስ አባ ለባሽ ቀይ ካፖርት እንግዳ ስለሆነ ለልዋጭነት ወይም ምሳሌነት እንደቀረበ ልጠረጥር ዘንድ እገፋፋለሁ። ግን ይሄን የቀለም አይነት በምን ልተረጉመው እንደሚገባኝ አላውቅም። የስሜት ሃያልነት? አደጋ?)
አስኮ ላገሩ በለፋው ልፋት ኦሪጂናሌ ብናደርገውም ወይም እንደዛ ብለን ብናስበውም የሚለብሰው ግን ሳልቫጅ ነው። ሳልቫጅ ሌላው ስሙ ‘ነፍስ ይማር’ ነው። የሞተው ማነው? ስለ ሴትዬዋ ሳይሆን ስለ አስኮ በጥልቅ ስለምናውቅ ሟቹ እሱ ሊሆን አይችልም? ጊዜ ታጥፎ የራሱን የድሮ ልብስ የለበሰ ሊሆን አይችልም? የሙት ቋሚ ሊሆን አይችልም? እነዚህ ስር ነቀል ግምቶች ሊሆኑ ይችላሉ። የህልውና ምት አይመስልም?
፯
የመጨረሻው ክፍል (ሰሌዳ ሀ’) በቀጥታ መስመራዊ አተራረክ የመጀመሪያው ክፍል (ሰሌዳ ሀ) ተከታይ ነው። አጨራረስ (Ending) በተራኪው ቁጥጥር ስር ነው። አዘጋግ (Closure) ግን በተራኪና በአንባቢ መሀል ያለውን ውጥረት የምናይበት ነው። ፍርሰቱ የተዘጋው በመጨረሻው አንቀጽ (ሀ’) አስኮ በተናገረው ‘ታስፈሩኛላችሁ’ በተባለው ቃል ማዕከላዊነት ነው።
የዚህን ትርጉም የምናገኘው ዐውድ ፈልገን ነው። ዐውድ ቀደም ሲል የነበረው ትረካ ውስጥ ነው (ሰሌዳ ሀ-ለ)። ምን ያህል የቋንቋ ክህሎቱ ቢናጋ ነው ‘እናንተ’ የሚለውን ተውላጠ ስም ሸውኮ በአጭር የተናገረው? ከቃል በታች ሊኖረው የሚችል ምን አይነት ቃል ነው?
የአስኮ የአነጋገር ጥልቀት ቢገባንም እዚህ ላይ ሁሉ ነገሩን በአንድ ቃል አስሮ ማለፍ የፈለገ ይመስላል። ቃልዋ ሲጢታ ትመስላለች። ሲጢታ ንኡስ ድምጽ ናት። የቋንቋ ጽንብር (Limit) ላይ የደረሰ ይመስላል። ‘ምን ማለትህ ነው?’ ተብሎ ማብራሪያ የማይሰጥበት የደከመበት ደረጃ ነው። አንዳንድ ጊዜ ጥልቅ የሆነን የአእምሮን ወይም የስሜት ልምድን ለመግለጽ የሚከብድበት ጊዜ አለ። የአረጋሽ ሰይፉ አንድ ግጥም ትዝ ይለኛል፤
ቃል አልቦ
“… ከቋንቋ የላቀ፣
ከቃል የመጠቀ፣ …
ሲባዛ ገደቡ ዝም … ዝም … ዝም … ዝም …
እንዲያ ነው ሚገለጥ …
ጥላቻም፤ ፍቅርም።
(አረጋሽ ሰይፉ፤ (፲፱፻፺) “እኛ 170 ግጥሞች”)
በባህላችን ከቋንቋ መራቅ የተለመደ ነው። ምንኩስና (ለምሳሌ) ከዓለማዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን የቋንቋ ተፈጥሯዊ ስፍራ ከሆነው ማሕበረሰብ ርቆ ቋንቋን በዋሻና (በአካል) አርምሞ (ኢ-ቦታዊ/አእምሮአዊ) አጥሮ ከሩካቤ ማሸሽ ነው። ሰዎቹ የረቀቀና የላቀ መንፈሳዊ ስብዕና እናገኛለን የሚሉት በዚህ ዓይነት የጸጥታ ገደብ በነገሰበት ዐውድ ውስጥ ነው። አስኮ ምንኩስና ላይ አይደለም። ገለልተኛነቱና ዝም ተባልነቱ ምን ያህል ንቃት እንደሚሰጠው ባንገምትም በአንድ ቃል ያልቃል ብለን መገመት ይከብደናል።
እዚህ ሁኔታና አጨራረስ ለመድረስ ግን አስኮ በብዙ ነገር ውስጥ አልፏል። ከዚህ ካለፈበት የህይወቱ ጉዞ ጋር አዝጋሚ ከሩካቤ የመራቅ የዝምታ ዝግመተ ምልዋጥ (A Process of Evolving Silence) እናያለን። ይሄን የምልዋጥ ሂደት ከላይ በሰየምኳቸው ሰሌዳዎች አሰራር ተራኪው የሰጠንን በምልሰት የተገነባ ድራሳን (ሰሌዳ ሀ-ለ-ሀ’) ወደ መስመራዊ አካሄድ (ሰሌዳ ለ-ሀ-ሀ’) ለመለወጥ በስምንት ተርታ ለማስቀመጥ እሞክራለሁ።
- [ማህበረሰብ አካል] – መሰማትና መነቀፍ (አንቀጽ 19)
- [ኢ-ሰብአዊ ማድረግ] – “የወፍ ቋንቋ” (አንቀጽ 23)
- [ራስን ሳንሱር ማድረግ] – “ከንግግራቸው መጠን ማለት ጀመሩ” (አንቀጽ 25)
- [ባይተዋርነት] – “እንደ ደረቀ ግንድ … ተለይተው ይታዩ ጀመር” (አንቀጽ 25) (“የአስኮ ጌታሁን ፊት የሸበተ አሮጌ ጉቶ ላይ የሰው መልክ የተቀረጸበት ይመስላል” (አንቀጽ 1) ከሚለው ጋር የተስማማ ንፅፅር እናያለን።)
- [ማህበረሰቡ ተጠቃሎ መሰረዙ] – “የለም፣ የለም ወዲህ ነው፤ ከራሴ ጋር ነው” (አንቀጽ 25)
- [ለቅሶ] – “እንጉርጉሮ ነገር ያሰማል” (አንቀጽ 15) እና “አያለቅስም፣ ድምጽ የለውም። እንዲሁ ብቻ ያነባል።” (አንቀጽ 13)
- [ማግለል] – “አጠገቡ ሲደርሱ የሱን ወሬ ለመከላከል (ደንበኞቹ) እርስ በርሳቸው ማውራታቸው የተለመደ ነው” (አንቀጽ 15)
- [መዝጊያ] – ከዚህ ወደ ፀጥታና ወደ ፍጹም መሰወር ጉዞ ላይ እያለ “ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገር” (አንቀጽ 30)
በዚህ የአስኮ ጉዞ የምናየው ቀስ በቀስ ቋንቋ እየተሰወረ መሄዱንና አስኮ ያለበት ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ መክረር ነው። ይሄ የቋንቋ መጥፋት ከሕብረተሰቡ በፍጹም ለመለያየት ፍጥጥሞሽ ማድረጉ ነው። አማራጭ አልነበረውም? ሌላውን መስሎ መኖር?
አስኮ ‘ታስፈሩኛላችሁ!’ ብሎ ሲናገር ያዳመጡት “ከቶም የማይረሳ ነገር ተናገረ” ይሉታል (አንቀጽ 30)። የምንጠይቀው የተለመደ ጥያቄ ለመሆኑ እንዲህ ከተናገረ በኋላ የአባባሉ ተጽዕኖ አካባቢው ላይ ምን ያህል ነው? የሚመስለኝ ይሄ ነው።
ድምጽ ድርጊት ነው። ድምጽ ማውጣት በምልክትነቱ ጫማ ከመስራት፣ ከመሳደብ፣ እየዞሩ ከመተረብ፣ ከዝምታ የሚለየው ነገር እንጂ የዕድሜው ጊዜያትን በአንድ ቃል ውስጥ ሰብስቦ የተነፈሰው ነው። አዘጋጉ የሚጠቅሰው አስኮ በመናገሩ የተጣለበትን የዝምተኛነት ፍርድ መጣሱ ሲሆን (እንደ አንድ ግለሰብ ‘ወንዳታ’ ቢሆንም) የቃሉ መሰማት ከማሚቶ የበለጠ አይሆንም።
ቃሉ በትምህርተ ጥቅስ በመታቀፉ ራሱ ውስጥ የቀረ አይሆንም? ማሚቶ አይሆንም? ይኼ ማሚቶ በቅርጽ ደረጃ ሰሌዳዎቹም በራሳቸው ውስጥ የሚያደርጉት ቅብብል ነው። የህልውናው ምት እንደ ማሚቶ ነው። የቦታው ምት የማሚቶ ጸባይ አለው። ማሚቶ ከራሷ ሌላ የምትረባው አዲስ ነገር የለም። ተዳክማ ከመሰወር ወይም ኅቡዕ ከመሆን ሌላ ግብ የላትም።
አስኮ አንዲትን ለመሰወር የደረሰች ቃል ጮሆ ከምንምነት ቢያመልጥም አካባቢው ላይ ያለው ተጽዕኖ አይገለጽም። ቃሉ በረዥም የጊዜ ሂደት ተቀናቃኝ የስር ነቀል ድርጊት ማስነሻ ይሆናል ብለን ለመገመት የቀረበልን ሌላ ተፃራሪ የትረካ መስመር የለም። ካፖርት የለገሰችው ሴትዮ ከእርጥባን ዘልቃ መሄድ የምትችል አልነበረችም። ከዛ ውጭ ያን ድምጽ የሚጠብቀው አዛኝ ልቡና፣ ተንታኝ አእምሮ የለም። ዝምታ አይሆንም?
‘ከቶም የማይረሳ’ ብንባልም ዋስትና የለንም። የዛ የመጨረሻ ጩኸት መነሻ ምክንያት ለኗሪው እስከ መቼም ሳይብራራ ይቀራል። ያቺ ጩኸት ለእነሱ አንድ አካላዊ ክስተት (Physical Phenomenon) ብቻ ናት። ዴሲቤል ናት። ለእነሱ ያ ቃል አስገራሚ የሆነበት ምክንያት ብቻውን ከታሪክ፣ ከሂደት የተፋታ ቃል ስለ ሆነባቸው ነው።
መስማታቸው አንድ ጉዳይ ሳይሆን ባይቀርም ስለ እነሱ ካለን ዕውቀት የትም እንደማይደርስ ነው። ምናልባት ቢብስ ይሄን ጩኸት ያብራራል የሚሉት ሌላ የከተማ ትውፊት (Urban Legend) ይፈጥሩለት ይሆናል። የዛ ማሕበረሰብ ልዩ ስጦታ ይሄ ነው።
ተራኪው የፈለገው “ታስፈሩኛላችሁ” የምትባለዋን ቃል በማንሳት አስገራሚ አጨራረስ ወይም ንሮሽ (ከመ ታደሰ ሊበን) ሊከስትልን አይደለም። ይሄን ቃል ቀድሞ ሌሎች ገጾች ላይ አንድ ሁለቴ አንብበነዋል። አስኮ ምንም ነገር ቢደራረብበት የተቻለውን መልስ ሳይሰጥ እንዳላለፈ ተራኪው ሊነግረን ነው።
ጃፓናዊው ገጣሚ ሶቢ ሺጌቺ የሚለውን ያስታውሷል፤
“I may be silent but
I am thinking
I may not talk, but
Do not mistake me for a wall.”
ሚስቱን እናቱን ልጁን አስተማሪነቱን አጥቷል። አስኮ ምንም የለውም። ከውስጡ ሁሉ ነገር ተጎልጉሎ ተዘርፏል። እዚህ ባዶ ውስጥ ድምፅ ይኖራል? ከዚህ አሟጦ ከጨረሰ ህልውና፣ ከዚህ ‘ገዋ’፣ ከዚህ ጨለማ ድምፅ ለመምጣት የግድ ይላል።
ትናንትና በትውስታ ውስጥ ሳትሞት አለች – የቁጭት ዕንቁላል የጣለች። ተክለ ሃይማኖት አደባባይ የአስኮ ጌታሁን ማመጫው ናት – ያቺ የመጨረሻ ቃሉን የሚወልድባት (አለነገር ወዲያ ወዲህ ለምን አለ? አለነገር ለምን ተቁነጠነጠ?)
፰
‘በመጀመሪያ ቃል ነበር’ ሲል መጽሐፉ ዐቢይ ነገር ሲጠቅስ ነው። ሲጀመርና ሲጀምር ያምላክ የሩካቤው ማዕከል ቃል ነው። ባቢሎን ላይ ያደረገው ስልጣኔ የማፍረስ የመጀመሪያው ቅጣቱ የተሰራው በቋንቋ ማማከያነት ነው። ምርቃትና እርግማን ቋንቋ ናቸው።
ስም ቃል ነው። ግለሰቦችንም አንዱን ከአንዱ መለያ ነው። በሕብረተሰባችን ሁለት አለማት አሉ። የደግና የክፉ። የእግዚአብሔርና የሳጥናኤል። በዓለማዊው ዓለም ውዥንብርና መምታታት እንዳይፈጠር ዓለማዊ የሰርክ ስማችንን እንይዛለን። ከመልካም መንፈስ ጋር ታሻርከን እኩይ መናፍስትን ለመዋጋትና ከእነሱ ንጀሳ ለመከላከል የሚስጥር ክርስትና ስም ይኖረናል።
ይሄ በሆነ መልክ የዶስ (Power) ጨዋታ ነው። ጀግኖችና ጠቢባን በፈረሶቻቸውና (አባ ነፍሶ፣ አባ ታጠቅ፣ ወዘተ) በሊቅነታቸው ጥልቀት (አራት አይናው ማንትስ፣ ወዘተ) ይጠራሉ። በተጨማሪም በየቀኑ ድርጊታቸው/ሁኔታቸው የተቀሰቀሰ በወዳጆቻቸው ወይም በሚቀርቧቸው ሰዎች አማካኝነት ቅጽል ስም ሊወጣላቸው ይችላል።
አዲስ አባ ውስጥ ‘አስኮ የጫማ ፋብሪካ’ የሚባል ነበር። ባለቤቱ የውጭ አገር ሰው መሰሉኝ። ለአቶ ጌታሁን የቅጽል ስሙ ‘አስኮ’ የማሾፍ አባባል ነው። “ጌታ ለመሆን ነው እንደ አስኮ ጫማ” ብሎ ይመልሳል (አንቀጽ 29) ለምን ይሄን ሙያ እንደያዘ ሰዎች ሲጠይቁት። ምንም እንኳን በማሾፍ ቢናገረውም፣ እሱ የሚናገረውን ፋይዳ ሳይሰጥ ራሱን ይሰውር የነበረው የሰፈር ጆሮ አባባሉን ዘርፎና አዙሮ ቅጽል ለጥፎበታል።
‘አስኮ’ የሚለው ስያሜ ገለልተኛ ይመስላል እንጂ አይደለም። አስኮን በዚህ ቅጽል መጥራት ሁለት ጥቅም አለው። አንደኛ፤ የባዕድ ስም ፊቱ በመገተር ባይተዋርነቱን አጥብቆ የስደተኛነት ጋቢ የማልበስ ሲሆን፣ ሁለተኛም፤ የማሾፍ ነው። ሁልጊዜ የአስኮ ጫማ የሚያደርግ ጎረምሳ ወይም ሰው ወይም በመሰለ ሁኔታ የተያያዘ ‘አስኮ’ ተብሎ ስሙ ቢቀጸል እውነተኛነት ስለሚኖረው ያስቀን ይሆናል። ጌታሁን ‘ሁልጊዜ በአስኮ ፋብሪካ የተሰሩ ግን የተቀደዱ ጫማዎችን ብቻ ነው የምጠግነው’ ብሎ ቢል ኖሮ መልካም ቅጽል ይሆን ነበር።
አስኮ የተሰጠው ቅጽል ከመውደቁ ከባይተዋርነቱ ከአንቱ ወደ አንተ ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው። አዝናኝነት፣ አሳቂነት የለውም። ስያሜ ከውጭ ሲመጣ ደፋሪና ነውረኛ ነው። በሌላው ሰው በማይገባው ልንቀበለው በማንችል ርዕዮት የተቀመመ ማንነትን መመጠኛ ስልት ነው። ለራስ ጌታ መሆንን ማጣት ነው። ስያሜ ቋንቋ ስለሆነ ለራስ የተከለለን ቋንቋ በሌላ ሀይል መወረስ ነው። ድምፅንም መነጠቅ ነው።
፱
ግን ስለ ዝምታ ሲጻፍ አያኖ ይሆናል። ድምጽ ስለሌላቸው ሰዎች ሲጻፍ ሰዎቹ በሆነ መልክ አልሞቱም። በሆነ መልክ ድምጽ አላቸው።
አለቃ ዘነብ ‘ቀለም በቀንድ ሳለ ድዳ ነው፣ በተጻፈ ጊዜ ግን ምላሰኛ ነው’ ይላሉ። አስኮ ጫማ ሰሪውና አስተማሪው መልካሙ ሰውዬ ያለ ድምጽ ቢያልፉም በትረካው አማካይነት በኅሊናችን እንዲቀሩ ሆነዋል። ያለ ዝምታ ወደ እብደት እንደገባ ሪፖርት ተደርሶልናል።
የአስኮ ድርጊት ሰው በቦክስ ማስፈራራት፣ ተኩሶ መግደል ወይም የመሳሰለ ቅጣት አይደለም። አስኮ ያ አቅም የለውም። ያለው አቅም ዝምታውን ማፍረሱ ነው። ለተራኪው አስኮ ‘የሚነገርለት’ የሆነው ለዚህ ነው። የዚህ ታሪክ ወረቀት ላይ መስፈሩ የግድ ይላል።
የአስኮ ዝምታ ወረቀት ላይ በሰፈሩ ቃላቶች ድምጽ ይካሳል።
.
አዳም ረታ