መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (1817 – 1900)

በኅሩይ አብዱ

 .

በ1948 ዓ.ም በአዲስ አበባ “መጽሐፈ ሰዋስው ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ በገበያ ዋለ። ይህ የግእዝ-አማርኛ ሰዋስው እና መዝገበ ቃላት የሦስት ትውልድ ሊቃውንት የምርምርና የትጋት ውጤት ሲሆን ላለፉት ስድሳ ዓመታት ዋነኛው የግእዝ ቃላት መፍቻ ሆኖ አገልግሏል። እስከዛሬ ድረስም ቢሆን በአገራችን ምትክ የሚሆነው መጽሐፍ ሊገኝለት አልተቻለም።

በዚህ ጽሑፍ የዚህን ዕጹብ መዝገበ-ቃላት ሥራ ወጣኝ የነበሩትን የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስን የሕይወት እና የድርሰት ታሪክ አቀርባለሁ።

.

ተማነት (1817 – 1842)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግንቦት 14፣ 1817 ዓ.ም በአንኮበር ተወለዱ። ከአርባ ቀንም በኋላ በሰኔ 23 ስለተጠመቁ ሰማዕቱ ጊዮርጊስን ለመዘከር ስማቸው “ክፍለ ጊዮርጊስ” ተባለ። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ እንደጻፉልን መምህር ክፍሌ አንኮበር ቢወለዱም አብዛኞቹ ዘመዶቻቸው ከሐር አምባ ናቸው (“አንኮበር ይእቲ ምድረ ሙላዱ ወሐር አምባ ርስተ ነገዱ።”)

አንኮበር

አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነግሩን መምህር ክፍሌ የሕይወታቸውን የመጀመሪያ ሃያ አምስት ዓመታት ያሳለፉት በሸዋ ሲሆን አብዛኛውን የቤተ ክርስትያን ትምህርት የተማሩትም በዚሁ ወቅት በአንኮበር ነበር። ይህም ማለት ከመሠረታዊው ንባብና ጽሕፈት በመጀመር ዜማ ቤት፣ በመቀጠልም ቅኔ ቤት ገብቶ መማር ነው። የሚቀጥለው ደረጃ የአንድምታ (መጻሕፍት ቤት) ትምህርት ሲሆን፣ ለዚህም ጠለቅ ያለ የግእዝ ሰዋስው እውቀት ያስፈልጋል።

የግእዝ ሰዋስውን አገባብ እና የቅኔ መንገድ በመማር የቅኔ መምህርነት ደረጃ መድረስ ለአዲሱ የአንድምታ ትምህርት ጥሩ መሠረት ይሆናል። ተማሪው መጻሕፍት ቤት ገብቶ በመጀመርያ የሐዲስና የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን ትርጓሜ (አንድምታ) በቃል በመያዝ ይማራል። በመቀጠልም የመጻሕፍተ ሊቃውንትን (ቄርሎስዮሐንስ አፈወርቅሃይማኖተ አበውፍትሐ ነገሥት …) ትርጓሜ ይማራል። ፍላጎት ያለው ተማሪም በተጨማሪ የመጻሕፍተ መነኮሳትን (ማር ይስሐቅ ፊልክስዮስ፣ እና አረጋዊ መንፈሳዊ) አንድምታ በመማር የመጻሕፍት ቤትን ትምህርት ያጠናቅቃል።

የግዕዝ መምህርና ተማሪዎች 1840ዎቹ አካባቢ

በ1830ዎቹ እና 1840ዎቹ በአንኮበር በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ አሰባሳቢነት ታላላቅ ሊቃውንት ይገኙ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከላይ የተጠቀሱትን ትምህርት ዓይነቶች እዛው በአንኮበር በመጀመሪያ ሳያስኬዱ አልቀሩም። በሃይማኖትም ረገድ፣ ለደቀ መዝሙራቸው ለኪዳነ ወልድ እንደነገሩት “የጸጋ ልጆች” ትምህርትን በሕፃንነታቸው ያስተማሯቸው ዓይነ ስውሩ መምህር ወልደ ሥላሴ ናቸው።

.

 ምህር (1842 – 1867)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ቀጣዩን ሃያ አምስት ዓመታት በተለያዩ የትምህርት ማዕከሎች እንዳሳለፉ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይገልጻሉ (“ … ወዕሥራ ወኀምስቱ ዓመት በብሔረ ጐዣም ወዐምሐራ፣ በላስታ ወበቤጌምድር፣ በጐንደርሂ ወበስሜን፣ በትግሬሂ ወበሐማሴን።”) በዚህ ዘመን የታወቁት የአንኮበር ሊቃውንት (እነ አለቃ ሥነ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ተክለ ጽዮን፣ እንዲሁም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ) ከሞጣው ጊዮርጊሱ አራት ዓይና ጐሹ ተምረው በብሉይ ኪዳን መምህርነት እንደተመረቁ ይነገራል። የተማሩበትም ዘመን በደጃች ተድላ ጓሉ ጊዜ እንደመሆኑ እስከ 1850ዎቹ አጋማሽ ባለው ዘመን የነበረ ይመስለኛል።

ከአራት ዓይና ጐሹ ተምረው እንደጨረሱ የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛ ባለቅኔው ተክለ ጽዮን ዲማ ወርደው ቅኔ አስተማሪ ሲሆኑ፣ እሳቸው ደግሞ ወደ ጐንደር አቀኑ። እዛም ከታላቁ ሊቅ ከግምጃ ቤት ማርያሙ ከወልደአብ ወልደሚካኤል ዘንድ የአንድምታ ትምህርታቸውን (መጻሕፍተ ሐዲስና ሊቃውንትን) አስኬዱ።

ከዚህም በኋላ ስለ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ያለን መረጃ በአንኮበር ሚካኤል በሚገኝ ብራና ላይ ያለው የቤት ሽያጭ ውል ነው። ይህም ውል፣ “ይመር ጐጅ ለቄስ ክፍለ ጊዮርጊስ በ፫ ብር ከ፰ ጨው ሁለት ቤት ሸጠዋል” ይላል።

አንኮበር ሚካኤል 1830ዎቹ አካባቢ

ውሉ የተጻፈው በአጼ ቴዎድሮስ መንግሥት (1847-1860 ዓ.ም) በዘመነ ማቴዎስ ነው። ይህም ውሉ የተፈጸመበትን ዓመት 1849፣ 1853 አሊያም 1857 ዓ.ም. ያደርገዋል። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በጐዣም እና በጐንደር ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመት በትምህርት ሊያሳልፉ ስለሚችሉ ውሉ የተፈጸመበት ዘመን በ1853 ወይም በ1857 ቢሆን የበለጠ ያሳምናል።

ከጐዣም እና ጐንደር ቆይታቸው በኋላ ሁለቱ ጓደኛሞች (ተክለ ጽዮን እና ክፍለ ጊዮርጊስ) የብሉያትን አንድምታ አንኮበር ተመልሰው ማስተማር እንደጀመሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይናገራሉ። ለምን ያህል ጊዜ አብረው እንዳስተማሩ ባይታወቅም፣ አንደኛው ኦሪት ዘፍጥረት ሲተረጉም ሌላኛው የመሐፈ ነገሥትን አንድምታ እንደሚያስተምር፣ አንዱ ትንቢ ኢሳይያስን ሲተረጉም ሌላው ትንቢ ኤርምያ አንድምታ እንደሚያስኬድ አለቃ ኪዳነ ወልድ ይነግሩናል።

ከዚህ ቀጥሎ ስለ መምህር ክፍሌ የምናገኘው መረጃ አለቃ ኪዳነ ወልድ ስለ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ዘርና ትርጓሜ ፍለጋ ከመምህራቸው ሰምተው አንድ መጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራና ላይ (አሁን በኢየሩሳሌም በደብረ ገነት ቤተ መጻሕፍት የሚገኝ) በጻፉት መቅድም ውስጥ ነው። በዚህም ጽሑፍ ላይ እንደሚተረከው የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ትርጓሜ ትምህርት በአገሪቱ ውስጥ የሚሰጥበት ብቸኛ ቦታ ጐንደር ሆኖ ነበር። በጐንደርም ያሉት የአንድምታ መምህራን ትምህርቱን በድብቅ ቤት ዘግተው ለብቻቸው በማድረጋቸው እነሱ በተለያየ ምክንያት ሲሞቱ ትምህርቱም አብሮ ጠፋ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እንደሚሉት፣

“የብሉይ፣ የሐዲስ፣ የሊቃውንትና የመነኮሳትን ትርጓሜ ትምህርት እንደጨረስኩ የነቢዩ ሕዝቅኤልን መጽሐፍ ፍለጋ አድባራትን፣ ገዳማትን፣ ደሴታትን ሳስስ ምንም አላረፍኩም።”

በዚህም ምክንያት መምህር ክፍሌ ‘ትክክለኛው’ ሕዝቅኤልን ፍለጋ ወደ ስሜን ወደ ደረስጌ ማርያም ያመራሉ። እዛም ሁለት የሕዝቅኤል መጽሐፎች ያገኛሉ። ብራናዎቹ ግን አላስደሰቷቸውም፣ በተለይ አንደኛው ብዙ የተቆራረጠና የተደላለዘ ነበር። ነገር ግን በመጽሐፈ ሕዝቅኤል ገለጻ ታላቅ ቦታ ያለውን “ሥዕለ ኤስከዴሬ” እና ትርጉሙን የያዘ አንድ ጥራዝ ስላገኙ ልክ የተቀበረ ሳጥን እንዳገኘ ሰው በመደሰት ጥራዙን በሞላ ገለበጡት። ይህ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ፍለጋ ጉዞ ወደሚቀጥለው የሕይወታቸው ምዕራፍ ይወስደናል።

.

 ስደት (1867-1878)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናን በማሰስ ላይ እንዳሉ የታላቁ ሊቅ የአለቃ ወልደአብ መጻሕፍት በከረን እንደሚገኙ ይሰማሉ። በዚህም ምክንያት ለሚቀጥሉት አስራ አንድ ዓመታት መጠለያ ወደሚሆናቸው ወደ ምጽዋ እና ከረን ካቶሊክ ሚሽን (ቤተ አፍርንጅ) ያመራሉ።

ምጽዋ እና አካባቢዋ (“ቤተ አፍርንጅ” ከመሀል)

በከረንም ተስተካክለው የተጻፉ፣ ያልተቆረጡ፣ ያልተደለዙ ሁለት የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ብራናዎችን አገኙ። ብራናዎቹንም በኋላ ለሚሰሩት የሕዝቅኤል አንድምታ ዘር እንዲሆን እንዳለ ገለበጡ። (ይህንንም መጽሐፈ ሕዝቅኤል” ተማሪያቸው አለቃ ኪዳነ ወልድ አደራ ተቀብለው፣ የእብራይስጡንም ዘር አካተው በ1916 ዓ.ም ያትሙታል)

አለቃ ኪዳነ ወልድ ግን ለመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ስደት ሌላም ምክንያት ያቀርባሉ። መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስመግቢያ ላይ ስለዚሁ ምክንያት ባጭሩ ጽፈው ነበር። ነገር ግን በ1948 ዓ.ም. መጽሐፉ ሲታተም አሳታሚው ደስታ ተክለወልድ ባልታወቀ ምክንያት ከመጽሐፉ አስቀርተውታል። ጽሑፉ እንዲህ ይል ነበር፤

“… የስደታቸውም ምክንያት ባጭር ቃል ይህ ነው። … ፬ኛው ሐፄ ዮሐንስ … መምህር ክፍሌንም እንደ ዋልድቤ እንግዳና እንደ ዙራንቤ እንግዳ እንደ መምህር ተክለ አልፋ ምላሳቸውን ለመቁረጥ፣ ለማሰር፣ ለመግረፍ፣ ወይም በጭራሽ ለመሰየፍ በግር በጥፍር ያስፈልጓቸው ነበሩና፤ በዚህ ምክንያት፣ ‘ከመሞት ይሻላል መሰንበት’፣ ‘ከመታሰር ይሻላል ማስተማር’ ብለው ምጽዋዕ ገብተው ከዚያ ሳይወጡ ፫ ዓመት ያህል ኑረዋል።”

እንግዲህ አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት፣ አፄ ዮሐንስ ግንቦት 1870 ዓ.ም. ባካሄዱት የቦሩ ሜዳ የሃይማኖት ጉባኤ የ“ጸጋ ልጆች” ከተሸነፉም በኋላ፣ ንጉሡ የ“ጸጋ” አስተሳሰብን ተከታዮች (የመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ጓደኛን መምህር ተክለ ጽዮንን ጨምሮ) ያሳድዱ ስለነበር ከዚህ አደጋ ለማምለጥ መምህር ክፍሌ ወደ ምጽዋ ተሰደዱ።

ባለቅኔውም ተክለ ጽዮን የሁለቱን ጓደኛሞች የስደት ዕጣ በግእዝ መወድስ ቅኔ ዘግበው ነበር (ቅኔው ከነአማርኛ ትርጉሙ እነሆ)፤

በሰሚዐ ቃሉ ለሳውል ቢጸ ኤርምያስ 

ሠለስተ ዓመተ ኢነትገ አንብዕነ 

ለዝኒ ብካይ ሀገረ ሳውል ኢኮነ

ነግደ ወፈላሴ  

እስመ ሰብአ ቤቱ ለብካይ ንሕነ

ቀዳሚ ኀበ ለመድነ 

በላዕለ ትካዝ ትካዘ ወበላዕለ ሐዘን ሐዘነ  

ሶበሂ ተዘከርናሃ ለደብረ ሊባኖስ እምነ 

ህየ ውስተ አፍላጋ ነበርነ ወበከይነ 

እስመ ማየ ዕድሜነ ኀልቀ ከመ ንዘረው ኵልነ

መንፈቅነ በምሥራቅ እንዘ በምዕራብ መንፈቅነ።

.

“የኤርምያስ ጓደኛ የሆነው የጳውሎስን ቃል በመስማት፤

ሶስት ዘመን እንባችን አልጎደለም፤

ለዚህም ልቅሶ የጳውሎስ አገር እንግዳ አልሆነንም፤

የልቅሶ ቤተሰቦች ነንና፤

በትካዜ ላይ ትካዜን፣ በሐዘንም ላይ ሐዘንን ቀድሞ ከለመድን ዘንድ።

እናታችን ደብረ ሊባኖስንም በአሰብናት ጊዜ፤

በዚያ በወንዞች ተቀመጥንና አለቀስን፤

እኩላችን በምዕራብ እኩላችንም በምሥራቅ፤

ሁላችን እንድንበተን እድሜያችን አልቋልና።”

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም በምጽዋ ከአቡነ ዮሴፍ ሳሉ ከረን በሚገኘው የካቶሊክ ሚስዮን የግእዝ መምህር እንዲሆኑ ይጠየቃሉ። በሀሳቡም ከተስማሙ በኋላ ኢየሩሳሌምን ተሳልመው ሲመለሱ ከረን ማስተማር ይጀምራሉ። በከረንም ቆይታቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከማስተማር በተጨማሪ የተለያዩ መጻሕፍት ዝግጅት ላይ ተሳታፊ ነበሩ።

በመጀመሪያ ያዘጋጁት መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን መጽሐፈ ሰዋስው ነበር። ከጥር 1871 እስከ ታኅሣሥ 1872 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከላዛሪስት ሚስዮን ማተሚያ ቤት የወጣው ይህ መጽሐፍ ስድስት ክፍሎች ነበሩት። የመጀመሪያው ክፍል “የርባታ ዓመል” ሲሆን (በአሁኑ ጊዜ ‘ርባ ቅምር’ ከምንለው ጋር ይቀራረባል) የተለያዩ የሰዋስው ደንቦችን ያስተምራል።

ሁለተኛው ክፍል “ሰዋስውና ቅጽል” ሲሆን ሰምና ወርቅ፣ ባለቤትና ዘርፍ፣ ቅጽል … የመሳሰሉትን ይዳስሳል። ሦስተኛው ክፍል “ዐቢይ አገባብ” (የግስ አገባብ ባሕርይ)፣ አራተኛውና አምስተኛ ክፍል ደግሞ “ንኡስ አገባብ” እና “ደቂቅ አገባብ” (የስሞች አገባብ ባሕርይ) ያቀርባሉ። ስድስተኛው ክፍል ስለ “አኃዝ” (ቁጥር) ካስረዳ በኋላ በመጨረሻ “አእመረ” እና “ይቤ” የተሰኙት የግእዝ ግሶችን እርባታ ያቀርባል። ይህ መጽሐፍ የአባ ገብረ ሚካኤልን ብቻ ሳይሆን የመምህር ክፍሌንም የግእዝ ሰዋስው እውቀት የሚያሳይ ነው።

በሚቀጥሉት ዓመታትም መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ከካቶሊኩ ሚስዮናዊ ኩልቦ (Jean-Baptiste Coulbeaux) ጋር በመሆን በ1876 ዓ.ም ኢሚታስዮ – ክርስቶስን ስለ መምሰል፣ በ1880 ዓ.ም ደግሞ ትምህርተ ክርስትያን” የተሰኙ ድርሰቶችን ከላቲንና ጣሊያንኛ ወደ አማርኛ ተርጉመው በሚስዮኑ ማተሚያ ቤት አሳትመዋል። እንዲሁም በ1878 ዓ.ም. ያዘጋጁት መዝሙረ ዳዊት በከረን ታትሟል።

በቦሩ ሜዳ በጉባኤ ላይ በንጉሡ ዳኝነት ተረተው የተሰደዱትን “የጸጋ ልጆች” አስተሳሰብ መምህር ክፍሌ በ1875 ዓ.ም ሃይማኖተ ቅድስት ሥላሴ በሚል ርእስ አዘጋጁ። የረቂቁ የመጀመሪያ ሦስት ምዕራፎች የራሳቸውን የ“ጸጋ ልጆች” ቡድን አስተሳሰብ ሲያቀርብ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ደግሞ የተቃዋሚዎቻቸውን “ካሮች” እና “ቅብዐቶች” አስተሳሰብ ያቀርባል።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም ከከረን እና ምጽዋ አስራ አንድ ዓመታት ቆይታቸው በኋላ፣ ከሚስዮኑ አለቃ ከአባ ተክለሃይማኖት ጋር ብዙም ባለመስማማትና “ሮሜን ለማየት” ወደ ጣሊያን አገር ወደ ሮማ አመሩ።

.

ሕር ማዶ (1878 – 1889)

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ሮም እንደደረሱ ቫቲካን (Vatican) ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያውያን ኮሌጅ ግእዝ ማስተማር ጀመሩ። በዚህም ወቅት ምጽዋ እና ከረን ሳሉ የጀመሩትን የሮማይስጥ (Latin) ቋንቋ ጥናት በማጠናከር ቀጠሉ። በቆይታቸውም ዘመን ከጣሊያኑ የቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ሊቅ ጒዲ (Ignazio Guidi) ጋር ይተዋወቃሉ። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ለደቀ መዝሙራቸው ለአለቃ ኪዳነ ወልድ እንደተናገሩት፣

“ሮሜ ሄጄ ከፈረንጅ ሊቃውንት ሁሉ በእውቀት የሚበልጥ፣ የጽርዕ (Greek) እና እብራይስጥ (Hebrew)፣ እንዲሁም ሱርስት (Syriac) እና ዓረብ ዐዋቂ ሰው አገኘሁ። ይህም ሰው፣ ‘ኢትዮጵያዊ ሊቅ ሆይ! ግእዝና አማርኛ አስተምረኝ፣ እኔም የፈለግከውን አስተምርሃለሁ’ አለኝ።”

ይህም ትውውቅ ሁለቱ ሊቃውንት እርስ በርስ እንዲማማሩና ከዚህ በፊት ለፈረንጅ ምሁራን ይከብድ የነበረውን የአማርኛ ጽሑፎችን ጥናት በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እርዳታ ጒዲ ሊካንበት አስችሏል። ጒዲ በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ እገዛ ካሳተማቸው ሥራዎቹ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ምሳሌዎች፣ ግጥሞች እና ተረቶች የተሰኘው ነው። ሌሎች በእሳቸው እገዛ ከወጡት ሥራዎች መካከል፣ የነገሥታት ግጥምመርሐ ዕዉርየኢትዮጵያ ቅኔዎችፍትሐ ነገሥት እና እንደዋና ሥራው የሚቆጠረውን “የአማርኛ-ጣሊያንኛ መዝገበ ቃላት መጥቀስ ይቻላል።

.

 መጨረሻ (1889 – 1900)

ከአስራ አንድ ዓመታት የጣሊያን ቆይታም በኋላ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ወደ ኢየሩሳሌም አመሩ። ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ዕድሜያቸው ሰባዎቹ ላይ ደርሶ ስለነበር ፍላጎታቸው የሕይወታቸውን የመጨረሻ ዓመታት በጸሎትና በጥናት ለማሳለፍ ነበር። እዛም ለሚገኙት ኢትዮጵያውያን እውቀታቸውን ለማካፈል ቢሞክሩም፣ ጥናትና ምርምር ላይ መስራት የሚፈልግ ሊያገኙ አልቻሉም።

ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ግን ከሳቸው ጋር ለመስራት ችሎታና ፍላጎትም ከነበረው ከወጣቱ ኪዳነ ወልድ ጋር ይገናኛሉ። የሁለቱ መገናኘትም ያስገኘልን ትልቁ ነገር የ1948ቱ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የተሰኘው የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ነው።

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ደስታ ተክለ ወልድ

መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በኢየሩሳሌም አስራ አንድ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ጳጕሜ 3፣ 1900 ዓ.ም በሰማንያ ሦስት ዓመታቸው አረፉ። ከአንኮበር ጓደኛቸው ከባለቅኔው ተክለጽዮን አጠገብም ተቀበሩ።

.

(በክፍል 2 ይቀጥላል)

ኅሩይ አብዱ

ሚያዝያ 2009

 .

ምንጮች

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – መዝገበ ቃላት – መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፣ አዲስ አበባ 1948 ዓ.ም ገጽ 7-8

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (ኪወክ) – ሃይማኖተ አበው ቀደምት ውስተ Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 268-274

ሮጀር ካውሊ Roger Cowley, “A Geez Prologue concerning the Work of Mämhér Kéfla Giyorgis on the Text and Interpretation of the Book of Ezekiel”, ውስተ A STANISLAV SEGERT – ANDRAs J.E. BOOROGLIGETI (eds.), Ethiopian Studies: Dedicated to Wolf Leslau on the Occasion of his Seventy-Fifth Birthday, November 14th, 1981, by Friends and Colleagues, Wiesbaden 1983. ገጽ 99–114

ብርሃኑ አበበ – Berhanou Abebbe (ed.) – Kidana Wald Kéfle, ሃይማኖተ አበው ቀደምት La foi des pères anciens, 1. Texte éthiopien. Enseignement de Mamher Kefla Giyorgis …, Stuttgart 1986 ገጽ 7-17

ቮልክ እና ኖስኒትሲን – Ewa Wolk and Denis Nosnitsin, “Kéflä Giyorgis” ውስተ Encyclopaedia Aethiopica ቅጽ 3 ገጽ 370-371 

11 thoughts on “መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻)

 1. ያለፈው ታሪካችንን ለትውልድ ማቆየት ትልቅ ብልህነት ነው በእውነቱ በፍቅር እና በተመስጦ አንብቤው እጅግ ተማርኬበታለሁ በእውነቱ እንዲህ የማይገኝ ታሪኮችን ለወደፊቱም እንጠብቃለን እናመሰግናለን

  Like

 2. እግዚአብሄር ይስጥልን ! ለተከታዩ ትውልድ የማንነት ፍለጋና የእማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ የምርምር ሥራዎች ጠቋሚ መረጃ ይሆናል:: ሀገራችን ያስተሳሰብ ድህነት የሌለባት የራሷ ሊቃውንት የነበሯት መሆኑንም በግልጽ ያሳያል::

  Liked by 1 person

 3. There is something behind yesterday. And digging that out is joyful and exactly interesting. GOD BLESS YOU!

  Like

 4. Thank you, Hiruy. An excellent piece. ለሁሉም ቀደምት ታሪኮቻችንን ያለማወቃችን ዘመናዊ ነን ብለን ግልብ ከመሆን ማንነታችንን የሚያሳይ ጥሩ ትምህርት ያለው በመሆኑ ከልብ አመሰግናለሁ

  Like

 5. የኢትዮጵያ የቋንቋ ሞግዚቶች አልቀው እንኳን አዲስ ሥራ መሥራት ያለውን መጠበቅ ማስተዋወቅ ባልተቻለበት ይህን ያህል ደክማችሁ ለአንባብያን ማቅረባችሁ ከባለታሪኮቹ ተርታ እንድትሰለፉ አድርጓችኋ በርቱ ጠንክሩ፡፡
  የታሪክ ፥ የቋንቋ ፥የባህል ባለፀጋ አድርገው ከዓለም ታላላቅ ሀገራት ተርታ በክብር ፥ በኩራት እንድንሰለፍ ለደከሙልን እኛ ግን እንኳን ድካማቸውን ስማቸውን በሀገር ደረጃ ሁላችንም የማወቅ እድሉን ያላገኘነው የሀገራችንን ክብርና ታሪክ ለማወቅ ለመጠበቅ እግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛልን፡፡
  ጥያቄ
  የታተመው “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” የሚሸጥበት ልዩ ቦታ የት ነው?
  አስተያየት
  አሁን ያለው ትውልድ በአመዛኙ የ “ሀለሐመ” ን የፈፊደል ተራ እንጂ የጥንቱን የ “አበገደ” የፊደል ተራ ስለማያውቅ
  ከአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ድንቅ መጽሐፍ ከ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ” ላይ ቃላትን ፈልጎ በቀላሉ ማግኘት ስለማይቻል እንደ “oxford dictionary ” ተዘጋጅቶ በመረጃ መረብ (በኢንተርኔት) ብታዘጋጁልን፡፡
  ወይም ጥረት ብታደርጉልን ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ሥርዓት የሚዘረጋበት ሁኔታ ቢመቻች እኛም ድርሻችንን ብንወጣ፡፡
  በቋንቋው ለመጠቀምና ቋንቋውን ለማሳደግ አስተዋፅዖ ይኖረዋልና፡፡

  Like

 6. በቃ!! ኢትዮጲያ እንዲህ የሚለፋላት አጥታ እኮ ነው የምትንገዳገደው፡፡ የዚህ ትውልድ አባል በመሆኔ ባለኝ የችሎታ መጠን ተደግፌ ይህን ታሪካችንን በፊልም መልክ ሰርቶ ለማቅረብ ውስጤን አነሳስታችሁታል ተመልከቱ ሌላውም እደኔ በሌላ የጥበብ ዘርፍ ሊያቀርብ ይችላል እና እያረጋችሁ ያላችሁትን ነገር እንደቀላል እዳታዩት ትውልድን የማዳን ትልቁ ቁልፍ ይህ ነው እና በርቱልኝ እግዜር ያክብራችሁ፡፡

  Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s