ግስ ዘመምህር ክፍሌ
(መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ – ክፍል 2)
.
በኅሩይ አብዱ
.
መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ (፲፰፻፲፯-፲፱፻) መላ ሕይወታችውን በትምህርትና ምርምር ዙርያ በአገራቸው እንዲሁም በስደት እንዳሳለፉ የሕይወት ታሪካቸው ያሳያል። በዚህኛው ክፍል ደግሞ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የወጠኑት “ግስ” በ1948 ዓ.ም ለታተመው “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” እንዴት መሠረት ሊሆን እንደቻለ ለማሳየት እሞክራለሁ።
በቅድሚያ ግን ስለ የግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላት ታሪካዊ አጀማመር እና በመምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ዘመን የነበረበትን ደረጃ በአጭሩ አቀርባለሁ።
.
የግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት ታሪካዊ ሂደት
“መዝገበ ቃላት” በቁሙ የቃላት መሰብሰብያ፣ ማከማቻ ወይም መድበል ነው። ቁምነገሩ ግን እነዚህን በተለያየ ምክንያት የተሰባሰቡትን ቃላትን መፍታት ወይም መተርጎሙ ላይ ነው። ስለዚህ ስለ መዝገበ ቃላት ሲነሳ የትኞቹ ቃላት ተመርጠው እንደሚሰበሰቡ፣ ከዛም በምን መልክ እንደሚተረጎሙ አብሮ መታሰብ አለበት።
አብዛኞቹ የመጀመሪያዎቹ መዝገበ ቃላት በአንድ የጽሑፍ ቋንቋ (ለምሳሌ ግእዝ) የሚገኙትን ከባድና ያልተለመዱ ቃላት ወደ ጊዜው የንግግር ቋንቋ (ለምሳሌ አማርኛ) ለመተርጎም የተዘጋጁ ናቸው። “መዝገበ ቃላት” የሚለውም ቃል በ20ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ከመለመዱ በፊት ጽንሰ ሐሳቡ “ነገር” እና “መጽሐፈ ግስ” በተባሉት ቃላት ውስጥ ተካቶ ነበር።
የመጀመሪያዎቹ ከ1600ዎቹ በፊት የተዘጋጁ የግእዝ-አማርኛ መፍቻዎች ዓላማ በግእዙ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ከግሪክ ወይም እብራይስጥ የተገለበጡ ቃላትን ወደ አማርኛ መተርጎም ነበር። እንደዚህ ዓይነት ድርጊት የማያሳዩ (ግስ ያልሆኑ) ቃላቶች በግእዝ ሰዋስው “ነባር” ይባላሉ። አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚሉት፣
“ዘርነት የሌለው፣ ከዘር አንቀጽ የማይገኝ የቋንቋ ቤተሰብ እየኾነ በውጥንቅጥነት የሚገኝ ጥሬ ቃል ኹሉ ነባር ይባላል፤ ትርጓሜውም የማይፈልስ የማይናወጥ የማይጠፋ የማይለወጥ ስም ማለት ነው።”
እኒህም የነባር ቃላት መፍቻዎች በድሮ ዘመን (እንደ መጽሐፉ ዓይነት) “ጥሬ ኦሪት”፣ “ጥሬ ነገሥት” ይባሉ ነበር ። ለምሳሌ ከኦሪትና ከነገሥት የሚከተሉትን ማየት ይቻላል።
ሂጳጳ – ታላቅ አሞራ፣ የማይበር (ዘዳግም 14፡17)
ለሮን – ይብራ ሦስት ጕተና ያለው (ዘዳግም 14፡15)
ልንጴኔ – አልጋ፣ መከዳ፣ ብርኩማ (1 ሳሙኤል 26፡5)
ሐሜላት – መጠምጠምያ፤ ሕባኔ (1 ነገሥት 19፡13)
ሐንጶን– እንዘዝ፣ አርጃኖ (ዘሌዋ 11፡30)
በመቀጠል ከ17ኛው እስከ 19ኛው ክ/ዘመን በተዘጋጁ የሰዋስው ብራናዎች ላይ የምናገኘው “ነገር” በሚል ምደባ ቃላትን እየከፋፈለ ከግእዝ ወደ አማርኛ የሚተረጉም መዝገበ ቃላትን ነው።
ቃላቱንም ለመፍታት አብዛኞቹ ብራናዎች ይህን መሠረታዊ ቅርጽ ይጠቀማሉ፣
(ግእዝ ቃል) ብ (አማርኛ ፍቺ)
(“ብ” ማለት “ብሂል” የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን በአማርኛ “ማለት” ወይም ሲል” ተብሎ ይተረጎማል።)
ለምሳሌ፣ ውኂዝ ብ፣ፈሳሽ
ወይም ባሁኑ አማርኛ “ውኂዝ ሲል ፈሳሽ ማለት ነው”።
አብዛኞቹ የ“ነገር” ብራናዎች ቀዳሚው ክፍላቸው “እጽሕፍ ነገረ ሰዋስው” በማለት ይጀምርና
“ሰዋስው ብ (ማለት) መሸጋገርያ ወመሰላል” ብሎ የመጀመርያውን ትርጉም ይሰጠናል።
ከዛም የተለያዩ የሰዋስው አገባብ ቃላትን ይፈታል፣
ላዕለ ብ በላይ
ማዕዜ ብ መቸ
አይቴ ብ ወዴት ….
ቀጥሎም አንድ ዓይነት ትርጉም ያላቸውን የግእዝ ግሶች ይተረጉማል፣
ሖረ፣ አመልአ፣ ነገደ ብ ሄደ
ሐለየ፣ ተዘከረ፣ አስተሐመመ ብ አሰበ … የመሳሰሉት።
አብዛኞቹ “ነገር” ብራናዎች ከ30 በላይ ክፍል አላቸው። አብዛኛዎቹ ክፍሎች ከዚህ በፊት እንደተጠቀሱት “ጥሬ ኦሪት፣ ጥሬ ነገሥት” የመጽሐፍ ቅዱስን ነባርና ከባድ ቃላት ፍቺ ይሰጣሉ። ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍትም አብዛኞቹ የየራሳቸው ክፍል አላቸው፣
ለምሳሌ ያህል፣
እጽሕፍ ነገረ ሕዝቅኤል፤
እለ ቄጥሩ ብ ዖፍ ዘራብዕ ርእሱ (ወፍ ባለአራት ራስ)
ተርሙስ ብ አደንጓሬ ….
ሐዲስ ኪዳንም “ነገረ ወንጌል፣ ነገረ ጳውሎስ፣ ነገረ ሐዋርያት” በሚል መደቦች ተከፍሏል። በተጨማሪም ሌሎች የቤተ ክርስቲያኑ ዋና መጻሕፍት (ሲኖዶስ፣ ቄርሎስ …) የየራሳቸው ክፍል አላቸው። በተጨማሪም ስለ መላእክት፣ ሰማዕታት፣ ሐዋርያት፣ ወራት …. ነክ ቃላት ትርጉም የሚያስረዱ ክፍሎችም አሉ።
የተረፉትን ክፍሎች ደግሞ ሕይወት ካላቸው ነገሮች ጋር የሚገናኙ (እንደ ነገረ አራዊት፣ ነገረ አዕዋፍ፣ ነገረ ዕፅዋት፣ ነገረ አዝርዕት፣ ነገረ ሥጋ፣ ነገረ ሕዋሳት/መልክዕ፣ ነገረ ሕማም …) የመሳሰሉ ክፍሎች ይገኛሉ። ከነዚህ ውጭም እንደ ነገረ ሥርዓተ መንግስት፣ አልባስ (ልብስ)፣ አጽር (አጥር)፣ ማያት (ውሃዎች)፣ ሐጻውንት (ብረቶች)፣ አብያት (ቤቶች)፣ አዕናቊ (ዕንቁዎች)፣ ወርቅ …. የመሳሰሉም ይገኛሉ፡፡
ለምሳሌ “ነገረ ሕማም” የተሰኘው ክፍል፣ በዚህ መልክ ህመም-ነክ ቃላትን፣ ግሶችንና ሀረጎችን ይፈታል፣
እጽሕፍ ነገረ ሕማም
ብድብድ ብ ቸነፈር
ጼደናታት ብ መጋኛ ጉስምት
ፈጸንት ብተቅማጥ
በደዶ ብ ፈንፃፃ
ዝልጋሴ ሕንጳጴ ብ ቊስለ ሥጋ
ቀበር በድን ብ እሬሳ
ዝኅር ብ መቃብር
እንፎራ ሳውዕ ማር ካህን ብ ቄስ
አንኰለሎ ብ አዞረው
ኖመ ኀለፈ ብ ሞተ
ለይልየ ብ ወይ እኔ
ወይ ሊተ አሌ ሊተ ብ ወዮ ለኔ
“ነገረ ሕማም” ምንም እንኳ ከህመም ዓይነቶች (መጋኛ፣ ጉስምት …) ቢጀምርም፣ ህመሙ ሲብስ የሚመጣውን (አዞረው፣ ቁስለ ሥጋ፣ ሞተ …)፣ በማስከተልም ቀብርን (እሬሳ፣ መቃብር …)፣ የቀብሩን ሥርዓት አስተናጋጆች (ቄስ …)፣ እና በለቅሶ ወቅት የሚባለውንም (ወይ ለኔ፣ ወዮ ለኔ …) ያካትታል።
ታዲያ አንዳንድ የ18ኛ እና 19ኛ ክ/ዘመን “ነገር” ብራናዎች የተወሰኑትን ቃላት ብቻ “ነገር” ስር ከመደቧቸው በኋላ፣ የተቀሩትን ቃላት ደግሞ በሞላ በአንድ ትልቅ ክፍል ይከቷቸዋል። ይሄም ወደፊት ለሚመጣው “የቅኔ ቤት ግስ” መነሻ ሳይሆን አይቀርም።
.
የቅኔ ቤት ግሥ
የቅኔ ቤት ግሥ በአብዛኛው የሚገኘው በ19ኛው እና በ20ኛው ክ/ዘመን በተዘጋጁ ብራናዎች ላይ ነው። ይህ አይነት መዝገበ ቃላት የተዘጋጀው በቃላቱ መድረሻ ፊደል ቅደም ተከተል ስለሆነ ቅኔ እና ሌሎች ግእዝ ግጥሞችን ለመድረስ ይረዳል።
በዚህም ምክንያት እስካሁን ድረስ በቅኔ ቤት ተፈላጊነት ስላለው፣ ተማሪው ወይም በእጁ ይገለብጠዋል አሊያም ከታተሙት አንዱን “መጽሐፈ ግስ” ገንዘቡን አጠራቅሞ ይገዛል።
የግእዝ ፊደላት 26 ቢሆኑም የቅኔ ቤት ግስ 21 ክፍሎች አሉት። ምክንያቱም ሀ ሐ ኀ፣ ሠ ሰ፣ አ ዐእና ጸ ፀአብረው አንድ ክፍል ውስጥ ስለሚመደቡ ነው።
ከ19ኛ ክ/ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የሚገኙት የቅኔ ቤት ግስ ብራናዎች በቅድሚያ ቃላቱን በመድረሻ ፊደል ወደ የተለያየ ቤት ይመድባሉ (ለምሳሌ፣ ሰአለ፣ ሠረቀ፣ ኖለወ)። በመቀጠልም እያንዳንዱ ቤቱ ውስጥ (ለምሳሌ “ረ”) ደግሞ ከእንደገና በቃላቱ መነሻ ፊደል ይደረደራሉ።
ለምሳሌ የ “ረ” ቤት ቅደም ተከተሉ፣
ሐሥረ፣ ሐረረ፣ ኀብረ፣ ሖረ
ለወረ፣ ለጠረ
መሀረ፣ መሐረ
…
አመረ፣ አሰረ፣
ገብረ
ፈጠረ
የረ መድረሻ ቤትም እንደተጨረሰ “ሩ” እያለ እስከ “ሮ” ድረስ ይቀጥላል፤
ለምሳሌ ሪ ላይ፣
ሰንኮሪ
ታስሪ
ቴጌሪ
ባለፉት ሃያ አመታት የታተሙት የቅኔ ቤት ግሶች ደግሞ ተማሪው እንዲቀለው በማለት ከነጠላው ግስ በማስከተል ከግሱ የሚወጡትን ዘሮች (ቅጽሎች፣ ስሞች) ይደረድራሉ።
ለምሳሌ፣
መሀረ አስተማረ
ምሁር ውስጠ ዘ (የተማረ)
መምህር ባዕድ ቅጽል (አስተማሪ)
መሀርት መድበል (አስተማሪዎች)
ትምህርት ባዕድ ከምዕላድ (በቁሙ፣ ትምህርት)
ትምህርታት በብዙ (ትምህርቶች)
.
የመምህር ክፍሌ ግስ አወጣጠን
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወደ ግእዝ-አማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሥራ እንዴት ሊገቡ እንደቻሉ፣ “መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” መግቢያ ላይ የመምህራቸውን ኑዛዜ እንዲህ አቅርበውታል፤
“…ኋላም በጊዜ ሞት አስር ዓመት ምሉ ከርሳቸው ጋራ ለነበረው ለሀገራቸው ልጅ ለተማሪያቸው እንዲህ ብለውታል፤ ‘ልጄ ሆይ ይህነን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደ ገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ በመዠመሪያው አበገደን ጥፈኽ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው። አንባቦችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፤ የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ፣ ዘር ኹን፣ ዘር ያድርግኽ፤ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለሀገርኽ ያብቃኽ’ ብለው ተሰናበቱት።”
ዲልማን (August Dillmann) የተሰኘ ጀርመናዊ የቋንቋ እና መጽሐፍ ቅዱስ ሊቅ በርካታ የግእዝ መጻሕፍትን በመመርመር በ1857 ዓ.ም “Lexicon Linguae Aethiopicae” የተሰኘ የግእዝ-ላቲን መዝገበ ቃላት አዘጋጅቶ ነበር። መምህር ክፍለ ጊዮርጊስም የዲልማንን መዝገበ ቃላት አይተው፣ “ሥራን መንቀፍ በሥራ ነው እንጂ በቃል ብቻ መንቀፍ አይገባም” ብለው የጀርመናዊውን መዝገበ ቃላት በሥራ ነቅፈው አዲስ ግስ (መዝገበ ቃላት) የጀመሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ እንደሚነገሩን ምጽዋ በስደት ሳሉ ነበር።
መምህር ክፍሌ በ1870ዎቹ መጀመርያ የግእዝ-አማርኛ ግሳቸውን (መዝገበ ቃላት) ረቂቅ ሲልኩ ይህንንም መልእክት አብረው ልከው ነበር፤
“የዚህ ግሥ ሥራው አልተጨረሰም፤ ስምና ግዕዘ ብሔር ቀርቶታል። ጊዜ ቢገኝ ሲታተም ይጨረሳል። ተራም ቤቱን ሳይለቅ አንዳንድ የፊደል ተራ ተዛውሮ ይገኛል። ኋላ ይቀናል። አማርኛው ለሰው እንዲሰማ የሀገረ ሰብ አማርኛ አለበት፤ ‘ሥር፣ ሥራ’ በብዙ አንድ አማርኛ ይሆናሉ። ሥራ ሲበዛ ሥሮች፣ ሥርም ሲበዛ ሥሮች ይባላል። እንዲህ ያለ ሲገኝ ያለ መምህር ለሁሉ አይሰማም። ስለዚህ ሥራ ብሎ በብዙ ‘ሥራዎች’ እንደ ማለት ያለ ይጥፋል። እንዲሰማ ነው እንጂ መልካም አማርኛ አይደለም።
“ሦስቱ ‘ሀሐኀ’፣ ሁለቱ ‘ሠሰ’፣ ሁለቱ ‘አዐ’ እንዳይሳሳቱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። አለዚያ ተራ ይበላሻል። የፊደልም ተራ ‘ሀላዊ’ ሳይል ‘ሀለደ’ አይልም። ከ‘ላ’‘ለ’ ይቀድማል ብሎ ‘ሀለደ’ ይቅደም ቢል ከ‘ዊ’‘ደ’ አይቀድምም ይላሉ። ሁሉ እንዲህ ነው፣ ቤቱን ካለቀቀ ግዕዝ ሐምስ ቢቀዳደሙ ግድ የላቸውም። ሦስተኛው ፊደል ያለ ተራው እንዳይገባ ይጠብቃሉ።
ፍችም አእማሪ ‘ያወቀ’፣ አእማሪት ‘የወደደች’፣ እንዲህ ያለ ፍች አለው፡ ያንዱ ፍች ለሁሉ ይሆናል። የፊደል ግድፈት ተጠንቅቃችኁ ተመልከቱ፤ ዕለቱን ተጨርሶ ሳይታረም መጥቶላችኋል። ሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ አሜን።”
መምህር ክፍሌ ከምጽዋ የላኩት ‘ግስ’ በአሁኑ ወቅት በሦስት ግልባጭ ይገኛል።
ሁለቱ አቡነ አሥራተ ማርያም በ1920ዎቹ ያስገለበጡዋቸው ሲሆኑ በEthiopian Manuscripts Microfilm Library (EMML) በፕሮጀክቱ ፊልም ተነስተዋል – EMML 2334 እና EMML 2335 ይሰኛሉ። ሌላኛው ግልባጭ ደግሞ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተመራማሪ ፈረንሳዊው ኮኸን (Marcel Cohen) በ1915 ያስገለበጠው ሲሆን እሱ እንደሚለው ዋናው ኮፒ አሊቴና ሳይገኝ አይቀርም። ከዚህ በተጨማሪም አሁን የት እንዳለ ባናውቅም፣ አለቃ ኪዳነ ወልድ ከመምህር ክፍሌ የወረሱት እና በኋላ ያስፋፉት ሌላ ግልባጭ መኖሩንም ማስታወስ ያስፈልጋል።
.
ይዘት
መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ ግሳቸውን ከምጽዋ ሲልኩ “የዚህ ግሥ ሥራው አልተጨረሰም .. ጊዜ ቢገኝ ሲታተም ይጨረሳል … የፊደል ግድፈት ተጠንቅቃችኹ ተመልከቱ፤ ዕለቱን ተጨርሶ ሳይታረም መጥቶላችኋል” በማለት ነበር። ስለዚህ ግሱም መታየት ያለበት እንደ መጀመርያ ሙከራ (ረቂቅ) ነው።
ግሱ ከመጀመሩ በፊት ተጠቃሚውን እንዲረዳ መለስተኛ ርባ ቅምር (የግስ እርባታ አመል) የሆነ አጭር መግቢያ ተዘጋጅቷል። መግቢያውም፣
“ግሥ ከሁለት ፊደል አይወርድም፤ ከሰባት ፊደል አይወጣም” በማለት ይጀምራል።
በመቀጠልም ስለ ግስ አመሎች የተወሰኑ ፊደሎች (ሀ፣አ እና ወ፣የ) በግስ እርባታ ቅርጽ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ሲናገሩ፣ “እሊህ ያሉበት ግሥ ከቤቱ ዘር ጥቂት ጥቂት ይለወጣል” በማለት ምሳሌ ይሰጣል።
ቀጥሎም ሰላሳ ሁለቱን የግስ ሠራዊትና ስምንቱን የግስ አርዕስት (ቀተለ፣ ባረከ፣ ጥሕረ፣ ኖለወ፣ ቀደሰ፣ ደንገፀ፣ ተጋብአ፣ አናኅሰየ) ዘርዝሮ ሳቢዘር ስለሚገኝባቸው ግሶች ያወራል። በመጨረሻም ግሱ ውስጥ ስለሚገኙ ‘የግሥ ምልክት’ (ጥ – የሚጠብቅ፣ ላ – የሚላላ) በማለት ያስረዳል።
መምህር ክፍሌ ግሳቸውን ለመስራት ሲነሱ በቤት መምቻ ፊደል የተደረደረውን የዘመኑን የቅኔ ቤት ግሳቸውን በመያዝ ነው።
የቅኔ ቤት ግስ በቤት መምቻ ፊደል መሰደሩን እንዲሁም በአማርኛ ሞክሼ ፊደላት የሚባሉት መዳበላቸው ስላልተስማማቸው በአዲስ መልክ አዲስ ግስ ይሰራሉ። ከEMML 2335 መረዳት እንደምንችለው የቅኔ ቤት ግሱን ወስደው፣ አብረው የተዳበሉትን (ሀ፣ሐ፣ኀ)፣ (ሠ፣ሰ)፣ (አ፣ዐ) እና (ጸ፣ፀ) መለያየት ይጀምራሉ። ከያንዳንዱ ቤትም በ ‘ሀ’ የሚጀምሩትን ለብቻ፣ በ ‘ለ’ የሚጀምሩትን ለብቻ …. አድርገው ግሱ በመድረሻ ፊደል መደርደሩን ትቶ በመነሻ ፊደል መሰለፍ ይጀምራል።
አንድ ግስ የሚደረደረው በቀደማይ (ያለቀ ድርጊት – ‘ኖረ’) አንቀጹ ሲሆን፣ በመቀጠልም እዛው መስመር ላይ ካልኣይ (ያላለቀ ድርጊት – ‘ይኖራል’) እና ሣልሳይ አንቀጾች (ዘንድ/ትእዛዝ ‘ይኖር ዘንድ/ይኑር’) ነው። ከዚያም የግሱ አርእስት (ንዑስ አንቀጽ – ‘መኖር’) ይከተላል። ግሱም የሚተረጎመው በግሱ አርእስት መሠረት ነው።
ሀለጥወ፣ ይሄሉ፣ የሀሉ፣ ሀልዎት – መኖር
በመቀጠልም ሣልስ ውስጠ ዘ (‘ኗሪ’) እና ሌሎች ዘሮች (ዘመድ፣ ሳቢ፣ ጥሬ፣ መ ስም) ይተረጎማሉ። ግሱ አድራጊና ተደራጊ አምዶችም ካሉት (‘አኖረ’ ‘አስኖረ’ ‘ተኖረ’) እዛው ተተርጉመው ዘሮቻቸውም (‘ኑሮ’ ‘አኗኗር’) ይቀርባሉ።
ሀላዊ፣ ዊት – ነዋሪ
ሀላውያን፣ ያት – ነዋሮች፣ የሚኖሩ
ሳድስ ውስጠ ዘ (ህልው ‘የሚኖር’) እና በሳድስ የሚጀምሩ ዘሮች (‘ህላዌ’ ‘ህልውና’) ግን በፊደል ተራቸው ሳድስ ፊደሉ (‘ህ’) ላይ ይደረደራሉ።
ህሉና – አነዋዎር
ህሉት – የምትኖር
ህልው – የሚኖር
ህልዋን – የሚኖሩ
ህልዋት – የሚኖሩ፣ ኑዋሮች
ህላዌ – አነዋዎር፣ አካል፣ ባሕርይ
ህልውና – አነዋዎር
በመቀጠልም የቃሉን አጠቃቀም ከግእዝ ሥነጽሑፍ በመጥቀስ ከትርጉሙ ይዘታዊ ዐውድ ጋር ያቀርባሉ።
፫ ህላዌ በአካላት፣ ፩ ህላዌ በመለኮት – አነዋዎር ሲል
ኢሐመ በህላዌ መለኮቱ – ባህርይ ሲል
አበዊነ ሰመይዎሙ ለህላውያት አካላተ – አካል ሲል።
መምህር ክፍሌ ለአብዛኛው ግሶች (ከ50 በመቶ በላይ) ምስክር ወይ ጥቅስ ይቀርባሉ። በብዛት ግን ጥቅሶቹ ከየት እንደሆኑ አይነግሩንም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑትን የተወሰኑትን ግን ምንጫቸውን ያቀርባሉ፣ ለምሳሌ መጽሐፈ ምሥጢር፣ ጾመ ድጓ፣ አቡሻክር … የመሳሰሉትን።
በተጨማሪም መዝገበ ቃላቱ በተሻለ መልክ እንዲነበብ አንዳንድ ማመላከቻዎችን አስገብተዋል።
በቊሙ – ትርጉሙ ካማርኛ አንድ ሲሆን።
ምሳሌ፣ ሃይማኖት – በቊሙ
ጥሬ – ከድሮ የቃላት ዝርዝር (ጥሬ ኦሪት፣ ጥሬ ነገሠት) ሲገኝ፣
ምሳሌ፣ ሐመድ – በጥሬ ኦሪት መድልው ይለዋል።
ቦ – ሌላ አጻጻፍ ሲኖረው፣
ምሳሌ፣ ሐሔሬኤል – ቦ ሐኤሬኤል
ቋንቋ ምንጭ – አብዛኛው ጊዜ አረብኛ፣
ምሳሌ፣ ህላል – ሠርቀ ወርኅ (አረብ)
የግስ ቤት – ከ32 የግእዝ “ሰራዊት” ውስጥ በየት እንደሚመደብ
ምሳሌ፣ ለሐወ – የባልሐ ቤት ነው።
እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ ገለጻ መምህር ክፍለ ጊዮርጊስን ለመዝገበ ቃላት ሥራ ያነሳሳቸው ምንም እንኳ የዲልማን ሥራ (“Lexicon Linguae Aethiopicae” 1865) ነው ቢሉንም፣ የመምህር ክፍሌ ግስ በቃላት አመራረጥና አፈታት እንዲሁም በጥቅስ ምርጫው የራሱን መንገድ የቀየሰ ይመስላል።
የመምህር ክፍሌ “ግስ” ከዲልማን የግእዝ-ላቲን “ሌክሲኮን” እንዲሁም ከአለቃ ኪዳነ ወልድ “መዝገበ ቃላት” ጋር በተወሰኑ መስፈርቶች ከታች በሰንጠረዦች ተነጻጽሯል።
የሆሄ ቅደም ተከተል – አገራዊ እንዲሁም የሳባ ቋንቋ የሚጠቀመውን “ሀ ለ ሐ መ” የፊደል ተራ ወይስ አረብኛና ዕብራይስጥ (እንዲሁም ግሪክና ላቲን) የሚጠቀሙትን “አ በ ገ ደ” ተራ እንደመረጠ ያሳያል።
የግስ ማግኛ ዘዴ – አንድን ቃል (ግስ፣ዘር) ለማግኘት በግሱ ኀላፊ ጊዜ (ቀዳማይ አንቀጽ) ወይስ በሌላ (አርእስት) እንደተመረጠ ያሳያል። ለምሳሌ “ጻፈ” የሚለውን ግስ ብናይ ኀላፊ ጊዜ ጸሐፈ ሲሆን አርእስት ደግሞ ጽሒፍ፣ ጽሒፎት – መጻፍ ነው።
የግስ ዘሮች አቀማመጥ – ከግስ የሚገኙ ዘሮች አብረው ይደረደራሉ ወይስ በተለያየ ቦታ ይገኛሉ? ለምሳሌ ጸሐፈ (ጻፈ) ከሚለው ግስ ጸሓፊ፣ ጽሑፍ፣ መጽሐፍ፣ ጽሕፈት … የመሳሰሉ ዘሮች የት የት ተደርድረዋል?
ጥቅስ – የአንድን ቃል አጠቃቀም ለማሳየት ጥቅስ፣ ምስክር ይቀርባል ወይ?
ነባርና ግስ – ለነባር ቃላት ግስ ይፈለጋል ወይ? ለምሳሌ በተለምዶ ሀገር የሚለው ቃል ግስ የለውም። አለቃ ኪዳነ ወልድ ግን ሀገረ የሚል ግስ ያቀርባሉ።
የቋንቋ ንጽጽር – ቃሉ ከተዛማጅ ቋንቋዎች ጋር ይነጻጸራል ወይ?
.
.
.
ማሳረጊያ
መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ በ1870 ዓ.ም አካባቢ ያዘጋጁትን “ግስ” በሕይወታቸው መጨረሻ በ1900 ዓ.ም ለተማሪያቸው ለኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአደራ መልክ እንዲህ ብለው አስረከቡ፣
“የጐደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው። ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ። ዘር ኹን፤ ዘር ያድርግኽ፤ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ፤ ለሀገርኽ ያብቃኽ።”
አለቃ ኪዳነ ወልድም የፊደሉን ተራ ቀይረው (‘ሀ ለ ሐ መ’ ወደ ‘አ በ ገ ደ’)፣ ረጅም ሰዋስው አስገብተው፣ መዝገበ ቃላቱንም አስፋፍተው አጠናከሩት። እሳቸውም በሕይወታቸው መጨረሻ ለተማሪያቸው ለደስታ ተክለ ወልድ በአደራ በ1936 ዓ.ም አስተላለፉ።
ደስታ ተክለ ወልድም የተሰጣቸውን መዝገበ ቃላት አርመውና አስተካክለው በ1948 ዓ.ም መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ ብለው በመሰየም በአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት አሳተሙት … ይህ እንግዲህ ሌላ ታሪክ ነው፤ ታሪኩንም ወደፊት በአንድምታ ለማቅረብ እንሞክራለን።
.
ኅሩይ አብዱ
ግንቦት 2009 ዓ.ም
ስለግስ አጠር ያለ ገለጻ የለውም። ስለተለያዩ የግስ አይነቶች በትክክል የሚገለጽበት መንገድ የለውም። በርግጥ ይህ እንደ ኢትዮጲያ አዲስ ምእራፍ ነው። እናመሰግናለን
LikeLike
ኅሩይ አብዱ – የአለቃ ክፍሌን ታሪክና ሥራ በተከታታይ እንዲህ በጥንቃቄ አሳምረህ በማቅረብህ ትመሰገናለህ። አንተም ሊቅ ነህ ወንድሜ።
LikeLike