“የአጭር ልብወለድ ታሪክ”
ከታደሰ ሊበን
.
[በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]
.
“መስከረም” በተባለው በመጀመሪያው መጽሐፌ በመቅድሙ ላይ አጭር ልብወለድ ምን ዓይነት ድርሰት እንደሆነ፣ ጣዕሙን፣ አስፈላጊነቱን፣ መጠኑን፣ የመነጨበትን አገር፣ ያመነጩትን ሰዎች፣ እንደዚሁም ደግሞ በእድገቱ የተሳተፉትን ብዙ የየሀገሩን ደራሲዎች (ስማቸውን ጭምር) ከብዙው በጥቂቱ አድርጌ ገልጬ ነበር።
“አጭር ልብወለድ ታሪክ ከጥበበ ቃላት (Literature) ጥንታዊ ክፍሎች አንዱ ክፍል ነው። እንዲያውም እሱ ከሁሉም ቀዳሚ ነው ይባላል። ምክንያቱም ጥንት በዋሻ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የዋሻ ሰዎችና አዳኞች ማታ ማታ እሳት ዳር ቁጭ ብለው ስለ ቀኑ ጀብዱአቸው ሲያወጉ ይህንኑ ብልኀት ሳያውቁት በልማድ ይሰሩበት ነበር። እሱም አሁን በዘመናችን ተረት ተረት እየተባለ የሚወጋው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይበልጡንም በብሉይ ኪዳን ይኸው ጥበብ በብዙ ተሰርቶበት ይገኛል። እሱም፣ ለምሳሌ ያህል፣ ‘ነቢዩ ዮናስና የእግዚአብሔር ፈቃድ’ እና ‘ኢዮብና ሰይጣኑ’ ናቸው።
በአውሮፓ ውስጥ አጭር ልብወለድ በልዩ ልዩ አቅድ ተዘጋጅቶ እየቀረበ ከዚያ በፊት ካለፉት ዘመናት ሁሉ በጣም ተስፋፍቶ ይገኛል። እንዲያውም በዚህ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሌላ እንደ አጭር ልብወለድ በፍጥነት የሚያረካ፣ የሕይወትን ትርጉም በመጠኑ የያዘ፣ ደግሞም መደሰቻ የሆነ የጥበብ ቃላት (Literature) ክፍል ፈጽሞ የለም ይባላል።


የዚሁም እድገት ምክንያት በጠቅላላው እነሱ እንደሚሉት ባገራቸው ውስጥ በየጊዜው እየተሻሻለ በሚሄደው ከልብወለድ ጽሑፍ መስፋፋት የተነሳ ነው። ያንባቢዎቻቸው ቁጥር እየበዛ በመሄዱ፣ ተከታይ ትውልድንም የሚመግብ ቤተ መጻሕፍት በየስፍራው በመገኘቱ፣ ብዙ አንጎሎች ነቅተው ብዙ ብዕሮች በኪስ በመዋል ፈንታ ከወረቀት ላይ እንዲውሉ በመሆናቸው ብዙ ጥሩና ደግሞም መካከለኛ የረጅም ልብወለድ ታሪክ (Novel)፣ የትያትር (Play)፣ የግጥም (Poetry)፣ እንዲሁም ደግሞ ያጭር ልብወለድ ታሪክ ጸሐፊዎች በየጊዜው ተፈጥረዋል።
ዛሬ አጭር ልብወለድ በነዚህ አገሮች ከዚህ በላይ በገለጽኩት ምክንያት የተነሳ ዓላማው በጣም ተስፋፍቷል። የአጭር ልብወለድ ሕይወት ታሪክ ሲነበብ እንደሚገኘው በአስራ ስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ የዚሁ አገር የጥበበ ቃላት ሰዎች አጭር ልብወለድን እንደ ደንበኛ ጽሑፍ አይቆጥሩትም ነበር። በአስራ ዘጠንኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ አጭር ልብወለድ የረጅም ታሪክ (Novel) አጠር ያለ መግለጫ ወይም አንድ ደራሲ ሥራ በፈታ ጊዜ የአንጐሉ ማንቀሳቀሻ እንዲሆን የሚያደርገው ጽሑፍ ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር።
ነገር ግን በዚሁ በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ አንዳንድ ለዚሁ ሙያ ተሰጥዎ የነበራቸው ደራሲዎች አጭር ልብወለድ በራሱ ሙሉ የሆነ (እንዲያውም ከረጅም ልብወለድ የተለየና ይበልጥ አጥጋቢነት ያለው) መሆኑን ገለጹ። ስለዚህ በዚሁ ጊዜ አጭር ልብወለድ ራሱን የቻለ አንድ የጥበበ ቃላት (Literature) ክፍል ሆኖ ተቆጠረ። በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ በጋዜጦች ላይና በመጻሕፍትም ይኸው ጽሑፍ በጣም ተፈላጊ ሆነ። ስለዚህ ብዙ የአጭር ልብወለድ ደራሲዎች ከየስፍራው በየጊዜው መፈጠር ጀመሩ።


አጭር ልብወለድ ታሪክን ብዙ ሊቆች ምን እንደሆነ ተንትነው ለመግለጽ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሙከራ አድርገው ነበር። ነገር ግን አጥጋቢ አድርጎ ለመግለጽ አዳጋች ሆኖባቸዋል። በመጨረሻም አጭር ልብወለድን መግለጽ ሕይወትን ተንትኖ ለማስረዳት እንደ መሞከር ነው ከማለት ደርሰዋል።
አጭር ልብወለድ በጠቅላላው እንደ ረዥም ልብወለድ የታሪክ ባለቤቶች (Characters)፣ የታሪክ አወራረድ (Plot) እና አጥጋቢ የሆነ መደምደሚያ (Climax) እንዲኖረው ያሻል። ረዥም ልብወለድ ከምዕራፍ ወደ ምዕራፍ ካንድ ሁኔታ ወደ አንድ ሁኔታ መስፋፋት ወይም መሸጋገር ይችላል።
አጭር ልብወለድ ግን ይህን ሁሉ ለማድረግ ጊዜ ወይም ስፍራ የለውም። ታሪኩን ባንድ ጠቅላላ ሐሳብ በተወሰኑ የታሪክ ባለቤቶች በሚገባ በፍጥነት መግለጽ ግዴታ አለበት። ጥሩ አጭር ልብወለድ ባጭሩ አነስ ያለ ልብወለድ ነው። በውስጡም ባንድ በትንሽ የእረፍት ጊዜ ሊነበብ የሚቻል የሚያሳዝን ወይም የሚያስደስት ታሪክ ያለበት ነው። ለዚሁም ጥሩ ምሳሌ ይህ የሚቀጥለው ያገራችን ወግ ነው፤ ‘አሞራና ቅል ተጋቡ። ቅሉ ተሰበረ። አሞራውም በረረ።’
አጭር ልብወለድ ታሪክ ልክ እንደዚህ እጥር፣ ምጥን፣ ጣፈጥ ማለት አለበት።
ይኸው ሙያ ዛሬ በየትም ቦታ ሊወሳ በተነሳ ቁጥር፣ ምንም ቢሆን ስማቸው የማይዘነጉ፣ ቢሞቱም የማይሞቱ፣ ብዙ የየሀገሩ ደራሲዎች አሉ። ከነዚህም ጥቂቶቹና ዋና ዋናዎቹ በፈረንሳይ አገር Guy de Maupassant (ጊ ደ ሞፓሳ)፣ Anatole France (አናቶል ፍራንስ)፣ Honoré de Balzac (ኦነሬ ደ ባልዛክ)፤ በእንግሊዝ አገር Edward Morgan Forster፣ Hector Hugh Monro (Saki)፣ Joseph Conrad፣ William Somerset Maugham፤ በሩሲያ Anton Chekhov (Анто́н Че́хов)፣ Leo Tolstoy (Лев Толсто́й)፤ በአሜሪካ ደግሞ Edgar Allan Poe እና Ernest Hemingway ናቸው።
አንባቢው ባጭሩ የነዚህን የጠቀስኳቸውን ደራሲዎች አጭር ልብወለድ ድርሰቶች ቢያነብ አጭር ልብወለድ ምን እንደሆነ፣ እኔም ስለሱ ምን ለማለት እንደፈለግኹና እንደሞከርኩ መረዳት ይችላል።



እንዲሁም ደግሞ ይህንኑ ለመሳሰለ ዘመናዊ ሙያ ገና ጐልማሳ ሁና ለተገኘች አገር፣ እንደዚሁ እንደቀሩት በጣም እንደገፉት አገሮች እሷም ደርጅታ አንድ ቀን ይህንኑ በመሳሰለ ዘመናዊ ሙያ ተካፋይ ሆና በበኩሏ እንድትራቀቅ፣ መሪዋና ባለሥልጣኖቿ ትምህርት ቤት በመክፈትና የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት በማቋቋም ሲደክሙላት በሚታዩት፣ ቡቃያዎቿ ድንገት ለዚሁ ጥበብ ፍሬ መስጫ የሚያስፈልገው ጊዜያት ረዘም ያለ ሆኖ፣ ለደካሚዎቹ የድካማቸውን ዋጋ በቶሎ በብዛት ሊሰጡ ሳይችሉ ቀርተው ይዘግዩ እንጂ፣ መቸም አንዳንድ እንደዚሁ በየጊዜው አለፍ አለፍ እያሉ ደርሰናል የሚሉ ምንም ቢሆን አይታጡም።
ሆኖም የዚሁ ደረስኩ ደረስኩ የሚለው፣ አዲስ ዘመናዊ ደራሲ ትልቅ ችግር አንባቢዎች ጽሑፌን ይወዱልኝ ይሆን? ጽሑፌ የአጭር ልብወለድን ደንበኛ ሕግ የተከተለ ይሆን? እንደ ሌሎቹ አገሮች ደራሲዎች አሳዛኝነት፣ አስደሳችነት፣ ጣፋጭነት ይገኝበት ይሆን? ያገሬን ስም ከቶ ላስጠራበት እችል ይሆን?
እናንተ ናችሁ ፈራጆቹ። እስቲ እየዘለቃችሁ እዩልኝ። እኝሁና የኔዎቹም። ‘ጅብ ነች’፣ ‘የተበጠሰ ፍሬ’፣ ‘ሰውዬው’፣ ‘ውሻውና መንገዶቹ’ እና ‘ትንሹ ልጅ ’” … ብዬ ነበር።


ነገር ግን የኔዎቹን ልብወለዶች “አጠረ!” እና “አይ ታደሰ! – ምነው ትንሽ ቢያስረዝመው!” ወይም “ታደሰን ጠላሁት – ታሪኩን ከመሀል ቆመጠው” የሚሉ አሳቦች ከአንዳንድ በታሪኩ ከተመሰጡ አንባቢዎቼ አንደበት ሳይወጣና አልፎ ተርፎም ከኔው ጆሮ ሳይደርስ አልቀረም።
ነገር ግን “አላሳጠርኩትም” ወይም “የድርሰቱ ደንቡ ነው” ወይም “አንባቢዎቼ እንደዚህ የሚሉት የአጭር ልብወለድን ጣዕም ለማወቅና ለመለየት ስለማይችሉ ነው” ብዬ ማናቸውንም ይህንን የመሳሰለ መከላከያ (የጽሑፉ ባለሥልጣን በመምሰል ወይም በመሆን) ከማቅረቤ ይልቅ፣ ዛሬም በአሳብ ከአንባቢዎቼ ሳልርቅ አብሬ ሆኜ በነገሩ ሁኔታ ባዝንና በሚቻለኝ መጠን ደግሞ ደግሜ ማስረዳትን ብሞክር እወዳለሁ።
እርግጥ ነው አጭር ልብወለድ በኢትዮጵያችን አዲስ ነገር ነው። አንባቢዎችም ዛሬ በጽሑፉ ግር ቢሰኙበትና የመሰላቸውንም ሐተታ ቢያቀርቡበት የሚታሙ ወይም የሚወቀሱ አይደሉም። ሆኖም ከአንድ የጥበቡ አገልጋይ ነኝ ከሚል ደራሲ (ራሴን በአፌ ሙሉ ነኝ ማለቴ ሳይሆን) ‘አጭር ልብወለድ ታሪክ ነው’ ተብሎ በወረቀት ላይ የሰፈረ ድርሰት አንድ ሙሉ የሆነ፣ ሲጨረስም ያለቀ መሆኑን መመርመርና ማወቅ ዛሬ የያንዳንዱ አንባቢ ግዳጁ ሊሆን የሚገባ ነገር ነው።


ባጭሩ፣ አጭር ልብወለድ ታሪክ የትልቅ ታሪክ ብጫቂ ወይም ቁራጭ ነገር አይደለም። አንድ አጭር ልብወለድ በራሱ ቋሚ የሆነ አንድን አሳብ ወይም አንድን ጠባይ (ማለት አንድ የተለየ ሰውን) በሚገባ የሚገልጽ ራሱን የቻለ የጥበበ ቃላት (Literature) ክፍል ነው። ስለዚህ ከአንዳንድ አንባቢዎቼ አንደበት የወጣው ሁሉ ካለመግባባት የሆነ አስተያየት ነው።
አንድ አጭር ልብወለድን የአንድ ረጅም ልብወለድ ታሪክ ቁራጭ ነው ማለት አንድ እንጐቻን የአንድ እንጀራ ብጫቂ ወይም ኩርማን ነው እንደማለት ያህል ነው። ነገር ግን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንባቢዬ እንደሚያውቀው ሁሉ እንጐቻ እንጀራ የአንድ ትልቅ እንጀራ ቁራጭ አይደለም።
አንድ እንጐቻ፣ እርግጥ በመጠን አነስ ይበል እንጂ፣ እንደ አንድ እንጀራ ሙያን የሚያሳይ ዓይን ያለው ክብ የሆነ ጠርዝ ያለው፣ እንደ አንድ ትልቅ እንጀራም በምጣድ ላይ አክንባሎ ተደፍቶበት፣ እንዳይነፍስበትም መጨቅጨቂት ተደርጐበት፣ ጋጋሪዋንም እንደ ትልቁ እንጀራ ጊዜ ጭስ አሞጫሙጯት፣ እሳት ለብልቧት የተጋገረ ትንሽ እንጀራ ነው።
እንደዚሁም አንድ አጭር ልብወለድ እንደ አንድ ረዥም ልብወለድ ታሪክ አይርዘምና አይስፋፋ እንጂ እሱም በበኩሉ ሊያወሳ የተነሳበት አንድ ሙሉ የሆነ አሳብ የያዘ፣ የታሪክ ሰዎች ሳይበዙ በጥቂቱ ያሉበት፣ ራሱን የቻለ፣ ሲጨረስም የተፈጸመ እንጂ ያልተቆረጠ፣ ደራሲውንም በደንብ ያደከመ አንድ የጥበበ ቃላት ክፍል ነው።
ሆኖም፣ በዚሁ ጽሑፌ ወደ መጀመሪያው ላይ እንዳተትኩት ሁሉ፣ ያለውን ትክክል ያልሆነ ግምት ከአንባቢያን አእምሮ አስወግዶ፣ እንደዚህ ያለውን የጥበቡን ትክክለኛ ትርጉም ለማሳደር በየጊዜው እንደዚህ ለመግለጽ ከመሞከር ይልቅ ዝም ብሎ አንባቢያንን በብዙ አጭር ልብወለድ ታሪኮች ማበልጸግ የተሻለ መንገድ ነው።
እኔም ይህንኑ በመገንዘብ ባለኝ ትርፍ ጊዜዬ ይህንኑ በማዘጋጀት ላይ እገኛለሁ።
ታደሰ ሊበን
1952 ዓ.ም
.
(በደራሲው መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)
[ምንጭ] – “ሌላው መንገድ” (፲፱፻፶፪) ገጽ ፱-፲፬፤ “መስከረም” (፲፱፻፵፱) ገጽ 5-10።