“የጉለሌው ሰካራም” (ልብወለድ)

“የጉለሌው ሰካራም”

በተመስገን ገብሬ

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሠፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ፣ ሰካራሙ ተበጀ፣ ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል።

የሕይወቱ ታሪክ ፍጹም ገድል ነው። ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው። ራሱን ጠጉር ውሀ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም። ማለዳ አይናገርም። በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ማታ ሲራገም ወይም ሲሳደብ፣ ሲፈክር ወይም ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል። ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኘው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል። ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኘው ሁሉ ጋራ ማታ ይስቃል። ቢያውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው። ከሰላምታው ጋራ ድምጥ ትሰማለችሁ። ከአፉ ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም።

ቡን በተፈላ ጊዜ በጉለሌ በየምድጃው ሥር የሰካራም ተረት የተጫወተው ሰው ሁሉ የተናገረ በተበጀ ላይ ነው። መልኩን አይተውት ያላወቁ ባልቴቶች እንኳ ከፍንጃል ቡኑን ፉት እያሉ የሌላውን ሰካራም ተረት በተበጀ ላይ ይላክኩት ነበር። ይህ እውነት ነበር። በጠባዩ ከተባለበት የባሰ ሰካራም ይሁን ወይም የተሻለ የጉለሌ ባሕር ዛፍ ውስጥ ወጥቶ አንድ አዲስ እንግዳ ሰው ሆኖ ለአዲስ አበባ ታይቷል።

ከዱሮው የእንጨት ጉምሩክ አጠገብ ወደ ምሥራቅ ሲል ካለው ወንዝ ማዶ ድልድዩን ወደ ምሥራቅ ተሻግሮ መጀመሪያ የሚገኘው አነስተኛ ሳር ክዳን ቤት የተበጀ ቤት ማለት ያ ነው። በዚያው በቤቱ በዚያው በጉለሌ በሠፈሩ ኖረ።

እንጨቱን ተሸክሞ አፈሩን ቆፍሮ ቤቱን የሰራው እርሱ ነው። ዋጋ ከፍሎ አስከድኖታል።

ተበጀን ኩራት ተሰማው። ቆይቶ ደግሞ ዓይኖቹ እንባ አዘሉ። በጉንጩም የእንባ ዘለላ ወረደው። በግራ እጁ መዳፍ ከጉንጩ የተንከባለለውን እንባ ጨፈለቀው። ዓይኖቹ እንባ ያፈሰሱ ለራሱ ጎጆ ስላለው ነው። ሊነገር በማይቻል ደስታ ልቡ ተለውሷል።

ዝናብ ያባረራቸውም ከቤቱ ጥግ ሊያጠልሉ ይችላሉ። ቤት የእግዚአብሔር ነውና ወዥብ እንዳያገኛቸው ከቤት ውስጥ ዝናቡ እስኪያባራ ይቆያሉ። ተበጀን “ቤትህን ይባርክ” ሊሉት ነው።

“እንግዲህ መንገደኛው ሁሉ ‘ይህ የማን ቤት ነው?’ ብሎ ሲጠይቅ የተበጀ ሊባል ነው” አለ።

ቀጥሎ ደግሞ፣

“ ‘ተበጀ የትኛው ነው?’ ሲባል ‘ዶሮ ነጋዴው’ ሊባል ነው” አለ።

“ ‘ዶሮ ነጋዴው የትኛው ነው?’ ሲባል ‘ያ የጉለሌው ሰካራም’ ሊባል ነው። አወይ! እኔ ተበጀ፤ ተበላሽቻለሁ”

አለና ደነገጠ።

“ከዚህ በኋላ ስለ ቤቱ ክብር እንኳ መጠጥ መተው ይገባኛል” አለ።

መጠጥ ለመተው ያሰበበት የመጀመሪያ ጊዜው ይህ ነው። ሰካራምነት ጉዳት መሆኑ ተሰምቶት እንደሆን ይናገር ስለ ቤት ክብር ማለቱ ግን ወደ ዳር ይቆይ። ስለ ቤት ክብር ምን ያውቃል? ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ አይደለምን?

ሰካራሙ ተበጀ የሰራውን የገዛ ቤቱን ከፍቶ፣ ገበና ኩራዙን አስቀምጦ፣ ክብሪቱን ለመጫር ሲያወጣ በሐሳብ ተሰቅዞ እንደዚህ አሰበ፣

“መምረጥ አለብኝ። ከዚህ ቤት ያለው መጠጥ ሁሉ አንድ ሳይቀር እየወጣ ይፍሰስ። ከዚህ በኋላ ክብሪቱም ኩራዙም በቤት ይደር። በአዲሱም ቤት ብርሃን ይዙርበት። አለዚያም በአዲሱ ቤት መጠጥ ይዙርበት። ኩራዙና ክብሪቱ ከቤት ይውጣና ይፍሰስ። ሊደረግ የሚገባ ከሁለቱ አንዱ ነው እንጂ፤ በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት በአንድነት ይህች ውሸት” አለና ሳቀ።

ከሁለቱ አንዱን ለማድረግ ሳይቆርጥ መብራቱን አቃጠለና ተቀመጠ። እንደገና ደግሞ እንደዚህ አሰበ።

“አያድርገውና ዛሬ ሰክሬ ይህ ቤት ቢቃጠልብኝ አመዱን አይቶ በሰካራሙ ተበጀ ላይ ለመሳቅ ድፍን ጉለሌ ነገ ከዚህ ነው የሚቆም! ጉለሌ ምን ባለኝ? ወሬ ከማቡካት በቀር ጉለሌ ምን ሥራ አለው? ለአዲስ አበባም የስድስት ወር መሳቂያ በሆንኩ ነበር። መንገድ አላፊዎችም ነገ በዚህ ሲያልፉ አመዱን አይተው ይህ የተቃጠለው ቤት የማን ነበር ሲሉ የተበጀ ሊባል ነው። በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት ባንድነት ይህች ውሸት!”

ወደ ውጭ እንደ እርም ወርውሮት የነበረውን የመጠጥ ጠርሙስ ሁሉ በጨለማው ዳብሶ አንድ በአንድ ለቃቀማቸው። አንዱን ግን ቀና አደረገና ከአፍንጫው አስጠግቶ አሸተተው። በጠርሙሱ ቅርፅ የመጠጡን አይነት አወቀው። ዊስኪ ነበርና ስለዚህ ነው ሰው እንዳይሰማ ቀስ ብሎ የሳቀ። የጠርሙሱን ግማሽ ከጠጣ በኋላ ግን በአፉ ቡሽ ቢወትፉበት ለሳቁ መጠን የለውም።

“ጉለሌ ተኝቷልና ከዚሁ ከባሕር ዛፍ ሥር ቁጭ ብዬ ብጠጣ የሚታዘበኝ የለም” አለና አሰበ።

እውነቱን ነው። ጉለሌስ ተኝቶ ነበር ነገር ግን አሁን እርሱ ጠጥቶ የሰከረ እንደሆነ ጉለሌን ሊቀሰቅሰው ነው እርሱ ከጠጣ በጉለሌ ማን ይተኛል?

ጠርሙሱን ከከፈተው በኋላ ብርጭቆ ያስፈልገው እንደነበር ትዝ አለው። ሶስት የሚሆን ደህና ጉንጭ ጠርሙሱን ከአፉ አስጠግቶ ጨለጠ። ከዚያ በኋላ የሚጠጣበት ብርጭቆ ሊያመጣ አሰበ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በሦስት ጉንጭ ምን ያህል ጠርሙሱን እንዳጐደለው ለማወቅ ጠርሙሱን ቀና አድርጎ በጨረቃዋ ተመለከተ።

“ግማሹን ያህል ሰርጉጀዋለሁ” አለና በሳቅ ፈነዳ።

“ለዚችስ ብርጭቆ ማምጣት አያሻም” እያለ ጠርሙሱን አምቦጫቦጨው።

በቀኝ ክንዱ መሬቱን ተረክዞ የቀረውን ጅው አድርጎ ወደ ውስጥ ወረወረው። ባዶውን ጠርሙስ ደግሞ በጁ እየጠነቆለ፣

“አንተን ደግሞ ለአንድ ዶሮ ለውጬ ሞያ አስይዝሃለሁ የዊስኪ ቅርፍቱም ዋጋ አለው አይጣልም” አለ።

እንዲሁ ሲጠጣ ሌሊቱን አጋመሰው። ቀጥሎ ከእግሩ በታች የወደቀውን ጠርሙስ እየቆጠረ፣

“ይህን ሁሉ እንደጠጣሁት አላምንምና በጉለሌ አፈርሳታ ይደረግልኝ እነ ናቄ እነ ተሰማ አጐቴም ይጠጣሉ” አለ።

የጠርሙሱ መጠጥ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ ከዚያው ከዛፉ ሥር ተቀምጦ ያን ጠንካራ ትምባሆውን ከአፉ አለየውም። በሳቀ ጊዜ ብቻ መልሶ ዝም እስኪል ድረስ መጠጡ ወይም ትምባሆው ከአፉ ያቋርጣል። የመጠጥና የትምባሆ ጊዜው ተበጀ ይህ ነው።

ማለዳ በቀዝቃዛ ውሀ ታጠበ። ቋንጣም እንቁላልም ጠበሰና በዳቦ በላ። የጦም ቀን ነበር፣

“ለአባ ተክለ አረጋይ አልናገርምና ነፍሴ ሆይ ግድ የለም” አለ።

የነፍስ አባቱን ማለቱ ነው። ምናልባት በአመት እንኳ አንድ ጊዜ ጠይቋቸው ወይም ጠይቀውት አያውቁም። እርሱንም አያደርሰውም፤ እርሳቸውም ከበዓታቸው አይወጡም። አንዳንድ ጊዜ የዛሬውን እሑድ ዕረፍት አደርገዋለሁ ያለ እንደሆነ እግሩን ደህና አድርጎ የሚታጠብበት ቀን ማለት ነው።

ደክሞት ነበርና ደህና እንቅልፍ ተኝቶ ነበር። ዝናቡን ነጐድጓዱን ጐርፉን ውሀ ምላቱን አልሰማም። አንዳች ነገር ሰማ። ዘፈንና እልልታ የሰማ መሰለው። ትናንት ከጠጣው መጠጥ ኃይል መሰለውና ይህስ እብደት ነው እንጂ ስካር አይደለም አለና ተመልሶ ተኛ።

እንደገና አዳመጠ። የእርዳታ ጥሬ ጩኸት ሰማ። ከአልጋው ዘልሎ ከወረደ በኋላ ቤቱን ለመዝጋት ጊዜ አላገኘም። በትልቁ ወንዝ ዙሪያ ቁመው ይጮሁ የነበሩ ሰዎች የውሀው ምላት የሾገሌን ገረድ እንደጠለፋት ነገሩት። ጐርፍ የወሰደው ሾገሌን ራሱን ቢሆን ወይም የሾገሌን ገረድ ለተበጀ ማዕርግ ምኑም አይደለም።

“ገረዲቱን እናንተ በመጨረሻ ያያችኋት ወዴት ነው?”

ብሎ ጠየቀና እየጠለቀ በዋና ይፈልግ ጀመር። ስለ ሾገሌ ገረድ በትኩስ ውሀ ምላት ለመግባት አንሠዋም ያለው ጉለሌ በዳር ተሰልፎ ቁሞ ተበጀን ይመለከት ነበር።

ብዙ ጠልቆ ከቆየ በኋላ ብቅ አለና፣

“አገኘኋት መሰለኝ” ብሎ በዳር ላሉት ጮሆ ተናገረ።

ለሰው ሁሉ ደስታ ሰጠው። ከሁሉም ይልቅ እርሱን ደስ አለው። የጠለቀውና የዋኘው ረጅም ጊዜ ስለሆነ ደክሞት ነበር። ነገር ግን ሊያወጣት ይገባዋል። ጠለቀና አገኛት። በአሸካከሙ ላይ ጥበብ ያስፈልጋል። አለዚያስ ውሀው ምላት እንደገና ይነጥቀዋል። እንደተሸከማት ውስጥ ለውስጥ ዋኘና ከዳር ብቅ አለ።

ከሸክሙ ክብደት ኀይል የተነሳ ወዲያው ወደቀ። እርዳታ ተነባበሩለትና ጐትተው እርሱንም እርሷንም አወጧቸው።

ተበጀ ተንዘራግቶ በብርቱ ውጋት እያቃተተ የጉለሌ ሰው በሳቅ ሲፈነዳ ሰማ – ከራሱ በኩል ቀና አለና፣

“ሴትዮዋ ድናለች?” ብሎ በርኅራሄ ድምፅ ጠየቃቸው።

አንዱ ቀረበና፣

“አሳማ ነው ያወጣኸው” አለው።

የሚያቃትተው ተበጀ ከወደ ራሱ ቀና አለና፣

“አሳማ?” ብሎ ጠየቀው።

“ለመሆኑ ከእናንተ ውሀ የወሰደባችሁ ሰው ነበር ወይስ አሳማ ኑሯል?” ብሎ ተበጀ ጠየቀና ያቃትት ጀመር።

ጎረቤትህን እንደ ነፍስህ ውደድ ቢባልም ሰዎችን እነ እቲላን ነበር እንጂ የእቲላን አሳማዎች አልነበረም። እቲላ ጎረቤቱ አሳማ አርቢ ነው። ውሀው ምላት ነጥቆ ወስዶ የነበረ የእቲላን አሳማ ሳለ፣ ያላዩትን ቢያወሩ ግድ የሌላቸው ሰዎች የሾገሌን ገረድ ውሀ ወሰዳት ብለው አውርተው የተበጀን ነፍስ ለአንድ አሳማ ነፍስ ሊያስለውጡት ነበር።

መልካሙ የሰማዕትነት ሥራው ሁሉ ደግሞ እንዲሁ ርካሽ ሆኖ የሚቆጠር የሆነበት ዘወትር የሚሰክር ሆኖ ስለታወቀ ነው። በግብረ ገብም መሠረት አደረግሁት የሚለውን ሁሉ ሳያውቀው እንደሚያደርገው ይቆጥሩበታል።

“በጎ ሥራህን ሁሉ በትኩስ መቃብር ውስጥ አፈር አልብሰው አንተ ሰው ሁን ሚስት አግባ ልጆች ይኑሩህ” ይሉና ይዘልፉት ነበር።

ድኃ ቢሆን ወይም ባለጠጋ፣ ሰካራም ቢሆን ወይም ትኅርምተኛ፣ ሁሉም የጉለሌ ልጆች ነን አባታችንም ጉለሌ ነው ብሎ ራሱን የሚያኮራ እርሱ ተበጀ ብቻ ነበር።

.

ከሚያሰክር ሁሉ ትኅርምተኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ አስቦ ነበር። ሰክሮ ያደረበት ሌሊት አልፎ ብርሃን በሆነ ጊዜ ከእንግዲህ ወዲህ “መጠጥ አልቀምስም” እያለ እየቀኑ በብርሃን ተበጀ ምሏል። በነጋው የበለጠ ጠጥቶ የባሰ ሰክሯል። ለመስከር ይጠጣል። ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል። ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል። ይህ ነው ተበጀ።

“ይህን መስከርህን ካልተውህ ላንተ አበ ነፍስ አልሆንህም”

ብለው የመጀመሪያ ንስሐ አባቱ ብዙ ከመከሩት በኋላ መንፈሳዊ ልጅነቱን ከርግመት ጋራ አስወግደውታል።

ገረዶቹም ለርሱ ተቀጥሮ መስራትን ከውርደት ቆጥረውት እየነቀፉት ሂደዋል። “መጠጥ ካልተውህ አናገባህም” ብለው እየጊዜው ለጋብቻ ጠየቋቸው የነበሩ በቁመናው አሰናብተውታል። በሰምበቴም በማኅበርም ማኅበረተኛ ለመሆን የጠየቃቸው ነፍሱን ሳይቀር ንቀዋታል።

ይህ ሁሉ በእርሱ ዘንድ ከኢምንት አይቆጠርም። ያሉትን ቢሉ እርሱ ምን ቸገረው? ገንዘብ እኮ አለው፣ ገንዘቡም ጥሬ ብር ነው። ባለጠጋ ነው። መስከርም የባለጠጎች ነው። ትኅርምተኛ መሆንም የድሆች ነው። እንደ ልዩ ዓመፅ አድርገው ለምን በእርሱ ይቆጥሩበታል? እንዲህ በተከራከረ ነበር።

ነገር ግን ልዩነት አለው። እርሱ ብዙ ጊዜ ሰክሮ ኦቶሞቢል በላዩ ላይ ሂዶበታል። ሰክሮ በበነጋው ከእንቅልፉ ሲነቃ ብዙ ጊዜ በእስር ቤት ውስጥ አድሮ ራሱን አግኝቶታል። በጉለሌ መንገድ ዳር ባሉት በብዙ የውሀ ጉድጓዶች ሰክሮ ገብቶባቸው እየተጮኸ ጉለሌ አውጥቶታል። ሰክሮ የጐርፍ ውሀ ከወሰደው በኋላ ብዙ ጊዜ የእሳት አደጋ ደርሶለታል። ሰክሮ ከቤቱ መድረስ እያቃተው ከወደቀበት ባቡር መንገድ ሳይነሳ ብዙ ጊዜ ጐርፍ በላዩ ላይ ሲሄድበት አድሯል።

ይህ ሁሉ ውርደት እና ርክሰት ነው እንጂ ክብር ከቶ አይደለም። እንግዲያውስ ክቡር ድሀ ነው። ገንዘብ ስለሌለው ራሱን መግዛት ይችላል። ባለጠጋ ደግሞ መናኛ ተራ ነው። ገንዘብ ስላለው ራሱን መግዛት አይችልም። ይህን ሁሉ አሰበ። ስለኖረ ባይማር እንኳ ብዙ ከማወቅ ደርሷል።

“ባለጠጋ ሆነ ወይም ድሀ፣ ሰው ከራሱ የበለጠ መሆን ይገባዋል” አለ።

ቤቱን ከሰራ ከአምስት ወራቶች በኋላ ጀምሮ ተበጀ መጠጥ ከቶ አልጠጣም። ስለቤቱ ክብር መጠጥ እርም ነው ማለት ጀምሯል። ያለፈውንም ዘመን መራርነት እያሰበ ተንገፍግፏል። አንድ ብሎ ለመጀመር ከወደቀበት ትቢያ አንስቶ ዕድሉን ሲያራግፍ እንደ ራእይ ያያል።

ያበላሸው እድሉ አሳዘነው፣

“በዚህ እድሜየ ሁሉ ሚስትም አላገባሁም ልጅም የለኝም” አለና አዘነ።

ውሾቹ እየተባሉ ሲጫወቱ ተመለከተና፣

“አመሌ ውሻ ነበርና ከውሾች ጋር ኖርሁ” ብሎ ራሱን ረገመ።

በውሾቹ ፈንታ አሁን በዚህ እድሜው ልጆቹ ዙሪያውን እየተጫወቱ ሲፈነጩ ባየ ነበር እንዲሁ አሰበ።

ቀልድና ወዘበሬታ ስለሚያውቅ እንደዚህ እያለ ይቀልድ ነበረ፣

“ጐጃም የአበባውንና የግራር ማሩን ይጭናል። የተጉለትና የአምቦ ወረዳ ጌሾውን ያቀርባል። የሆላንድ የቢራ ፋብሪካ ቢራውን ያወጣል። የኢጣሊያ ፋብሪካ ነቢት ያፈላል። መደቅሳና ዘቶስ በግሪክ አገር ይጣራል። በስኮትላንድ ዊስኪ ይጠመቃል። ይህ ሁሉ የሚደረገው በአራዳ የሚቀመጡትን እንዳይጠማቸው ነው። በዚህም ምክንያት በዋሻዋ እንደምትጮህ ጉጉት ሰካራሞች በከተማይቱ ይጮሃሉ።

“በደብረ ሊባኖስ ግን ድምጡን ዘለግ አድርጎ የሚናገር ወፍ እንኳ የለም። ውሀ እንኳ የሚጠጣ በመቅኑን ነው። በአራዳ ይሁን ወይም በገዳም ምንም ገንዘብና ቤስቲን ለሌለው ውሀ ደግሞ እጅግ አድርጎ ይጣፍጣል።”

ይህን የመሰለ ቀልድ ይቀልድ ነበረ።

ሰካራሙ ተበጀ ግን ገንዘብ እያለው ውሀ ጣፍጦታል። ልዩ በሆነው በዚያ ማታ ወደ አልጋው ወጥቶ በተኛ ጊዜ መጠጥን እርም ካደረገው አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀን እንደሆነው ጊዜውን ቆጥሮ አወቀው። ጊዜውንስ ማወቅ ለምን አስፈለገው? “እንደ ጥንብ መጣያ ትንፋሼ ተበላሼ፤ አፌም እንደ እሬት መረረኝ። ሹልክ ብዬ ዛሬ ብቻ፣ ጥቂት ብቻ፣ አንድ ጊዜ ብቻ፣ እኔ ብቻ፣ ብጠጣ ምን ይጐዳል” ብሎ ተመኝቶ ስለነበረ ነው።

ነገር ግን ወደ አልጋው ወጥቶ ተጋደመ። ከተጋደመም በኋላ ተነሥቶ ወደ መጠጥ ቤት ለመሄድ ከባድ ከነበረው እንቅልፉ ለመላቀቅ ታገለ። በመጨረሻ ወደ መጠጥ ቤት በሄደ ጊዜ በውኑ ወይንም በህልሙ እንደነበረ ራሱም ተበጀ አላወቀውም።

የጠጣም እነደሆነ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ይደረግ በነበረው የአረመኔ ቅጣት እጁና እግሩ ከመቆረጥ ይደርሳል ብሎ አላሰበም። አናጢ የጠረበው እንጨት ከቅልጥሙ ይቀጠላል ብሎ ክፉ ህልም አላለመም። አንድ ሰካራም አንካሳ በአንድ ዓመት ስንት የእንጨት እግር ይጨርሳል ብሎ ስለ ዋጋው አልተጨነቀም። ደህና ምቾት ያለው አንካሳ ለመሆንም ገንዘብ ያስፈልጋል።

አንካሳው ሰው ሰካራም እንደሆን በእንጨት እግሩ በሰላም ጊዜ ይሄድበታል። በሁከት ጊዜ ደግሞ ይማታበታል። ሲማታበት ይሰበራል ሲሰበርም ሌላ የእንጨት እግር መግዛት ያስፈልገዋል። ስለዚህ የእንጨት እግር የሚሰሩ አናጢዎች ለደንበኞቻቸው ትርፍ መጠባበቂያ እግር በሜንጦ ሰቅለው ያስቀምጡላቸዋል ይባላል። ተበጀን እንደዚህ ያለ ሕይወት አያጋጥመውም።

በበቀለች ዓምባዬ መጠጥ ቤት ደረጃውን ተራምዶ ተበጀ በገባ ጊዜ የጥንት ወዳጆቹ ሰካሮች በእቅፉ ላይ ተነባበሩ። እንደተወደደ መሪ በጫንቃቸው ላይ ተሸክመው እየተቀባበሉት በእልልታ ጮሁ። ከመጠጥ ቤት ጠፍቶ የነበረው ተመልሷልና በሰካሮች ሁሉ ዘንድ ደስታ ሆነ።

እንኳን በደህና ገባህ! የመጠጥ ጠርሙሶቹን እንደ ዘንባባ ይዘው ተቀበሉት። ቁማርተኛው ያረጀ ግሪክ እየሳለ ተናገረ። ሁሉም በደስታ ይጮሁ ስለነበረ አንድም የሰማው የለም። ረስቶት የነበረው መጠጥ ጣዕሙን ገና ሳያውቀው ገና ከጫንቃቸው ሳይወርድ በጩኸቱም በመጠጡም ተበጀ ሰከረ።

ከጫንቃቸው ወደ ቁልቁል ጣሉት።

የሕፃንነትህ ዘመን አልፏልና ራስህን ችለህ መሄድ ይገባሃል አሉት። ሰማህ? አቅም አንሶህ መሄድ አቅቶሃል እንደ ኩብኩባ እየዘለልህ መሄድ ትችል እንደሆነ ምርኩዜ ይኸውልህ ብሎ አንካሳው በየነ አቀበለው። ምርኩዙን ለመያዝና ለመጨበጥ እጁን ሲዘርር በግምባሩ ከበሬት ላይ ተደፋ። እንደወደቀም ሳለ፣ እስኪነቃ ድረስ በመካከሉ ስንት ሰዓት አልፎ እንደነበረ ለማስተዋል አልቻለም።

የመጠጥ ቤቱ እመቤት ጊዜ አልፏልና ከውጭ ጣሉትና ቤቱን ዝጉት ብላ አዘዘች።

ወደ ቤቱ የተመለሰ መስሎት ሄደ። ማወቅ አልቻለምና ወዴት እንደሄደ ግን አላወቀም። አንድ መንገድ ሲያቋርጥ ተሰናከለና ወደቀ። ከወደቀበትም ምድር ላይ በዳሰሰ ጊዜ ለእጁ የገጠመው የባቡር ሐዲድ ነው። ቤቱ ያለ በጉለሌ ነው። የሰከረበት ደግሞ የበቀለች መጠጥ ቤት ነው። መጠጥ ቤቱም ከዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው።

ምን ያህል ቢሰክር ነው የጉለሌ መንገድ ጠፍቶት እስከ ባቡር ሐዲድ ድረስ ተሳስቶ የሄደ? ራሱን ይዞ ለመጮህም ራሱ ወዴት እንዳለ ማወቅ አቃተው። እንደ ቤቱ መንገድ ጠፋበት።

ጥቂት መስማት ከቻለ በኋላ ጩኸት በስተኋላው ይነፋ የነበረ የእሳት አደጋ ወይስ ባቡር ኑሯል? እያፎደፎደ ሲሄድ ከወደ ኋላው በኩል ምን እንደገፋው አላወቀም፤ ከኋላው በኩል ትልቅ ኀይል መታው። ከፊቱ በኩል የቀበሮ ጉድጓድ ተቀበለው። እግሩ እንደ ብርጭቆ ነከተ። ከወደቀበትም ሌሊቱን ሁሉ ደም ከእግሩ ዘነበ። ትንኝም እንደ ንብ በላዩ ሰፍሮ ደሙን መጠጠው።

ቀና ብሎ በአጠገቡ የወደቀውን የአህያ ሬሳ አሞራዎች ሲግጡት አየ። የቀረው ልቡ በድንጋፄ ተመታ። የእርሱ እድል ከአህያው ሬሳ ዕድል ቀጥሎ ሆነ። በስካሩ ምክንያት እስከ ዘላለም ድረስ ከአህያ ሬሳ እንደማይሻል ተረዳው። ነገር ግን የአሁኑ መረዳት ለምን ይበጀዋል? ማወቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ አልፏል።

በሕይወቱ ሳለ እንደወደቀ ያህያ ሬሳ መነሳት አልቻለምና በተራው አሞራዎቹ ዓይኑን ሊመነቁሩት ነው። ሥጋውን በልተው ከጨረሱት በኋላ አጥንቱን ሊግጡት ነው። ሌሊት ደግሞ ቀበሮዎች ሊረፈረፉበት ነው። ይህን እንዲያመልጥ ለመሸሽ ከወደቀበት ሊነሳ እያቃተተ ሞከረ። ባልተቻለው ጊዜ ግን ተጋደመ።

በደሙ ላይ እንደተጋደመ አራት ቀኖች አለፉ። እግሩ እንደ ቀርበታ ተነፋ። እንደ ቅጠልያ ያለ እዥ ወረደው። ከወደቀበት ያነሳው የመንግሥት አምቡላንስ ባገኘው ጊዜ ፈጽሞ በስብሶ ነበር።

ዶክቶር ክሪመር ባዩት ጊዜ ከሰማይ በታች ሊደረግለት የሚችል ሕክምና ምንድር ነው? ደሙ አልቋል። በሽተኞችን ለመርዳት በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች የተለገሰውን ደም ለሚሰክር ጥጋበኛ አልሰጥም። እርሱን መንካትም መርዙ ያስፈራል። ከዚህ በፊት ይህ እንዳይደርስበት እንዳይሰክር ብዙ አስጠንቅቀነው ነበር አሉ።

ከንፈሩ ተንቀሳቀሰ። ላብ በፊቱ እንደ ውሀ ፈሰሰ። ለመናገር ጣረ። በመጨረሻ ግን መናገርም ሳይሆንለት ቀረ።

ሐኪሞችም የገማውን ልብሱን ገፈፉት። እንደ ቅባትም ያለ መድኀኒት ቀቡት። ከግማሽ ሊትር የበለጠ ደም ሰጡት። በመጠጥ ከተጐዳው ከልቡ ድካም የተነሳ ኤተር ለመቀበል አለመቻሉን ከተረዱ ዘንድ የሚያፈዝ መድኀኒት ጀርባውን ወግተው ሰጡት።

አንዱ ሐኪም ከጉልበቱ ይቆረጥ አለ።

ሌላው ግን ሁለተኛ እንዳይሰክር ከቂጡ አስጠግቼ እቆርጠዋለሁ አለና ከቂጡ አስጠግቶ ቆረጠው። የተቆረጠውን እግሩን ከፊቱ መዝናችሁ አስታቅፉት ብሎ አስታማሚዎችን አዘዘ።

እግሩን ከፊቱ መዘኑትና አሥር ኪሎ የሆነው እግርህ ይኸውልህ ታቀፈው ብለው አስታቀፉት።

በዚህ ጊዜ በአጥንት የተጣሉት ውሾች በላዩ ላይ ተረፋረፉበትና በድንጋፄ ከእንቅልፉ ነቃ።

ይህ ሁሉ የደረሰበት በህልሙ እንደነበር ማወቅ አቃተው።

ከአልጋው ላይ ወረደና ገረዱን ወይዘሮ ጥሩነሽን ከመኝታቸው ቀስቅሶ እየጮኸና እየተንዘረዘረ፣

“ስንት እግር ነው ያለኝ?” ብሎ ጠየቃቸው።

ወይዘሮ ጥሩነሽም፣

“ዱሮ ስንት እግር ነበረዎ ጌታ?” ብለው ጠየቁት።

እየጮኸ ሦስት ጊዜ፣

“ሁለት ሁለት ሁለት ነበረኝ” አላቸው።

ሦስት ጊዜ ሁለት ስድስት ማለት ነው።

“ልጆቼን ያሳደገች ላም ካራት እግር የበለጠ አልነበራትም። ሰለዚህ የእርስዎም እግሮች አራት ናቸው” አሉት።

“የምሬን ነው የምጠይቅዎ!” አለና ጮሆ ተንዘረዘረ።

“በእርግጥ ሁለት እግሮች አሉዎት ጌታ” አሉት።

ተበጀ እግሩን አጐንብሶ ለመሳም ሞከረና ራቀው። ወደ ሰማይ እያየ፣

“መጠጥ ማለት ለእኔ ሞት ማለት ነው” አለ።

ጊዜውም ሌሊት ነበር።

“እንደዚህ የማሉበት ሌሊት ያልፋል” ብለው ወይዘሮ ጥሩነሽ መለሱለት።

.

ተመስገን ገብሬ

1940 ዓ.ም

.

(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

[ምንጭ] – “የጉለሌው ሰካራም”። ኅዳር ፲፱፻፵፩። ገጽ 1-13።

2 thoughts on ““የጉለሌው ሰካራም” (ልብወለድ)

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s