የበአሉ ግርማ ገጸባሕርያት

“የበአሉ ግርማ ገጸባሕርያት”

ከብሩክ አብዱ

.

በአሉ ግርማ (1931-1976 ዓ.ም) ልጅነቱን ያሳለፈው በሱጴ (ኢሉባቦር)፣ ጉርምስናውን ደግሞ በአዲስ አበባ (“ልዕልት ዘነበወርቅ” እና “ጀነራል ዊንጌት” ት/ቤቶች) ነበር። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና በMichigan State University የጋዜጠኝነትና የፖለቲካል ሳይንስ ትምህርቱን ተከታትሏል። የሥራ ዘመኑንም ባብዛኛው ያሳለፈው በማስታወቂያ ሚኒስትር በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች ነበር።

በአሉ ስድስት ተወዳጅ ልቦለድ ሥራዎችን አሳትሟል። እኒህም “ከአድማስ ባሻገር” (1962 ዓ.ም)፣ “የህሊና ደወል” (1966 ዓ.ም)፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” (1972 ዓ.ም)፣ “ደራሲው” (1972 ዓ.ም)፣ “ሀዲስ” (1975 ዓ.ም) እና “ኦሮማይ” (1975 ዓ.ም) ናቸው። ከኒህም በተጨማሪ በርካታ መጣጥፎችን፣ ቃለ-መጠይቆችን እና ርእሰ አንቀጾችን ጽፏል።

በዚች ጽሑፍ፣ በአሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” መጽሐፉ ላይ የተጠቀመባቸውን አንዳንድ የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቶች በቅርበት ለማሳየት እሞክራለሁ።

.

“ከአድማስ ባሻገር”

ይህ መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለንባብ የበቃው በ1962 ዓ.ም ነበር። ምንም እንኳን ዳግመኛ እስኪታተም ሁለት አመት ቢፈጅበትም በወጣበት ዘመን በሰፊው ተነቧል (ከ1962 እስከ 2004 ዓ.ም ዘጠኝ ጊዜ ታትሟል)። ከ1980ዎቹ ጀምሮ ደግሞ በሬድዮ ትረካ ቀርቧል።

ከአድማስ ባሻገር” የበአሉ ግርማ የመጀመሪያ የልብ ወለድ መጽሐፍ ቢሆንም በኩር የፈጠራ ሥራው አልነበረም። ከዚያ በፊት በአሉ በተለያዩ የተማሪ መጽሔቶች (የጄነራል ዊንጌቱ “Chindit” እና የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ “News and Views”) ግጥሞቹን ማቅረብ ለምዶ ነበር። ከፈጠራ ድርሰት ባሻገርም በጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅነት (“News and Views”፣ “Addis Reporter”፣ “መነን” እና “አዲስ ዘመን”) የበርካታ አመታት ልምድ ነበረው። በኒህም አመታት በተቻለው መጠን የአዘጋጅነቱን ሚና በመጠቀም (በተለይ በ”መነን” እና “አዲስ ዘመን”) በርካታ ኪነጥበባዊ አምዶችን (ለምሳሌ “አጭር ልብወለድ”፣ “ከኪነጥበባት አካባቢ”) አስጀምሮ  ነበር።

ስለዚህ ከመጀመሪያው ልብወለዱ ኅትመት በፊት በአሉ ቢያንስ ለአስር አመታት ያህል ኪነጥበባዊ ጽሑፎችን ሲያነብ፣ ሲጽፍና ሲያዘጋጅ የከረመ ደራሲ ነበር። እናም የበኩር መጽሐፉ እምብዛም የጀማሪ ድርሰት የጀማሪ ድርሰት ባይሸት ብዙ ሊያስደንቀን አይገባም።

ከአድማስ ባሻገር” ታሪኩ በግርድፉ የሚከተለውን ይመስላል። እድሜውን በዘመናዊ ትምህርት ያሳለፈ አንድ ኢትዮጵያዊ ወጣት (አበራ) የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በአንድ ወገን፣ ብዙም ስሜት በማይሰጠው ሥራ በመትጋት ንብረትና ልጆች እንዲያፈራ ወንድሙ (‘ጋሽ’ አባተ) ቤተሰባዊ ግዴታውን ያስታውሱታል። በሌላ በኩል ደግሞ፣ “ጥሪውን” በመስማት ሥራውን ለቆ ሙሉ ሕይወቱን በሰአሊነት እንዲያሳልፍ አብሮ አደጉ (ሀይለማርያም) እና አዲሲቷ ፍቅረኛው (ሉሊት) ይገፋፉታል። አበራ ግን የሚፈልገውን የሚያውቅ አይመስልምና መምረጥ ይቸግረዋል።

የአበራም ወላዋይነት በራሱ፣ በቤተሰቡ፣ በጓደኛውና በፍቅረኛው ሕይወት ውስጥ የሚያስከትሉትን ለውጦችና መዘዞች ድርሰቱ በጥልቀት ይተርካል። እግረመንገዱንም፣ ደራሲው የዛሬ ሀምሳ አመት ግድም በነበረው የአዲስ አበባ ማኅበረሰብ ውስጥ ይፋጩ የነበሩትን “ባህላዊነት” እና “ዘመናዊነት”፣ “ሀላፊነት” እና “ጥሪ”፣ “መተማመን” እና “ቅናት” በገጸባሕርያቱ በኩል ያሳየናል።

ይህ ልብወለድ ከ50 በላይ ገጸባሕርያትን አቅፎ ይዟል። ከእነዚህም አራቱ ዋና ገጸባሕርያት (አበራ፣ ሀይለማርያም፣ ሉሊት፣ ‘ጋሽ’ አባተ)፥ ሰባቱ ጭፍራ (‘እሜቴ ባፈና፣ ሰናይት ‘ሱቅ በደረቴ’ …)፥ ሃያዎቹ አዳማቂ (ሱዛን ሮስ፣ ትርንጐ፣ ሚኒስትሩ …)፥ እና ከሃያ በላይ ደግሞ ስውር ገጸባሕርያት (ወፍራም ዝንብ፣ ባይከዳኝ …) ናቸው።

‘ዋና’ ገጸባሕርያትን እንደድርሰቱ አጥንት፣ ‘ጭፍራ’ ገጸባሕርያትን ደግሞ እንደትረካው ሥጋ ልናያቸው እንችላለን። ያለኒህ አስር ግድም ገጸባሕርያት “ከአድማስ ባሻገር”ን አንብቦ ለመረዳት በጣም ያስቸግራል (አንድ ተማሪ “መጽሐፉን ወደ ተውኔት ለውጠህ ጻፍ” ወይም “ልብወለዱን ላናበቡ ጓደኞችህ በአጭሩ ተርክ” ቢባል እኒህኑ ዋና እና ጭፍራ ገጸባሕርያት መጠቀሙ አይቀርም)። በተመሳሳይ መልኩ “አዳማቂ” ገጸባሕርያትን እንደ ክት አልባሳት ብናያቸው ያስኬዳል፤ እጅጉን ባያስፈልጉም ድርሰቱን በሚገባ ያስጌጡታልና።

ታዲያ የደራሲውን ጥበብ ለመረዳት አንዱ መንገድ የፈጠራቸውን ገጸባሕርያት በምን መልኩ ተንከባክቦ እንዳሳደጋቸው ለመረዳት መሞከር ነው። በመቀጠልም፣ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ወሳኝ ባይሆንም ጠቃሚ ሚና ከሚጫወቱት ሃያ “አዳማቂ” ገጸባሕርያት አምስቱን መርጬ እንዴት አድርጎ በአሉ ግርማ እንደሳላቸው ለማሳየት እሞክራለሁ።

እኒህንም አዳማቂ ገጸባሕርያት የመረጥኩበት ምክንያት እንደሚከተለው ነው። አብዛኛውን ጊዜ ደራሲዎች የዋና እና ጭፍራ ገጸባሕርያት አሳሳል ላይ ልዩ አትኩሮት (እንዲሁም በርካታ ገጾችን) ይሰጣሉ። በዚህም ምክንያት፣ የገጸባሕሪ አሳሳል ችሎታቸውን በሚገባ ለመመዘን ያስቸግረናል … ብዙም ባልተካነ ደራሲ እጅ እንኳን የዋና ገጸባሕርያት አሳሳል የስኬት ሚዛን ሊደፋ ይችላልና።

በአንጻሩ፣ በልብወለዱ ወሳኝ ሚና የማይጫወቱትን “አዳማቂ” ገጸባሕርያትን ለመሳል ደራሲው በአማካይ ከአንድ ገጽ በላይ ቀለም አያጠፋም። እኛም እንደ አንባቢነታችን እኒህን መስመሮች በቅርበት በማስተዋል “ደራሲው ባለው ውስን እድል ገጸባሕሪውን በሚገባ አዳብሮታልን?”፣ “የገጸባሕሪው ልዩ የሆነ ምስል በምናባችን ሊሳል ተችሏልን?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ መሞከር እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም ደራሲ በበርካታ ገጾች ገለጻ እና ንግግር አንድን ገጸባሕሪ በጉልበት ምናባችን ውስጥ ቢያስገባውም፣ ጥበበኛ ደራሲ ግን በአንዲት አንቀጽ ብቻ አይረሴ ምስል በአእምሯችን ሊቀርፅ ይችላል።

እናም የዚህ መጣጥፍ ጥያቄ፤ “በገጸባሕርያት አሳሳል ረገድ በአሉ ግርማ ምን አይነት ደራሲ ነው?” የሚል ይሆናል።

.

የአዳማቂ ገጸባሕርያት አሳሳል

የአንድ ልብወለድ ገጸባሕርያት ደራሲው በፈጠረላቸው ህዋ እና ባበጀላቸው ምሕዋር ይሽከረከራሉ። ይህም በሞላ ጎደል የሚቀየሰው በገጸባሕርያቱ ንግግርና በተራኪው ገለጻ ነው። የተራኪው ገለጻ የገጸባሕሪውን አጠቃላይ ገጽታ ሲወስንልን፣ የገጸባሕሪው ንግግር ደግሞ አስተሳሰቡንና ስሜቱን ቀንጭቦ ያሳየናል። በኒህም ሁለት ስልቶች በመደጋገፍ ደራሲው በኛ ባንባቢዎች ላይ የገጸባሕርያትን ምስል ለመቅረጽ ይሞክራል።

በ“ከአድማስ ባሻገር” በአሉ በርካታ የፈጠራ ህዋዎችንና ምሕዋሮችን ቀይሷል፤ የተራኪው “ሁሉን አውቅ” ባይ መለኮታዊ እይታ፣ የአበራ ውጥንቅጥ ሀሳቦችና ምኞቶች፣ የገድሉ “ሉሊት-ከበብ” ምሕዋር፣ የሀይለማርያም “አበራ-ተኮር” እሽክርክሪት … ወዘተ። በሌላ አነጋገር፣ በልብወለዱ ውስጥ አበራ የድርሰቱ “ፀሐይ” ሲሆን፣ እነ ሀይለማርያም እና ሉሊት ደግሞ ከአበራ ስበት ማምለጥ አቅቷቸው እሱኑ የሚሽከረከሩት ዓለማት ናቸው። በልብወለድም ውስጥ አብዛኛው ፍትጊያና ግጭት ያለው በነዚሁ በዋና እና በጭፍራ ገጸባሕርያቱ መሀል ነው።

በተቃራኒ መልኩ፣ በድርሰቱ ወሳኝ ሚና የሌላቸው “አዳማቂ” ገጸባሕርያት ግን ብዙ ጊዜ የተረጋጋ ህልውና ያሳያሉ። አንድም፤ ምሕዋራቸው ከዋናው ገጸባሕሪ (አበራ ወርቁ) እጅግ የራቀ በመሆኑ፣ አንድም ደግሞ፤ እንደተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ብለው ስለሚጠፉ የጭፍራ ገጸባሕርያትን ያህል የድርሰቱ እሳትና ፍትጊያ ብዙም አያሳስባቸውም። በዚህም ምክንያት የደራሲውን ጥበብ ለመለካት ጥሩ መስፈርት ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

በመቀጠል፣ በነዚህ ለታሪኩ ወሳኝ ሚና በማይጫወቱ አዳማቂ ገጸባሕርያት ላይ ደራሲው የተጠቀመውን የአሳሳል ስልት እዳስሳለሁ።

1. ሱዛን ሮስ

“ከአድማስ ባሻገር” ትረካው የሚጀምረው ዋና ገጸባሕሪው አበራ ብቻውን በሀሳብ ባሕር እየዋኘ ማንነቱን ሲፈትሽ፣ ከዛም የድሮ ፍቅረኛውን (ሱዛን) ሲያስታውስ ነው። ተራኪው ስለዚች ገጸባሕሪ የሚከተለውን ዘርዘር ያለ ገለጻ በጥቂት ገጾች ይሰጣል (በመጽሐፉ ገጽ 8-12)፤

‘የሰላም ጓድ ልኡካን ባልደረባ’፣ ‘ያለሙዚቃ ሰውነቷ አይፍታታም’፣ ‘ውርጭ ውስጥ እንዳደረ ብረት የሚቀዘቅዝ ጭን’፣

‘ረጅም ጠጉሯ ስር ውሎ እንደዝሆን ጥርስ የነጣ ማጅራት’፣ ‘የታጠፈ ቀሚስ’፣ ‘ሲቃ የያዘው ድምጽ’፣

‘ጉንጮቿ ላይ የነበረው ደም ቁልቁል የወረደ’፣ ‘ጸሀይ ያልነካው በሽተኛ ይመስል የገረጣች’፣

‘ከሩቅ ሲመለከቱት ነጭ ከቅርብ ሲያዩት ሽሮ የሚመስል ጥርስ’፣ ‘በረጅሙ ተንፍሳ’፣

‘ረጅም ጠጉሯን በሁለት እጆቿ ጭምድድ አድርጋ’፣ ‘እጆቿ ላይ ያሉት የደም ስሮች እንደሽምጥ አጥር ተገትረው’፣

‘የቀሉት ትናንሽ ውብ አይኖቿ’፣ ‘እንባ እየፈለቀ የገረጡትን ጉንጮቿን ያርሰው’፣

‘የየሙዚቃውን ስልት በግለት በስሜት … ትጠብቅ’፣ ‘ጸሀይ እንዳየች የጽጌረዳ እምቡጥ ወከክ ትርክክ’

ከላይ የምናየው ተራ ገለጻ አይደለም። ደራሲው የተራኪውን ድምጽ በሚገባ በመጠቀም የሱዛንን ሰውነት ብቻ ሳይሆን ስሜቶቿንም በሰፊው ስሎልናል። ቢሆንም በአሉ በዚህ አላበቃም። የራሷንም አንደበት በመጠቀም የአስተሳሰቧን ህዋ ይስልልናል። ሱዛንም ስትናገር ከሌሎች አዳማቂ ገጸባሕርያት ተለይታ የምትሽከረከርባቸውን የቃላት ምሕዋር መለየት እንችላለን። እኒህም “መስጠት”፣ “ሙዚቃ”፣ “ትዝ”፣ “አብረን”፣ “ደስ/ደስታ”፣ “ደንታ”፣ “ጽጌረዳ” እና “ፍጹም” ናቸው። እስቲ ለምሳሌ ያህል ሦስቱን በቅርበት እንመልከት፤

ሙዚቃ

ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ።”

ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ።

ያለሙዚቃ አይሆንልኝም ፍጹም አይሆንልኝም።”

ትዝ

“አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል።”

“እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች።”

ደስ/ደስታ

“ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል።”

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል።”

“እንዳንተ ያሉ … ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል።”

ሱዛን ደምቃ የምትታይ “አዳማቂ” ገጸባሕሪ ናት። ከ“ሽሮ” ጥርሷ ጀምሮ እስከ “ደስ” የሚሏት ወንዶች በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። በአሉ በጥቂት መስመሮች ይህን ሁሉ በምናባችን መሳሉ የሚያስደንቅ ነው። እንዲያውም ተጨማሪ ገጾች እና ሚና ቢጨምርላት “ጭፍራ” ገጸባሕሪ ሆና መመደብ ትችል ነበር።

2. ትርንጐ

ትርንጐ በድርሰቱ የአበራ የልጅነት የቤት ሠራተኛ የነበረች ናት። ተራኪው ስለዚች አዳማቂ ገጸባሕሪ የሚከተለውን ይገልጻል (በመጽሐፉ ገጽ 13)፤

‘እድሜዋ ከእርሱ እድሜ ገፋ ያለ’፥ ‘ፊቷ እንደውድቅት ጨለማ ጠቁሮ በወዝ የተንጨፈጨፈ’

‘ጠጉሯ አንድ ባንድ የሚቆጠር’፥ ‘ፍርጥምጥም ያለች ጉጭማ’

‘መደብ ላይ ተጋድማ’፥  ‘ከባይከዳኝ ጋር ስትዳራ’፥ ‘ደንግጣ ከላይዋ ላይ ስትወረውረው’

ይህ ጥሩ ምስል-ሳይ አካላዊ ገለጻ ነው። ቢሆንም ስሜቷን በሚገባ አይገልጽልንም፤ የምናውቀው ድንጋጤዋን ብቻ ነው። ታዲያ ከአንድ ገጽ ባነሰች ስፍራ ደራሲው ስሜቶቿን ከዚህ ይበልጥ ሊገልጽ ቢያዳግተው ሊያስደንቀን አይገባም (ለ“ሱዛን” አራት ገጽ መመደቡን እያስታወስን)። በተጨማሪም፣ ከአንደበቷ የምንሰማው ንግግር ተለይቶ የሚሽከረከረው በሁለት ቃላት (“ና ” እና “እንጫወት“) ዙርያ ነው፣

ና እንጫወት።”

ምን ቸገረህ እኔ አሳይሀለሁ።”

የኒህም ቃላት ምናባዊ ሀይል በንግግሯና በተራኪው ገለጻ በመደጋገፉ (‘ታጫውተዋለች’፣ ‘ከባይከዳኝ ጋር ስትዳራ’) ሳይጠነክር አልቀረም። እናም ትርንጐን ስናይ፤ እንደሱዛን ያልደመቀች፣ ግን የራሷ የሆነ ልዩ ፍካት ያላት ገጸባሕሪ ሆና እናገኛታለን። ደራሲው ይህችን ገጸባሕሪ በሚገባ ለማድመቅ ያልመረጠበትን ምክንያት ግን (የቦታ ማጠር ይሁን ለታሪኩ ሂደት ከዚህ በላይ መግለጽ አለማስፈለጉ) በእርግጠኝነት ለማወቅ ያስቸግራል።

3. ሴተኛ አዳሪ

“ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ አበራ ስሜቱን “ለማውጣት” (ለመወጣት) በተደጋጋሚ ሴተኛ አዳሪ ፍለጋ ይሰማራል። በድርሰቱ ላይ ተራኪው የሚከተለውን ገለጻ ይሰጠናል (በመጽሐፉ ገጽ 45-46፣ 88)፤

‘ቀያይ መጋረጃዎቹን እየገለጡ ከየደጃፉ ብቅ ብቅ’፥ ‘ድምጿ ጨለማውንና ጸጥታውን ቀደደው’

‘ከየሴቶቹ ቤት የሚመጣ የእጣንና የከርቤ ጢስ’፥ ‘በቀይ መብራት አንዷን ከሌላዋ መለየት አስቸጋሪ’

‘ሁለቱ ያገር ልብስ የተቀሩት … ሰውነት ላይ ልክክ የሚሉ ቀሚሶች ለብሰው’፥ ‘ዳሌዋ ሰፋ ብሎ የታየችው’

‘ሲገባ እንደሌሎቹ ወከክ ያላለችለት’፥ ‘በቅናት አይን ቆዳዋን ገፈፏት’፥ ‘የተቀባችው ሽቶ የተስማማው አይመስልም’

‘የሸማኔ መወርወሪያ ይመስል ወዲህና ወዲህ ይሯሯጣሉ’፥ ‘አንገቷን እንደእስክስታ ወራጅ እንክት’

በአሉ የሴተኛ አዳሪዎችን ገጸባሕሪያት በአንድ ክርታስ በጅምላ የሳላቸው ይመስላል። ከገለጻው ውስጥ በሚገባ ተነጥላ የምትታይ ሴተኛ አዳሪ የለችም፤ “መጋረጃ እየገለጡ”፣ “ወዲህና ወዲህ ሲሯሯጡ”፣ “በቀይ መብራት ሲዋሀዱ” ነው የምናስተውለው። በንግግራቸውም ቢሆን ሴተኛ አዳሪ ገጸባሕርያት በተወሰነላቸው የቃላት ምሕዋር (“አንቱ” እና “ኡኡቴ”) ነው የሚሽከረከሩት።

አንቱ

አንቱ ዛሬ ደግሞ ዉስኪ ይዘው መዞር ጀመሩ እንዴ?”

“ጋሼ አንቱ ምን እንጋበዝ ታዲያ?”

“ምን የሚያስቅ ነገር አገኙብኝ አንቱ?”

ደራሲው እዚህ ላይ ግለሰባዊ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ መልክ ያለው የሴተኛ አዳሪዎችን ምስል (በገለጻ እና ንግግር ታግዞ) ለመቅረጽ የመረጠ ይመስላል። በአሉም ይህን ያደረገበት ምክንያት በልብወለድ ድርሰቱ ውስጥ የሴተኛ አዳሪ ገጸባሕርያት በታሪኩ ፍሰት ላይ ወሳኝ ሚና ስለማይጫወቱ ይሆናል። ዋናው ገጸባሕሪ አበራም ቢሆን “ስሜቱን ለማውጣት” ብቻ እንደፈለጋቸው ስናስታውስ ደራሲው በጅምላ ለምን እንደሳላቸው መረዳት እንችላለን።

4. በቀለ “ሽክታ”

በቀለ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ከአበራ የመስሪያ ቤት ባልደረቦች አንዱ እና አይረሴው ነው። ተራኪው ይህን ገጸባሕሪ በሚከተለው መልክ ይገልጸዋል (ገጽ 70-73፣ 97)፤

‘ረጅም ቀጭን ቁመናውን እንደ ሽመል እያውዘገዘገ’፥ ‘የተቀባው ሽቶ ክፍሉን ሁሉ አውዶ’፥ ‘የሚናገረው በጥድፊያ’

‘ሲናገር እንደሴት ይቅለሰለሳል’፥ ‘ሲሄድም ይውዘገዘጋል’፥ ‘ልብሱ ዳለቻ ሆኖ ከሀር ጨርቅ የተሰራ’

‘ቀይ ክራቫት አስሮ’፥ ‘የፈነዳ ጽጌረዳ ቅርጽ ያለው … መሀረብ የደረት ኪሱ ላይ ሰክቶ’

‘ረዥም ዞማ ጠጉሩ በቅባት ወደኋላ ተለጥጦ’፥ ‘ዘወትር ሙሽራ’፥ ‘ሴታ ሴት መልኩ ላይ የሚወራጭ ስሜት’

‘ረጃጅም አርጩሜ መሳይ ጣቶች’፥ ‘ጀብዱ ለማውራት … ልብሱን ለማሳየት ከቢሮ ቢሮ መዞር ግዴታው’

‘እዩኝ የሚል’፥ ‘በመስኮቱ መስተዋት የክራቫት አስተሳሰሩንና የጠጉሩን አበጣጠር እያየ ሲመጻደቅ’

በአንደበቱ ንግግርም በኩል የበቀለ “ሽክታነት” በአስተሳሰቡም መሆኑን በሚከተሉት ቃላት ይታየናል።

አላማረብኝም?

“ስላንዷ ሴት የሰባ ወሬ ነበረኝ።”

ታዲያ የበቀለ “ሽክታነት” እና ጀብዱ ለወግ ያህል እንደመሆኑ፣ ሌሎች ገጸባሕርያት ንግግሩን እና ጀብዱዎቹን ከምር የወሰዱት አይመስልም። (እንዲያውም በሕይወቱ ሴት ነክቶ የማያውቅ ቢሆን አያስደንቅም!)

5. ሚኒስትሩ

በስማቸው የማይጠቀሱት “ሚኒስትሩ” በልብወለዱ ውስጥ የአበራ የበላይ በላይ አለቃ እንዲሁም የታላቅ ወንድሙ የ’ጋሽ’ አባተ ወዳጅ ናቸው። ገጸባሕሪውን ተራኪው በሚከተለው መልክ ይገልጻቸዋል (ገጽ 79-80)፤

‘የቢሯቸው ስፋትና የጠረጴዛው ግዙፍነት … የማነስ ስሜት ያሳድራል’፥ ‘ግርማ ሞገስ ሳይወዱ በግድ ያስደገድጋል’፥

‘ወፍራም ድምጽ’፥ ‘ጥያቄአቸውን ከትእዛዝ ለይቶ ለማወቅ ያዳግታል’፥ ‘ቀና ብለው ሰው አለማየት ልማድ’

‘ሰው የሚያስበውን አስቀድመው የማወቅ ችሎታ ያላቸው የሚመስላቸው’

‘ቁጭ በል ማለት አያውቁም’፥ ‘ዝም ካሉ ማሰናበታቸው’

ይህን ገለጻ ስናነብ አንዳንዶቻችን ሳንወድ በደመነፍስ የምንሽቆጠቆጥላቸውን ሰዎች ሊያስታውሰን ይችል ይሆናል – ጠንካራ ምስል-ሳይ ገለጻ ነውና። በዚህም ሳያበቃ ደራሲው በገጸባሕሪው አንደበት በርካታ የቃላት ምሕዋሮችን (“ለመሆኑ”፣ “ለማንኛውም”፣ “ልጅ/ልጅነት”፣ “ብቻ”፣ “ችሎታ”፣ “አልሰማህም?”) በምናባችን ያሽከረክራል። እስቲ ሦስቱን እንመልከት፤

ለመሆኑ

ለመሆኑ ስንት አመትህ ነው?”

ለመሆኑ ሚስት አግብተሀል?”

ብቻ

ብቻ ያስጠራሁህ ለዚህ አልነበረም።”

ብቻ አንድ ቦታ ረግተህ ለመስራት አትችልም።”

ብቻ እናንተ ወጣቶች ሁሉንም ባንዴ ለማድረግ ትጣደፋላችሁ።”

አልሰማህም?

“የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ሲባል አልሰማህም?

“ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል የሚለውን ምሳሌስ አልሰማህም?

እኒህ ተደጋጋሚ ቃላት ከተራኪው ምናባዊ ገለጻ ጋር አንድ ከራሳቸው ጋር የሚነጋገሩ “ምክር አከፋፋይ” ባለስልጣንን ምስል ይፈጥራሉ።

.

ማሳረጊያ

ደራሲው ከላይ በመጠኑ በተዳሰሱት አምስት ገጸባሕርያት አማካኝነት፤ ነጥሮ የወጣ ግለሰባዊነትን (“ሱዛን”)፣ ቡድናዊ ባህሪን (“ሴተኛ አዳሪዎች” እና “ሚኒስትሩ”)፣ አዝናኝነትን (“በቀለ ሽክታ”)፣ እንዲሁም የብዥታን ምስል (“ትርንጐ”) በሚገርም መልኩ በምናባችን በቀላሉ ለመሳል ችሏል።

በአሉ ግርማ “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ እኒህን እና የተቀሩትን 50 ገጸባሕርያት ሲስል እጅጉን ተጠቦበት እንደነበር ለማስተዋል አያዳግትም። ይህም ልብወለድ ዘመን-ተሻጋሪ ተወዳጅነትን ለማግኘት ካስቻሉት ምክንያቶች አንዱ የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቱ ሳይሆን አይቀርም። ለበአሉ የመጀመሪያው ልብወለድ መጽሐፉ መሆኑን ስናስታውስ ደግሞ የድርሰት ጥበቡን ብስለት ያሳየናል።

ታዲያ ድርሰቱ ውስጥ የሚገኙትን የገጸባሕርያት አሳሳል ስልቶች ሙሉ በሙሉ ገና አልተገነዘብንም። የበአሉ ግርማን ጥበብ በሚገባ ለመረዳት “ከአድማስ ባሻገር” ውስጥ ያሉትን ዋና፣ ጭፍራ እና ስውር ገጸባሕርያትንም በቅርበት ማጥናት ያስፈልጋል። በዚሁ ድርሰትም ያየነውን የገጸባሕሪ አሳሳል ስልት በሌሎቹ አምስት ልብወለዶች (“የህሊና ደወል”፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ”፣ “ደራሲው”፣ “ሀዲስ” እና “ኦሮማይ”) ዳብሮ ወይ ቀንጭሮ እንደሄደ ማየት ይኖርብናል። ይህንንም ለመረዳት እያንዳንዱን ልብወለድ በተናጠል፣ ከዚያም ስድስቱን የፈጠራ ድርሰቶች በንፅፅር ማጥናት ሳይጠቅመን አይቀርም።

ምናልባት ያኔ፣ የበአሉ ግርማን የገጸባሕርያት አሳሳል ጥበብ በሚገባ ተረድተናል ለማለት እንችል ይሆናል።

.

ብሩክ አብዱ

ሐምሌ 2009

.

አባሪ

(የ“ከአድማስ ባሻገር” አዳማቂ ገጸባሕርያት ንግግርና ቃላት)

.

ሱዛን

“ብልጫ ያለውን ነገር የሚመርጡ ወንዶች ደስ ይሉኛል። ምክንያቱም ለውድና ለከፍተኛ ነገሮች የሚጣጣሩ ወንዶች ሲያጋጥሙኝ እኔ ስለራሴ ያለኝ አስተያየት ውሃ እንዳገኘ ጽጌረዳ ይለመልማል።” (ገጽ 8)

ሙዚቃ ስጠኝና ፍቅር ልስጥህ።”

ሙዚቃ ስጠኝ ነው የምልህ።”

“እውር ነህ ለማየት አትችልም።” (ገጽ 9)

“ያለሙዚቃ አይሆንልኝም ፍጹም አይሆንልኝም። ፍቅሬን ለወንድ አሳልፌ ከመስጠቴ በፊት ነፍሴ ወደ ሙዚቃ አለም መግባት አለባት። ከዚያ በኋላ ነጻነት ይሰማኛል። ውስጤ እንደ ጽጌረዳ እምቡጥ ይከፈታል። ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዝግጁ እሆናለሁ።” (10)

“አበራ ለምን እንዲህ ትላለህ? ለቀለም ደንታ እንደሌለኝ እዚህ መምጣቴ ሊያረጋግጥልህ አይችልም?” (ገጽ 10)

“መልካም ፋሲካ ስኳር ወለላዬ። የትም ብሆን አብረን የሰማናቸው ጥኡም ሙዚቃዎች ትዝ ይሉኛል። የማዝነው አንተ ለጋብቻ ፍጹም ደንታ ስለሌለህና ብዙ ሙዚቃዎችን አብረን ሳናዳምጥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በመለያየታችን ነው። ሆኖም ቅሬታ የለኝም። እያንዳንዷ ደቂቃ ትዝ ትለኛለች።” (ገጽ 10)

“ወንዶችን ማሞላቀቅ ደስ ይለኛል። እንዳንተ ያሉ የእግር ጥፍራቸውን መቁረጥና የብብት ጠጉራቸውን መላጨት የማይችሉ ሳገኝ ደግሞ የበለጠ ደስታ ይሰማኛል።” (ገጽ 12)

ትርንጐ

እንጫወት።”

ምን ቸገረህ እኔ አሳይሀለሁ።” (ገጽ 13)

የጣልያን ገረድ

“ብስብስ የወንድ ።” (ገጽ 16)

የበግ ነጋዴ

“ሀምሣ ብር።”

“ስድሳ ብር።” (ገጽ 25)

“ጮማነታቸው ላይ።”

“ከስድስት ባውንድ አይቀንስም።”

“ፋሲካ።”

“ታዲያ በግ ተራ ለምን መጡ?” (ገጽ 26)

ሴተኛ አዳሪዎች

አንቱ ዛሬ ደግሞ ዉስኪ ይዘው መዞር ጀመሩ እንዴ?” (ገጽ 45)

“ጋሼ አንቱ ምን እንጋበዝ ታዲያ?” (ገጽ 46)

“ምን የሚያስቅ ነገር አገኙብኝ አንቱ። ሄደው መሳቂያዎን ይፈልጉ።”

“ታዲያ በማን ነው?”

ኡኡቴ እርስዎ ከማን በለጡና!” (ገጽ 88)

እንጀራ አባት

“አንተ ወስላታ ተነስተህ በሩን አትከፍትም?” (ገጽ 51)

ባልቻ

“ማን ነው የቀደመኝ? ስሮጥ የመጣሁት ለተሰማ ክብሪት ልሰጥ ነበር።” (ገጽ 69)

“አበራ ምን ነው ዛሬ የከፋህ ትመስላለህ? ሀዘኑንና ብስጭቱን ለኔ ተውና ይልቅ ቡና በለን። ተሰማ እንደሆን ዛሬ እማማ የኪስ ገንዘብ አልሰጡትም መሰለኝ። (ገጽ 70)

“አርፌ ሲጃራ እንዳልቃርምበት ነው ይህ ሁሉ። ደሞዝ ጭማሪ መጥታለች መሰለኝ።” (ገጽ 72)

“ለመሆኑ ሰርግሽን መቼ ነው የምንበላው?” (ገጽ 76)

“እንዲያው ስለእግዚአብሔር ብላችሁ ሰላሳ ብር አበድሩኝ።” (ገጽ 98)

በቀለ “ሽክታ”

“ይህንን ልብስ በስንት ገዛሁት? እስቲ ገምቱ። አላማረብኝም?” (ገጽ 70)

“ፋሲካን ያሳለፍኩት ከአንዲት አገር አሸነፈች ከየምትባል ኮረዳ ጋር ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል እያለቀሰች ስቃዪዋ ደስታ ላይሆነኝ። (ገጽ 71)

“አበሳ ነው እንጅ። ስለአንዷ ሴት የሰባ ወሬ ነበረኝ። ለሹመት ታጭተሀል እንዴ?” (ገጽ 73)

“ሉሊት ታደሰ ማን ናት?” (ገጽ 97)

“እንደኔ ያለው ወንድ ባያጋጥማት ነው። ግን ማን ነው ያልከው? አዎን ገድሉ የአበራ ጓደኛ ከሆነ አንተን ከመላክ እሱ ራሱ ለምን አይነግረውም?” (ገጽ 98)

ተላላኪ

“ሚኒስትሩ በአስቸኳይ ይፈልጉሀል።” (ገጽ 78)

ሚኒስትሩ

“ያንን ጥናት ምን አደረስከው?” (ገጽ 79)

“የእምቧይ ካብ ይሆናል ለማለት ነው? ችግሩ ሳይገባህ አይቀርም። ብቻ ያስጠራሁህ ለዚህ አልነበረም። የአባተ ወንድም አይደለህም? አዎን ትመሳሰላላችሁ። ጥሩ ችሎታ እንዳለህ ሰምቻለሁ። እኔም ራሴ ደርሼበታለሁ። ብቻ አንድ ቦታ ረግተህ ለመስራት አትችልም። ስህተት ነው። የረጋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ሲባል አልሰማህም? ብቻ እናንተ ወጣቶች ሁሉንም ባንዴ ለማድረግ ትጣደፋላችሁ። ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል የሚለውን ምሳሌስ አልሰማህም? ብቻ ለማንኛውም ነገር ብዙ ታስቦልሀል። ልጅ እንደሆኑ ዘለአለም አይኖርም። ረጋ ብለህ ስራ። ለመሆኑ ስንት አመትህ ነው?” (ገጽ 79)

“በጣም ልጅ ትመስላለህ። ግን አርጅተሀል። ለመሆኑ ሚስት አግብተሀል?” (ገጽ 79)

“ታዲያ ምን ትጠብቃለህ? ሁሉም በልጅነት ሲሆን ያምራል። ለእድገትም ሆነ ለማንኛውም ነገር የቤተሰብ ሀላፊነት ጥሩ ዋስትና አለው። አባትህ ስመ ጥር ጀግና ነበሩ። ታዲያ አስብበት እንጂ። ችሎታ ብቻውን መቼ ይበቃልና።” (ገጽ 80)

 

4 thoughts on “የበአሉ ግርማ ገጸባሕርያት

  1. ሰላም ለእናንተ ይሁን አንድምታዎች!… እነበብኩት፤ “የበአሉ ገጸባሕርያት” የሚለውን። እናማ መጣጥፉ ገጸ ባሕሪያቱን ግልጥ ግልጥ-ልጥ አድርጎ ገልጦ ሸጋ ሆኖ ሳለ አጻጻፉ እንዳይሆን እንዳይሆን ሆነ።… ማለቴ…አንዳንድ ቃላት እና ሆህያትን እንደ ወጋቸው፥ እንደ እናቱ ተደርገው አልተጻፉም።
    እንዲያው ለእሰጥ አገባ እንዲሆን፦
    ፩ኛ) በአሉ ወይስ በዓሉ?…
    በአሉ የሚለው ቃል የበዓሉ ስመ ተጸውዖ አይደለም፤ አይሆንምም።…. ለምን ቢሉ?… በአ ማለት ባ ማለት ነው። ሉ ሲጨመርበት “ባሉ” ይሆናል ማለት ነው። ባሉ ማለት ደግሞ አበዋራው ይሆናል። እና የደራሲው ስም አበዋራው ግርማ መሆኑ ነው!… ስለዚህ በዓሉ ነው መሆን ያለበት። ምክንያቱ “በዓሉ” የሚለው በዓል ከሚለው ቃል የወጣ ስለሆነ።… በተጨማሪም፥ “ባሉ” የሚለው እንደ በግ ጮኹ ማለትም ይሆናል።
    ፪ኛ)
    አራተኛው አንቀጽ ላይ፦ “ስለዚህ ከመጀመሪያው ልብወለዱ ኅትመት በፊት በአሉ ቢያንስ ለአስር አመታት ያህል ኪነጥበባዊ ጽሑፎችን ሲያነብ፣ ሲጽፍና ሲያዘጋጅ የከረመ ደራሲ ነበር፥” የሚል ዓረፍተ ነገር ይነበባል።… በዚህ ዓረፍተ ነገር ውስጥ “ልብወለዱ፥… ኅትመት፥… በአሉ፥… ለአስር አመታት፥… ኪነጥበባዊ፥” የሚሉት ቃላት ተፋሰስ አልጠበቁም፤ ሆሄ(ህ)ያቸው ከላይ እንደ ጻፍኩት እንደ እናታቸው አልተጻፉም።
    ፫ኛ) አመት ወይስ ዓመት?
    አንቀጽ ሁለት ላይ፥ “ከፈጠራ ድርሰት ባሻገርም በጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅነት (“News and Views”፣ “Addis Reporter”፣ “መነን” እና “አዲስ ዘመን”) የበርካታ አመታት ልምድ ነበረው። በኒህም አመታት በተቻለው መጠን የአዘጋጅነቱን ሚና በመጠቀም (በተለይ በ”መነን” እና “አዲስ ዘመን”) በርካታ ኪነጥበባዊ አምዶችን (ለምሳሌ “አጭር ልብወለድ”፣ “ከኪነጥበባት አካባቢ”) አስጀምሮ ነበር፥” የሚል ተጽፏል።
    ይህ አባባል እንደ ሆሄያቱ ትርጉም ከተተረጎመ ፥ “ከፈጠራ ድርሰት ባሻገርም በጋዜጣና መጽሔት አዘጋጅነት (“News and Views”፣ “Addis Reporter”፣ “መነን” እና “አዲስ ዘመን”) የበርካታ አገልጋዮች ወይም ገረዶች ልምድ ነበረው። በኒህም አገልጋዮች ወይም ገረዶች በተቻለው መጠን የአዘጋጅነቱን ሚና በመጠቀም (በተለይ በ “መነን” እና “አዲስ ዘመን”) በርካታ ኪነጥበባዊ አምዶችን (ለምሳሌ “አጭር ልብወለድ”፣ “ከኪነጥበባት አካባቢ”) አስጀምሮ ነበር፥” የሚል ትርጉም ነው የሚሰጠው።

    ፬ኛ) ልብወለድ ሌላ ቦታ ላይ ልቦለድ ተብሎ ተጽፏል። ለመጣጥፉ አንዱን ብቻ ቢወሰድ ተፋሰስ ይጠብቃል።
    ኅትመት በኃያሉ ኀ እና በሆይ (በሀሌታው ሀ) አይጻፍም፤ በሐመሩ ሐ እንጅ።
    “ለአስር አመታት” የሚለው ሐረግ እንደታሰበው ትርጉም አይሰጥም። “ለገረድ አስር (በእግር ብረት ወይም በጋንዣ) ያህል…” የሚል ትርጉም ይሰጣል፤ እንዳጻጻፉ።
    ፭ኛ) ገጸባሕሪ፦ በመጀመሪያ ነገር አንድ ቃል አይደለም።… ገጸ-ባሕሪ ወይም ገጸ ባሕሪ ተብሎ ሊጻፍ ይገባል።…
    ገጸባሕርይ፥ ገጸባሕርያት የሚልም ተደጋግሞ የተጻፈ አለ። ገጸ ባሕሪ ሲረባ ገጸ ባሕሪያት መሆን ይችላል። ግን ገጸ ባሕርያት አይሆንም። ይሁንና ገጸ ባሕሪ ተብሎ ከተጻፈ ገጸ ባሕሪያት ተብሎ ቢረባ የእርባታ ሕግ አይጥስም። ይጠብቃል።

    ፭ኛ) ሀይል ወይስ ኃይል?… እንዲህ ከሆነ፥… “ኻይል፥ ሃይል፥ ሐይል፥ ሓይል፥” ብለን የሆሄያቱን ግርማ ሞገስ ገፍፈን፥ ክብር አልነፈግናቸውምን?!
    ፮ኛ) “ኪነጥበባዊ” የሚለውም አንድ ቃል አይደለም፤ ሁለት እንጂ። ኪነ-ጥበባዊ ወይም ኪነ ጥበባዊ ተብሎ ቢጻፍ አማረኛ ቋንቋ ለዛው ሳይጠፋ ማዕረጉን እንደ ጠበቀ ይኖራል።
    በመጨረሻም፥
    “…ፍቅሬን ለወንድ አሳልፌ ከመስጠቴ በፊት ነፍሴ ወደ ሙዚቃ አለም መግባት አለባት፥” የሚል ዓረፍተ ነገር አለ። በዚህ ዓረፍተ ነገር ላይ “አለም” የሚለው ቃል ካለ ትርጉሙን አባክኖታል። መሆን የሚገባው “ዓለም” ነው። ይሁንና አለም ማለት ተናገረም ወይም በሕይወት ኖረ ወይም በእጃችንም ይገኛል ማለት ይሆናል።
    ብተረፈ አቀራረቡን በጣም ወድጀዋለሁ። እሶ!… ቀጥሉ!… እኔም አነባለሁ!…
    ቅኔዬን መልሱ እንዳታሳንሱ! ቸር ይግጠመን።

    Like

    1. አስተያየትዎን ካነበብኩ በኋላ፤ ልበ-ወልድ ለመጻፈ የነበረኝን ድፍረት ቆም ብዬ እንዳስብ ርድተውኛል። ለመሆኑ አማሪኛን በዚህ መንገድ ለመረዳትና ለማወቅ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ምክርዎን ቢለግሱኝ፤ እጅግ እወዳለው። ክብረት ይስጥልኝ።

      Like

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s