“አለቃና የምኒልክ እናት” (ወግ)

“ትዝታ ዘአለቃ ለማ”

መንግስቱ ለማ እንደጻፈው

.

(ቅንጫቢ)

.

*** አለቃ ለማ የታላቁ ባለቅኔ የመንግስቱ ለማ አባት ናቸው። በቤተክህነት እጅግ ብዙ የተማሩ ሊቅ ነበሩ። የሕይወት ታሪካቸውን በአንደበታቸው በሚያወጉን “ትዝታ ዘአለቃ ለማ” ከሚባለው መጽሐፋቸው የተቀነጨበ ወግ። ***

ዕንግዲት ፤ ያባቴ እናት – እንደርሷ ያለ፣ ወንድ እንኳ የለም እንኳን ሴት። ብርታቷ፣ ምክር ስታውቅ! ንብረት የተሰናከለበት እንደሆነ ‘ወይዘሮ ዕንግዲት ይምከሩህ፣ ከሳቸው ምክር ተቀበል’ ይባል ነበር። የተናገረችው ነገር ይሆንላታል። ባል አግቢ ሲሏት ጊዜ፣ እምቢ አለች፣ ቁርባኔን አላፈርስም አለች። ሟቹ የልጃገረድ ባሏ ናቸውና፤ ባል አላገባም አለች። በብዙ ወገን ያም ይመጣል፣  ያም ይመጣል፣ አይሆንም ትላለች።

ውሽን ገብረ ሚካኤል ልጅ የላቸውምና ትወልድልኝ መስሏቸው አገባለሁ እቆርባለሁ አሉ። ማይም ናቸው፤ ያርሳሉ ባለጠጋ ናቸው።

ያባቴ እናት ልታገባ ስትል ያባት ዘመዶች ‘እኛ ልጃችን የንጀራ አባት አያይምና እንወስዳለን! ልጃችን በንጀራ አባት አያድግም’ አሉና መጡ ሊወስዱ።

‘እኔ ከልዤ አልለይም!’ – እናቲቱ – ‘እኔ ልዤን አልሰጥም ባል አላገባም ይቅርብኝ!’

ኋላ እኒያ አቡነ አሮኖች፣ ካህናቱም መምሩም ሽማግሌው ሁሉ ‘ምነው እንዲህ ታረጋላችሁ? እንዴት በልጅነት ባል ሳታገባ እንዲህ ሁና ትቀር?’ አለና ሽማግሌ ተቈጣቸው።

ልጁን ይዤ እሄዳለሁ ብለዋል ትኩ ፈንታ (የሟቹ ባል ዘመድ) የንጀራ አባት አያሳድገውም ብለው ነው።

ከብት ቀረበ (የሟቹ ባል ንብረት)፤ ሃያ አራት ሆኑ ከብቶቹ። አስራ ሁለት ያባት አሥራ ሁለት የናት ሆነ። ዕጣ ወደቀ ተከፍሎ። የሷማ እሷው አለች፤ ያባቱ ፈንታ ለልጁ ነው።

ተቈጠረና፤ ያ ባል የተባለው ቀረበ የሚያገባት።

“ይኸ ከብት ይኸው፣ የላሟ ወተት የበሬው ጉልበት ለልጁ ደመወዙ ነውና፤ ዝንጀሮ እንዳይጠብቅ ከብት እንዳይጠብቅ እንዲማር ብቻ። ከተማሪ ቤት በቀር ከምንም ከምንም ከትእዛዝ እንዳይገባ” ተብሎ ለልጁ ተሰጠ። ተነጋግሩ በዚህ አለቀ።

እኒያ ትኩ ፈንታ ሚስታቸው ለምለም ገብረሥላሴ ትባል ነበር። ‘ልጁን ይዤ እመጣለሁ ብያት ነበረ ለምለምን። ባዶ እጄን ስሄድ ትሰቀቃለች’ አሉና ከዚይ ከቀረበው ከብት አንዷን ጥጃ ያዙና – ያን ጊዜ ያገራችን ድግ ይኸ መቀነቱ አርባ አርባ ክንድ ነበረ የሚታጠቁት – ድጉን ፈቱና ኻንገቷ ታሠረ፤ አሽከር ያዘ፤ በዚያ ተጐትታ እንደ ፍየል ይዘው ሄዱ።

ዕንግዲት በብዙ ብዙ ጭቅጭቅ ውሽን ገብረሚካኤልን አገባች። ማኅፀኗ አርሮ ቀርቷል በዚያ በባሏ ኅዘን፤ ምንም ሳትወልድ ቀረች።

ውሽን ገብረ ሚካኤል ያጤ ምኒልክ አጎት መሆናቸው ነው በናታቸው – የናታቸው ወንድም ናቸው። ያጤ ምኒልክ እናት የኛ አገር ሴት አይደሉም ባባታቸው? አድያሞ ለማ፣ እሱ አይደለም ያጤ ምኒልክን እናትን የወለደ? አባትየው የላስታ ተወላጅ የመቄት ተወላጅ ናቸው። በጌምድር ወርደው – ደብረታቦር አጠገብ ነው፤ አሞራ ገደል ይባላል – የዚያን ባላባት ልጅ አግብተው አድያሞ ለማን ወለዱ።

እንግዴህ ያን ጊዜ አገራችንን የሚገዙ ወረሴኾች ይባላሉ – የጆች ይገዛሉ። ይኸ አድያሞ ለማ ከየጆች ሰው ገደለ፤ ባምባጓሮ ተጣላና አንዱን ወረሴኽ ገደለ። የጆች አገረ ገዦች ናቸውና ያን ጊዜ ባገር ለመኖር የማይቻለው ሆነ። በዚያ አመለጠና፤ ተሰደደና፣ ሸዋ መጣ። እዚህ ሎሌነት ገባ ለሣህለሥላሴ አያት።

ሲኖር ያ አድያሞ ለማ ከመንዝ ሴት ወልዷት ያጤ ምኒልክን እናት፤ ‘በደሙ ታርቀናልና ና’ አሉት ተነስቶ ሄደ። ‘መጥቼ ልጄን እወስዳለሁ’ ብሎ ሄደ፣ ኸዚያ ወዲያው እንዳለ ቀረ ቀረ። እንግዲህ የምኒልክ እናት ባባቷ መቄት ናት።

መጣችና ኻለቃ ምላት ቤት ግርድና ገባች። ያንኮበር ሚካኤል አለቃ ናቸው፤ አለቃ ምላት በዚህ አገር ክቡር ናቸው እንደ ጳጳስ። ልጅ እግር ናት፣ ማለዳ ግብር ውሀ ወጥተዋል ከጓደኞቿ ጋራ

“ዛሬ እንዲያው ሲጫዎትብኝ አደረ ቅዠት።”

“ምንድነው?”

“ኧረ እንዲያው ምኑን አውቀዋለሁ? – ከብልቴ ጠሐይ ወጣች” አለች

እነዚያ ልጃገዶች ሣቅ! ሃይ! ሃይ! ሣቅ!። እየተሳሳቁ እቤት ገቡ። ጠሐይ ከብልቴ ወጣች አለች ሲሉ ያ የቤቱ ምስለኔ ሰማ። ኻለቃ ምላት ዘንድ ገባ፤

“ኧረ ጌታዬ ይች ዕንግዳ ገረዳችን ጉድ አመጣች!”

“ምን አረገች – ምን አረገች”

“ጠሐይ በብልቴ ወጣች አለች። አሁን አሽከሮቻችን ሁሉ ይሳሳቃሉ” ብሏቸዋል።

“እህ! ታዲያ ይች ከኛ ዘንድ ምን አላት? ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት” አሉ።

አንኮበር ቤተ መንግስቱ ኸላይ ነው፤ ጉባ ነው ቤተ መንግስት ያለበት። (አንኮ ኦሮሞይቱ ባላባት ናት፤ የሷ ከተማ ናት አንኮበር። እሷን ወግተው አስለቅቀው የሣህለ ሥላሴ አያታቸው ገቡ።)

ተመለሰ ሄደና

“ኧረ ጌታ እኮ መልካም ተረጎሙላት”

“ምናሉ?”

“ኸላይኛው ቤት ውጪ በሏት፤ ከኛ ምናላት? ብለው አሉ”።

ጓደኞቿ ሁሉ ሰምተዋል ተሳሳቁ።

ውሀ እሚቀዱት ከቤተ መንግሥቱ ጋር ካንድ ነው እታች ከሚካኤል ግርጌ ነው። ይችም ዕንግዳዋ ወንዝ ወረደች አንድ ቀን። እነዚያ የቤተ መንግሥቱ ሥራ ቤቶች የማያውቋት ናቸውና

“ይችም የናንተ ናት?”

“አዎ”

“የየት አገር ናት?”

“ኧረ ይቺማ ጉድ ያላት ናት! ከብልቴ ጠሐይ ወጣች ብላ እልም አይታ፣ ጌታ ቢሰሙ ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው አሏት ተባለ ትርጓሜው”።

አለቃ ምላትን መላው ሸዋ ይጠብቃቸዋል አነጋገራቸውን። እኒያ ሥራ ቤቶች ሰሙና ወጡ፤

‘ኧረ አለቃ ምላት ቤት አንዲት ገረድ ገብታለች! … እንዲህ እንዲህ ብላ አለመች አሉ…ኸላይኛው ቤት ውጪ ብለው ተረጎሙ አሉ’ ብለው ማውራት። የሣህለ ሥላሴ ባለቤት የነኃይለ መለኮት የነሰይፉ እናት ሰምተው፤

“ጥሩልኝ ያችን ልጅ” ተጠራች። መጣች።

“አገርሽ የት ነው?”

“መንዝ”

“ኸኔ ጋር አትቀመጭም ልጄ?”

“ምን ከፋኝ”

“ተቀመጭ። በሉ ጥጥ አምጡላት – የጅ ስራ ታግባ”

ዛዲያ የሸዋ ሴት ለእጅ ሥራ የጥጥ ነገር እንዲያ ነው፤ ደስ አሰኝቷቸዋል። ምንጣፉን ልብሱን እሳቸው ካሉበት ተኝ ብለው ሰጧት።

ኸልጆቻቸው ሰይፉን ነው የሚወዱ ሴቲቱ። ያ ጠሐይ ከሰይፉ እንዲወለድላቸው፤ ‘እንዲህ ያለች ልጅ ይዤልሃለሁ – እንዲህ ያለች እንዲህ ያለች’ ብለውታል ለሰይፉ።

ሰነበተች። አንድ ቀን ‘ማታ እልክለሃለሁ’ ብለውታል። እንግዴህ ከሣህለ ሥላሴ ቤት ግብር ይበላሉ ልጆቹ ኻባታቸው ቤት። በልተው ጠጥተው፤ ሽንጥም ታናሽም ቢሆን ደሞ ይጨመርና ጠጁ ይሆንና መሶቡ ወጡ መጥቶ – የልጆች ቤት አለ – በላይ ኃይለ መለኮት ይቀመጣል፤ ቀጥሎ ሰይፉ ነው፤ በወዲያ በኩል ዳርጌ፣ ደሞ ኃይሉ ነበሩ የይፋት – እነዚያ ይቀመጣሉ። ባለሟሎች ይቀመጣሉ። የቀረው ይቆማል። እንደገና ግብር ይገባል፤ ቅልጥ ይላል።

እናቱ ያቺን ሴት ለሰይፉ ወሰዱና ሰጡ – ሄዳችሁ ኸሰይፉ ምኝታ አስቀምጧት አሉና፤ ላኩለትና፤ መጥታ ተቀምጣለች። ሰማ። ሰይፉ የሚወዳት ሌላ ሴት አለችው።

“ወንድሜ የምትመጣ ሴት አለችብኝ?” አለ ኃይለ መለኮትን።

“የለችብኝም።”

“እሜቴ አንዲት ሴት መርተውብኛል። የኔ እገሊት ትመጣለች፤ አሁን ተመልሳ ሁለተኛ አላገኛት፤ እባክህ አንተ ውሰድልኝ።”

“እኔ ምን ቸገረኝ!” ኃይለመለኮት።

ወጣችና ልጅቱ ከኃይለመለኮት ምኝታ ገባች። በበነጋውም መጣች፣ ኸዚያው። በበነጋውም መጣች፣ ኸዚያው። ምኒልክ ተጸነሰ።

ከሰይፉ ጸነሰችልኝ ብለው ደስ ብሏቸው ሳለ እናትዮዋ፤

“ከኃይለ መለኮት እኮ ነው የጸነሰችው!” አሏቸው ሥራ ቤቶቹ።

“እንደምን?!”

“ሰይፉ አይሆንም ብሎ”

“ጥሯት” አሉ።

“አንቺ ከማን ነው ያረገዝሽው? ምነው እኔ የሰደድኩሽ ከሰይፉ አይደለም ወይ?”

“እሱማ ሌላ አለችብኝ ብሎ ለኃይለ መለኮት ሰጠኝ።”

በእግር ብረት! ታሠረች።

ኋላ እኛ አማችየው የሣህለ ሥላሴን ሴት ልጅ ያገቡ ሰሙ።

“ምነው እመቤቴ! ምነው በሴት ልጅ እንዴት ይጫወታሉ!”

“እ! ወንድማማቾቹን ልታጋድል – ከኃይለ መለኮት አረገዝኩ ትላለች!”

“ታዲያ እነሱ ይተዋወቃሉ … ሰይፉ አይሆንም ሲል ጊዜ  ምንታርግ .. ” አሉ፣ አስለቀቁ።

ሣህለ ሥላሴ ሰሙ፤ መጸነሷን ሰሙ። ምኒልክ ተወለደ። ስትወልድ ጊዜ፤ ጐረቤላ (ኻንኮበር ማዶ ጉባው ነው) ቦታ አደረጉና ድርጎ አመላላሽ አርገው፣ ጠባቂ ሁሉን አደረጉ፤ እዚያ አስቀመጡ። ሰንብተው ‘አምጡ አሳዩኝ’ አሉ። መጣ ያ ልጅ።

አዩ “ምን ይልህ” ያሉ ሣህለ ሥላሴ ናቸው። “እንግዲህ አንተን ሸዋ ምን ይልህ? ሸዋ ምን ይልህ!” አሉ። ‘ምኒልክ’ ያለ ተማሪ ነው – ለቅኔ – በድሮው ምኒልክ። እሳቸው ያሉ ‘ምን ይልህ’ ነው።

ምኒልክ ያስራ ሁለት ዓመት ልጅ ናቸው እጃቸውን ሲሰጡ ለቴዎድሮስ። ቴዎድሮስ

“አባትህ ምናለህ? ምናለህ እንዲያው ምን ነገረህ?” ቢሏቸው፤

“ምንም የነገረኝ የለ፤ ይችን” – ካንገታቸው ክታብ – “ይችን ሰው አይይብህ ብለውኛል እንጂ።”

አለቃ ለማ

1959 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ። ፲፱፻፶፱። ገጽ ፭-፲፪።

One thought on ““አለቃና የምኒልክ እናት” (ወግ)

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s