“የብዕር አሟሟት ሌላ”
ከጸጋዬ ገብረ መድኅን
.
(1959 ዓ.ም)
.
[በደራሲው ቤተሰብ ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]
.
.
.
የቃለ – ልሣን ቅመሙ
የባለቅኔ ቀለሙ
ነጠበ እንጂ ፈሰሰ አንበል፣ ቢዘነበል እንኳ ደሙ
ሰከነ እንጂ ከሰለ አንበል፣ ቢከሰከስ እንኳን ዐፅሙ፤
የቃል እሳት ነበልባሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር – ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።
እስካልተዳፈነ ፍሙ
እስካልተሰበረ ቅስሙ
እስካልተቀበረ ስሙ
የደራሲ ዐፅመ – ወዙ
የብዕር ቀስተ – መቅረዙ
ሕዋሳቱ እስካልቀዘዙ፤
አልፏልና ከሥጋ – ሞት
በቃሉ ሚጠት ስልባቦት
በፊደሉ አድማሰ – ፍኖት
በኅብረ ቀለሙ ማኅቶት
በሥነ – ግጥሙ ምትሃት
በግሱ ንጥረ – ልሳናት
በነባቢቱ ነፍስ እሳት፤
ይነዝራልና ደም – ሥሩ፣ አይሞትምና ፀዳሉ
ቢሞት እንኳ ሞተ አትበሉ …
የብዕር አሟሟት ሌላ
ሲፈስ የብሌኑ ኬላ
የፊደል መቅረዝ አሟሟት
ከውስጥ ነው እንደ ጋን መብራት
በቁም ነው እንደ ቁም ፍትሐት
የሚያጨልም የነፍስ እሳት፤
እንጂ ብዕር ሞተ አትበሉ፣ እሳቱን ሳያስለመልም
ነበልባሉን ሳያከስም
ውጋጋኑን ሳያጨልም።
ቃለ – ምንጩን ካልመሰነ፣ ስለቱን ካልጐለደፈ
መቅረዙን ካልተዳፈነ፣ ከፊደሉ ካልነጠፈ
ዐፅመ – ወዙን ካልደረቀ፣ ጧፉን ቀልጦ ካልሰፈፈ
ጡጦ እንደጠፋበት አራስ፣ ቁም ተዝካሩን ካልለፈፈ
ብዕሩ ቀርቶ ምላሱ፣ በሃሜት ካልተንጠፈጠፈ፤
የቃለ – እሳት ነበልባሉ
የድምፀ ብርሃን ፀዳሉ
የኅብረ ቀለማት ኃይሉ
አልባከነምና ውሉ
የዘር – ንድፉ የፊደሉ
ቢሞት እንኳን ሞተ አትበሉ።
.
ጸጋዬ ገብረ መድኅን
.
“ለካሳ ተሰማ”።
1959 ዓ.ም – ቆቃ።
.
(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)
.
[ምንጭ] – “እሳት ወይ አበባ”። 1966 ዓ.ም። ገጽ 37-38።
.
እንዲሁም ክቡር ሎሬት ጸጋዬ …ሞተ አትበሉ ይኖራልና በኢትዮጵያውያን ልብ ለዘላለም በጹሁፎቹ፤ በግጥሞቹ፤ በድርሰቶቹ…
LikeLike
የማይተካ የብእር አባት
ማን እንደ እርሱ…..
ቃሉ ሐውልቱ ነው የታሪክ ክስተት
LikeLike
ብርካን/ብሩካት የአንድምታ አዘጋጆች አምላክ በመከናወን ይባርካችሁ። በዚህ እንኳን ለአማርኛ፥ ለግዕዝም ትንሣኤ ቢታሰብ እጅግ መልካም በሚኾንበት ወቅት ሥራችሁ ታሪክ የማረሳው አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስባለሁ። እሰይ፥ አመሰግናለሁ። መጋቢ መላኩ ትዕዛዙ።
LikeLike