“የጋሽ ጸጋዬ ግጥሞች ቅኝት”

“የጸጋዬ ገብረ መድኅን ግጥሞች”

ከነቢይ መኮንን

.

.

እውነት ለመናገር ስለ ስነግጥም ከመናገር መግጠም ይሻላል። በተለይ እንደ ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ያለውን የግጥም ነዶው ተከምሮ የማያልቅ ገጣሚን ሥራ መናገር “ሂማሊያን በሁለት ቆራጣ እግር-አሊያም አባይን በጭልፋ” እንደማለት ያለ ነገር ነው። ራሱ ጋሽ ጸጋዬ እንደሚለውም “አንድ ምእመን የሃይማኖቱን ድንጋጌ ከማተቱ ይልቅ፤ በቀጥታ እግዚአብሔርን በእምነት ማገልገሉ እንደሚበልጥበት ሁሉ፤ ባለቅኔም የሥነ-ግጥሞችን የአደራደር ሥርዓትና ድንጋጌ (Form) ከማተቱ ይልቅ ቅኔውን ተቀኝቶ፣ ደርሶ፣ ፍሬ-ሃሳቡን (Content) ማበርከቱ ይበልጥበታል።”

አንድ የአገራችን አጭር ልብ ወለድ ጸሐፊ የጻፈውን ውርስ መነሻ በማድረግ አንድ ምሳሌ በመስጠት የግጥምን ባህሪ ለማሳየት ልሞክር –

“አንድ አይነ-ሥውር፣ መንገድ መሪውን ባንዲራችን ምን ዓይነት ነው?” ብሎ ይጠይቀዋል። “አረንጓዴ ቢጫ ቀይ” ይለዋል መንገድ መሪው። ዓይነ ስውሩም “ቢጫ ምን ዓይነት ነው?” ሲል ደግሞ ይጠይቃል። መንገድ መሪውም ግራ ይገባውና አዘውትረው የሚሄዱበትን ጠጅ ቤት አስታውሶ “ቢጫ ቀለምማ ጠጅ የመሰለ ነው!” አለው። አይነ ስውሩ “አሃ!” ይላል በመደምደም።

ቀጥሎ ሌላ ጥያቄም ቀጥሏል። ለጉዳያችን እዚሁ ጋ ላቁመውና፣ እንዲያው የዓይነ ስውሩን ግንዛቤ ለማሰብ ብንሞክር – በጆሮው የሰማውን ጠጅ፣ በምላሱ በማጣጣም፣ የባንዲራው ቢጫ ምን መሳይ እንደሆነ በሚያውቀው ግንዛቤ ሊያስብ ነው የሞከረው ማለት ነው። ስለዚህም ባንዲራ ይጣፍጣል። ባንዲራ ያሰክራል። ከበዛ ደግሞ ያማል። ባንዲራ እንደተርጓሚው የግንዛቤ አቅም ይታያል። እንግዲህ ባንዲራ ይህን አይነት ግንዛቤ የመፍጠሩን ያህል፤ እንደሚታወቀው በውስጡ ግን ያለው ታሪክ፣ ዓላማ፣ ህብር … ብዙ የታጨቀ ነገር ነው።

ይሄው ባንዲራ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ወይ ጥሩነሽ ዲባባ በሩጫ ሲያሸንፉ በሰው አገር ላይ ከፍ ብሎ ስናየውና፤ የኢትዮጵያ መዝሙር ሲታከልበት፣ ልዩ ሳግና እንባ ጭምር እንዲፈጠርብን የሚያደርግ ግጥም ይሆናል። ባንዲራው ውስጥ የታመቀው ሃሳብ፣ የጨርቁና የሰንደቁ ምጣኔ፣ ቀለሙና የቀለሙ ህብር፣ ከዜማው ጋር ተዋህዶ ቢታሰብ፣ ግጥም ይባላል እንደማለት ነው። ስልተ-ምት ያለው፣ ውበት የተላበሰ፣ ቁጥብ፣ እምቅ፣ በተመረጡ ቃላት የተጻፈ፣ አይረሴና የጣፈጠ ግጥም!!

የጥበብ ሥራው ይዘት – ከቅርፅ የሰመረ ሆነ እምንለው ይሄንን ነው። ስለጋሽ ጸጋዬ የአጻጻፍ ዘይቤ ስንመለከት፣ ራሱ ጋሽ ጸጋዬ እንደሚለው፤

የወል ቤት፣ ቡሄ በሉ ቤት፣ ሰንጎ መገን ቤት የተለመዱት ሲሆኑ፣ እኔ በስምንት የስንኝ ስልት ድንጋጌ ላይ ነው የምደረድረው። ይህም በአደራደርና በሰረዝ ነጥብ ተከፍሎ ይታያል። አንዳንድ ምሁራን የዚህን ድንጋጌ ዘይቤ (ስታይል) ስም ስላላገኙለትና እኔም ስላልሰየምኩት ‘የጸጋዬ ቤት’ ይሉታል” ብሏል።

አስረጅ –

“… አበባው ምድሩን ሲንተራስ፣ ያፈር ፅዋ ረፍቱን ሲገድፍ

ቢራቢሮ ያንቺስ ሞገስ፣ ለምንድን ነው አብሮ እንደሚረግፍ?”

.

“የጸጋዬ ግጥምና የወል ግጥም ልማድ”

.

የጋሽ ጸጋዬን ግጥም በወል አነባበብ ዘዴ ልማድ የተካነ ሰው ሲያነበው ስሜት ሊያጣበት ይችላል። ትንፋሽ አወሳሰዱም ሊያቅተው ይችላል። ዜማው ሊሰበርበትም ይችላል። በዚህም ምክንያት ግጥሙ – ግጥም ግጥም አይልም። በአጠቃላይ የወልና የጸጋዬ አገጣጠም ካንድ ልማድ ወደ ሌላ የመሸጋገርን ያህል ሊከብድ ይችላል።

ለዚህ ሳይሆን አይቀርም ጋሽ ጸጋዬ ለተዋንያን የሚያዘጋደውን ቃለ-ተውኔት በዝርው፣ በስድ ግጥም መልክ ወደ አግድም እየጻፈ እንዲቀልላቸው የሚያደርገው። መገንዘብ ያለብን ግን በጸጋዬ ቤት የተጻፈውን ግጥም ወደ ወል ግጥም ስልት መለወጥ መቻሉን ነው።

ለአብነት አንድ የጸጋዬን ግጥም እንይ – ዜማውን ልብ በሉ።

በጸጋዬ ቤት የተጻፈው – አዋሽ

“አዋሽ ህመምህ ምንድነው? ህመምክስ አንተስ ምንድነው?

ከውሃ ወዝ የተለየ፣ መቼስ ልዩ  ንግርት የለህ?

እንደ ሴቴ ሸረሪት ፅንስ፣ ራስክን በራስ ዋጥ ያለህ …”

.

ይህንኑ ግጥም ወደወል ቤት ስልት ስለውጠው፣

“አዋሽ ሆይ ህመምክስ፣ አንተሳ ምንድን ነህ

ከውሃ ወዝ ልዩ፣ መቼስ ንግርት የለህ?

የሴቴ ሸረሪት፣ ፅንስ ዘር እንዳለው

ራስክን በራስህ መዋጥህ ለምን ነው?” ተብሎ ሊቀርብ ይችል ነበር።

ያም ሆኖ በሁለቱም ዘይቤ ቢሆን ቃላትን መምረጡና ሐረጋትን መቀመሩ የራሱ የሆነ ግጥማዊ ክህሎትን ይጠይቃል። Metaphor በሚባለው ወይ ተኪ-ተምሳሌት በሚባለው አንጻር ጋሽ ጸጋዬን ሳየው ምንም እንኳ ከአስመስሎ ቃሉ (Simile) አንጻር ያነሰ ቢሆንም፤ ብዙ ጊዜ ሲጠቀምበት እናያለን።

አሁንም በጋሽ ጸጋዬ ልሳን ግጥምና ቃል እንዲህ ተገልጧል።

ገጣሚው “ውስጣዊና ህያዊ ባህርዩን፣ መርጦ፣ አቅንቶ፣ ውበት አክሎ፣ በአስተዋይ ህሊናችን ውስጥ ቁስሉን የመፈወሱን ጥረት፤ ያደርጋል … ቃል ኃይል ነውና። ቃል ሕይወት ነውና”። ገጣሚው እኛ ውስጥ ፈውሱን ያገኛል። ለእኛ ደግሞ በፈንታው ፈውስን ይሰጠናል ማለቱ ይመስለኛል።

“ግጥም እርቃነ ልቦናችንን ወደ አልባሌው ሰው የየዕለት ህይወት ገልጠን የምንቀምረው ነው…” – እንደሕፃን ንጹህ ልብ ይዘን እንቀርባለን ማለቱ ነው። “ሸክላ ሠሪ ጡቧን – ባለቅኔው ኪነትን  ከምርጥ ቃለ-ሕይወት ዳግመኛ ይፈጥራሉ” ይለናል። ቃላት መምረጥ ያለክህሎት፤ ያለሙያ ያለስል ብዕር ሊሆን እንደማይችል ሲያስገነዝበን ነው።

“ፀሐይ ግንባሯን ቀልሳ፣ ከጭለማ ክንፍ ስትሸሽ ብርሃኗ በሌት ተዳፍኖ ዓይኗም ፈገግታዋም ሲሰንፍ” የሚለውን በአስረጅነት ይገነዘቧል።

ከጭለማው ክንፉን ሲዘረጋ ፀሐይ ግንባሯን እንደምትቀልስ በተኪ-ተምሳሌት (Metaphor) (ክንፍ እና ግንባር) እንዳስቀመጠው እንይ። ዓይኗና ፈገግታዋ ሲከስም፣ ወይም ሲጠፋ የሚለውን የተለመደ ግሥ ሳይጠቀም አላለም፤ ይልቁንም “ሲሰንፍ” የሚል ቀሰ በቀስ የመፋዘዟን ነገር የሚጠቁም፣ ውብ ቃል ይጠቀማል። ምርጥ ቃለ-ሕይወት እንዲል።

.

የጋሽ ጸጋዬ የሥነ ግጥም ጭብጦች

በ “እሳት ወይ አበባ”

.

  1. ማህበረሰባዊ/ግለሰባዊ ችግሮች

‘የምታውቀኝ የማላውቅህ’

“ለሩቅ ገጠሬ ነባሩ

ለማላውቅህ ለዳር ዳሩ

… ከረን ነህ መለሎ ብሌን

ከሁመራ ነህ ወይስ ገለብ

ማነህ

አጋው ነህ ወይስ ሺናሻ

ቅማንቴ ነህ ወይ ፈላሻ

ስምህ የሆነብን ግርሻ …”

ቦታው የማይታወቀውን፣ ዘር-ሐረጉ የተረሳውን፣ የሩቅ ገጠሬ በመጠይቃዊ አጻጻፍ ህሊናችን ላይ እንዲከሰት በማድረግ በረቂቁ ይወቅሰናል።

ግራ ጎንደር ነህ መተከል

ባላዋቂ የምላስ ቅርስ

የዘር ንፍገት ስትቀበል

ያለዳህ ስምህ ሲበከል

እምትችል እምትቀበል፣ እማትሞት እማትነቀል።”

እያለም፤ ስሙን ማንነቱን የተበከለውንና የተነጠቀውን ሳያጤኑ መነፈጉን ይነግረናል።

“እረኛ ነህ የከብት አርቢ

ሐማል ነህ የግመል ሳቢ

አራሽ ነህ የአገር ቀላቢ”

እያለ ኑሮውን ለማሟላት ሲል ገጠሬው ደፋ-ቀና የሚልበትን ሙያ፣ እንጀራውን መሠረት አድርጎ ለምን ይበደላል ከሚል የተቆርቋሪነት መንፈስ ይሞግተናል። መቻሉን መቀበሉን ግና በምንም ዓይነት እሱን መንቀል አለመቻሉን የማይሞት ጥኑ ገጠሬ መሆኑን አበክሮ ይነግረናል።

‘አይ መርካቶ’፣ ‘ማነው ምንትስ’፣ ‘ረሀብ ስንት ቀን ይፈጃል’፣ ‘አስቀመጡህ አሉ’‘ጎል’ እንዲሁ የማህበራዊ ፍሬ ጉዳይ የሚያነሱ ናቸው።

.

  1. ጥበብን በተመለከተ ቁርቋሬ

‘የብዕር አሟሟት ሌላ’

‘መትፋት ያስነውራል’ … ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው

.

  1. ፖለቲካዊ ሸንቋጮች

የጋሽ ጸጋዬ ግጥሞች ሀገራዊ ጉዳዮችን በብዛት ያነሳሉ ለኤድዋርዶ ሞንድላንድ ለሞዛምቢኩ ታጋይ የጻፈው ጥሩ አብነት ይሆነናል።

እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ

“አልጠራቸውም አይጠሩኝ

አይንኩኝ ስሜን አያንሱኝ”

ብለህ እንዴት ትመኛለህ፣ እንደማይተዉህ ስታውቀው

የተወጋ በቅቶት ቢተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው?

የጅምሩን ካልጨረሰው?”

ያ ታጋይ በዳሬሰላም አደባባይ ነው የተገደለው። ከዚያ ድረስ ተከታትለው ነው የገደሉት። ጋሽ ጸጋዬ ለሱ ተቆርቁሮ ብቻ ሳይሆን የተለመደውን ተረትም ሰብሮታል፤ ህጉን ጥሶታል። “የተወጋ በቅቶት ቢተኛ የወጋ መች እንቅልፍ አለው” ይለናል። የሚታወቀው አባባል “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” ነው። ጸጋዬ በግልባጩ ነው የገለጸው። የተወጋ በቃኝ ብሎ ቢተኛ የወጋው አይተኛልህም። ተከታትሎ ይጨርስሃል ነው የሚለን።

‘እግር እንይ’ በስላቃዊ ዘይቤ የጻፈልን ነው፣ ‘ምንም አልል’፣ ‘አዋሽ’ በሲምቦሊክ በምልክታዊ መልክ ያቀረበልን ነው። ‘እንዳይነግርህ አንዳች እውነት’፣ ሌሎችም በርካቶች አሉት።

.

  1. የፍቅር ጉዳይ

በፍቅር ፍሬ ጉዳይ ዙሪያም እንደብዙ ገጣምያን ጋሽ ጸጋዬም ተመስጦበታል። ከነዚህ ግጥሞቹ መካከል በወል የአጻጻፍ ዘይቤ የጻፈው ‘መውደድ አባ ፀፀት’ ይገኝበታል። ‘መሸ ደሞ አምባ ልውጣ’ ሌላው ነው። ‘ተወኝ’፣ ‘ጌራ’‘አብረን ዝም እንበል’፣ ‘ትዝታ’ እያለ ይቀጥላል።

[“አብረን ዝም እንበል”። ጸጋዬ ገብረ መድኅን። 1996 ዓ.ም።]

.

  1. የታሪክና ጀግንነት ጉዳይ

‘የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ’‘ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት’፣ ‘ቦረን’ (የሃዩ አላኬ ሊበን ቀረርቶ)፣ ‘ዋ ያቺ አድዋ!’

ለአብነት ያህል ‘መተማን በህልም’ የሚለውን እንይ

“… ከራስ ዳሽን አድማስ ግርጌ

ከዞብል መቃብር ማዶ

መተማ የተኛ ዘንዶ

ተምዘግዝጎ ጠረፍ ንዶ

እንደሰሎሜ ምሳሌ፣ እንደሄሮድስ ሴት ልጅ ሽንጥ

በኖባ ተራራ ጥምጥም፣ ሠራ አካሉን ቢያንቀጠቅጥ…”

የሴት ልጅ ሽንጥን ዙሪያና የኖባን ተራራ አመሳስሎ ከመሳልም ባሻገር ሠራ አካሉን የማንቀጥቀጡን ሥዕል እንዴት እንደተጠቀመበት ስናስተውል እጅግ ድንቅ ምስል እናያለን።

.

  1. የሕይወት ፍልስፍና

ከ‘ሕይወት ቢራቢሮ’ አንጻር አንድ ምሳሌ ቆንጽለን እንይ ፦

“… ምን አይተሻል ከቄጤማ፣ ምን አይተሻል ከለምለሙ

ቀን አብረሽ አብበሽ ውለሽ፣ ሲመሽ አብረሽ መስለምለሙ?…

አስተምሪኝ ቢራ ቢሮ፣ ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ …

ሲተረትም ሲወጋ፣ ከየብልጭታው ውጋገን

የሰው የአራዊት የአእዋፍ፣ ውስብስብ ነገደ-ጉንዳን

ሲነሳ ሲሮጥ ሲደፋ፣ ሲያጋድል ሲያዛባ ሚዛን

በማይመጠን ታላቅ ኃይል፣ የተፈጥሮ ግዙፍ ሥልጣን

ሊፍተለተል ይወለዳል፣ ሳይነቃ ይወድማል ይባላል

ልደቱ ዕድሜና ሞቱ፣ አለማቋረጥ ይጓዛል፤

ይኸ ይሆን አልፋ-ኦሜጋ? ይኸ ይሆን አስቀድሞ ቃል?”

በሕይወት ላይ መፈላሰፍ የየገጣሚው አመል ነው። ከሕይወት ጋር ያልተሳሰረ ምንም አይገኝም። ሕይወት ወረት ናት። ከሚያምረው ጋር አብራ አብባ፣ ከሚከስመው ጋር የምትጠወልግ መሆኗ ለምንድን ነው? ብሎ ይጠይቃል ጋሽ ጸጋዬ። በቢራቢሮም ይመስላታል። የአያሌ በሳል የዓለም ገጣሚያን ታላቅ ጥያቄ ሰው የተባለ ፍጡር ከየት መጣ? መድረሻውስ ወደየት ነው፤ ነው የሚለው። ጋሽ ጸጋዬ ዥጉርጉር ቀለም ያላትን ውብ ቢራቢሮ በሕይወት መስሎ ይሄንኑ ታላቅ ጥያቄ ያነሳባታል፤

“ሰው ለመባል አለኝታዬ

ቀድሞ የት ነው መነሻዬ

ሲመሽ የት ነው መድረሻዬ” እያለ።

ፍጥረት ሁሉ በማይመጠን ግዙፍ ታላቅ የተፈጥሮ ኃይል የተፈጠረ ነው የሚለውን ንድፈ ሀሳብ እየነገረን ያም ቢሆን የውጋጋን ብልጭታ ታህል የሚነገር ተረት መሰል ነገር ነውም ይለናል። መውለድ፣ መኖርና መሞት ያለ የነበረ መሆኑን እያመላከተ ምናልባት የፍጥረት አልፋና-ኦሜጋ ይህ ነው ተብሎ ቀድሞ የተጻፈው ቃል ይሆን ወይ? ብሎም ይጠይቃል፣ እንድንመራመር ያተጋናል። ጋሽ ጸጋዬ ይሄን ሁሉ ከመልከ-ብዙዋ ቢራቢሮ እንደሚነጋገር አድርጎ ነው የሚያጫውተን። ተምሳሌታዊ ውክልናው በጣም ማራኪና ኃይለኛ ነው።

‘እሳት ወይ አበባ’ ‘ድንቅም አደል?’፣ ‘ወንድ ብቻውን ነው የሚያለቅስ’ ዓይነቶቹ ግጥሞች እያንዳንዱ ግጥሙ ውስጥ ፍልስፍና ያለውን ያህል ራሱ በፍልስፍና ላይ የተመሠረት ግጥምም እንደሚጽፍ ያሳያል።

.

  1. ባህላዊ እሴት

ባህላዊ እሴት ላይ ሲያተኩር ደግሞ ‘በራ የመስቀል ደመራ’ን ጽፏል። ‘በየት አባቱ ሞትም ይሙት!’ ደግሞ የጋሞ ባህላዊ ሥርዓት በሞት ላይ ድል መጎናጸፍ መሆኑን ያበስረናል።

‘ለኢልማ ጋልማ’ – አባ ጋዳ የጻፈው ‘ቦረን’ (የሙርቲ -ጸሎት – ጥሪ)

“ጸጥታ ይሁን ፈረሱን አቅና

እምቦሳን አጥባ

ጊደሩን አርባ

ኮርማውን አስባ” ብሎ በሥነ ግጥም ይባርከናል።

‘አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ’፤ 1962 – ባሌ ጎባ የተጻፈውን ተመልከቱ፤

“ለካ እንደትዝታ አስታምሞ

እንደዘነጉት የእናት- ጡት፣ ከዘመን ጋር አገግሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ፣ እጄን በትዝታሽ ያዢኝ

በሕልም ጣቶችሽ ሳቢኝ

መቼም … በውን አልሆንሺም፣ እንዲያው በሰመመን ዳሺኝ”

ትዝታዋ ያጠመደውን የባሌ ኦሮሞ እስኪያመው ድረስ ይስታውሳታል። እጅ ለእጅ መያያዛቸውን ለማስታወስ ለትዝታ ነው ኃይሉን የሰጠው። ሩቅ ሃሳብ መሆኑን ለማሳየት ጣቶቿ ሁሉ የህልም ጣት እንዲሆኑ አድርጓል። ዳሰሳዋን እንደሰመመን ስስ አድርጎታል።

የኔ እጅ እኮ እርፍ አይጨብጥም

የኔ ክንድ እኮ ተልም አይተልምም

የኔ ጣት አረም አይነቅልም

በፊደል መፈደል በቀር፣ ጉልጓሎኮ አይጎለጉልም

ለስልሻለሁ፣ ሠልጥኛለሁ፣ ሰይጥኛለሁ አልሆንሽም።”

ጋሽ ጸጋዬ ‘ፊደል’ የሚለውን ስም ወደ ግሥ ለውጦ ‘መፈደል’ ማለቱ ሳያንስ ጭራሽ ከጉልጓሎ ጋር ያነጻጸረዋል። መሠይጠን፣ መሠልጠን መሆኑን፣ መሠልጠን ደግሞ መለስለስ መሆኑን፣ መናገሩ ሳያንስ፤ የዚህ ዓለም ሥልጣኔ በጥንት የባህልና የልማድ አብሮ-አደጎቻችን ላይ ዛሬ ክፉ መሥራት መሠይጠን መሆኑን ያስረዳናል።

“… የማር እሸት እንቁረጥ ተይ፣ የጥቅምት አበባ እንቅጠፍ

ነይ ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ

ጣት ለጣት እንቆላለፍ

በዐይን ጥቅሻ እንገራረፍ

ከአውድማችን አፋፍ ለአፋፍ፣ በዳሰሳ እንጠላለፍ

ተይ ፍቅር እንዘራረፍ

በህልም እንኳ እንተቃቀፍ…

አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ።”

የማር እሸት እንቁረጥ ተይ በሚለው መስመር ውስጥ ተይ በሚለው የማማለያም፣ የመማጸኛም ቃል የልጅነት ጨዋታውን ሊነግረን ፈልጓል። “ሸጎዬ አብረን እንግዘፍ” ሲለንም እንቅስቃሴውን ለመግለጽም፣ ግዙፍ እንሁን ለማለትም፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ገድሏል። በዳሰሳ እንጠላለፍ ሲልም ጉዳዩን ወደ ህልም ሲለውጠው ነው። “ተይ ፍቅር እንዘራረፍ” ማለቱን አስተውሉ። ፍቅርን እንደቅኔም፣ እንደሚነጠቅ ንብረትም የማየት ቅኔያዊ ውበት ነው የሰጠው። በህልም እንኳ እንተቃቀፍ የሚለው ውብ አጻጻፍ የትዝታን አስተቃቀፍ የሚያጠናክርልን ነው።

የመጀመሪያውን ስንኝ የመጀመሪያ ሐረግ ከመጨረሻው ስንኝ ብናስተሳስረው የጅምሩንና የፍጻሜውን መጣጣም እናስተውላለን፤

ለካ እንደትዝታ አስታምሞ

እንደዘነጉት የእናት ጡት፣ ከዘመን ጋር አገግሞ (ይሄ የመጀመሪያው ስንኝ ነው)

አዎን ዕድሜም ያማል ከርሞ

አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ (ይሄ ደግሞ የግጥሙ መደምደሚያ ነው።)

.

  1. መልክዓ ምድራዊ ይዘት

መልክዓ ምድራዊ ይዘት ያላቸው እንደ ‘አባይ’ እና ‘ሊማሊሞ’ ያሉ ግጥሞችንም ጽፏል ጋሽ ጸጋዬ። ምስልና ማመሳሰያ ቃላት እንደልብ የሚያጠግበን በነዚህ ዓይነቶቹ ግጥሞቹ ነው። ከ‘ሊማሊሞ’ ጥቂት መስመሮቹን እንመልከት፤

“የሰማይ የምድሩ ኬላ፣ የየብስ የጠፈሩ ዋልታ

አይበገር የአለት ጣራ፣ አይመክተው መከታ

ሊማ-ሊሞ አድማስ ሰበሩ፣ በጎማ ፈለግ ይፈታ?

በትሬንታ እግር ይረታ?…”

ሊማሊሞን የጻፈው ለፈረደ ዘሪሁን ነው። ፈረደ ዘሪሁን እንግዲህ የታዋቂው ደራሲ የብርሀኑ ዘሪሁን ወንድም መሆኑ ነው።

ጸጋዬ በዚህ ግጥሙ ውስጥ ልዩ ልዩ እኩያ እየፈጠረ ሊማሊሞን እሱ ባየበት ዐይኑ ሲያሳየን እናገኘዋለን – ሊማሊሞ የምድር ኬላ ነው። ሊማሊሞ ለምድር ዘብ የቆመ ነው። ሊማሊሞ ለጠፈሩ ደግሞ ዋልታ ሆኖ የቆመ ነው። ሊማሊሞ የማይበገር አለት ነው። መከታና ጋሻ ነው። ሊማሊሞ በዐይናችን የምናየውን ሰፊ አድማስ ሰብሮአል።

ይሄ ሁሉ መሬት ቆመን ከኛ እያነጻጸርን ስናየው የሚፈጠርብን ስሜት ነው ማለቱ ነው። ወደ ሽቅብ ከሰማዩ ጋር ስናየው ደሞ ሊማሊሞን እንደቆመ ወንዲስ ሰው አድርገን እፊታችን እንድናይ ለማድረግ ከደመናው በላይ አልፎ ይታየናል ይለናል። አለፍ ብሎም ከሰማይ ጋር ይለካካል። ጉም እንደቀሚስ አጥልቋል። የፀሐይቱን ጨረር ደግሞ እንዳንገት ልብስ ሸብ አድርጎታል። ከአንገቱ ይጀምርልንና “በብብቱ ጉም ታቅፎ” እያለን፤ ግራና ቀኝ የጮራ ዘርፍ እንደሰራ በመጥቀስ ያሞካሸውና “ፍም አንጥፎ እንደስጋጃ” ብሎ እግርጌ ያደርሰናል።

በግዙፍ ተራራ መልክ የቆመ የሰው ምስል ነው የሰጠን። ሆኖም ይሄ የማይበገር ተራራ “በድማሚት ተፈልፍሎ፤ ድልድይ ይሁንና ይረፍ ወይ?” ብሎ ነው የሚደመድምልን። ሥልጣኔ የማይረታው የተፈጥሮ አካል የለም እንደማለት ነው የተጠቀመበት – ምስለታውን።

.

ነቢይ መኰንን

.

[ምንጭ]አዲስ አድማስ ጋዜጣ/ አንድምታ መጽሔት (ቁጥር 9)። ኅዳር 2000 ዓ.ም።

.

 

2 thoughts on ““የጋሽ ጸጋዬ ግጥሞች ቅኝት”

አስተያየት ለመስጠት

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s