“ስለ ቅኔ ባህል”
(በምስጢር የተሞላ)
.
ከበዕውቀቱ ሥዩም
.
.
በዚህ መጣጥፍ ውስጥ የምናገረው ስለ ኢትዮጵያዊ የሀሳብ ዘይቤ (ቅኔ) ቢሆንም ለማነፃፀሪያነት ከባሕር ማዶ መጥቀሴ አይቀርም። ስለጐንጁ ተዋነይ ተናግሬ ስለአውሮጳ ሊቃውንትም አነሳለሁ። ይህ በኔ ግምት ተገቢ ነው። ሰዎች ከአንድ በላይ ዜግነት ይዘው በሚኖርበት ዓለም ከማዶም ከወዲህም እያቆላለፉ ማውጠንጠን ያዋጣል።
አንድም፣ የሌሎችን ሀሳብ ማስታወስ የራስን በተሻለ መንገድ ለመገንዘብ የሚያመችበት አጋጣሚ አለ። ለጊዜው ‘አውሮጳ ተኮር ጥበብ’፣ ‘አፍሪቃ ተኮር ሥልጣኔ’፣ ‘አፍሪቃዊው ሶቅራጥስ’፣ ‘ጥቁሩ አውግስጢኖስ’ በሚለው እሰጥ-አገባ ውስጥ ተሳታፊ የምሆንበት አቅም የለኝም።
አንዳንዶቹ “የኛን” ሀሳቦች ከሌሎች ጋራ ተበርዘው ልዩ መልካቸው እንዳይደመሰስ በመፍራት አጥረው ያስቀምጧቸዋል። በሌላ በኩል የሌሎች ሀሳብ “እንዳይውጣቸው” በመስጋት የሚከላከሉ ይኖራሉ። በውጤት ሀገርኛ ሀሳቦች ከሌሎች ጋራ የማይውሉ የማይወዳደሩ ዓይናፋር የቤት ልጆች ሁነው ቀሩ። ከማዶ የሚያንኳኩ ዘይቤዎች ደግሞ በዝጋ ብርሃን ፖሊሲ ምክንያት ወደ ውጭ ተጥለው ቀሩ። ይህ አይነቱ ልማድ ግን የማያዛልቅ መሆኑን የተረዱ ሊቃውንት አልጠፉም።
ለዚህ መጣጥፍ ማዳመቂያ አለፍ አለፍ እያልኩ የምጠቅሳቸው ዕጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” በሚለው መጽሐፋቸው የሚከተለውን ብለዋል፤
“… የሥልጣኔ መንፈስ ወደ ፈቀደበት ይነፍሳል። ለመቃወም አይቻልም፤ የሚገባም አይደለም። ምክንያቱም የሥልጣኔ ሀብታት ከሰው የኅሊና ጥረት የሚገኙ ስለሆነ በየትም ቢወለዱ ዘመዳሞች ናቸው። ለመዓት ወይም ለምሕረት የሚቸኩል ሰው ሳይሆን፣ አስተዋይ ተመልካች የሆነ እኒህን ዘመዳሞች የሚያስተዋውቅ ሽማግሌ ያስፈልጋል።”
ቅኔ በሀሳብ በሰዋስው መምህራን አማካኝነት ከግዕዝ ጋራ ብቻ ተቆራኝቶ ቆይቷል። በኔ ግምት በሌሎች ቋንቋዎች የመቀጠል ዕድል አላጣም። ይህም በሀሳቡ ላይ ባለን ፍቺ ስምምነት የሚወሰን ይሆናል። በቅኔ ምንነት ዙሪያ የሰዋስው ምሁራንና ሀሳብ አመንጭ ሊቃውንት የተለያየ አቋም አላቸው። ሁሉም ግን “ምስጢር የተሞላ” በሚለው መስፈርት ይስማማሉ። “ምስጢር መሞላት” ማለት በሰምና ወርቅ ሀሳብን መሸሽግና መግለጥን አያመለክትም። ሰምና ወርቅ ቅኔ፣ ወርቁ የተገለጠ ቀን ምስጢርነቱ ያከትማል። የተጋረደብንን የህልውና ዕውቀት የሚገልጥልንን ምጥን የጽሑፍ ዘይቤ በዚህ ስም ልንጠራው እንችላለን።
በዚህ ረገድ ከፍ ያለ ጥበብ ያለውን ግጥም ሁላ ቅኔ ልንለው እንችላለን። ሰሎሞን ዴሬሣ ባንድ ወቅት እንደጻፈው በኢትዮጵያ የሥነጽሑፍ ፈሊጥ ውስጥ ስድ ጽሑፍ የቅኔን ያክል አላደገም ወይም የዝርው ጽሑፍ ሥርዓት ለቅኔ የተሰጠውን “ምስጢር የተሞላ” የተባለ ማጎላመሻ አላገኘም። የቅኔን ያክል ተደጋግመው የሚነበቡ ዝርው ጽሑፎች አሉ። የራሱ የሰሎሞን ‘የልጅነት መግቢያ’ በኔ ግምት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው። ቤት ባይመታም ላቅ ያለ ሀሳብና ጥበብ ያለው በምስጢር የተሞላ ዘይቤ ሁላ ቅኔ ነው።
.
“ያልተጻፈ”
ሊቃውንትና ባልቴቶች ተባብረው እንደሚነግሩን የቅኔ አባት ተዋነይ ነው። ልክ የሙዚቃ አባት ያሬድ እንደ ሆነ። የኖረበትን ዘመን አጥኚዎች በ15ኛው ክፍለ ዘመን ያደርጉታል።
በነገራችን ላይ ተዋነይ የስሙን ገናናነት ያክል ብዙ ቅኔ አናነብለትም፤ አብዝቶ ስላልተቀኘ ሳይሆን አብዝቶ ስላልመዘገበ። በኢትዮጵያ የቅኔ ሥርዓት ትውፊት ውስጥ የምዝገባ ባህል ደካማ ነው። ደካማ የሚለውን ቃል በመጠኑ ላርመው። ታድያ የጥንቶቹ ደራሲዎች ቅኔያቸውን በጥንቃቄ መዝግበው ለምን አላስቀመጡልንም? መጀመሪያ ትሕትና መስሎኝ ነበር። በኋላ ግን ራሴን አረምኩ። አብዛኞቹ ታላላቅ ባለቅኔዎች እንደ ጻድቃን ትሑታን አልነበሩም። “ዕቡይ” የሚባል ቅጽል እስኪሰጣቸው ቀና ቀና ባይ ነበሩ።
ሌላው ምክንያት የጽሑፍ ባህል አለመዳበር ነው። ይኼ እንዲያውም ለውይይት የማይበቃ ሰበብ ነው። ጥንታውያኑ ጽፎ በማስቀመጥ ረገድ ወደር አልነበራቸውም። ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዳሉት ከሆነ እንግሊዞች ብቻ ከቴዎድሮስ ቤተመጻሕፍት 375 መጻሕፍት ወስደዋል።
ለጊዜው የምገምተው ምስጢር የቅኔ ጠባይ ለምዝገባ ምቹ አለመሆኑ ነው። ቅኔ ለጥንቶቹ በንግግር የሚተባ ሀሳብ ነው። (ፈረንጆች፣ ለምሳሌ የArt That Heals ጸሐፊ Jacques Mercier ቅኔን “Rhetorical Poetry” የሚለው ለዚህ ነው።) በዚህ ምክንያት ለብራና የሚመጥን አይደለም። የጽርእ (ግሪክ) ሊቃውንት ይኼን ያውቁታል። ሃና አሪቲ አፍላጦንን (Plato) ጠቅሳ እንዳቀበለችን ዋናውና የክቱ ሀሳባችን ካፋችን የሚወጣው ሲሆን የሚጻፈው ግን ቢጤው፤ ወይም ጥላው ነው።
አንድም፣ ቅኔ የላቀ ጥበብነቱ ከሙዚቃ ያላነሰ አድርጎታል። ዓለማየሁ ሞገስ ቅኔ ምን እንደሆነ ሲነግሩን “ምስጢር የተጎናፀፈ መዝሙር” ብለው ነው። የምዕራብ ባለቅኔዎች ፈታውራሪ ኒቸ “ዛራቱስትራ”ን በዝርው ቅኔ እንደጻፈው ያውቃል። ግን ሥራውን ለመረዳት “ሙዚቃ የማጣጣም ጥበብ” እንደሚጠይቅ ተናግሯል።
ይህንን ይህንን ስናይ ጥሩ ባለቅኔ እንደሞዘቀ ይሰማናል። ዘርዓ ያዕቆብ የድምፁን ጎርናናነት እንዲያካክስ ያደረገው ልቦናው ለቅኔ ብሩህ መሆኑ ነው። በዚህ ምክንያት ቅኔን መጻፍ መንፈሱን ማጉደል መሆኑ የተሰማቸው አበው ምዝገባውን ብዙ የተጨነቁበት አይመስለኝም። ከነተረታቸው “የቅኔ ቋንጣ የለውም”።
.
“ሥጋዊ ወመንፈሳዊ”
ስለ ተዋነይ ታሪክ የሚነግሩን ተራኪዎች የእውነትና የተረት ቅልቅል ያቀርቡልናል። እውነቱም ተረቱም ግን ቅኔና ባለቅኔ የሥጋና የመንፈስ ታዛዥ መሆኑን የሚያጠያይቁ ናቸው። ተዋነይ ምትሐተኛ እንደነበረ፣ የአፄ እስክንደርን ሚስት አማልሎ እንዳስኮበለለ፣ በአጋንንት እርዳታ ልዩ ልዩ ጥበብ እንደፈጸመ፣ በማይታዩ ሴቶች አማካኝነት ወደ ጣና ደሴት ተጠልፎ እንደተወሰደ … ሌላም ሌላም ይተረካል።
ይህ የሚያነሳብን ጥያቄ አለ። ቅኔ በቤተክርስቲያን በኩል ነው የደረሰን፣ የቤተክርስቲያን ዋና ተልዕኮ ደግሞ መንፈሳዊነትን ማላቅ ነው። መንፈሳዊነትን የሚያጋንኑ ምሁራን የሥጋን ህልውና ቸል ይላሉ። ለምሳሌ ወሲብና መፀዳዳትን እንውሰድ። ወሲብ እስካሁን ያለው ስሙ ግብረ-ሥጋ ነው። የሥጋ ሥራ እንደማለት ነው። ስለዚህ የጻድቃንን አኗኗር ብናነብ ታሪካቸው ወይ የድንግልና ነው፤ አሊያም የመበለትነት ነው።
መፀዳዳትም እንዲሁ ነው። የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ታሪክ ሲነገረን የሚከተለውን እንሰማለን። አባ ጊዮርጊስ በሄደበት ሁሉ እመ ብርሃንን ያሞግሳታል። ከእለታት አንድ ቀን፣ ሽንት ቤት ቁጭ ብሎ ሲያመሰግናት ተገለጠችለትና ባረከችው። ከዚህ በኋላ “ይህ አይሁንብህ” አለችው። እሱም ከዚያ በኋላ ወደ መፀዳጃ ቤት አልተመለሰም።
ለአባ ጊዮርጊስ የተሰጠው ቡራኬ ከሥጋ ሥራ የሚያድን ነው … ወይም በተሻለ አባባል ከሥጋ የሚነጥል ነው። በዚህ ረገድ የቅኔ ትውፊት ከቤተክርስቲያን ቀኖና ይነጠላል። የቅኔ ትውፊት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ ነው። ከስሙ ብንጀምር ተዋነይ ከመንፈሳዊው ምክር ያፈነግጣል። ተዋነይ በግዕዝ “ተጫዋች” ማለት ነው። ቀላጅና ቧልተኛ ልማዱን የሚያሳይ መጠሪያ ነው። ከሴቶች ጋር የተቆራኘው ገድሉ በወሲብ ላይ ያለውን አንክሮ ይጠቁመናል። ልክ ነው። ያለ ወሲብ፣ ቅድስና እንጂ ቅኔ የተሟላ ሊሆን አይችልም። ስለ “የነገሮች ባህሪይ” (De Rerum Natura) የጻፈው ሉቅርጢያስ (Lucretius) እንኳ ቅኔውን የሚጀምረው የግጥምን አምላክ ቸል ብሎ የወሲብን አምላክ በማሞገስ ነው።
.
“የስሜት ጡዘት” (Ecstasy)
ሊቃውንት ስለ ስሜት ጡዘት ሲያብራሩልን ቃል ሲያጥራቸው በአስረጅነት ወይ ሙዚቃን ይጠቅሱልናል፤ ወይ ከወሲብ ማጠናቀቂያ የእርካታ ሰከንዶችን እንድናስብ ይነግሩናል። በስሜት ጡዘት ውስጥ አካባቢን፣ እራስንና ጊዜን መቆጣጠር አዳጋች ነው። ይህን ኃይል በወሲብ ብቻ ሳይሆን በቅኔም ውስጥ እንደምናገኛቸው ከሀዲስ አለማየሁ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ሁለት ትረካዎችን ልጥቀስ፤ የመጀመሪያው የበዛብህና የሰብለወንጌል ባፍ ውስጥ የመቅለጥ ትርኢት ነው።
“… ሁለቱ ንጹሐን ይህንን የተበላሸ፣ ይህንን በክፉ ነገር ያደፈ የጎደፈ አለም ጥለው ወደ ሌላ አለም ወደ አንድ አዲስ አለም ገቡ።”
በሌላ ቦታ፣ አለቃ ክንፉ የተባሉ ባለቅኔ ሲቀኙ እንዴት እንደሆኑ ሀዲስ እንዲህ ብለው ይተርካሉ፣
“… ከጉባኤ ቃና ጀምረው እመወድስ ሲደርሱ እንደ ሁልጊዜው ሞቅ አላቸው። ብድግ ብለው እንደ ፎካሪ ከወዲያ ወዲህ እየተንገዳገዱ ማዕበሉን ያወርዱት ጀመር … አለቃ ላባቸው እየተንጠፈጠፈ ደሞ እንደገና ‘ተቀበል!’ ብለው ጉባኤ ቃና ሲጀምሩ መምህራኑ ወደ ፎቅ ወጡና ለምነው ወደ ምኝታቸው ወስደው አስተኟቸው። ገላጋይ ባይደርስ ደክሟቸው እስኪወድቁ ድረስ ይዘርፉ ነበር … ቅኔ ሲያሰክራቸው፣ በዚህ አለም መኖራቸውን ሲረሱት፣ ከጻድቃን ከሰማዕታት ከምዕመናን ከመላእክት ጋር በሌላ አለም የሚጫወቱ ሲመስላቸው፣ ያን ጊዜ ሳያውቁት ሳይሰማቸው የሚያወርዱት የቅኔ ማዕበል የእውነተኛው የተዋነዩ ደቀመዝሙር አሰኝቷቸው ቀረ …”
የፍቅረኞቹ በአፍ ላፍ መቅለጥና የአለቃ ክንፉ የቅኔ ስካር እጅግ ተቀራራቢ ትርኢት ገልጧል። ፍቅረኞቹም ባለቅኔውም ከጊዜና ከቦታ እግረ ሙቅ ላፍታ ነጻ ወጥተዋል። ስሜታቸው ወደ ነበረበት ሲመለስ ሁሉም የሰውነት መዛልና መራድ ደርሶባቸዋል።
እንዲህ አይነቱ የስሜት ነውጥ በባለዛር እንጂ በባለቅኔ ውስጥ ይገኛል ብለን አንገምትም። ምናልባት ጥንታዊ ጽርአውያን ሊቃውንት (ይልቁንም ሶቅራጥስ) ቅኔን የመለኮት ኃይል ወይም የከያኒ መናፍስት ሀብት ነው ብሎ ማመኑ፣ ባለቅኔዎችም የኒህ መናፍስት መስፈሪያ ከመሆን ያለፈ እርግጥም የሆነ ዕውቀት እንደሌላቸው ማስተማሩ፣ ከዚህ አይነት ትርኢት በመነሳት ይሆናል። ሀዲስ አለማየሁ የአለቃ ክንፉ ቅኔ ሳያውቁትና ሳይሰማቸው የሚወርር መሆኑን በማመናቸው ከሶቅራጥስ ትይዩ ቆመዋል።
ከመለኮትም መጣ ከሰው ልቦና፣ ቅኔ ከወሲብ ጋር የሚመሳሰል የስሜት ንረት ማጎናጸፉ ለብርቅነቱና ለተወዳጅነቱ ሰበብ ሆኗል።
.
“ጽሙና”
ስለ ኃያልነቱና ስለ ድንገተኝነቱ ቅኔ በሀዲስ አለማየሁ ‘ማዕበል’ ተብሎ ተጠርቷል። እንዲያ ከሆነ ከማዕበሉ መውሰድ በፊት ባህሩ ፀጥ ማለት አለበት። የብዙ ባለቅኔዎች ገድል የጽሙና ገድል ነው። “ጽሙና” በኪዳነወልድ ክፍሌ ፍቺ፤ ‘ጭምትነት፣ ፀጥታ’ ማለት ነው። አበው እንደሚነግሩን ባለቅኔው እየተንጎራደደ ወይም ተቀምጦ ሲያውጠነጥን በዙርያው ያሉትን ሁሉ ሊዘነጋ ይችላል።
ክፍለ ዮሐንስ የተባለው ባለቅኔ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ በፊቱ በአጀብ ሲያልፉ ቅኔውን እያስተካከለ ስለነበር እጅ አይነሳም። ይኽኔ በወርቅ ጠጠሮች ወርውረው በመምታት ‘ከጽሙናው’ ቀሰቀሱት። እሱም እንደመባነን ብሎ፣
“ድንጋዮች ከእስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ፣ ኢያሱ ወገረኝ በወርቁ!” ብሎ ተቀኘ።
ተዋነይ ከጣና ደሴቶች ባንዱ (ደቅ) ገብቶ ለረጅም ጊዜ በጽሞና እስኪቆይ ድረስ የቅኔን ስልት የሚያሻሽልበት ጥበብ እንዳልተገለጠለት ሊቃውንት ይናገራሉ። ጽሞናና ብሕትውና ለባለቅኔ (ለሌላውም ከያኒ) እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን የተቹ ብዙ ጸሐፊዎች አሉ። ዕጓለ ገብረዮሐንስ “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” ብለው በደረሱት መጽሐፍ ውስጥ የዛራቱስትራን የተራራ ላይ ቆይታ በማንሳት እንዲህ ብለው ነበር፤
“… ወደ ኋላ መሸሽ መሸሸግ፣ ወይም እንደ ዛራቱስትራ ወደ ተራራ ወጥቶ ከሳር ከቅጠሉ ከንስር ከእባቡ ጋር መኖር ከገዛ ራስ ጋር በመጠያየቅ፣ በመከራከር፣ በመወደስ መንፈስን ማደርጀት ያስፈልጋል። እንዲህ ያለ ዘዴ በሰዎች ዘንድ ቀርቶ በእንስሳት ዘንድ እንኳ ያለ ነው። በግና በግ እንኳ ተጣልተው ሲዋጉ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው ቀጥሎም መንደርደራቸው አንድ ምክንያት አለው። ይህም ኃይል ጉልበት ለማግኘት ነው። ሰው የመንፈስ ጉልበት ለማከማቸት የሚችለው በዕለት ትርኪ ምርኪ ወዲያና ወዲህ በማለት መባከኑ ቀርቶ ወደ ራሱ ተመልሶ መንፈሱን የቆጠበ ያደረጀ እንደሆነ ነው።”
.
“የላቀ ንቃተ ኅሊና”
ኢትዮጵያ ከመልክአ ምድሯ በተሻለ በጊዜና በኃይል መፈራረቅ ምክንያት የማይዋዥቅ ሌላ ምስል አላት። እሱም የብዙ ጥንታዊ መናፍስት ማኅደርነቷ ነው። ኢትዮጵያ በጃርሶ ‘ሞትባይኖር’ ኪሩቤል የማያዳግም አገላለጽ “Mystical Entity” ናት። ይህ የዕውቀቷም፣ ያለማወቋም ምንጭ ተደርጎ የሚወሰድ ዕጣዋ ነው። የኢትዮጵያን የሀሳብ ታሪክ አብዝተው የሚያውቁት ያገርም ሆነ ያገር ውጭ ሊቃውንት ደግመው ደጋግመው የሚያትቱት ክርስትናዋን ነው። የኪነጥበብ ታሪኳ ግን የብዙ ውጥንቅጥ መናፍስት መናኽሪያ እንደነበረች ነው።
ቅኔ ለአያቶቻችን ወደ መለኮት የሚያሻግር መሰላል ነው። ይሁን እንኳ፣ መሰላሉ የሚሰበርበት ጊዜም ነበር። የተዋነይ አንዱ ቅኔ እንዲህ የሚል ነው፤
“የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ
ካልኣን እንዘ ይትኤዘዙ ይሰግዱ ቅድሜሁ
ለጠይቆ ዝኒ ነገር ከመ እስራኤል ይፍርሁ
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ
ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ።”
.
(ትርጉም)
“ዓለም ሁሉ ራሱ በፈጠረው ያምናል፤ ይገዛልም
ሌሎች እየታዘዙ በፊቱ ይሰግዳሉ
ይህንን ነገር በመረዳት እስራኤል እንዲፈሩት
ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ
ፈጣሪም እሱን መልሶ ፈጠረው።”
.
ይህ ቅኔ ተዋነይ ላለማመኑ የሰጠው ምክንያት ነው። እግዜርን የሙሴ እጅ ሥራ አድርጎ መግለጡ ብቻ ሳይሆን፣ የፈጠረውን መነሻ የማስገበር ፍላጎት መሆኑን ገምቷል። ይህንን ሀሳብ ከምእተ ዓመታተ በኋላ የተመለሰበት ኒቸ “The will of God is the preservation of priestly power” ይላል (“The Anti-Christ”)። ይሁን እንጂ እሱ እንደገመተው ሃይማኖት ከበላይነት ፈቃድ ጋራ የማገናኘቱን ዘይቤ በማግኘት የመጀመሪያው ሳይሆን ቀርቷል። አበው በቅኔ ቤት በኩል አስቀድመው ሰምተውታልና።
ይህንን ቅኔ ያገኘሁት በቤተክርስትያን የቅኔ ስብስብ ውስጥ መሆኑ እንቆቅልሽ ነው። ግን ቅኔ መሆኑ በቀኖና አክባሪ ሊቃውንት እንዳይሽቀነጠር አግዞታል። ቅኔ “በምስጢር የተሞላ” በመሆኑና በአሻሚኒቱ ከእምነት መፈክሮች ጋራ ተመሳስሎ የመቆየት ዕድል ነበረው። በዚህ አይነት ቅኔ ለዘመናዊ ንቃተ ኅሊና በር ከፍቷል።
.
“ሙሾ”
እዚህ አዲስ አበባ በቅኔ ላይ ውይይት በተካሄደ ቁጥር የወጣቶች ጉድለት ተብሎ የሚጠቀሰው “ጨለምተኝነት” ነው። በ“ኗሪ አልባ ጎጆዎች” የግጥም መድብሌ ላይ አስተያየታቸውን በሚድያ የገለጹልኝ ሰዎች ደግመው ደጋግመው “ስለ ጨለምተኝነቴ” ነግረውኛል። አንዳንዶቹ ለዚህ ምክንያቱ “የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ” መሆኑን በማብራራት ሊያግዙኝ ሞክረዋል። በበኩሌ ብያኔውም ሆነ ለብያኔው የተሰጠው ማስተባበያ ጉድለት አላቸው። ሀያሲዎች ጨለምተኝነት የሚሉት ሙሾ ሙሾ የሚለውን ሃዘን ያጠላበትን ግጥም ነው። ግንኮ ሊቃውንት በሊቃውንት መዝገበ ቃላት ውስጥ ያለውን የቅኔ ፍቺ “ተቀነዬ፣ ሙሾ አወጣ፣ ግጥም ገጠመ፣ አራቆተ፣ ተናገረ፣ አዜመ፣ አንጎራጎረ” የሚል ነው። (ዓለማየሁ ሞገስ)
“የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ” ለጨለምተኝነት ሰበብ ሆኖ መጠቀሱ አያዋጣም። የአሜሪካ ሕዝብን ሃዘን በኢትዮጵያ ሕዝብ ሃዘን የሚያበላልጥ ቁና አለ ብዬ አላምንም።
“ሥልጣኔ ምንድነች?” በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ከበደ ሚካኤል ጦርነት ለቅኔና ሙዚቃ ማደግ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጽፈው ማንበቤን አስታውሳለሁ። ሰው ሆነን ስናስበው አባባሉ ያስደነግጣል፤ የኪነጥበብ ዘፍጥረት መርማሪያዎች ሆነን ስንነሳ ግን ብዙ እውነት እናገኝበታለን። የሰርግ ዘፈኖችና የሙሾ ግጥሞችን ብናወዳድር የተሻለ ጥበብ የምናገኘው በሙሾ ውስጥ ይመስለኛል። ጦርነት ላቅ ያሉ የሀሳብ ዘይቤዎችን ገላጭ ሆኖ የተወሰደው የነፍስ በር ከፋች የሆነውን ሞትን ስለሚያሳስብ ይሆን? (ዮፍታሔ ንጉሤ ያማሩ ግጥሞቻቸውን የጻፉ በሙሶሎኒ ጦርነት፣ ዘርዓ ያዕቆብ ሐተታውን የጻፈው በሃይማኖት እርስ በርስ ጦርነት ወቅት ነው።)
ጦርነት ሞትን፣ ሞት ደግሞ የህልውናን ምንነት ያመላልሳል። የሰው እውነተኛ ድምፅ የሚሰማው ከዚህ ክስተት ጋር ሲጋፈጥ ነው። በሰው ያመኑ እናቶች እንዲህ የሚል ግጥም ትተዋል፣
“ወይ እኛና ዶሮ፣ አሞራና ሞት
ሲመጣ መንጫጫት፣ ሲሄድ መርሳት።”
.
እኛ ኢትዮጵያውያን የፊደል ሰዎች ሁለት ምርጫ ያለን ይመስለኛል … ወይ ሁኔታችንን መለወጥ፣ ወይ ካለው ሁኔታ ውበትና ዕውቀትን መፈለግ።
.
በዕውቀቱ ሥዩም
.
[ምንጭ] – አንድምታ ቁጥር 3። ግንቦት 1998 ዓ.ም። ገጽ 6-8።
.
ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ
የሚለውን በቀጥታ /በእማሬው/ እንረዳው? እንደሱ ከሆነ ተዋነይ የዘርአ ያእቆብ ደቀመዝሙር ነበራ። አመሰግናለሁ።
LikeLike
Hi tthanks for sharing this
LikeLike