“ቡሌ እና ዋርዴ” (ወግ)

“ቡሌ እና ዋርዴ”

ከሀዲስ አለማየሁ

.

(1948 ዓ.ም)

.

.

ያንድ ሰው ሁለት አህዮች ነበሩ። እነዚህም አህዮች አንዱ ዋርዴ፣ ሁለተኛው ቡሌ ይባሉ ነበር። ቡሌ ጌታውን በቅንነት ለማገልገል ባለመልካም ፈቃድና ቅን ነበር። ዋርዴ ግን ልግመኛና አሳቡ ሁሉ በተንኮል የተሞላ ነበር።

መጫኛና መደላድል ይዘው ሲቀርቡት፣ አስቀድሞ ለጥ ብሎ ይተኛል። ከዚያም ያስነሱት እንደሆነ ለመጫን የሚቀርቡትን ሰዎች ይራገጣል። አንዳንድ ጊዜም የገረመ መስሎ ሲጭኑት ሆዱን ነፍቶ ይቆይና ጫኞቹ አገር አማን ነው ብለው መንገድ ሲጀምሩ ጭነቱን አንሻቶ እየጣለ ግራ ያጋባቸዋል።

ስለዚህ ጌታው በየቀኑ ከሱ ጋራ መታገሉ አሰለቸውና ነፃ ለቀቀው። ዋርዴም እንደልቡ ሳሩን እየጋጠ ያልል ጀመር።

ቡሌ ግን፣ ጉልበቱ ከቻለ የልግምና የተንኰል አሳብ በጭራሽ ስላልነበረው ጌታው የጫነውን ሁሉ ዝም ብሎ ይጫናል። ከተጫነም በሁዋላ ተጠንቅቆና አስቦ፣ እተፈለገበት ቦታ በደህና ለማድረስ ይጣጣራል። ስለዚህ ጌታው ጥሩ አህያ ነው እያለ ጭነት ሲያስብ መጫኛና መደላድሉን ይዞ ወደ ቡሌ ብቻ ይሄዳል። እንዲሁም፣ ዘመድ ወዳጆቹ መጥተው አህያ ሲለምኑት “ዋርዴ ክፉ ነው፤ ቡሌን ውሰዱ” ይላቸዋል ወይም ለማኞቹ ሁለቱን አህዮች የሚያውቁ እንደሆነ “ዋርዴ በጄ አይለንምና ቡሌን ስጠን። እርሱ ነው ጥሩ አህያ” ይሉታል።

በዚህ አህዋህዋን ቡሌ ጌታውን ብቻ ሳይሆን የጌታውን ዘመድ ወዳጆች ጭምር እያገለገለ፣ ዋርዴም በጤና ሳሩን እየጋጠና እያለለ ሲኖሩ ቡሌ ከጭነት ብዛት የተነሳ አንዱ ቁስሉ ሳይድን እሌላ ቦታ እየተተኰሰ፣ ጀርባው በሙሉ የተገጣጠበ ኮሳሳ ሆነ።

ዋርዴ ግን ጠጉሩ ዘይት እንደተቀባ የሚያብለጨልጭና አካሉም የዳበረ ሆነ። ስለዚህ ባዝሮች የነበሩዋቸው በቅሎች ለማስወለድ፣ ባለሴት አህዮችም እንደርሱ ወደል አህዮች ለማስወለድ ሲፈልጉ አሞሌ ጨው ለጌትየው እየሰጡ ለምነው ይወስዱታል። ካሞሌው ጨውም የሚበዛው እየተከሰከሰ፣ ቡሌ ተጭኖ ከሚያመጣው ገብስ ወይም ሽንብራ ወይም ሌላ እህል ጋር ተደባልቆ ሀይል እንዲሰጠውና መልኩን እንዲያሳምረው ይቀርብለታል። ዋርዴ ያን እየተመገበ ካህዮች ለጥቂቶች እድለኞች ብቻ የተሰጠውን የድሎት ኑሮ ይኖር ጀመር።

ቡሌ ተጭኖ ውሎ ፣ ዋርዴ ሲያልል ውሎ ሲመለሱ ለዋርዴ ቡሌ ተጭኖ ካመጣው ገብስ ወይም ሽንብራ ከጨው ጋራ ይሰጡታል። ቡሌን ግን አንድ ጊዜ በዱላ ይደውሉና አተላ ወይም አመድ መሳይ ቢያገኝ ወደሚቆምበት ያባርሩታል።

“እንዴት ያለ ተሳስቶ የሚያሳስት አለም ነው እባካችሁ?“ ይላል ቡሌ፣ ይህን ሁሉ ግፍ ይመለከትና ሲገርመው።

“በቅንነት የሚያገለግለውን በዱላ መምታት፣ ላመፀኛው ገብስ በጨው መስጠት፣ እስኪ እንዲህ ያለው ፍርድ ይባላል?” ይላል ቡሌ ራሱን እያወዛወዘ።

አንድ ቀን ምርር ሲለው ጊዜ፣ እንደ ዋርዴ ልግመኛ ሆኖ ለመሞከር አሰበና ሊጭኑት ሲመጡ እግሮቹን ዘርግቶ ለጥ አለ። የዚህን ጊዜ ጌታው፣

“ሆሆ፣ ይህ ገጣባ ደግሞ ዋርዴን እንዳየኮ ጀርባዬን ጭነት አይንካው ማለቱ ነው” አለና በዱላ ሲያቀምሰው ጊዜ ቶሎ ብድግ ብሎ ተነስቶ ጭነቱን ተጫነ።

እንዲሁም በየጊዜው ጭነት እያንሻተተ በማስቸገርም፣ በመራገጥም እንደ ዋርዴ ኑሮውን ለማሻሻል ቢሞክር ከዱላ በቀር ሌላ ትርፍ ለማግኘት ስላልቻለ ቡሌ እንደ ድሮው አመሉን አሳምሮ ለመጫን ወሰነ። ቢሆንም እሱ ጌታውን በቅንነት ስላገለገለ፣ በየቀኑ ሸክሙ እየከበደ የሄደበት፣ ዋርዴ ግን ልግመኛ ስለሆነ ከሸክም ነፃ የወጣበት ብቻ ሳይሆን እሱ ‘ቡሌ’ ተሸክሞ ያመጣውን እንዲበላ የተወሰነበት ምክንያት ሊገባው አልቻለም።

አንድ ቀን ተጭኖ ውሎ ሲራገፍ እንደ ልማዱ አመዱ ላይ ተንክባለለና ትንሽ አረፍ ብሎ ጀርባውን ካበረደ በኋላ፣ ግጦሽ ፍለጋ በሄደበት፣ አንድ የእድሜ አዚም የከበደው አረጋዊ አህያ እግሮቹን ሰተት አድርጎ ዘርግቶ ፀሐይ ሲሞቅ በሩቁ ስላየ ወደርሱ ሄዶ በታላቅ ትህትና ሰላምታ ሰጠው።

አረጋዊውም እንደ ምንም ብሎ ራሱን ቀና አድርጎ፣

“እንዴት ዋልህ ወዳጄ ምን ትሻለህ?” አለው።

“አባቴ ‘ነገር ላመመው ልብ ጠበሉ የሽማግሌ ምክር ነው’ የሚባለውን የጋፋቶቻችነን ተረት በመከተል ልቤ በነገር ስለታመመ ምክርዎን ፈልጌ ነው የመጣሁ“ አለ ቡሌ።

“አንተም ሽማግሌ ትመስላለህ! ታድያ አንተ የማታውቅው ምን ምክር እሰጥሃለሁ። የዛሬ ዘመን አህዮች፣ እንኩዋንስ ባንተ እድሜ፣ ግልገሎችም ቢሆኑ ‘እንምከራችሁ’ ይሉናል እንጂ ‘ምከሩን’ ብለውን አያውቁም” አለ ሽማግሌው።

“ኧረ መጉላላት አለ እድሜዬ ጣለኝ እንጂ ሽማግሌም አይደለሁ። ወዲያውም ምክር ስጡን ከሚሉት እንጂ ምክር እንስጥ ከሚሉት ወገን አይደለሁም” አለ ቡሌ ትህትና በተሞላ ቃል።

“ስንት አመትህ ነው?”

“ቡሌን ጅብ በበላው ማግስት ነው የተወለድኩ።”

“ማነው ቡሌ አላውቀውም።”

“የጌታዬ አህያ ነበር፤ እሱን ጅብ ስለበላው በሱ ስም ተጠራሁ። በዚያን ጊዜ ጅብ አህያውን ሁሉ ይፈጀው ነበር ይባላል።”

“አአ! የክፉ ቀን ጊዜ መሆኑ ነዋ። እንግዲያማ ሰባት አመት ያህል ይሆንሀል ማለት ነው። እውነትም ልጅ ነህ” አለ ሽማግሌው።

“ከድፍረት አይቁጠሩብኝና እርስዎስ ስንት አመት ይሆንዎታል የኔታ?“ አለ ቡሌ።

“እኔስ ሀያ አመቴ ነው።”

“አ ሀ ሀ! ብዙ ነው” አለ ቡሌ በመደነቅ።

“አዎን ክብሩ ይስፋ። ለዛሬ ዘመን ያህያ እድሜ ትንሽ አይደለም። ጓደኞቼ ሁሉ አልቀው ብቻዬን ቀርቻለሁ“

አለ አረጋዊው፣ ያለቁት ጓደኞቹ ትዝ ብለውት እየተከዘ።

“እንግዲህ ይፍቀዱልኝና የመጣሁበትን ችግሬን ልንገርዎ” አለ ቡሌ።

ሽማግሌውም መፍቀዱን ራሱን በማነቃነቅ አሳየ።

“ለጌታችን እኔና አንድ ዋርዴ የሚባል አህያ ብቻ አለነው። እኔ ከግልገልነቴ ጀምሮ፣ ያለ ተንኰልና ያለ ልግም አገለግላለሁ። ዋርዴ ግን እየተራገጠና እየተኛ አልጫንም ስላለ፣ እምልልዎታለሁ፣ ከተወለደ ጀምሮ ጀርባውን መደላድል ነክቶት አያውቅም። ስለዚህ የኔን ብቻ ሳይሆን፣ የርሱን ፈንታ ጭምር እየተጫንሁ ይኸውልዎት የርሱንም የኔንም እድሜ ኖሬ አረጀሁ። ደግሞ የሚገርመኝ፣ እኔ ተጭኜ ውዬ እንደሚያዩኝ ግጦሽ ፍለጋ በፀሐይ ስንከራተት፣ እርሱ በጥላው ውስጥ ተኝቶ ውሎ፣ እኔ ተሸክሜ ካመጣሁት ገብስም ሆነ ሽንብራ ወይም ሌላ በጨው ይበላል። እንደርሱም ልግመኛ ለመሆን ብሞክር ጌታዬ እንደ ዋርዴ አልተወኝም፤ በዱላ እየደበደበ ይጭነኛል። ስለዚህ፣ የሚያሳርፈኝ ምክር እንዲሰጡኝ ነው ወደ ርስዎ የመጣሁ።”

“ዋርዴ እንዲያው ምንም አይሰራ?“ አለ ሽማግሌው።

“ኧረ እንዲያው ባህያ ምእመናን ሁሉ እምልልዎታለሁ፤ ከማለል በቀር ምንም አይሰራ። ቅድም እንደነገርኩዎ እኔ ተጭኜ ያመጣሁትን እየበላ መልኩን አሳምሮ ሲያልል መዋል ብቻ ነው።”

“ጥፋቱ ያንተ ነው ልጄ፤ መጀመሪያውን መድሀኒት የሌለው ጥፋት አጥፍተሃል” አለ ሽማግሌው ራሱን እያወዛወዘ።

“እንዴት የኔታ?” አለ ቡሌ።

“እንዴት ማለት አስተዋይነት፤ እየው፣ መጀመሪያ ቅንነትህን ሁሉ ባንድ ላይ ማሳየት አይገባህም ነበር።”

“እኔማ በሙሉ ቅንነት ጌታዬን አገልግዬ ደስ ሳሰኘው፣ እርሱም በበኩሉ ደስ አሰኝቶ ያኖረኛል ብዬ ነበር።”

“የለም ተሳስተሃል፤ ሰዎች በጎነትህን እንዲያው ከምትሰጣቸው፣ በዋጋ ሲገዙት ከፍ ብሎ ይታያቸዋል። ሁሉንም ባንድ ላይ ከምትሰጣቸው፣ እየቆጠብህ ትንሽ በትንሽ ስትሰጣቸው ይወዳሉ። ሁሉንም ባንድ ላይ፣ በከንቱ ስትሰጣቸው ግን፣ ገንዘባቸው ያደርጉትን እንደገና ልቀንስ ብትል ያው ያየህው ዱላ ነው ትርፉ።”

“ታዲያ አሁን ምን ይሻለኛል?”

“ዝም ብለህ መጫን።”

“ዝም ብዬ ለመጫንማ ምን ምክር ያስፈልጋል የኔታ!”

“ምክር ዱሮ ቀረ ልጄ።”

“እና እንግዲህ የሚያሳርፈኝ ነገር የለም ማለት ነው?” አለ ቡሌ ተስፋ ቆርጦ።

“የሚያሳርፍህ አንድ ነገር ብቻ ነው” አለ ሽማግሌው።

“ምን?”

“ሞት።”

“ወዴት አገኘዋለሁ?”

“ግድ የለም እርሱ ፈልጎ ይመጣልሃል።”

“ኧረ ታገኘሁትስ እኔ በፈለግሁት።”

“አታገኘውም፤ በጣም ሰራተኛ ነው። በአለም ሁሉ ብቻውን የሚሰራ ስለሆነ፣ እዚህ ውሎ፣ እዚህ አደረ አይባልም።”

“ምናልባት ባጋጣሚ ባገኘው እንዴት ያለ ነው?”

“ስሙን ካልሆነ መልኩን የሚያውቀው የለም። ጠላት እየፈራ፣ መልኩን ያለዋውጣል ይባላል።”

“እርስዎ እንደሚሉት ከችግር የሚያሳርፍ ከሆነ ምን ጠላት ኑሮት ይፈራል። ግድ የለም፤ የሚያሳርፈኝ ከሆነ አላጣውም እፈልገዋለሁ” ብሎ ቡሌ ከሽማግሌው ተሰናብቶ ሞትን ፍለጋ ሄደ።

ያኑ እለት ሌሊት፣ ባንድ በኩል ጌታው ሲፈልገው፣ ቡሌ ጫካ ለጫካ ሞቱን ፍለጋ በሄደበት ጅብ አገኘው። ቡሌ ግን፣ አውጪኝ ነፍሴን ጋልቦ ወደ መንደር ተጠጋና አመለጠ።

በበነጋው ወደ ሽማግሌው አህያ ሄዶ፣

“የኔታ ያን ትናንት የነገሩኝን ሞት የሚባለውን ከንቱ ሳላገኘው፣ እርሱን ፍለጋ ጫካ ለጫካ ስነሁዋለል፣ ጅብ ሊበላኝ እንደ ምንም ሮጨ ለጥቂት አመለጥሁ” አለ።

ሽማግሌውም ሳቀና፣

“ሞትን ከፈለግህ ለምን ሮጥህ?” አለው።

“እንዳይበላኝ ነዋ የኔታ፤ ሞትን ፈለግሁ እንጂ ጅብ አልፈለግሁ!”።

“ምነው ትናንት ነግሬህ ‘ሞት በጅብ፣ በበሽታ፣ በረሀብ ወይም በሌላ ነገር ተመስሎ ይመጣል እንጂ፣ በራሱ መልክ ተገልጾ ታይቶ አያውቅም’ አላልሁህም ነበር?“

“እርስዎስ ብለውኝ ነበር። ብቻ ትናንት ያገኘሁት ጅብ ያው እውነተኛው ጅብ ነው እንጂ፣ በጅብ የተመሰለ ሞት አልነበረም። ይመኑኝ የኔታ!“ አለ ቡሌ።

.

ሀዲስ አለማየሁ

.

[ምንጭ] – “ተረት ተረት የመሠረት”። 1948 ዓ.ም። ገጽ 19-26።

3 thoughts on ““ቡሌ እና ዋርዴ” (ወግ)

  1. ይሄንን ወግ አንብቤ ትዝ ያለኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ አህዮች እና ሌሎች የቤት እንስሳት የሚደርስባቸው ጭካኔ የተሞላበት አስተዳደር ነው። መደብደብ፣ ማስራብ፣ ከመጠን በላይ ማሰራትና የመሳሰሉትን። Ethiopia needs animal rights advocate and the law should back them. Perhaps modernizing the traditional farming practice and improving goods transportation would ease the load from the animals.

    Liked by 1 person

አስተያየት ለመስጠት