“የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያናት” (ታሪክ)

“የላሊበላ ውቅር ቤተ ክርስቲያናት”

.

(ሕይወት ከተማ)

.

.

ላሊበላን ሄደው ሲጎበኙ የተለያዩ ስሜቶች ይፈራረቃሉ። የመጀመሪያ ጊዜ ከሆነ “እንዴት እስከዛሬ ሳላየው ቀረሁ?” የሚል የቁጭት ስሜት፣ ከዚህ በፊት አይተውት ከሆነ ደግሞ “እንዴትስ ድጋሚ እያየሁት እንደ አዲስ ያስደንቀኛል?!” የሚል የመደመም ስሜት። እኔም በየተራ ሁለቱ ስሜቶች በተለያየ ጊዜ ተሰምተውኛል።

በአሁኑ ጊዜ ላሊበላ የሚጎበኘው እንደድሮው በከብት ጀርባ ተጭኖ፣ ሲመሽም ባስጠጋ ጎጆ ታድሮ፣ ወራትንም ፈጅቶ አይደለም። አውሮፕላኑ ከአዲስ አበባ አንስቶ ሰአት ሳይሞላ ላስታ አንከብክቦ ያደርሳል። ባለታክሲውም በግማሽ ሰዓት ወደ ቱሪስት መናኸሪያዋ ላሊበላ ከተማ ገስግሶ ያወርዳል። ሆቴሎችም እንደአሸን ናቸው። ‘ቤተክርስቲያኖቹ በየት ናቸው’ ተብሎ ቢጠየቅም ከሕጻን እስከ አዋቂ መንገድ ያሳያል።

ከከተማው እምብርት በስተምዕራብ ዳገቱን ወጥተው ሲጨርሱ የዩኔስኮ ድንኳን በሩቁ ይታያል። ድንኳኑ ባይኖር ቤተ ክርስቲያኖቹን በሩቅ መለየት የሚከብድ ይመስለኛል። አንዴ ግን አጠገቡ ከደረሱ በኋላ የሚታየው የቤተክርስቲያናቱ ግዙፍነትና የራሳችን ትንሽነት ብቻ ነው።

ላሊበላ በዓለማችን ካሉት አስደናቂና አስደማሚ ክስተቶች መካከል ይሰለፋል ብል ማጋነን አይመስለኝም። በዓይን ካላዩት ግን የማስደነቁን ጥልቀት መረዳት የሚቻል አይመስለኝም።

ቤተ ገብርኤል (ላሊበላ)

ላሊበላን ስንጎበኝ በአእምሮዋችን የሚመላለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናት እንዴት ተሠሩ? መቼ ተሠሩ? በማን ተሠሩ? ለምንስ ተሠሩ? በዚህም ጽሑፍ ስለነዚህ ጉዳዮች ያሉን የጽሑፍ መረጃዎች ምን እንደሚሉ መርምሬ በአጭሩ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ።

.

አንዳንድ ምስክሮች

.

ስለ ላሊበላ ብዙ ተብሏል፤ ተጽፏልም። በሀገራችን ደራሲዎች ቢያንስ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የንጉሡ ላሊበላን ገድል፣ እንዲሁም ባለፉት ምዕተ ዓመታት ስለ ንጉሡ አዳዲስ አፈ ታሪኮች እና ጥናቶች እንደገና ተከልሰው ቀርበዋል። በውጭ ጸሐፊዎችም በተለይ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን  ጀምሮ እስካሁን የአጥኚዎችና የደራሲዎችን ቀልብ እንደሳበ ነው። በዛ ያሉ የውጭ ሃገር መጻሕፍትም በላሊበላ ዙርያ ለኅትመት በቅተዋል።

አጼ ላሊበላ የነገሠውና እነዚህን አስደናቂ ሕንጻዎችም የተሰሩት ከስምንት መቶ አመታት በፊት በ1200ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ ይነገራል። የላሊበላ ገድል እንደሚገልጸው ንጉሡ ሁለተኛዋን እየሩሳሌም በላስታ ለማስገንባት እንዳለመና ቤተክርስቲያኖቹም ማሰራት እንደጀመረ ነው።

Lalibela ms
የ15ኛው ክ/ዘመን “ገድለ ላሊበላ” (British Library Or 719፣ ቅጠል 169)

ስለ ሕንጻዎቹ ታሪክ የሚያወጋው የመጀመሪያው ጽሑፍ መረጃ በ15ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በተጻፈው “ገድለ ላሊበላ” ነው። ይህም ገድል ከአፄ ላሊበላ ሞት ሁለት መቶ አመታት በኋላ እንደተጻፈ ሲገመት የገድሉም ጸሐፊ የላሊበላን ቤተክርስቲያናት ሲያደንቅ እንዲህ ይላል፣

“ወዳጆቼ ሆይ! ተመልከቱ እንጂ። ይህ ሰው በእጆቹ የተገለጹለት እነዚህ ግንቦች በየትም በሌሎች ሀገሮች አልተሰሩም። ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሠራር በምን ቃል ልንነገራችሁ እንችላለን? የቅጽራቸውንም ሥራ እንኳ መናገር አንችልም። የውስጡንስ ተዉት ታይቶ አይጠገብም፣ አድንቆና አወድሶም ለመጨረስ አይቻልም። በላሊበላ እጅ የተሠራ ይህ ድንቅ ሥራ በሥጋዊ ሰው የሚቻል አይደለም። በሰማይን ከዋክብት መቁጠርን የቻለ፣ በላሊበላ እጅ የተሰራውን መናገር ይችላል። እናም ለማየት የሚፈልግ ካለ ይመልከት። በላሊበላ እጅ የተሠሩትን የአብያተ ክርስቲያኖቹን ሕንጻዎች ይምጣና በዓይኖቹ ይመልከት!”

(ርእዩኬ ኦ ፍቁራንየ ዘከመዝ ብእሴ ዘበእዴሁ ተከሥታ እሎን ህንጻ ማኀፈድ ዘኢተገብረ ዘከማሆን በኀበ ካልኣን በሓውርት። በአይ ልሳን ንክል ነጊረ ግብረቶን ለእሎን አብያተ ክርስቲያናት። ወግብረተ ቅጽሮንሂ ኢንክል ነጊረ ኅድጉሰ ዘእንተ ውስጦን ዘርእየሂ ኢይጽግብ በነጽሮ ወበአንክሮኒ ኢይክል ፈጽሞ። እስመ መንክር ተገብረ በላዕለ እደ ላሊበላ ዘኢይትከሀሎ ለሥጋዊ ከመ ይኈልቆሙ ለከዋክብተ ሰማይ ይኆልቆሙ ለመንክራትኒ ዘተገብራ በእደ ላሊበላ። ወለእመሰ ቦ ዘይፈቅድ ከመ ይርአይ ግብረ ሕንጻሆን ለአብያተ ክርስቲያናት ዘተገበረ በእደ ላሊበላ። ይምጻእ ወይርእይ በአዕይንቲሁ።)

ከአንድ መቶ አመታት ያህል በኋላም በ1520ዎቹ ፍራሲስኮ አልቫሬዝ የተሰኘ ካህን ከፖርቱጋል መልእክት ለማድረስ መጥቶ ለስድስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ ነበር። በዚህም ወቅት የላሊበላን ውቅር ቤተክርስቲያናት ለመጎብኘት እድል አግኝቶ እያንዳንዱን ሕንጻ ከገለጸ በኋላ በመደነቅ እንዲህ ብሏል፣

“ስለነዚህ ሕንጻዎች ከዚህ በላይ መጻፍ አልችልም። ምክንያቱም ከዚህ በላይ ብጽፍ የሚያምኑኝ አይመስለኝም። እስካሁን የጻፍኩትንም እውነት አይደለም ይሉኛል ብዬ እፈራለሁ። እኔ ግን በኀያሉ እግዚአብሔር እምላለሁ የጻፍኩት ሁሉ እውነት ነው! እውነታው እንዲያውም ከዚህም ከጻፍኩት እጅግ የበለጠ ነው። ውሸታም እንዳይሉኝ ግን ትቼዋለሁ።”

ቤተ መድኀኔ ዓለም (ላሊበላ)

ይህንንም አድናቆቱን በ1532 ዓ.ም በመጽሐፍ መልክ አሳትሞት የውጪው ዓለም ላሊበላን እንዲያውቅ አድርጓል። ስለ ላሊበላ ሕንጻዎች በጽሑፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመግለጽ የሞከረው የውጭ ሐገር ተጓዥ አልቫሬዝ ነበር። የአልቫሬዝ ገለጻ ምናልባትም ላሊበላ ከኢማም አሕመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ አሕመድ) ዘመን በፊት ምን ይመስል እንደነበር በመጠኑ ይገልጽልናል።

አልቫሬዝ ላሊበላን ከጎበኘ ከ10 አመታት በኋላ ኢማም አሕመድ በላሊበላ አካባቢ ሰፍሮ እንደነበረ ይነገራል። ኢማም አሕመድ ንዋየ ቅድሳቱንና ንብረቶቹን ከመውሰድ ውጭ እንደሌሎቹ ቤተክርስቲያናት ላሊበላን ለማቃጠል እና ለማውደም እንዳልሞከረ አንዳንድ ምንጮች ይጠቁማሉ። በቤተ ክርስቲያናቱ አሰራር ኢማም አሕመድም ተደምሞ የነበረ ይመስላል።

በድጋሚ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ከመጡ ጎብኚዎች ጀምሮም ብዙዎች ለላሊበላ አድናቆታቸውን በተለያየ ጊዜ ጽፈዋል። ነገር ግን በአፄ ላሊበላ ዘመን የነበሩ ምስክሮች የጻፉት ታሪክም ሆነ ስለ አሰራሩ የሚነግሩን መረጃዎች እጅግ ጥቂት ናቸው። በመሆኑም የተለያዩ አጥኚዎች ምሁራዊ መላምታቸውን በየጊዜው ሲሰጡን ከርመዋል።

.

 የላሊበላ ቤተክርስቲያናት እንዴት ተሰሩ?

.

በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ክፍል ከተሰሩት ውቅር ሕንጻዎች አንዳንዶቹ ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ከተበጁ ዋሻዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ከዋሻውም በመነሳት የተለመደውን የሕንጻ አሰራር አስመስሎ ድንጋዩን በመፈልፈል የሚሰሩ ናቸው። አንዳንዶቹ ግን አንድ ሙሉ ትልቅ ቋጥኝ ድንጋይን በመፈልፈል ከመሬት በታች ወይም ከተራራ በጎን በኩል ተፈልፍለው ይሰራሉ።

የላሊበላ ቤተክርስቲያናት ከመሬት በታች ወይም ጎን ተፈልፍለው ከሚሰሩት አይነቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው። ይህም የሚሰራው እንደተለመደው የሕንጻ አሰራር ከመሰረቱ ተጀምሮ ወደላይ የሚቆለል ሳይሆን ከጣራው ተነስቶ ወደ ታች የሚፈለፈል ነው። ይህም አይነት አሰራር ከሕንጻ ስራ ይልቅ ቅርጻ ቅርጽ ከመቅረጽ ጋር ይነጻጸራል። የቅርጻቅርጽ አሰራርን ዝነኛው የመሀከለኛው ዘመን ቀራጭ ሚኻኤል አንጀሎ ሲገልጸው “እያንዳንዱ ድፍን ድንጋይ ውስጥ ቅርጽ አለ … የቀራጩም ስራ ይህንን ቅርጽ ከታፈነበት ድንጋይ ነጻ ማውጣት ነው” በማለት ነበር።

የ15ኛው ክፍለ ዘመን የገድለ ላሊበላ ደራሲም በተመሳሳይ መልኩ የላሊበላ ቤተ ክርስቲያናትን ቅርጽ አሰራር ሲገልጽ እንዲህ ይላል፣

“በላሊበላ እጅ እኒህ አብያተ ክርስቲያናት ከምድር ልብ ወጥተው የሚሠሩበት ጊዜ ደረሰ … ምድርን ከፈጠረ ጀምሮ ተሠውሮ የነበረውን ሕንጻ እንዲገልጥ እግዚአብሔር ወዷልና።”

ቤተ ጊዮርጊስ በወፍ በረር ቅኝት (ላሊበላ)

.

ወደ ቤተክርስቲያናቱ አሰራር ስንሄድ፣ የላሊበላ ገድል በድጋሚ እንዲህ ይላል፣

“ገብረ መስቀልም (ላሊበላ) ልዩ ልዩ የሆኑ የብረት መሣሪያዎችን አሠራ። ለመጥረብም የተሠራ አለ። ለመፈንቀልም የተበጀ ብረት አለ። ለመፈልፈልም የተሠራ አለ። እነዚህን ቋጥኝ ድንጊያ የመቅደስ ሕንጻ የሚፈጸምባቸውን አሠራ። ገብረ መስቀልም ከዚያን ጊዜ ወዲህ ምድራዊ ሐሳብን፣ ሚስቱንም ደስ ለማሰኘት ፈቃድ ቢሆንም አላሰበም። ሁሉንም በሙሉ መንፈስ ስለ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አሰበ እንጂ።”

የላሊበላ ገድል እንደሚያሳየው ሕንፃዎቹ በተለያዩ የእጅ መሳሪያዎች (የብረት መጥረቢያ፣ መፈንቀያ፣ መፈልፈያ) እንደተሰሩ ይገልጻል። አጼ ላሊበላም እራሱ ሥራውን ይከታተል እንደነበረ ይናገራል።

በሀገራችን የድንጋይ ፍልፍል ሕንጻዎች ታሪክ ላሊበላ የመጀመሪያው አይደለም። በተለይም በትግራይ አካባቢ ከላሊበላ በፊት የተሠሩ በርካታ ውቅር ቤተክርስቲያኖች ይገኛሉ። ታዲያ ላሊበላን ከሌሎቹ የሚለየው ምንድን ነው? የላሊበላ ውቅር ቤተክርስቲያናት በተለይ የሚታወቁት በአንድ አካባቢ እና ተቀራራቢ ጊዜ ከአስር የሚበልጡ ፍልፍል ሕንጻዎች በመሠራታቸው ነው። እንዲሁም ደግሞ ከሌሎቹ በተለየ ጥበብ የፈሰሰባቸው ስለሆነ ነው … የአሰራሩ ጥራት፣ የሕንጻዎቹ ግዝፈት፣ እንዲሁም የጌጥ አወጣጣቸው ብስለት ነው። ከቀራጮቹ ችሎታም በተጨማሪ ይህንን ማድረግ የቻሉት የላስታ አካባቢ ድንጋይ ለሥራው ተባብሯቸው ይመስላል።

ተራራው እና ውቅር ህንጻው (ቤተ ሊባኖስ፣ ላሊበላ)

 

ሁለቱን የድንጋዮቹን አይነት አጥንቶ የነበረው የሥነ ቅርስ ተማራማሪው David Phillipson እንዲህ ይላል፦

“በላስታ አካባቢ የተሰሩት ውቅር ቤተክርስትያናት በትግራይ ከተሰሩት ጓደኞቻቸው እጅግ ይለያሉ። በትግራይ የሚሰሩት hard sandstone ከተባለ በአካባቢው የሚገኝ ድንጋይ ሲሆን በላስታ የሚገኘው ድንጋይ ደግሞ ለስለስ የሚል volcanic tuff ነው። በትግራይ የሚገኘው ድንጋይ ለመቅረጽ ትንሽ ጠንከር ያለ ስለሆነ ብዙ ጌጦችን ለማውጣት እንዲሁም መስኮቶችን በትክክል ለማውጣት ስለማይመች፣ መስኮቶቹን በእንጨት ለመስራት ይገደዳሉ። በላስታ የሚገኘው የድንጋይ አይነት ግን ለስላሳና ለመቅረጽ የሚመች በመሆኑ ለተለያዩ ጌጦችና ቅርጾች የተመቸ ነበር። በአንጻሩ በትግራይ ያሉት ውቅር ቤተክርስቲያናት በድንጋያቸው ጥንካሬ የተነሳ ቅርጻቸውን በሚገባ ጠብቀው ለመቆየት ሲችሉ፣ በላስታ የሚገኙት ግን በውጭው አየር ዝናብና ንፋስ ለመበላሸት የተጋለጡ ናቸው።”

የአቀራረጹ ጥበብ (ቤተ መድኀኔ ዓለም፣ ላሊበላ)

.

የላሊበላ ቤተክርስቲያናት ለምን ከአንድ ድንጋይ ተወቅረው ተሠሩ?

.

አንድ ሕንጻን ከድንጋይ ፈልፍሎ ማውጣት እጅግ ከባድ ስራ እንደሆነ ግልጽ ነው። እንኳንስ አስር ትላልቅ ቤተክርስቲያናት ይቅርና አንድን ሙቀጫ ከድንጋይ ፈልፍሎ ማውጣት ምን ያህል እንደሚከብድ የሞከረው ያውቀዋል። ታዲያ አባቶቻችን ይህንን እልህ አስጨራሽ ሥራ ለመስራት ምን አነሳሳቸው ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ስለምን ከመሬት በታች? ስለምን ከአንድ ድንጋይ? ሕንጻ በድንጋይ አነባብሮ መገንባት አይቀልም ነበር?

አንድም ሕንጻዎቹን ዘላለማዊ ለማድረግ መፈለግ ይመስለኛል። ይህም በመጠኑ የተሳካ ይመስላል። ከብዙ መቶ አመታት በኋላ እኛም የእጅ ስራቸውን ለማድነቅ እነሱም የኛን ዘመን ሰው ለማስደመም በቅተዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አስደናቂ ነገር በመስራት ለአምላካቸው ክብር፣ ታላቅነትን ለማሳየት ሊሆን ይችላል። ሰዎች እምነታቸውን ለአምላካቸው ለማሳየት የማይቻለውን አድርገው፣ የማይሞከረውን ሞክረው ይሰራሉ። ይህም አንድም ለቀጣዩ አለም ክብርን ለመሰብሰብ አንድም ደግሞ ለራሳቸው ውስጣዊ ደስታ እና ለአምላካቸው ክብር የሚያደርጉት ነው። ላሊበላና የጊዜው የሕንጻ ጥበበኞች እምነታቸው ጠንካራ መንፈሳቸው ገራራ እንደሆነ ከስራቸው ለማየት እንችላለን።

አንድም ደግሞ ከመሬት በታች ቤተክርስቲያኖችን መስራት ከጠላት እይታ ለመሸሸግ ሊሆን ይችላል። ከመሬት በላይ ከተሰራ ማንኛውም ህንጻ ይልቅ ከመሬት በታች የሆነውን ጦረኛ ቢመጣ በቀላሉ እንደማያገኘው አስበው ይሆን? በጊዜው ጦርነቶች የተፋፋሙበት ዘመን እንደመሆኑ፣ ቤተክርስቲያናቱን ከእይታ ውጪ የማድረግን አስፈላጊነት አስበው እንደሆነ እገምታለሁ።

.

የላሊበላ ቤተክርስቲያናት በማን ተሰሩ?

.

እስከዛሬ የላሊበላን ውቅር ቤተክርስቲያናት ማን እንደሰራቸው በመገመት በተለያዩ ጊዜያት ብዙ መላምቶች ተሰጥተዋል። እስቲ ያለንን የጽሑፍ መረጃ ከኋላ ወደፊት እንይ።

“ገድለ ላሊበላ” በንጉሥ ላሊበላ አዛዥነት በሀገሬው ሰዎች እና በአማልክት እገዛ እንደተሰራ ይነግረናል፤

“ሕዝቡን ሁሉ ወደ እርሱ እንዲሰበሰቡ አዘዛቸው። በተሰበሰቡም ጊዜ በአብያተ ክርስቲያናቱ ሕንጻ ሥራ የምትረዱኝ ሁላችሁም የምትቀበሉትን ደሞዛችሁን ተናገሩ አላቸው፣ እግዚአብሔር እንድሠራ አዞኛልና። እናንተም በአንደበታችሁ ደመወዛችሁን እንዴት እንደምትቀበሉ ተናገሩ። በጠራቢነትም ሥራ የሚረዳ፣ ጥራቢውንም በማውጣት የሚረዳ ሁላችሁም በአንደበታችሁ ተናገሩ። እንደ አላችሁኝ እሰጣችኋለሁና። ያለ ፈቃዳችን አስገደደን እንዳትሉኝ። በአጉረመረማችሁ ጊዜ ድካማችሁ ብላሽ እንዳይሆን።

“ሁላቸውም ልባቸው እንዳሳሰባቸው ነገሩት። እሱም ስጦታቸውን ሳያጓድል እንዳሉት ሰጣቸው። የአብያተ ክርስቲያናቱን ሕንጻ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስከ ፈጸመ ድረስ ለሚፈለፍልም ሆነ ለሚጠርብ የቤተ ክርስቲያኑን ጥራቢ ለሚያወጣም ሆነ  ደሞዛቸውን በጊዜው ይሠጣቸው ነበር።”

.

Lalibela dawent
አፄ ላሊበላ በ16ኛ ክ/ዘመን ሰአሊ እይታ (ዳውንት የድባ ማርያም ቤተ/ክ፣ ወሎ)

በ16ኛው ክፍለ ዘመን ጊዜ ወደ ላሊበላ ተጉዞ ስለ ቤተክርስቲያኖቹ ጽፎ የነበረው አልቫሬዝ እንዲህ ይላል፤

“የእነዚህ ቤተክርስቲያኖች ሥራ ሃያ አራት አመታት ፈጅቷል ይህም ተጽፎ ይገኛል ብለው ነግረውኛል እናም የተሰራው በግብጾች እንደሆነም። ግብጾች ማለታቸውም ነጮች ማለታቸው ነው። ኢትዮጵያዊ ወሬ ነጋሪዎቼ ራሳቸው ይህንን አስደናቂ የጥበብ ስራ በዚህ ጥራት መስራት እንደማይችሉ ጠንቅቀው ያውቁታል።”

ምናልባትም አልቫሬዝ አንድ አፍሪካዊ ሕዝብ ይህንን መስራት ችሏል ብሎ ማመን የፈለገ አይመስልም። እንኳንና እሱ፣ የሀገራችንም ሰዎች በጊዜው ማመን ስላቃታቸው የጥበቡን ባለቤትነት ለግብጾች ያስታቀፏቸው ይመስላል።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የመጡት ተጓዦች (Gehrard Rohlfs፣ Raffray እና Simon) ሥራው ሙሉ ለሙሉ በውጭ ሀገር ሰዎች እንደተሰራ ማመናቸውን ጽፈዋል። የሀገሬው ሰው በምንም መንገድ ይህንን አይነት ሥራ መሥራት የሚችል ጥበብ እንዳላካበተ አምነው ተቀብለዋል።

IMG_3015
አፄ ላሊበላ በ15ኛ ክ/ዘመን ሰአሊ እይታ (IES Icon 4053)

አልቫሬዝ ‘ሀያ አራት አመታት ፈጅቷል ይህም ተጽፎ ይገኛል’ ብሎ የገለጸልን ጽሑፍ እስካሁን አልተገኘም። ምናልባትም በዘመን ሂደት ከጠፉት ብራናዎች መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል።

ይሁን እንጂ ከአልቫሬዝ ጽሑፍ 400 አመታት በኋላ በ1951 ዓ. ም ተጽፎ የታተመው “ዜና ላል ይበላል” የተባለው መጽሐፍ የተለያዩ የጽሑፍ መረጃዎችና አፈ ታሪኮችን ሲጠቅስ ፍንጭ ይሰጣል። ደራሲው ደጃዝማች ብርሃነመስቀል ደስታ የተጠቀሙት የጽሑፍ መረጃዎች ግን እስካሁን ስላልተገኙ ስለ መረጃው እውነትነት ማረጋገጫ አላገኘንም። መጽሐፉ የላሊበላ ሕንጻዎች በማን እንደተሰሩ ሲገልጽ እንዲህ ይላል፣

“[ላልይበላ] በነገሠ በ10 አመቱ መራ ከተባለው አጠገብ የነበረውን ቤተ መንግሥት ወደ ሌላ ለማዛወር አስቦ ቀይት ከተባለችው ባላባት ከሚዳቋ ገደል በላይ ከመካልት በመለስ ከጉሮ በታች ከገጠርጌ አፋፍ በላይ ያለውን ቦታ በአርባ ጊደር ገዝቶ ቤተ መንግሥቱን መካነ ልዕልት ብሎ እሰየመው ቦታ ላይ ሠራና በዚያው አቅራቢያ ታላላቅ ቋጥኝ ደንጊያዎች መኖራቸውን ስላረጋገጠ በግዛቱ የሚገኙትን ዜጋዎቹን አዞ ሕንጻ ቤት ክርስቲያኖቹን ማነጽ ጀመረ።

የሥራው መሪ ምንም ራሱ ቢሆን በዘመኑ የነበሩ ዜጎቹ ሁሉ ጥበብ ተገልጾላቸው በፈቃደ እግዚአብሔር እየተረዱ ሥራውን እያፋጠኑ ይሠሩ ነበር። እርሱም የሥራ መሪነቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ሕዝቡ ሁሉ በጉልበቱ ይሰራ ስለነበር … ጥንታዊው ጽሑፍ ሥራው 23 አመት እንደፈጀበት ሲናገር የቦታውም ስም ለተወለደበት ስፍራ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሮሐ አለው ይላል።”

ይህም ጽሑፍ ሥራው ስለፈጀው ጊዜ አልቫሬዝ ከጻፈው ጋር ተቀራራቢ የጊዜ መስፈሪያ ተጠቅሟል። ስለ መሬቱ ስሪትም ሌላ ቦታ ያልተገኙ መረጃዎችን አካቷል።  ነገር ግን ደጃዝማች ብርሃነመስቀል ይህንን መረጃ ከየት እንዳገኙት የሚገልጽ ነገር የለም። “ጥንታዊው ጽሑፍ” ብለው የጠቀሱትም በየት እንዳለ እስካሁን አይታወቅም።

Lalibela 12th
ላሊበላ ያሠራው መንበረ ታቦት (ቤተ መድኀኔ ዓለም፣ ላሊበላ)

 

በሌላ በኩል በ1960ዎቹ አባ ገብረመስቀል ተስፋዬ የተሰኙ የላስታ ገነተ ማሪያም ቤተ ክርስቲያን አለቃ ከዋሻ አግኝቼ ተርጉሜዋለሁ ብለው ‘ዜና ላሊበላ’ የተባለ ጽሑፍ ለቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ አቅርበው ነበር። ኦሪጅናሌው ግዕዝ ጽሑፍ እስካሁን ባለመገኘቱ ትክክለኛ መረጃነቱን ማረጋገጥ ባይቻልም አባ ገብረመስቀል ያቀረቡት የአማርኛ ዜና መዋዕል እንዲህ ይላል፤

“ከመንግስቱ ሕዝብ መካከል የሕንጻ ሥራ የሚችሉትን ጠበብት መረጠ አንድ መቶ ጠበብት አገኘ። ሕንጻውንም ለማነጽ መሳሪያ፣ የአፈሩ መዛቂያ አካፋ፣ መጥረቢያ፣ መዶሻ፣ መቆርቆሪያ፣ የሕንጻው ማለስለሻ ምሳር መሮ ተርዳ፣ መሰላል ሠረገላ ከብረታ ብረት አሰራ አዘጋጀ። የአስሩን ቤተመቅደስ ሥራ ወርዱን ቁመቱን ጐኑን ወለሉን ለክቶ ሥራውን ጀመረ። በመጀመሪያ ቅጽሩን ለየ ከዚህ ቀጥሎ መስኮቱን ደጃፉን ለየ …”

እስከ 1950ዎቹ ድረስ በውጭው አለም እንዲሁም በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን የላሊበላ ሕንጻዎች በውጭ ሃገር ሰዎች የመሰራቱ ታሪክ ለረጅም ጊዜ ታምኖ ቆይቶ ነበር። ነገር ግን ሀገር ውስጥ የተገኙት ጽሑፎች በሀገሬው እንደተሰሩ ደጋግመው ይናገራሉ። የውጭ ሀገር አጥኚዎችም በ1960ዎቹ ከብዙ ጥናት በኋላ በሀገር በቀል ጥበበኞች ሊሰሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህም ከላሊበላ በፊት የተሰሩ እንደሆነ የሚታመኑ ከአንድ ድንጋይ የተፈለፈሉ ውቅር ቤተክርስቲያኖች በላስታ አካባቢ እንዲሁም በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች (ለምሳሌ ገርአልታ) በመገኘታቸው ነው። ይህ የውቅር ሕንጻ ጥበብ ለብዙ መቶ አመታት ከላሊበላ በፊት ሲሰራበት የኖረ በመሆኑ፣ ጥበቡ ከየትም ሳይሆን አገር በቀል ለመሆኑ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የላሊበላ ሕንጻዎችን በቅርበት ስናያቸው ብዙ የሥነሕንጻ ባህሪዮቹ ከአክሱም ጀምሮ ሲጠቀሙበት እንደነበረ፣ እያንዳንዱ የህንጻውን ክፍሎች፣ ከጌጥ አወጣጥና የክፍሎች አወቃቀርን ጨምሮ ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራባቸው የኖረ ጥበብ እንደሆነ እናያለን። ቀድሞ ከነበሩት የሕንጻ ስራ ጥበቦች በተጨማሪ አንዳንድ አዳዲስ ጥበቦች በላሊበላ ስለሚታዩ ምናልባትም አንዳንድ የውጭ ሃገር ሰዎች በስራው ተሳታፊ ሆነው ሊሆኑ እንደሚችሉ መላምቱን ክፍት እተወዋለሁ።

.

.

ላሊበላ በአለማችን ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው ከተሰሩት ህንጻዎች የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አይደለም። በግብጽ ምድር ከላሊበላ ሕንጻዎች ሶስት ሺህ አመታት በፊት ንግሥት ሐትሸፕሱት ታላቅ ተራራ አስፈልፍላ ቤተ መቃበሯን አሰርታ ነበር። ከሷም በኋላ ብዙ ኀያላን ለራሳቸውም ሆነ ለሚያምኑበት ታላቅ አምላክ ተራራ ገምሰው ቋጥኝ ደርምሰው ሕንጻዎችን አሰርተዋል።

የንግሥት ሐትሸፕሱት ቤተ መቃብር (Dar el-Bahri, Egypt)

ለምሳሌ በህንድ አገር የሚገኘውን ከአለማችን ትልቁን ውቅር የቡድሂስት ቤተ መቅደስ (Khailasa Temple) እንዲሁም በሀገረ ጆርዳን የሚገኘውን ካዝነህ ቤተ መቅደስን (AlKhazneh Temple) መጥቀስ ይቻላል።

ካይላሳ ቤተ መቅደስ (Ellora, India)

.

ካዝነህ ቤተ መቅደስ (Petra, Jordan)

.

በኢትዮጵያም ከአክሱም ጊዜ ጀምሮ ህንጻዎችን ከአንድ ድንጋይ ፈልፍሎ መስራት የተለመደ ጥበብ ነበር። ላሊበላ ግን አስደናቂ የጥበብ እመርታ አሳይቶናል። በውቅር ሕንጻ ሥራ ጥበብ ብዙ እርምጃዎች ወደፊት መራመድ እንደሚቻል ያሳየበት ምርጥ የጥበብ ሥራ ነው።

ቤተ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን (ላሊበላ)

የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ጥናት እንዳደረገው፣ በኢትዮጵያ የውቅር ቤተክርስቲያናት ሥራ አሁንም አልቆመም። ባለፉት አስርት አመታት ሰዎች እንደ አቅማቸው አሁንም መሮ እና ዶማ ይዘው ተራራ እየፈለፈሉ ቤተክርስቲያኖች በመስራት የእምነታቸውን ጥንካሬ ለማሳየት ይጥራሉ። እነዚህ አዳዲስ ቤተ ክርስቲያናትም በቅርቡ እየተገኙ እንደሆነ ዩኒቨርሲቲው አሳውቋል።

.

ወደፊትስ ላሊበላን የሚወዳደር ውቅር ሕንጻ በአገራችን ተሰርቶ እናይ ይሆን?

.

.

ሕይወት ከተማ

(መጋቢት 2011 ዓ.ም)

.

ለበለጠ መረጃ

.

ደጃዝማች ብርሃነ መስቀል ደስታ። “ዜና ላል ይበላል”። 1962 ዓ.ም።

ተከለ ጻድቅ መኩሪያ። “የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ አክሱም ዛጔ”። 1965 ዓ.ም።

 “ገድለ ላሊበላ” [ግዕዝና አማርኛ]። የተለያዩ እትሞች።

Francisco Alvarez. (1540). Narrative of a Portuguese Mission to Ethiopia.

Marilyn Heldman & Stuart Munro-Hay. (1993). African Zion: Sacred Art of Ethiopia.

David Phillipson. (2009). Ancient Churches of Ethiopia.

Sergew Hable Selassie. (1972). Ancient and Medieval Ethiopian History.

Taddesse Tamrat. (1972). Church and State in Ethiopia.

 

“ሙሉቀን መለሰ” (ቃለመጠይቅ)

“ከሻይ ቤት ሀርሞኒካ እስከ ዳህላክ ባንድ”

በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር

(1973 ዓ.ም)

.

.

አንዳንድ ዘፈን አለ … ድንገት ደርሶ ድፍን አዲስ አበባን የሚያጥለቀልቅ። በየቡና ቤቱ፣ በየ መጠጥ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ በቴፕ ያሰሙታል። ካሴት ያላቸው ታክሲዎች ውስጥም ሲዘፈን ይሰማል። በመንገድ ጐረምሶች ዜማውን ያፏጩታል። ሴቶች ብቻቸውን ሆነው ልብስ እያጠቡ ወይም ወጥ እየሠሩ ለራሳቸው ይዘፍኑታል። ልጆች መንገድ ሲሄዱ ይዘፍኑታል … አልፎ አልፎ ባንድ እግራቸው ብቻ እየነጠሩ። ገና አፋቸውን የፈቱ ሕፃናትም ይኰላተፉበታል። የመንደር ሰካራሞችም ይንገዳገዱበታል። ባጭሩ፣ የከተማው ዘፈን እሱ ይሆናል።

ከጥቂት ወራት በፊት “ናኑ ናኑ ነይ፣ ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ!” እያለ ሲያስተጋባ ነበር የአዲስ አበባ ሕዝብ … ከሙሉቀን መለሰ ተቀብሎ ነበር የዘፈነው።

.

[“ናኑ ናኑ ነይ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1972 ዓ.ም።]

.

አንድ የሥራ ጓደኛዬ እድሜዋ ሶስት ዓመት ተኩል የሆነ ልጅ አለችው። አንድ ቀን፣

“አባዬ! ያቺ ኮ ስሟ ናኑ ነው” አለችው ወደ አንዲት ኰረዳ እያመለከተች።

“ኧረ?” ሲላት፣

“አዎን” አለች፤ “ብትፈልግ ትላንትና ‘ናኑ ናኑ ነይ፣ ካንቻለኝ ጉዳይ’ ስል ጊዜ መጣች!”

ጓደኛዬ ይህን ከነገረኝ በኋላ፣ “ያንን ሙሉቀንን ባወቅኩት እቺን አጫውተው ነበር” አለኝ።

Muluken 1973b

ሙሉቀን መለሰ አጠር ያለ፣ ወፈር ያለ፣ በጣም ቀይ የሆነ የሃያ ስምንት ዓመት ጐረምሳ ነው። ለሁለት ሰዓት ይህል ሲያነጋግረን እንደገመትኩት ሙሉቀን ሀሳቡን በቀጥታ የሚናገር ሰው ነው። ማለቴ፣ “እንዲህ ያልኩ እንደሆነ እንደዚህ ተብሎ ሊተረጐምብኝ ይችላል” የሚል ሥጋት የለበትም።

“ሙሉቀን ብለው ስም ያወጡልህ ለምንድነው?” አልነው።

“እህቴ ነች ያወጣችልኝ። እናቴ ‘ሙሉሰው’ ነው የምትለኝ። ከኔ በፊት አስወርዷት ነበር። ደሞ ታላላቆቼ አራቱም ሲወለዱ ምጥ ይበዛባት ነበር። እኔ ስወለድ ግን ይህ ችግር አልነበረም። ለዚህ ነው ‘ሙሉሰው’ ያለችኝ። ‘ስማቸው’ ይለኛል አባቴ። የመሬት ሙግት ነበረበት። ጠላቶች ነበሩት። እነሱን ስማቸው ማለቱ ነው።”

ሙሉቀን መለሰ በጐጃም ክፍለ ሀገር አነደድ ወረዳ ውስጥ ዳማ ኪዳነ ምሕረት በምትባል መንደር በ1946 ዓ.ም ተወለደ። አሥር ዓመት ሲሆነው እናቱ ስለሞቱ፣ አዲስ አበባ ይኖሩ የነበሩ አጐቱ እንዲማር ብለው አመጡት። ኰልፌ ሰፈር ጳውሎስ ትምህርት ቤት ገባ። ግን ብዙ አልተማረም። ያጐቱ ሚስት ይጠሉት ስለነበረ ብስጭት በዛበት።

እንግዲህ ኰልፌ አንድ የጡረታ ቤት ነበረ። ባንድ ጐኑ የልጆች ማሳደጊያ ነበረው። የሚረዱ አሉ ሲባል ሰምቶ ሙሉቀን ሄዶ ጠየቀ። ተቀበሉት።

“የበላይ አስተዳዳሪዋ ይወዱኝ ነበር። ‘ኤልቪስ’ ነበር የሚሉኝ። በሁለት ወር እንደዚህ ልብስ ይዘውልኝ ይመጡ ነበር። ውጭ አገር ልኬ አስተምርሃለሁ ብለውኝም ነበር። ይንከባከቡኝ ነበር። እወዳቸው ነበር። ውለታቸው በጣም ትዝ ይለኛል።”

እዚያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፈተ። አቶ ተፈራ አቡነ ወልድ ነበሩ አስተማሪው።

Muluken Melesse (1964) - Yemiaslekes Fikir & Hedech Alu (AE 440) 1b

ሙሉቀን ስድስት ወር ያህል እንደተማረ እህቱ ስለታመመች ወደ አገር ቤት ሄደ። ያን ጊዜ ነው አዲስ አበባ ውስጥ አክስት እንዳሉት ያወቀው። እሳቸው ይዘውት መጡና ከሳቸው ጋር መኖር ጀመረ። ቤታቸው የካ ሚካኤል ነው። እንግዲህ ሙሉቀን ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አልተመለሰም።

አክስቱ የወታደር ሚስት ናቸው፣ ጠላም ይነግዳሉ። ኑሮአቸው ጐስቋላ ነው። ልጁ አልተመቸውም።

አንድ ቀን ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄደ። ሊቀጠር። አልተቀበሉትም። ግን በእርዳታ መልክ ሻይ የማፍላት ሥራ ሰጡት።

“ምድጃዋ የኤሌክትሪክ ነበረች። ባንድ ቀን ውስጥ ሶስት ጊዜ ኮረንቲ ያዘኝ” አለ።

ስድስት ወር ያህል ከሰራ በኋላ ትቶት ወጣ። ጥቂት ወራት ተንከራተተ።

ከአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ወረድ ብሎ አንድ ሻይ ቤት ነበረ። የሻይ ቤቱ ባለቤት ሙሉቀንን ይወደዋል፤ ይረዳዋል። ሀርሞኒካ የሚጫወት ጓደኛ አለው ሙሉቀን። ሻይ ቤቱ ቁጭ ይሉና ጓደኛው ሀርሞኒካውን ይጫወታል። ሙሉቀን ይዘፍናል።

abunepetros1-620x310

አንድ ቀን ሙሉቀንና ጓደኞቹ አብረው ሲጫወቱ ያመሹና ወደ ሶስት ሰዓት ላይ አንዱን ጓደኛቸውን ለመሸኘት ይነሳሉ። ደጃች ውቤ ሰፈር ሲደርሱ የውቤ በርሀ ልዩ ልዩ ቀለማት መብራቶች በርተው ሙሉቀንን በጣም ያስደንቁታል። አንዱ ቤትማ ከሌሎቹም የበለጠ አሸብርቋል። ጓደኛሞቹ ይኸ ቤት ምንድነው ብለው ሲጠያይቁ፣ ይኸማ ‘ፈጣን ኦኬስትራ’ የሚጫወትበት ‘ፓትሪስ ሉሙምባ ናይት ክለብ’ ነው ይሏቸዋል።

ፊት ለፊቱ ካለው ሱቅ ሄደው፣

“ባለቤቱ ማነው የዚህ ናይት ክለብ?” ብለው ጠየቁ።

“ወይዘሮ አሰገደች አላምረው ናቸው” አለ ባለሱቁ።

“ሥራ ይሰጡኝ ይሆን ወይ?” ብሎ ጠየቀ ሙሉቀን።

“ፃፍና ጠይቃቸው” አለው ባለሱቁ ወረቀትና እስክሪፕቶ እየሰጠው።

እዚያው ቆሞ ደብዳቤውን ፃፈ። ጓደኛሞቹ ከፍርሃት ጋር እየታገሉ ከዚያ ከአስደናቂ ቤት ገቡ። ሙሉቀን ደብዳቤውን ለኦኬስትራው መሪ ሰጠው።

አነበበውና ሳቀበት።

“ምንድነው እሱ?” አሉ ወይዘሮ አሰገደች ከወዲያ ቁጭ ብለው።

ሰውየው ነገራቸው። ደብዳቤውን ተቀብለው አነበቡ።

“ፈትነው። ካለፈ ጥሩ … አለዚያም ሌላ ሥራ እሰጠዋለሁ” አሉ። የልጅ መልኩና ጎስቋላ ሁኔታው ሀዘኔታቸውን ቀስቅሶ ሳይሆን አይቀርም።

ያን ጊዜ ሙሉቀን እንደ ጥላሁን ገሰሰና እንደ ዓለማየሁ እሸቴ እያደረገ ይዘፍን ነበር። ባዶ እግሩንና በቁምጣ ሱሪ መድረኩ ላይ ወጣና ‘ለውነት እሞታለሁ፣ አልሳሳም ለነብሴ’ን እና ‘እንክርዳድ’ን ዘፈነ።

የናይት ክለቡ ሴቶች (በጣም ብዙ ናቸው) ዘፈኑን ወደዱለትና ያን ጊዜውኑ አንድ አራት መቶ ብር የሚሆን አዋጡለት።

“በበነጋታው ካኪ ልብስ ተገዛልኝ፤ ሱፍ ልብስ ተለካሁ። ቢትልስ ጫማ አደረኩ … እግሬን ታጥቤ!” አለ።

Muluken 1973d
ሙሉቀን በ1960ዎቹ መጀመሪያ።

እዚያው ክፍል ተሰጠው። ምግብም ከዚያው ነው። የዘፈን ሥራ ጀመረ።

ወደ ናይት ክለቡ የሚመጣው ሰው እየበዛ ሄደ። ወይዘሮ አሰገደች ሙሉቀንን ኮንትራት (ውል) አስፈረሙት። እሱ ማታ ማታ ሊዘፍን፣ እሳቸው በወር ዘጠና ብር ሊከፍሉት።

“ዘጠና ብር! ሚልየኔር የሆንኩ ነው የመሰለኝ!” አለን።

የቀድሞው አሜሪካን ቤተ መጻሕፍት አጠገብ ‘ዙላ ናይት ክለብ’ የሚባል ነበር። የዚህ የዙላ ባለቤቶች መጥተው አነጋገሩት ሙሉቀንን። በወር ሦስት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ለኛ ዝፈን አሉት። እሺ ብሎ ሄደ።

ሴትየዋ ኮንትራት አፍርሷል ብለው አሳሰሩት። ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ። አንዱ ፖሊስ እሳቸውን ለማስደሰት ብሎ ሙሉቀንን በጥፊ ሲለው ጊዜ ታዲያ በጣም ተቆጡት።

“እንድታስፈራሩልኝ ነው እንጂ እንድትጎዱት አይደለም” አሉ።

ከቤታቸው አልጋ መጣለትና ተረኛው መኰንን ክፍል ተነጥፎለት እዚያ አደረ። በነጋታው ተፈታ። ‘ዙላ ናይት ክለብ’ ገባ።

“ጋሽ ሰሎሞን ተሰማ የደረሰውን ‘የዘላለም እንቅልፍ’ እና አቡበከር አሸኬ የደረሰውን ‘ያላየነው የለም’ … ሁለቱን ዘፈን ይዤ በቴሌቪዥን ቀረብኩ።”

.

[“የዘላለም እንቅልፍ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ሰለሞን ተሰማ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

አዲስ አበባ ሙሉቀን መለሰን ሊያውቀው ጀመረ።

Muluken Melesse (1965) - Antarekm Wey & BeMistir Kiberign (PH 7-181) 1a

የፖሊስ ኦርኬስትራ አስተዋዋቂ ሻለቃ ወርቅነህ ዘለቀ (የቅጽል ስማቸው ‘ይቀጥላል’)፣

“አንድ አራት መቶ ብር እንክፈልህ፣ ና እኛጋ!” አሉት።

እሺ ብሎ ሄደ። የወር ደሞዙ ይመጣል ታድያ – አንድ መቶ ብር ብቻ!። እወጣለሁ ቢል ጊዜ፣ “ፈርመሃል!” ብለው አስፈራሩት። ልጅ ነዋ!

ሙሉቀን መለሰ ለፖሊስ ኦርኬስትራ በተቀጠረ በሦስት ቀኑ መቀሌ ከኦርኬስትራው ጋር የ “ወይዘሪት ትግራይ” የቁንጅና ውድድር ይደረግ ነበር። ሙሉቀን የጥላሁን ገሰሰን ዘፈኖች ዘፈነ። በጣም ወደደው ሕዝቡ። የኦርኬስትራው አባሎችም አለማየሁ እሸቴ ሄዶባቸው ስለነበረ ሙሉቀንን “ምትኩ” አሉት።

ተስፋዬ አበበ የደረሳቸውን ሦስት ዘፈኖች (“እምቧይ ሎሚ መስሎ” “እናቴ ስትወልደኝ መች አማከረችኝ” እና “ልጅነት” የተባሉትን) ሙሉቀን በሕዝብ ፊት ይዘፍን ጀመር። በነዚህ ዘፈኖች ታዋቂነትን አተረፈ። ጋዜጣ ላይም “ኮከብ ድምጻዊ ተጫዋች” ብለው ጻፉለት።

.

[“እምቧይ ሎሚ መስሎ”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1961-1964 ዓ.ም።]

.

ከፖሊስ ኦርኬስትራ ጋር ሦስት ዓመት አገልግሎ ወጣ … የማታ ክበቦች እንደገና መጫወት ጀመረ።

Muluken 1973f

ዛሬ በግዮን ሆቴል በ‘ዳህላክ ባንድ’ እየታጀበ ይዘፍናል።

አንድ አስር የሚሆን የሙሉቀን መለሰ ሸክላ ወጥቷል። ከአብዮቱ ወዲህ ዘፈኖቹ በካሴት ተሰራጭተዋል።

ከዘፈኖችህ በጣም የምትወደው የትኞቹን ነው? ብለን ጠየቅነው።

“እኩል ነው የማያቸው። ግን … በጣም የሚያረኩኝ … በዜማውና በዘፈኑ … ‘ሰውነቷ’ እና ‘ሆዴ ነው ጠላትሽ’ … እ …… በሙዚቃ ጥራትና ባሠራር ደግሞ፣ ሙላቱ አስታጥቄ ያቀነባበራቸውና ከዳህላክ ባንድ ጋር የዘፈንኳቸው ‘ቼ በለው’ እና ‘ውቢት’።”

Muluken Melesse (1967) - Chebelew & Wubit (A 004) 1b

[“ቼ በለው”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም/ዜማ) ተስፋዬ ለማ። Equators Band። 1967 ዓ.ም።]

[“ሰውነቷ”። ሙሉቀን መለሰ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ከድምፃውያን ተጫዋቾች ማንን ታደንቃለህ? አልነው።

“ዓለማየሁ እሸቴን። ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው። ካሉን ዘፋኞች ሁሉ የበለጠ የሙዚቃ እውቀት አለው። ሁላችንም በዘልማድ የምንዘፍን ሲሆን፣ እሱ ግን ሙዚቃን በማወቅ ከኛ ብልጫ አለው። ፕሮፌሽናል ኢንተርናሽናል (በአለም አቀፍ ደረጃ ባለሙያ) ዘፋኝ ያለን እሱ ነው ብዬ የምኰራበት ሰው ነው።

“በድምፅ ደሞ እንደ ምኒልክ ወስናቸው ያለ ዘፋኝ የለንም። የኦፔራ ዘፋኝ ድምጽ ነው ያለው … ጥላሁን፣ ዓለማየሁ፣ ምኒልክ፣ ብዙነሽ፣ ሂሩት፣ ማህሙድ – እነዚህን የሚተኩ ድምጻውያን መብቀል አለባቸው። ይኸ የአገሪቱ ኃላፊነት ነው … ይህን ሙያ ሲበዛ ነው የምወደው። በየዕለቱ ይበልጥ እያወቅከው … እየተማርከው ትሄዳለህ። ማቆሚያ የለውም … ሙዚቃን በትምህርት ሳይሆን በልማድ ነው የማውቀው።

Muluken 1973a

“አንደኛ የሚባል ዘፋኝ የለም። ሊኖርም አይችልም። ቢበዛ ‘የዓመቱ ኮከብ’ መባል ይችላል እንጂ … እያንዳንዱ ዘፋኝ የራሱ አይነት ልዩ ተሰጥዎ አለው።”

.

[“ላንቺ ብዬ”። ጥላሁን ገሰሰ። (ግጥም/ዜማ) ምኒልክ ወስናቸው። All-Star Band። 1963 ዓ.ም።]

[“እሩቅ ያለሽው”። ዓለማየሁ እሸቴ። (ግጥም) ኃይሉ መኩሪያ። ዓለም-ግርማ ባንድ። 1965 ዓ.ም።]

[“የእንጆሪ ፍሬ”። ምኒልክ ወስናቸው። ቀኃሥ ቴአትር ኦርኬስትራ። 1960ዎቹ።]

[“አትራቀኝ”። ብዙነሽ በቀለ። (ግጥም/ዜማ) ተዘራ ኃ/ሚካኤል። ዳህላክ ባንድ። 1969 ዓ.ም።]

[“እውነተኛ ፍቅር”። ሂሩት በቀለ። (ግጥም) ተስፋዬ አበበ (ዜማ) ንጉሤ ዳኜ። ፖሊስ ኦርኬስትራ። 1969 ዓ.ም።]

[“ትዝታ”። ማሕሙድ አህመድ። (ግጥም) ሸዋልዑል መንግሥቱ። አይቤክስ ባንድ። 1967 ዓ.ም።]

 [“መውደዴን ወደድኩት”። ሙሉቀን መለሰ። (ግጥም) ዓለምፀሐይ ወዳጆ። ዳህላክ ባንድ። 1971 ዓ.ም።]

.

ሙሉቀን መለሰ

(ቃለመጠይቅ በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር)

1973 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “ኪነት ዓምድ”። ፀደይ መጽሔት። ኅዳር ፲፱፻፸፫ ዓ.ም። ገጽ 12-14፣ 20።

.

 

“ባንዶቹ” (ራስ ባንድ)

“ባንዶቹ”

(ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ቡድኖች)

.

በሳይም ኦስማን

.

(ራስ ባንድ)

.

ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ‘ወርቃማ ዘመን’ ስናወራ እነዚያን መሳጭ ሙዚቃዎች ከዘፋኞች ኋላ ሆነው ስላቀነባበሩት ስለ ባንዶቹ ሳናነሳ አናልፍም።  በዚህ ጽሑፍ (እና በቀጣዮቹ ክፍሎች) የዋና ዋናዎቹን ዘመናዊ ባንዶች ታሪክ እና ባንዶቹን ስላቋቋሙት ሙዚቀኞች አጠር አድርጌ አቀርባለሁ።

በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ በጣም ተወዳጅ የነበሩት የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ባንድ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴአትር፣ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ኦርኬስትራ፣ እና የምድር ጦር ኦርኬስትራ ነበሩ። በ1953 ዓ.ም የታህሳሱ ግርግር የኃይለሥላሴን መንግስት ለመገልበጥ የተሞከረበት ጊዜ፣ ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ሁለተኛ ምዕራፍን ከፈተ። በዚህም ወቅት የክቡር ዘበኛ ኦኬስትራ ለበርካታ ወራት ለመበተን በቃ። ብዙዎቹ አባላቶቹም ከኦኬስትራው እየለቀቁ ሌሎች የሙዚቃ ቡድኖችን (ፖሊስ፣ ምድር ጦር እና ቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ቴያትር) መቀላቀል ጀመሩ። እነዚህ ዋና ዋናዎቹ ኦኬስትራዎች ቀስ በቀስ ወደ ብዙ ትናንሽ ባንዶች እየተቀየሩ መጡ።

እነዚህም ትናንሽ ባንዶች መጀመሪያ ስራ የጀመሩት በተለያዩ የአዲስ አበባ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ነበር። ለዚህም ይመስላል የባንድ ስማቸውን በሆቴሎቹ ስም ያደረጉት … እንደ “ራስ ባንድ”፣ “ግዮን ባንድ”፣ “ሸበሌ ባንድ” የመሳሰሉት። ብዙም ሳይቆይ ሆቴሎቹ በጣም ታዋቂ መዝናኛ ቦታዎች እየሆኑ መጡ። በተለይም አርብ ማታ እነዚህን የሙዚቃ ድግሶች ለመታደም የማይቀርበት ቦታ ሆኑ።

ras hotel 1950s
ራስ ሆቴል በ1950ዎቹ መባቻ።

.

ራስ ባንድ

.

የመጀመሪያው ራስ ባንድ የተቋቋመው በ1953 ዓ. ም ነበር። ባንዱንም የመሠረቱት ተፈራ መኮንን (ፒያኖ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክስፎን)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ባህታ ገብረሕይወት (አማርኛና ትግርኛ ድምፃዊ)፣ ግርማ በየነ (እንግሊዘኛ ድምፃዊ) እና ገብረአብ ተፈሪ (አስተናባሪና ገጣሚ) በመሆን ነበር። በዛሬ ዘመን በሕይወት በመሀከላችን የሚገኙት ጌታቸው ወልደሥላሴ፣ ባህታ ገብረሕይወት እና ግርማ በየነ ናቸው።

Ras Band 3
ራስ ባንድ በራስ ሆቴል (1953-1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 1|

የራስ ባንድ አባላት አብዛኛዎቹ ነርሲስ ናልባዲያን ባሰለጠነው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቲያትር ኦኬስትራ ውስጥ ይጫወቱ የነበሩ ናቸው። እነዚህም ተፈራ መኰንን፣ ጥላሁን ይመር፣ እና ባህሩ ተድላ ናቸው። እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስም ሶስቱ አባላት የክቡር ዘበኛ የጃዝ ሲንፈኒ ኦኬስትራ ውስጥ በፍራንዝ ዜልወከር ሥር ተምረው ነበር። በክቡር ዘበኛ ኦሮኬስትራ ውስጥ ተፈራ መኰንን ቤዝ ሲጫወት ጥላሁን ይመር እና ባህሩ ተድላ ደግሞ ድራም ተጫዋቾች ነበሩ። በ1953 ዓ.ም አጋማሽም የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ሲበተን ተጨማሪ ሙዚቀኞችን (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) እና ሁለት ድምፃውያንን ይዘው ወደ ራስ ሆቴል አመሩ።

“አርብ ማታ በራስ ሆቴል የሚያስደስት ጊዜ ነበር” ይላል ባህታ ገብረሕይወት – Addis Live ራዲዮ ኢንተርቪው ላይ፣ ባህታ የሆቴሉን ድባብ ሲያስታውስ ሁሉም የባንዱ አባላት በሚገባ ዘንጠው መገኘት ነበረባቸው። እያንዳንዱም የሆቴል ተጠቃሚ አለባበሱን አስተካክሎ መገኘት የሆቴሉ ህግ ነበር። በሚገባ አለባበሱ አልተስተካከለም ብለው ለሚያስቡት ተጠቃሚ ክራቫት ይሰጠው ነበር። ብቻቸውን የሚመጡ ተስተናጋጆች እምብዛም ናቸው። ሁሉም ጥንድ ጥንድ ሆኖ ይደንስ ነበር።

Ras Band
ራስ ባንድ በአክሱም አዳራሽ መክፈቻ በዓል (ታኅሣስ 4፣ 1956 ዓ.ም)። [ከግራ ወደ ቀኝ]፤ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ ጌታቸው ወልደሥላሴ (ሳክሰፎን)፣ ባህሩ ተድላ (ድራም)፣ ባህታ ገብረሕይወት (ድምፅ)፣ ዘውዱ ለገሰ (ትራምፔት)፣ ግርማ በየነ (ማራካስ/ፐርከሽን) … |ምስል 2|

ራስ ባንድ ውስጥ እያለ ነበር ባህታ ብዙዎቹን ስራዎቹን ያበረከተልን። እነ “አንቺም እንደ ሌላ”፣ “ደግሞ እንደምን አለሽ”/“ካላጣሽው አካል”፣ “ስቃይ ዝክኣል’ዩ”፣ “የጥላቻ ወሬ”፣ “ያ ያ” እና “ወደ ሀረር ጉዞ” የመሳሰሉትን።

[“ካላጣሽው አካል”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

ባህታ የትግርኛ ዘፈኖቹን ግጥም የጻፈው እራሱ ሲሆን፣ ብዙዎቹን የአማርኛ ዘፈኖች ግጥም ደግሞ ገብረአብ ተፈሪ ነበር የሚጽፋቸው። ሙዚቃዎቹን የሚጽፈውና የሚያቀናብረው ፒያኖ ተጫዋቹ ተፈራ መኰንን ነበር። ባህታም በዚህ ዘመን ከጻፋቸው ሙዚቃዎች ዜማ አንዱ እና ግርማ በየነን ከጥቂት ዓመታት በኋላ ታዋቂ ያደረገው ዘፈን ‘ይበቃኛል’ የተሰኘው ነበር።

AE690c Bahta

በዚሁ ራስ ባንድ በሚሰራበት ጊዜም ነበር ባህታ በትርፍ ጊዜው ተምሮ አካውንቲንግ ያጠናው። በ1964 ዓ.ም ከሙዚቃ ዓለም ሲርቅ ለግዮን ሆቴል እና ለፊልም ኮርፖሬሽን የሂሳብ ሰራተኛ ሆኖ ይሰራ ነበር። ባህታ እንደሚለው የኢትዮጵያ ሙዚቃ አካሄድ አላምር ብሎት ነበር ከሙዚቃ አለም የራቀው። በታህሳስ 1996 ዓ.ም ከብዙ አመታት በኋላ ባህታ ገብረሕይወት ‘አንቺም እንደሌላ’ን Either Orchestra ከሚባል ቦስተን ከሚገኝ የጃዝ ቡድን ጋር አቅርቦ ነበር።

[“አንቺም እንደሌላ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን/ራስ ባንድ)። 1957-1960 ዓ.ም።]

የመጀመሪያው የራስ ባንድ የተመሰረተው ከ1953 ዓ.ም ነበር። ታዲያ በ1956 ዓ.ም አጋማሽ ሁለቱ የባንዱ አባላት (ጌታቸው ወልደሥላሴ እና ዘውዱ ለገሰ) በሌሎች ሙዚቀኛች የተተኩ ይመስላል። ወዳጄነህ ፍልፍሉ ከዚህ ወቅት ጀምሮ ሳክሰፎን በመያዝ፣ አሰፋ ባይሳ ደግሞ ትራምፔት በመጫወት ራስ ባንድን ተቀላቀሉ። በሐምሌ 1956 ዓ.ም አካባቢም እንግሊዘኛ ድምፃዊው ግርማ በየነ ራስ ባንድን ለቀቀ። ብዙም ሳይቆይ በ1957 ዓ.ም የባንዱ አባላት ከራስ ሆቴል ወጥተው በግዮን ሆቴል ለተወሰኑ ዓመታት “ግዮን ባንድ” ተሰኝተው ተጫውተዋል።

Ras Band 2
ራስ ባንድ በነሐሴ 1956 ዓ.ም። [ከግራ ወደ ቀኝ] ባህሩ ተድላ (ድረምስ)፣ ጥላሁን ይመር (ቤዝ)፣ አሰፋ ባይሳ (ትራምፔት)፣ ተፈራ መኰንን (ፒያኖ)፣ ባሕታ ገብረሕይወት (ድምፃዊ)፣ እና ወዳጄነህ ፍልፍሉ (ሳክሰፎን)። |ምስል 3|

በድምፃዊነት እና በፐርከሽን ከሦስት ዓመት በላይ “ራስ ባንድ” ከተጫወተ በኋላ ግን ወጣቱ ግርማ በየነ በተራው የራሱን ባንድ ለማቋቋም ወሰነ።

Girma Beyene (old)
ግርማ በየነ በ1956 ዓ.ም መገባደጃ። |ምስል 4|

.

.

(ይቀጥላል)

.

ሳይም ኦስማን

.

[ትርጉም] – ሕይወት ከተማ

.

[ምንጭ] – Sayem Osman. (Ethio Jazz). “Bandochu.” 2006. Bernos.com

ትምክሕት ተፈራ መኰንን። የግል ምስሎች ስብስብ። [ምስል 1]

 “የአዲስ አበባ ትዝታ”። vintageaddis.com [ምስል 2]

ሰለሞን ተሰማ። “አስደሳቾቻችንን እንወቃቸው።” የጥበብ መጽሔት። መስከረም 1957 ዓ.ም። [ምስል 3፣ 4]

Peter Roth. “Modern Ethiopian Music Discographies”. http://www.funkfidelity.de

Francis Falceto. “Abyssinie Swing – Pictorial History of Modern Ethiopian Music.” 2001.

.

.

ተጨማሪ

የራስ ባንድ ሥራዎች

.

[“ወደ ሐረር ጉዞ”። ባህታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ (የቀድሞ ራስ ባንድ አባላት)። 1957-1960 ዓ.ም።]

[“ወደ ሐረር ጉዞ – 2”። ባሕታ ገብረሕይወት። ግዮን ባንድ። 1957-1960 ዓ.ም።]

“መሐመድ ኢድሪስ” (ቃለመጠይቅ)

“ቆይታ ከመሐመድ ኢድሪስ ጋር”

(ቃለመጠይቅ)

.
[ከአንድምታ ጋር የተደረገ ውይይት]

.

[አብዛኞቻችን መሐመድ ኢድሪስን በተወዳጁ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ በሚያቀርባቸው አጫጭር ልብወለዶቹ እናውቀዋለን። ከአጭር ልብወለዶች ባሻገር በርካታ የፊልም ጽሑፎችን ደርሷል። ባለፈው ዓመትም “ሣልሳዊው ዐይን” የተሰኘ ግሩም የአጭር ልብወለዶች ስብስብ መጽሐፍ አሳትሟል። አንድምታ መሐመድን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]

.

እስቲ ስለ ልጅነትህ ትንሽ ብታጫውተን?

የልጅነት ጊዜዬ፣ በጣም ወርቃማ ነበር። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያስተላልፋቸው የነበሩትን “ሙን ላይቲንግ”፣ “ፔሪ ማሰን”፣ “ትዋይላይት ዞን” የመሳሰሉትን ተከታታይ ፊልሞች እያዬሁ ነበር ያደግሁት።

ሰፈሬ አምባሳደር ሲኒማ ቤትም እገባ የነበረው፣ ከስድስት እስከ ዐሥራ ኹለት ሰዐት፥ ሦስት ፊልም፣ በሦስት ብር፥ በነበረበት ጊዜ ነበር። የቻርለስ ሑስተን እና የዮል ብሬነርን “ዘ ቴን ኮማንድመንት” ከሠላሳ አምስት ዓመት በፊት ነበር ያዬሁት። ያኔ ያዬኋቸው ፊልሞች፣ የሥነ ጽሑፍ እና የሲኒማ ፍቅር፡ እንዲሁም ደግሞ፥ ዕውቀት ሰጥተውኛል።

የመጀመሪያ አጭር ልቦለዴን የጻፍሁት፣ ስድስተኛ ክፍል እያለሁ ሲኾን፤ “ፀሐይን የጎበኘው ሰው” የተሰኜ ሳይንስ ፊክሽን ነበር።

ከ “አዲስ አድማስ“ ጋዜጣ ጋር እንዴት ግንኙነት ጀመርክ?

እኔ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፥ መጻፍ የጀመርሁት በ1993 ዓ·ም ነው። የመጀመሪያ ጽሑፌም፣ “ውዱ ስጦታ” የሚል አጭር ልቦለድ ነበር። በዛ ወቅት፣ አሰፋ ጎሣዬ በጣም ያበረታታኝ ነበር።

ወደ አጭር ልብወለድ ደራሲነት እንዴት ልታመዝን ቻልክ?

የአጭር ልቦለድ ጸሐፊ የኾንሁት፣ አስቸጋሪና ጥበብ የሚጠይቅ የሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ስለኾነና ስለሚያስደስተኝም ጭምር ነው። የታሪኮቼ ፍሰት፣ እንደፊልም የሚኾነው፥ ስጽፍ የሚታዬኝ፡ እንደዛ ስለኾነ ነው።

“ሣልሳዊው ዐይን“ የተሰኘው መጽሐፍህ አዘገጃጀት ሂደት እንዴት ነበር?

“የሣልሳዊው ዐይን” ዝግጅት፣ በጣም ጥሩ ነበር። በዋናነት፣ ከዚህ በፊት ጋዜጣ ላይ ወጥተው የነበሩትን ታሪኮች፣ ማስፋት ያስፈልግ ነበር። አድካሚ ቢኾንም፤ አስደሳች ነበር። ጥሩ ኤዲተር ስላገኘሁ፥ ሥራው፣ ሊሳካ ችሏል።

“የእኩለ ሌሊት ወግ“ እና ”የጉንዴ ቀለበት“ የተሰኙት ልብወለዶችህ ጀርባ ስላለው ታሪክ እስቲ ብታጫውተን …

“የእኩለ ሌሊት ወግ” የተጻፈው፣ «የሰው ልጅ ዕጣ ፋንታ፣ በፈጣሪ የተጻፈ ነው» ከሚለው፣ የእስልምና አስተምህሮ፥ ተነሥቶ ነው። “የጉንዴ ቀለበት” ደግሞ፣ ከራሴ የግል ሕይወት ተነሥቼ፥ የጻፍሁት ታሪክ ነው። ጉንዴ፣ በኔ ሕይወት ውስጥ ያለች፥ ጓደኛዬ ነች። ጉንዴን፣ በአጭር ልቦለድ መጻፍ፥ ከባድ ቢኾንም፤ ለማሳየት ግን ሞክሬያለሁ።

ከቀጣይ ስራዎችህስ ምን እንጠብቅ …የትኛውስ ቀድሞ ይወጣል?

በቅርቡ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የወጣ፥ “ሞያተኛው ቀብር አስፈጻሚ” የተሰኘ አጭር ልቦለድ አለ። በቀጣይም፣ “የበጋዋ እመቤት” በሚል ርእስ፥ ሌላ አጭር ልቦለድ ይቀጥላል። ከአኹን በኋላ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ፥ በየዐሥራ አምስት ቀን፥ ለመጻፍ ዕቅድ አለኝ።

በመጽሐፍ ደረጃ ደግሞ፣ “ሞገደኛው” የሚል ሳይንሳዊ ልቦለድ ለመጻፍ አስቤያለሁ፤ በፈጣሪ ፈቃድ።

እናመሰግናለን።

እኔም አመሰግናለሁ!

.

መሐመድ ኢድሪስ

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

መስከረም 2010 ዓ.ም

.

“ሕይወት ታደሰ” (ቃለመጠይቅ)

I

በልጅነት ምን ዓይነት መጻሕፍትን ታነቢ ነበር? 

በልጅነት መጀመሪያ ያነበብኳቸው የልጆች መጻሕፍት አልነበሩም። በስምንት ወይም በዘጠኝ አመቴ ያነበብኩትን የመጀመሪያ መጽሐፍን (“ግርዶሽ” በሲሳይ ንጉሡ) ጨምሮ በዚያን ጊዜ አካባቢና ከዚያ በኋላ ሁሉ ይታተሙ የነበሩትን ያካትታል። 

ቤታችን ውስጥ በርካታ ልብወለድ፣ የታሪክና ጥቂት የሚባሉ ከዚህ ውጪ የሆኑ መጻሕፍት ነበሩ። ልብወለዶቹ የሀገር ውስጥ ወጥ ስራዎች፣ ብዛት ያላቸው ትርጉሞችና ጥቂት በእንግሊዘኛ የተጻፉ ልብወለዶች ናቸው። በሀገራችን ታሪክ ዙሪያ በተለያየ ጊዜ የተጻፉ መጻህፍትም ቤት ውስጥ ነበሩ። እንዲሁም በይዘታቸው ለየት ያሉ በዚያ እድሜዬ የሚገርሙኝ አንዳንድ መጻሕፍት ነበሩበት፤ በቤት ውስጥ የህክምና እርዳታ አሰጣጥ ላይ የሚያተኩር ወደል የእንግሊዘኛ መጽሐፍና ‘ባሃኡላህና አዲሱ ዘመን’ የሚል አንድ ደቃቃ መጽሐፍ ለምሳሌ ያህል ትዝ ይሉኛል። 

በተጨማሪ በትምህርት ቤት ደግሞ እንደው ለይስሙላ በክፍል ውስጥ ይሰጡ የነበሩ እንደ ‘እጅ ስራ’ ያሉ ትምህርት ክፍለጊዜዎች ላይ የልጆች መጻሕፍትን የምታነብልን ታሪክ የምትባል መምህርት ነበረች። ለኔ በበኩሌ ባለውለታዬ ናት።  

‘የተኛችው ቆንጆ፣ ሲንደሬላ፣ አንድ ሺህ አንድ ሌሊት፣ ቲሙርና ቡድኑ ወዘተ’ በሙሉ መኖራቸውን ያወቅኩት በእሷ ምክንያት ነው። ብዙዎቹ እነዚህ መጻሕፍት ትርጉሞች ናቸው። ከትምህርት ቤት ተመልሼ ማታ ማታ እነዚያን ታሪኮች ለእህቶቼና ለእናቴ ስተርክ አመሻለሁ። ሳላስብበት ትረካን (story telling) ወደድኩ።

ቤት ውስጥ የነበሩትን ልብወለዶች በተለይ ትርጉሞቹን በሙሉ አንብቤያቸዋለሁ። ኢንተርኔት፣ ጉግል የመሳሰለውን በማላውቅበት ለአቅመ የብእር ጓደኛ ባልበቃሁበት እድሜ ላይ ስለነበር ያነበብኳቸው፣ በርካታ አስደናቂ ዓለማትን ለምናቤ ከፍተዋል። ከ1983 በኋላ ደግሞ ከዚያ በፊት ያለፈውን አስራ ሰባት አመት ታሪክ በተለያየ አኳኋን የሚዘክሩ መጻሕፍት መጡና ቀልቤን ማረኩት።

ከዚህ በኋላ ደግሞ እናቴ የBritish Council ቤተመጻሕፍት የአባልነት መታወቂያ አወጣችና የተለያዩ የእንግሊዘኛ መጻሕፍትን ማንበብ አስቻለችኝ። አባቴም የእንግሊዝ ሥነጽሑፍ ቁንጮ ጸሐፍትን ዘመን ተሻጋሪ ሥራዎች፣ ለታዳጊ ወጣቶች እንዲሆኑ አጠር ተደርገው የተዘጋጁትን፣ ከፍ ስንልም እንደዚያው ጠንከር ያሉ መጻሕፍትን ገዝቶ ያስነብበን ነበር።

በትምህርት ቤታችሁ የነበረው የንባብ ባህልስ ምን ይመስል ነበር? 

እስከ ስምንተኛ ክፍል በተማርኩበት የገዳመ ሲታውያን ማርያም ጽዮን ትምህርት ቤት (Cistercian Monastery Mariam Tsion School) የማስታውሰው የተለመደው የአማርኛ ቋንቋችንን የማዳበሪያ ተግባራት ይሰጡን እንደነበረ ነው፤ ግጥም መጻፍ፣ ክርክር ማከናወን የመሳሰሉት። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል ላይ ግን የአማርኛ መምህራችን ከዚህ በላይ ገፍቶ ያተጋን ነበር። ተውኔት ደርሰን አዘጋጅተን በክፍል ውስጥ ስናቀርብ አስታውሳለሁ። በአማርኛ ሥነጽሑፍ ውስጥ እስካሁንም የሚጠቀሱ አውራ ደራስያንና ስራዎቻቸው ላይ ሂሳዊ ንባብ እንዲሁም ግምገማዎችንም እንድናካሂድ ያደርገን ነበር። በዚህ መልኩ መምህራችን (አቶ ታሪኩ) የአማርኛ ሥነጽሑፍን እንደው ዝም ብሎ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ማጣጣምንም አስተምሮናል።የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን በተከታተልኩበት ሰላም የሕጻናት መንደር ትምህርት ቤት ደግሞ መደበኛ የመማሪያ መጽሐፉ ከሚጠቁመው በተጨማሪ ለማትሪክ የበለጠ ዝግጁ ያደርጋል ብለው ያሰቡትን ይዘት አክለው የሚያስተምሩን ሁለት የአማርኛ መምህራን ነበሩ። ስለዚህ ከተማርነው ይዘት ፈሊጣዊ አነጋገሩ፣ ቅኔው፣ ምሳሌያዊ አነጋገሩና ይህን የመሳሰለው ይበዛ ነበር። እና ደግሞ ቁጥር የለሽ (መምህራኑ ‘ጥሬ’ የአማርኛ ቃላት የሚሏቸው) በተለምዶ በሚነገረው አማርኛችን ውስጥ እምብዛም የማንገለገልባቸው አስገራሚ ቃላትን አጥንተናል። 

ድራማና ጭውውት ደርሶ አዘጋጅቶ መተወን በክፍል ውስጥ ብቻ  ሳይሆን፣ በክፍሎች መካከል በውድድር መልክ የሚካሄድና፣ በየማለዳው ቀኑን በጸሎት በምንጀምርበት አዳራሽ (ቻፕል) ውስጥ ለተማሪዎችና ወላጆች በሚቀርቡ ዝግጅቶችም ላይ የምንሳተፍበት ሁኔታ ነበር። 

20170918_113209

በቤት ውስጥስ ምን አይነት ሥነጽሑፋዊ ተጽዕኖ ነበር?

ወላጆቼ ራሳቸውም ማንበብ የሚወዱ ሰዎች በመሆናቸው፣ መጻሕፍትን ይሰበስባሉ። እኔም በግላጭ አግኝቼ ኮምኩሜያቸዋለሁ። ቤት ውስጥ በርካታ የትርጉም እንዲሁም ታሪክ ነክ መጻሕፍት የነበሩ መሆናቸው የራሱን ተጽዕኖ አድርጎብኛል ብዬ አስባለሁ። 

እናቴ ገጣሚም ነች፤ ትደብቃቸዋለች እንጂ ግጥሞችን ትጽፋለች። አባቴም በበኩሉ ያነበብኳቸውን መጻሕፍት ይዘት ጨምቄ እንድጽፍ ወይም በቃል እንዳቀርብ ሲያደርገኝ አስታውሳለሁ። በተጨማሪም በስራው ምክንያት ለወራት መስክ ላይ በሚቆይበት ወቅት የተለዋወጥናቸው ደብዳቤዎች በእንግሊዘኛ  ነበሩ። አንዳንዴ ሳከናውን የሰነበትኩትን ጉዳይ ለእሱ ለመግለጽ የሚረዳኝ የእንግሊዘኛ ቃል ፍለጋ ስለፋ ትዝ ይለኛል። 

ከዚህ ይልቅ ግን በእርግጠኝነት ከወላጆቼ የወሰድኩት መጻሕፍትን የማፍቀርን ነገር ነው። ስለ ሁለቱም የማይረሱኝን ሁለት አጋጣሚዎች ልግለጽ።

‘ምጽአተ እስራኤል’ የተባለ የማሞ ውድነህ የትርጉም መጽሐፍ የወጣ ሰሞን ነው። መኖሪያ ቤታችን ያን ጊዜ የአዲስ አበባ  ከተማ  ድንበር የሚባል ቦታ ላይ ነበር። ማንኛውም አይነት ትራንስፖርት ከሚገኝበት ዋና አስፋልት መንገድ ለሰላሳ ደቂቃ ያህል በከባድ ኮሮኮንች መንገድ ወደ ውስጥ ያስገባል። 

እናቴ ወጋየሁ ከስራ ወጥታ መጥታ እዚህ አስፋልት መንገድ ዳር፣ የመጽሐፍ መደብር ጎራ ስትል ይህን አዲስ መጽሐፍ ታገኛለች። ትጓጓለች። ነገር ግን ዋጋውን ስታየው ከቦርሳዋ በቂ ገንዘብ አልያዘችም። እስከ ነገ መጠበቅ ሊኖርባት ነው። እሷ ግን ያን ኮሮኮንች መንገድ ሰላሳ ደቂቃ ሄዳ ቤት ገብታ፣ ገንዘቡን ይዛ፣ ተመልሳ ወደ መደብሩ ሄዳ መጽሐፉን ገዝታ አደረች። በድምሩ በማግስቱ መግዛት ለምትችለው መጽሐፍ ያን ምሽት አንድ ሰዓት ተኩል በእግሯ ተጓዘች ማለት ነው። እናቴን ያሸነፋት ጉጉቷ ነው።

ሌላ ጊዜ ነው፤ ካልተሳሳትኩ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ይመስለኛል። እኔና አባቴ ፒያሳ አካባቢ በእግር እየተጓዝን በየሱቁ መስኮት አንዳንድ ነገር እናያለን፤ በትክክል ምን ልናደርግ እዚያ እንደሄድን አላስታውስም። ይህንን ግን አስታውሳለሁ። አንድ መጽሐፍ መደብር የመስታወት መስኮት ውስጥ  Lords of Poverty የተሰኘውን የግራሃም ሃንኮክ መጽሐፍ እናያለን። አባቴም እኔም ይህንን ጸሐፊ እንወደዋለንና የመጽሐፉን ዋጋ አጣራን። መቶ ብር ነው። 

መቶ ብር የዛሬ ኻያ አመት ገደማ ቀላል የሚባል ብር አልነበረም። ቢያንስ ቢያንስ ለእኔ ደህና ቆዳ ጫማ ይገዛል። አመነታን። እንግዛው አንግዛው እየተባባልን ጥቂት ደቂቃዎችን አባከንን። ከጀርባው የተጻፉ ነገሮችን፣ ማውጫውንና የመሳሰለውን እያየን ጥሩ መጽሐፍ ነው ተባብለን የዋጋው ጉዳይ ግን ያዝ አደረገን። ከተወሰኑ ደቂቃዎች መንቆራጠጥ በኋላ  ገንዘቡን ከኪሱ የሚያወጣው አባቴ ወሰነ። ለወትሮው አማረን ግዛልን የምንለው ነገሮች ላይ ቆጣቢ ቢሆንም ዛሬ ግን ‘እንግዛው ባክሽ፣ ድህነት እንደሆን ቂሙን አይረሳም’ አለኝ። እኔም አሁን ድረስ አንዳንዴ ዋጋቸው ቆንጠጥ የሚያደርጉ መጻሕፍትን ለመግዛት ወኔ ሲያንሰኝ ‘ድህነት ቂሙን አይረሳም’ የምትለዋን ቀረርቶ ለራሴ አሰማለሁ።

II

ሕግን ለማጥናት እንዴት ወሰንሽ?

ወፍራም እንጀራ ያወጣል፣ ያስተማምናል ስለተባልኩና፣ የተባልኩትን ስለሰማሁ!

ጉጉት፣ ጥያቄ፣ ቀጥታ ንግግር እና ትንሽ ድፍረት የምታሳይ፣ በትምህርት ቤት ደህና ውጤት ያላት ታዳጊ ስትሆን ጸሐፊ ወይም ተዋናይት መሆን ትችላለች ብሎ  የሚመኝልህ ብዙ ሰው አይኖርም፤ ነገረ ፈጅ እንጂ! 

ዩኒቨርሲቲ ስገባ  ምን ማጥናት እንዳለብኝ ብዙዎችን ሳማክር ተመሳሳይ ምላሽ ስላገኘሁ፣ ይህንኑ በመከተል ሕግን መረጥኩ።  

aau

የሕግ ሙያ ተምረው በርካታ የኪነጥበብ ዝንባሌ ያላቸው ምሩቃን ለምን ያሉ ይመስልሻል?

እውነት ነው። ሕግ ተምረው የኪነጥበብ ዝንባሌ  ያላቸው ምሩቃን ጥቂት አይደሉም። በተለይ ከመነሻው ትንሽም ቢሆን ኪነጥበባዊ ፍላጎት (interest) የነበራቸው ሰዎች ከሆኑ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳስብ የሚከተለው ይታየኛል፤ በተለይ በራሴው ልምድ ከተገነዘብኩት በመነሳት።

አንደኛ የሕግ ትምህርት የቋንቋ እና የግንዛቤ ክህሎትን ይሞርዳል ብዬ አስባለሁ። የሕግ ትምህርት የግድ ከባድ አይደለም፤ ግን እጅግ ሰፊ ነው። የሚነበበው ብዙ ነው፣ የሚተነተነው ብዙ ነው፣ የሚጻፈው ብዙ ነው። የምታነባቸው መጻሕፍት አይነትና ብዛት ቋንቋህ እና እውቀት አዘል ግንዛቤህ ላይ አይነተኛ ተጽዕኖ  አላቸው። በትምህርት እንዲሁም በስራ ወቅት እንድታዘጋጃቸው የሚጠበቁብህ የጽሑፍ አይነቶች የመተንተን፣ የማሰናሰልና የማስረዳት ክህሎትህ ላይ እንዲሁ ተጽዕኖ አላቸው።

ሁለተኛ ሕግ ራሱ ሁሉን ጠለቅ (pervasive) ባሕሪይ አለው። ሕግ የማይመለከተው ወይም የማይገዛው የሕይወታችን ክፍል የለም። ሕግ የሚባለው ምን እንደሆነ እና እንደምን እንደመጣ ለመረዳት መጀመሪያ ላይ የፍልስፍና ትምህርት፣ በመቀጠል የሕግ ፍልስፍና ትምህርት ስትወስድ ዘላለማዊ የሚባሉትን የሰው ልጅ ኀሠሣዎች ገረፍ አድርገህ ታልፋለህ። ከዚያ በኋላ በሕግ ግምትና  በሕግ አተያይ ሰው ከመሆን አንስቶ፣ የግለሰብን ሕይወትና ከግለሰብ፣ ከማህበረሰብ እና  ከመንግስት ጋር የሚኖር መስተጋብር፣ የሀገር እና የአለም አቀፍ ህብረተሰብን መስተጋብር፣ በየፈርጁ የሚፈትሹ ሃሳቦችን፣ የሚገዙ መርሆችን ታያለህ። 

በአጭሩ ሕግ መቼ ተፀነስክ ከሚለው የማህፀን ውስጥ ሀቅ ጀምሮ ቤትህን፣ ምድርን፣ ባህርን፣ አየርን እና አሁን ደግሞ ‘ቨርቹዋል’ የምንለውንም አለም እንዲሁም እዚህ ሁሉ ውስጥ ያለውን ክንውን ይቃኛል። ኪነትስ? በአንዳች አይነት መልኩ ይህንኑ አታደርግም?

የኔ ፍላጎት ሥነጽሑፍና ቴአትር ስለነበር፣ አባቴ አበበ ባልቻን ምሳሌ አድርጎ ሕግ ትምህርት ቤት እንድገባ አሳመነኝ። እኔ አብዛኛዎቹን አመታት ክፍል ውስጥ ግጥም እየጻፍኩ አሳለፍኳቸው። ቴዎድሮስ ሞሲሳ ዘፈን ሲያወጣ ጓደኞቼ ‘የሒዊ መጨረሻ’ ብለው ለወራት ተዝናኑብኝ።

በአአዩ  የነበረው ኪነጥበባዊ ድባብ ምን ይመስል ነበር? 

አአዩ በነበርኩበት ጊዜ፣ እኔና ጓደኞቼ እንሳተፍበት የነበረው የባህል ማእከሉን የግጥም ምሽት ነበር። በሳምንት አንድ ቀን የሚጽፉ ልጆች ግጥሞቻቸውን እና ወጎቻቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ ነው። በወቅቱ የነበረው የመብራት መጥፋት ወረፋ እንኳን ሳያግደው በመማሪያ  ክፍሎች ውስጥ በሻማ  ብርሃን ይከናወን ነበር። በ1993 በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተነሳው ግርግር ምክንያት ተቋርጠ። 

ከዚያ  በኋላም ተማሪዎች በቡድን ተሰባስበው መገኘት ስለተከለከሉ የሥነጽሁፍ ምሽቱን ማስቀጠል አልተቻለም። ለወትሮውም ቢሆን ከሚቀርቡት ጽሁፎች ውስጥ ጥቂት የማይባሉት ይዘታቸው ፖለቲካዊ እንደሆነ  የታወቀ  ነውና።

በ1993 የትምህርት ዘመን የሁለተኛውን ሴሚስተር ተምሮ ላለመጨረስና ፈተና ላለመውሰድ የወሰኑት መደበኛ ተማሪዎች በሙሉ ለአንድ አመት በትምህር  ገበታ ላይ እንዳይገኙ ተደርገው ተቀጡ። በመሆኑም በ1994 እንኳን እንደወትሮው የደመቀ የሥነጽሁፍ ምሽት ሊካሄድ፣ በግቢው ውስጥ የቀሩት እኛ የሕግ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በዚሁ አመት የገቡ አዲስ ተማሪዎች ብቻ ነበሩ። ምናልባት በሌሎች መርሃ ግብሮች የሚማሩ ተማሪዎችም ነበሩ ይሆናል፣ በትክክል አላስታውስም። የማስታውሰው እንደ ድንጋይ የሚካበደውን ጭርታ ብቻ ነው።

በ1995 ተማሪዎች ከተመለሱና  ነገሮች ከተረጋጉ በኋላ ግን እኔና የክፍል ጓደኛዬ የሆነው ይርጋ ገላው (ገጣሚና ደራሲ)፣ የተቋረጠው መድረክ መቀጠል እንዳለበት ስላሰብን በወቅቱ ወደ ነበሩት የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚደንቶችና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት በመሄድ የግጥም ምሽቱ በድጋሚ እንዲጀመር ጠየቅን። ግልጽና  ከፍተኛ  ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶን ተፈቀደ። 

መድረኩም በሌሎች እገዛ እንደገና ጀመረ። ልጆች አሁንም ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን በስራዎቻቸው መግለጽ አላቆሙም ነበርና ከባህል ማእከሉ ተቆጣጣሪዎች ተግሳጽና ምክር አንዳንዴም የ‘እባካችሁ ሁላችንንም እንዳታሳስሩን’ ልመናን አስተናግደናል።

ከባህል ማእከል ባለፈ ደግሞ ተለቅ ያሉ የሥነጽሁፍ መድረኮችን ከሌሎችም ጓደኞቻችን ጋር በመሆን እናዘጋጅ ነበር። 

Afroflag

በተለመደው በሳምንት አንዴ  በሚዘጋጀው መድረክ ከሌሎቹ ካምፓሶች የሚመጡት ተማሪዎች ቁጥር እምብዛም ስላልነበረ፣ አልፎ አልፎ እያዘጋጀን ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ አዳራሽ የምናቀርበው መድረክ እነዚህንና ሌሎችንም ይስብ ነበር። በስድስት ኪሎና አካባቢው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከይርጋ ጋር እየተዘዋወርን ትምህርት ቤቶቹ ከተማሪዎቻቸው መካከል መርጠው በእኛ ዝግጅት ላይ ግጥም የሚያነቡ ታዳጊዎችን እንዲልኩልን ስንጠይቅ ሁሉ አስታውሳለሁ።

እኔና ጓደኞቼ እንደሌሎች ብዙዎች ከግጥም ምሽቱ በኋላ የምናዘወትረው ልማድ ነበረን። ተያይዘን ‘አሴ ቤት’ ወይም ‘ማዘር ቤት’ እንሄዳለን። በዚያም ምሽቱን መድረክ ላይ በቀረቡት ስራዎች መንስዔነት የተለያዩ ሃሳቦች ተነስተው ይንሸራሸራሉ። በመሆኑም በተለያዩ ርእሰ ሃሳቦች ላይ በልዩ ሁኔታ ስምም የሆንነውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀራረብን የመጣን ልጆች አንዲት ማኅበር መሰረትን። 

ማህበሯም በተማሪዎች ዲን ጽ/ቤት እውቅና አግኝታ  በግቢው ውስጥ አንዳንድ ዝግጅቶችን በማከናወን መንቀሳቀስ ጀመረች። አላማዋ ለተማሪዎች/ለወጣቶች በሃገር በቀል ባህሎችና ማንነት፣ በአፍሪካዊ ማንነትና ትልሞች እና በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ነበር። የክዋሜ ንክሩማ ልጅ ጋማል ንክሩማ ተገኝቶ ለተማሪዎች ንግግር ያደረገበት በማህበሯ የተዘጋጀው መድረክ ከማይረሱኝ አንዱ ነው።

በኋላ ላይ የመስራቾች የመመረቂያ ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ፣ ማኅበሯን ከግቢ ውጪ እንደ ድርጅት የማስመዝገብ ሃሳብ መጣ፤ ተመዘገበችም። ከጊዜ በኋላ የነበርነው ነባር መስራቾች በተለያየ የግል ምክንያት ብንጎድልም፣ ከመካከላችን ጎበዛዝትና ምርጦች የሆኑት ግን ይዘዋት፣ ደግፈዋት ቀጥለዋል፤ ዛሬም ድረስ እየሰራች ነው።

በዚህ ዘመን የንባብሽ ምርጫ ምን ይመስል ነበር?

ከላይ እንዳልኩት በልጅነት በአብዛኛው ልብወለዶችን ከፍ ካልኩ በኋላ ደግሞ ጊዜው የከሰታቸውን የታሪክና ታሪክ ነክ መጻሕፍት አነብ ነበር። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ ዩኒቨርሲቲ የገባሁ ሰሞን ድረስ፣ ልብወለዶችን በተለይ የሩሲያ ጸሐፍትን ስራዎች ትርጉም ሳነብ አስታውሳለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ከመሰልቸት ይሁን፣ ወይም ‘አድጌያለሁ እኮ፣ እስካሁን ልብወለድ እንዴት አነባለሁ?’ የምትል ሚጢጢ ትምክህት ከልቤ አጎንቁላ፣ ልብወለድ የሚባል ማንበብ ተውኩ። 

ኢ-ልብወለድ የሆኑ ጽሑፎች በይበልጥ ይማርኩኝ ጀመር። ምናልባት እየዳበረ የመጣው ስብእናዬ በወቅቱ ከነበርኩበት የመማርና የልምድ ንፍቀ ክበብ (ዩኒቨርሲቲ) ጋር ተባብሮ ፈርጀ ብዙ እውቀት የማጋበስ ፍላጎት ፈጥሮብኝ ይሆናል። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ታሪክ፣ ስነልቦና፣ ሃይማኖት፣ የሃይማኖት ታሪክ እንዲሁም ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ኢ-ልብወለድ መጻሕፍትን ጊዜ፣ ተደራሽነትና አቅም በፈቀደ መጠን ለማንበብ ሞከርኩ።

ከዚያ፣ ‘ግራጫ ቃጭሎች’ የተሰኘ ትንግርት ተከሰተ።

በግራጫ ቃጭሎች መንስዔነት ፊቴን ወደ ልብወለድ መለስኩኝ፤ የአማርኛም የእንግሊዘኛም። አሁን ሁሉንም አቀላቅዬ ለማንበብ እሞክራለሁ። በተለይ ግን ግለ ታሪክ፣ የህይወት ታሪክና፣ ማስታወሻዎች በይበልጥ ቀልቤን ይገዙታል። በብዛት እና በተስማሚ ዋጋ ባለመገኘታቸው ምክንያት ከውጭ ሀገር መጻሕፍት ይልቅ በብዛት የሀገር ውስጦቹ ላይ የምበረታ ይመስለኛል።

III

  የሐማ ቱማን “The Case of the Socialist Witchdoctor” እና የሕይወት ተፈራን “Mine to Win” እንዴት ለመተርጐም ወሰንሽ?

“The Case of the Socialist Witchdoctor” (“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”) ጋር የተገናኘሁት በአጋጣሚ ነው። መጽሐፉ በሀገር ውስጥ እንደልብ የማይገኝ በመሆኑ ፎቶ ኮፒውን አግኝታ ያነበበች ጓደኛዬ ደጋግማ ስላነሳችብኝ ተውሺያት አነበብኩት። የመጀመሪያውን ክፍል ሙሉ በሙሉ ሳልጨርሰው ለመተርጎም ወስኜያለሁ። 

እንደ ሀገር እንደ ህዝብ ስለራሳችን ያልተቀበልናቸውና፣ ዘወትር ሸፋፍነን የምናልፋቸውን አስቀያሚ ገጽታዎቻችን እንዲሁም እርስ በእርስ የተደራረስነው ግፍ፣ የተገብርነውን ክፋት እያዋዛ ሆጭ አድርጎ ማሳየቱን ወደድኩት። ሰው ሁሉ እንዲያነበው ፈለግኩ። ስለዚህ ልተረጉመው ወሰንኩ። የደራሲውን አድራሻ ከጉግል ላይ አፈላልጌ ፍቃዱን ጠየቅኩት። የተቀረው፣ … እንደሆነው ነው።

በሌላ በኩል “Mine to Win” ደግሞ፣ ሕይወት ተፈራ ለማስተርጎም ፈልጋ ወዳጅ ጓደኞቿን ተርጓሚ እንዲጠቁሟት ስትጠይቅ፣ የኔ ስም በሁለት ወገን ይደርሳታል። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ትርጉም ብዙ ሰው ወዶት ስለነበር ነው እኔን መጠቆማቸው። ነገር ግን ሕይወት ሶስት ሰዎችን ለማወዳደር ነበር የፈለገችው። በተለይም ደግሞ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን አላነበበችውም ነበርና፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በስልክ ስንነጋገር፣ ይህንኑ ገልጻ ከ“Mine to Win” አንድ ምእራፍ ብቻ ሰጥታኝ ከሌሎች ሁለት ሰዎች ጋር እንደምታወዳድረኝ ነገረችኝ። ተወዳደርኩ። ዳኞች እኛ ተወዳዳሪዎች ያላውቅናቸው ሰዎች ናቸው፤ እራሷም አልዳኘችም። 

ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ የመጽሐፉ ታሪክ የሚያጠነጥንበትን መቼትና  ሁኔታ የሚመጥን ረቂቅ በማቅረቤ እኔ እንዳለፍኩ ተነገረኝና ስራውን ጀመርኩ። በእርግጥ ሙሉ የትርጉም ስራውን ከመጀመሬ በፊት የእንግሊዝኛውን መጽሐፍ ሳነበው ከዋናው ገጸ ባሕሪይ ከተውኔ (ተዋነይ) ጋር ልባዊ ቁርኝት መፍጠር ያስቻሉኝን በርካታ ነገሮች አገኘሁና፣ ተወዳድሬ እንዳገኘሁት ስራ ሳይሆን ፈልጌ፣ ጠይቄ  የተረጎምኩት ያህል አቅሜ የቻለውን ሁሉ ለማድረግ በቂ ውስጣዊ ግፊት ነበረኝ።

ከኒህ ሥራዎች በፊት የነበረሽ የትርጉም ልምድ ምን ይመስል ነበር? 

10475415_10152900246440681_5403672400978201655_oከዚህ በፊት የነበረኝ የትርጉም ልምድ በአብዛኛው ግጥሞችን መተርጎም ነበረ። ሙሉ ስራ ሳይሆን፣ እንዲሁ እዚህም እዚያም ሳነባቸው የወደድኳቸውን እና  ስሜቴን የነኩትን አንዳንድ ግጥሞች ተርጉሜያለሁ።

“የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ተርጉሜ ስጨርስ ጉዳዩ ለራሴውም ጥያቄ ሆነብኝ። አንብቤው እዚያው ለመተርጎም የወሰንኩበትን ቁርጠኝነት ከየት አመጣሁት? እስካሁን ለምን ሙሉ ስራ ለመስራት አልተነሳሁም ነበር? እና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ውስጤ ይመላለሱ ነበር። ይህን ጊዜ ነው ለመጀመሪያ  ጊዜ ትርጉም የሞከርኩበት አጋጣሚ ታልሞ  እንደተረሳ  ህልም ትውስ ያለኝ። 

አምስተኛ  ክፍል ነበር። I am Legend የተበለውን የሪቻርድ ማቴሰን መጽሐፍ ቤት ውስጥ አግኝቼ  አንብቤዋለሁ፤ እንግዲህ በአምስተኛ ክፍል እንግሊዘኛ ምን ያህል ገብቶኝ እንደሆነ አሁን በዝርዝር መግለጽ አልችልም። የማስታውሰው ግን አንዲት ጓደኛዬን “እንተርጉመው” ብያት በጠራራ ፀሐይ ይዘነው ሜዳ ላይ ቁጭ ብለን እንደሞከርን ነው። እንደሚጠበቀው አንድ አረፍተ ነገር እንኳን አልተሳካልንም።

ሥነጽሑፍን በተመለከተ፣ ግጥም እጽፍ ነበር፤ አብዛኛዎቹ በአአዩ ቆይታዬ የተጻፉና ባህል ማእከል የቀረቡ ናቸው። ገጣሚ እንዳልሆንኩ የገባኝ ለታ ግን መጻፍ ተውኩ። ባለፈው አስራ ሁለት አመት ውስጥ፣ እጅግ በጣም ስሜቴን የነኩት ነገሮች ገጥመውኝ አንድ ሶስት ግጥም ሳልጽፍ አልቀረሁም። ፌስቡክ ላይ ተለጥፈዋል። ድሮ የሞካከርኳቸው አጫጭር ልቦለዶችም ነበሩኝ።

ብዙ ጊዜ የምትጠቀሚው የትርጉም ስልት ምን የመሰለ ነው?

ስለ ትርጉም ስልቴ ለማብራራት “ኀሠሣ” ላይ የአርትኦት ስራ የሰራው ይኩኖአምላክ መዝገቡ በአንድ ወቅት ያለኝን ላካፍል። ስለ “ኀሠሣ” አንዳንድ ነገር ለመነጋገር እኔና  ሕይወት ተፈራ አግኝተነው ነው። “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ”ን ቀድሞ አንብቦት ነበረና ስለ ትርጉም ስልቴ የሚያስበውን እንደሚከተለው አጫወተኝ። ወደ እኛ ከመምጣቱ በፊት የሚነበብ ነገር ሲያገላብጥ አንድ ሰው ስለ ተርጓሚዎች በጣልያንኛ የተናገረውን ነገር አግኝቷል። ሰውየው “Traduttore traditore” ነው መሰለኝ ያለው። Translator, traitor ለማለት ነው በእንግሊዘኛ፤ “ተርጓሚ ከሃዲ ነው” እንደማለት። 

ማለትም አንድ ሰው የትርጉም ስራ ሲሰራ የሚከናወን የፈጠራ ስራ አለ፣ ምንም ያህል እናት/ምንጭ ስራውን ተቀራርቦ ሊተረጉም ቢሞክር እንኳን፣ የቋንቋ ብቃት፣ የራሱ አመለካከትና ንቃተ ህሊና፣ የራሱ ባህልና ስነልቦና የመሳሰሉት ነገሮችን ይጨምርበታል። ስለዚህ ትርጉሙ ዋናውን ሊመስል አይችልም። ተርጓሚው የራሱን አረዳድ ነው የሚጽፈው፤ በመሆኑም ከሃዲ ነው። ዋናው ባለስራ ወይም ዋናው ስራ ላይ የሚፈጽመው ክህደት አለ የሚል ነገር አጫወተኝና፣ “አንቺ ግን ከሃዲ አይደለሽም” አለኝ በስተመጨረሻ።

ትክክል ነው፤ እናት ጽሑፉ የግድ መጨመርን ወይም መቀነስን ካልጠየቀ  በስተቀር (ለሚተረጎምበት ቋንቋ አንባቢዎች ስምም ለማድረግ ሲባል) እንደተጻፈው መተርጎምን እመርጣለሁ። ይህንን ስልት አስቤበት መርጬው አይደለም። እስከዛሬ  ትርጉም ስሞክር ልቦናዬ  የመራኝ በዚያ  መንገድ ስለነበረ፣ መጠቀም የቀጠልኩበት ስልት ነው።

ዕለታዊ አሰራሬ ጠዋት ራሴን ከማስደሰት ይጀምራል። ቁርስ፣ ቡና በትልቅ ኩባያ፣ ትንሽ ፌስቡክ። ከዚያ ስራ፣ ምሳ፣ ለኻያ ደቂቃ ማሸለብ፣ ተነስቶ ስራ መቀጠል፣ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ስራ አቁሞ ሌሎች የሚያስደስቱኝን ነገሮች ማድረግ። 

በሌሎች የስራ ወይም የማህበራዊ ኑሮ ጉዳዮች ያልተረበሸ የስራ ቀኔ ይህን ይመስላል። በእርግጥ በየመሃሉ ቤቴ ውስጥ በተሰናዱት የዘቢብ፣ የቴምር፣ የሱፍ ፍሬ፣ የኦቾሎኒ እና የመሳሰሉት ጣቢያዎች ቆም እያልኩ ነዳጅ እሞላለሁ!

በልብወለድ ትርጉም ሥራ በርካታ የሀገራችን ደራሲዎች ተሰማርተዋል … እኒህን ሥራዎች እንዴት ታያቸው ነበር? 

ከፍ ብዬ እንደጠቀስኩት ለአማርኛ የትርጉም ስራዎች ከልጅነቴ ጀምሮ በልቤ ውስጥ ልዩ ስፍራ አለ። በብዛት ስላገኘኋቸውና ተስገብግቤ በማነብበት ወቅት ስለተዋወቅኳቸው፣ አድማሳትን ስላስቃኙኝ ተያይዞም ለተርጓሚዎቻችን ትልቅ አክብሮት አለኝ። እነዚያን ጣዕም የነበራቸው ቀናት የኖርኳቸው በእነሱ ስራዎች ውስጥ ነውና።

ቅርብ ጊዜ እንደገና ያነበብኳቸው እንኳን ጥቂት ናቸው። ደግሜ እንዳየኋቸው ከማስታውሳቸው ውስጥ፣ የከበደ ሚካኤል “ሮሜዮና ዡልየት”፣ የአውግቸው ተረፈ “የትውልድ እልቂት”፣ የለማ በላይነህ “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” እና የሣህለሥላሴ ብርሃነ ማርያምን “የኢየሱስ ሕይወት” በድጋሚ ቃኘት ቃኘት አድርጌያቸዋለሁ። 

አሁን እንደተርጓሚ ሳነባቸው ብዙ ሃሳቦች በጭንቅላቴ ውስጥ ይንጋጋሉ፤ ምንን እንዴት እንደተረጎሙት ብልጭታዎች ይታዩኛል። ብዙውን ጊዜ ግን ተርጓሚ መሆኔን ረስቼው እንደአንባቢ ሌላ ቦታ ይወስዱኛል። በተለይ “አንድ ሺህ አንድ ሌሊት” … ስራ አስትቶኝ ያውቃል።

IV

“ኀሠሣ”ን ስትተረጉሚ ከእናቱ ድርሰት (Mine to Win) ወጣ ብለሽ ላለመሄድ እንዴት ሞከርሽ?

ከላይ እንዳልኩት ‘traditore’ ላለመሆን የተቻለኝን ያህል ሞክሬያለሁ። እናት ድርሰቱ የተጻፈበት ዘመን መንፈስ (Zeitgest)፣ የተገለጸው የአኗኗር ሁኔታ፣ የአነጋገር ዘዬ፣ የአመለካከት አጥናፍ እንዳለ ወደ አማርኛ ቢመለስ፣ ትርጉሙ የመጣፈጥ እድሉ ይጨምራል። ደግሞ ይዘቱ ውስጥ የሚገኘው ቅኔ ነው፣ ትምህርት ነው፣ ኢትዮጵያዊ ጥበብና ፍልስፍና ነው ሕግጋትና ማፈንገጦች ናቸው። ለምን ወጣ ብዬ ለመሄድ እሞክራለሁ? ለዛውን ማሳጣት ይሆናል።

የዘመኑን (19ኛ ክ/ዘመን) የንግግር ዘዬ ለማምጣት ምን ስልት ተጠቀምሽ? 

ያደረግኩት ዝግጅት የተጠቀምኩትን ስልት ይገልጻል ብዬ አስባለሁ። በመጀመሪያ የሥነጽሁፍና የታሪክ ምሁር በሆነ ውድ ጓደኛዬ ትጋት ለዚህ ስራ ዝግጅት ላነባቸው የሚገባኝ መጻሕፍት ዝርዝር ወጣ። እኔም የራሴን አከልኩበት። ከዚህ በኋላ ዝርዝሩ ላይ ያሉትን መጻሕፍት አሰባሰብኩ። 

መጻሕፍቱ በአብዛኛው በ19ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የነበሩ/ያሉ ሊቃውንት፣ መምህራን፣ ዲያቆናት፣ ጸሐፌ ዜና መዋዕሎች፣ ደራሲዎች የጻፏቸው፣ ወይም ስለእነሱ የተጻፉ ናቸው። አንዳንዶቹ እኔ ራሴ ቤት ውስጥ ነበሩኝ፣ ሌሎች በግዢ፣ በውሰት ወይም ከበይነ መረብ በማውረድ (ለምሳሌ: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ መጻሕፍት) የተገኙ ናቸው።

ቀን ቀን መሰረታዊ የትርጉም ስራውን እየሰራሁ ማታ ማታ እነዚህን መጻሕፍት ማንበብ ጀመርኩ። እያነበብኩም ሊጠቅሙኝ የሚችሉ ቃላትን በማስታወሻ  እየሰበሰብኩ የራሴን ትንሽዬ ሙዳየ ቃላት አዘጋጀሁ። በእርግጥ ከዚህ በፊት የቤተሰብ አባላት ሲነጋገሩ በምሰማበት ወቅት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ወቅት፣ በንባብ ወቅት፣ ካገኘኋቸው ቃላት በትውስታዬ የተገኙትን ሁሉ በረቂቁ ውስጥ ተጠቅሜባቸዋለሁ። 

በመቀጠል ረቂቁን የማበልጸግ የመጀመሪያ ዙር ስራ ስሰራ ያጠራቀምኳቸውን ቃላት እንደሁኔታው ቦታ ቦታ አገኘሁላቸው። ከገጠር የኑሮ ዘይቤና ከቤተክርስቲያን ስርዓት ጋር የተያያዙ ብዙ ቃላትን እናቴ ጠቁማኛለች። በአቅራቢያችን ከሚገኘው ሰዓሊተ ምህረት ቤ/ክ የነበሩ ካህን አገናኝታኝ በቃለመጠይቅ ብዙ መረጃ ሰጥተውኛል።

በዚህ ጊዜ በብዛት ያገኘኋቸው መጻሕፍት የተጻፉት በሸዋ ልሂቃን እንደመሆኑ የረቂቁ አማርኛ የሸዋ አማርኛ ያመዘነበት ይመስለኛል። ጥንታዊዎቹን መዛግብተ  ቃላትና ተጨማሪ መጻሕፍትን በመጠቀም በበኩሌ የተቻለኝን ያህል የጎጃምን ዘዬ ለማምጣት ከሰራሁ በኋላ የቀረውን አርታኢዎች እንዲያዩት ተውኩላቸው። ያጎደልኩትን ሞሉልኝ፣ ያጣመምኩትን አቀኑልኝ።

ገና የእንግሊዘኛውን መጽሐፍ ማንበብ ስጀምርና ታሪኩ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ አካባቢ እንደሚያጠነጥን ስረዳ፣ የተገለጸልኝ ነገር የሚተረጎምበት አማርኛ የገጠር አማርኛ ብቻ ሳይሆን፣ የድሮ የገጠር አማርኛ መሆን እንዳለበትም ጭምር ነው። በዘመን ሂደት ቃላትም ጡረታ ይወጣሉና የተገኘው የገጠር አማርኛ ብቻ በቂ ላይሆን ይችላል፤ የቆየ መሆን አለበት፣ አሁን እምብዛም የማንሰማው፣የማንናገረው። ስለዚህ ‘ወደፊት’ ሳይሆን ‘ግፋኝ’ ጊዜውን የበለጠ ያሳያል …  

ቅድመ አያቴም፣ አያቴም ለምሳሌ “ተነስተሽ የማትሄጅ?” ሲሉ ሰምቼ አላውቅም። “ተነስተሽ እማትሄጅ?” ግን ይሉ ነበር። አርታኢዎችም በዚህ መንገድ የመጻፉን ሃሳብ አቅርበው ተቀብዬዋለሁ።

“ከ = ተ/ኸ” (ተአፋቸው፣ ታልኾነ፣ ኸቤታቸው)

“መ = ም” (ምንደር)

“ሄ = ኸ” (መኸድ)

“ሂ = ኽ” (እንኽድ)

መጀመሪያ ላይ በንግግሮች ላይ ብቻ ነበር እንዲህ አይነቱን አደማመጽ የተጠቀምኩት። በኋላ ግን መጽሐፉ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ፣ በተዋነይ በራሱ ስለሆነ፣ ለተዋነይ የራሱን የአነጋገር ዘዬ (accent) ብሰጠውስ ብዬ አሰብኩና ነው። ሌሎች ሰዎች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከእሱ ጋር ሲያወሩ የተናገሩትንም የሚጽፍልን እሱው ስለሆነ በተመሳሳይ መንገድ እዚያም ላይ ተጠቅሜዋለሁ። 

መጽሐፉ ውስጥ የምናገኛቸው እንደ ዐወቀ፣ አባ እና  ሠረገላ  ብርሃን ያሉ ሌሎች አውራ ገጸባሕሪያት ደግሞ፣ እንደው ሁሉም አንዳይነትና  ልሙጥ እንዳይሆኑ ትንሽ የአነጋገር ልዩነት ቀለም ልቀባባቸው ሞክሬያለሁ።

“ሁ = ኹ” (ኹለት፣ ተነሳኹ)

“ሆ = ኾ” (ታልኾነ)

“አ = ዐ” (ዐዘንሁኝ፣ ዕርሻ)

መቼም 100% ተሳክቷል ብዬ አፌን ሞልቼ ባልናገርም፣ አማርኛ እንዳሁኑ ሳይሆን፣ ከሞላ ጎደል በግዕዝ ፊደላት በሚጻፍበት ጊዜ ቃላቱ የሚጻፉበትን መንገድ ለመከተል ስለመረጥኩ ነው፤ ትርጉሙ ጊዜውን እንዲመስል። እንዳልኩት ታሪኩ የሚተረክልን በአንደኛ መደብ፣ በዋናው ገጸባሕሪ በተዋነይ ነው፤ ተዋነይ ደግሞ ሐዲስን ጠንቅቆ ጸሐፌ ዜና መዋዕል ለመሆን የታጨ ሊቅ ነው። አማርኛውን ዛሬ እኛ እንደምንጽፈው እያቀላቀለ ወይም የግዕዝን ድምጾች ባስወገደ መንገድ ይጽፈዋል ተብሎ መቼም አይጠበቅም ብዬ በማሰብ ነው። 

የቻልኩትንም ያህል ዋና ዋናዎቹን መዛግብተ ቃላት በመመልከት ለቅሜ ለመጠቀም ጥረት አድርጌያለሁ።

ከላይ እንዳልኩት ለጊዜውና ለቦታው እውነተኛ (authentic) በሆኑ ቃላት ነገሮችን ለመግለጽ መሞከሬ እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንድ ቃላት በጣም ዘመናዊ (modern) ወይም ዘመነኛ (contemporary) ሲመስሉኝ ቆየት ያለውን እቻቸውን ለመፈለግ ሞክሬያለሁ። አንዳንዴ አሁን ባለንበት ጊዜ እስኪሰለቹ ድረስ የምንጠቀማቸውን ቃላት በደራሲዋ ሕይወት ምክር የቀየርኳቸው ይኖራሉ፤ ለምሳሌ: ታዳሚው፣ ታዳሚያንን ትተን ‘እድምተኛው’ን መጠቀም መረጥን።

ከሕይወት ተፈራ ጋር የነበራችሁ የአሠራር ሂደቱስ? 

ትርጉሙን ጨርሼ ነው የሰጠኋት። ያው የመጀመሪያው ምእራፍ የተወዳደርኩበት ነው። ሌሎቹን ጨርሼ፣ በተደጋጋሚ አንብቤና አርሜ ሙሉውን ነው የሰጠኋት።

የስራው ሂደት እጅግ አስደሳች ነበር። ሕይወት ተፈራ በጣም አስተዋይ ናት፤ የረሳሁት መስመር ወይም በተሳሳተ መልኩ ተረድቼው የተረጎምኩት መስመር አያመልጣትም፤ የራሷን መጽሐፍ በልቧ ታውቀዋለች። በመሆኑም ረቂቁን አንድ ሶስቴ ኦዲት አድርጌዋለው፤ የጠፉ አናቅጽና  መስመሮች እንዳሉ ቆጠራ። 

ያልመሰላት ጉዳይ ላይ በግልጽ ታዋየኛለች፣ ታደምጠኛለች። ወይ አሳምናታለሁ፣ ወይ ታሳምነኛለች። የመጨረሻ ውሳኔ የእሷ ቢሆንም፣ ብዙ ጉዳዮች ላይ እስከመጨረሻ  ድረስ እንከራከር ነበር። ስለዚህ ራሴን ለመግለጽና ለማስረዳት ምንም ገደብ አላበጀችብኝም። አንዳንዴ እንዴት አድርጌ ሳዋራት እንደነበር ቤት ገብቼ  ሳስበው፣ እንደ እኩያዋ እንዳዋራት ያስቻለኝን ድባብ እንደምን እንደፈጠረችው ይደንቀኛል።

የትርጉሙን የመጀመሪያውን ረቂቅ አንብባ በመደሰቷ የራሷን መጽሐፍ “ለካ እንዲህ ቆንጆ መጽሐፍ ነበርንዴ?” ያለችኝ ዕለት፣ እኔም እጅግ ደስ ተሰኝቼበታለሁ።

መጽሐፉን አሁን መለስ ብለሽ ስታይው ትርጉምሽ ላይ ምን ማስተካከል ትፈልጊ ይሆን?

አንዳንድ አሁንም መስተካከል የሚችሉ ነገሮች አይጠፉም። ያው ለረጅም ጊዜ ከእጅህ ሳታወጣ ልታስተካክለው፣ ልታሰማምረው የምትችል ይመስልሃል። ግን የሆነ ቦታ ይህ ሂደት መቋረጥ አለበትና ነው እርማት ማድረግን የምታቆመው። በመሆኑም ትርጉሙን ያነበቡ እንዲሁም የገመገሙ ሰዎች አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ ባለማወቅ፣ በእንዝህላልነት ወይም በተሳሳተ ምክር ምክንያት የተፈጠሩ መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ታይተውኛል። ከነዚህ ውጪ ምንም ማከልም ሆነ  ማንሳት አልፈልግም።

በሁለተኛው እትም ላይ ያስተካከልነው የተወሰኑ የፊደል ግድፈቶችን፣ እና አንድን ቃል በተለያዩ ሆሄዎች በመጻፍ የተሰሩ ስህተቶችን ነው። በተጨማሪ፣ ኀሠሣ ላይ የእንግሊዘኛው ርእስ (Mine to Win) ሳይካተት ነበርና የታተመው፣ እንግሊዘኛው መውጣቱን ያላወቁ ሰዎች የየትኛው መጽሐፏ ትርጉም እንደሆነ ጥያቄ ስላበዙ፣ ይህንንም አንድላይ አርመናል። እንዲህ አይነት ትናንሽ እርማቶች ናቸው እንጂ ይዘቱ ላይ የተደረገ ለውጥ የለም። 

ከትርጉም ሥራዎች በተጨማሪ የራስሽ ወጥ ድርሰቶች እንዳሉ ትንሽ ብታጫውቺን …

በአሁኑ ሰዓት አቋርጬው የነበረ አንድ ረቂቅ የረጅም ልብወለድ ስራ እጄ ላይ አለ። በቅርቡ እመለስበትና እጨርሰዋለሁ ብዬ አስባለሁ። ያለፈው አርባ አመት የፖለቲካ ታሪካችን በሁለት ትውልድ ደጋግሞ የሚበጠብጠው ቤተሰብ ታሪክ ነው ባጭሩ።

የትርጉም ሂደትሽና የድርሰት አጻጻፍሽ ስልትሽ እንዴት ይለያል?

ከአሰራር ልማድ (routine) አንጻር ልዩነት የለውም። ከክህሎት አንጻር ግን አሁን ጀማሪ ተርጓሚ አይደለሁም፤ ግን ጀማሪ ደራሲ ነኝ፤ ሙልጭ ያልኩ አማተር። ስልቴን ገና እያፈላለግኩት ነው። ኀሠሣ ስልት ላይ ነኝ ማለት ይቻላል።

የሚቀጥለው ሥራሽ ምን ላይ የሚያተኩር ነው?

ወጥ ስራን በተመለከተ፣ ከላይ በአጭሩ አስቀምጬዋለሁ። ትርጉምን በተመለከተ፣ በአሁኑ ሰዓት ቅርብ ጊዜ ገበያ ላይ ውሎ ተወዳጅነት ያተረፈውን የዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉን “መንገደኛ” ወደ እንግሊዘኛ እየመለስኩ እገኛለሁ። ሌሎችም ልተረጉማቸው የምፈልግ መጻሕፍት አይጠፉም።

 

እናመሰግናለን።       

እኔም አመሰግናለሁ

ሕይወት ታደሰ

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

መስከረም 2010 ዓ.ም

“ሙሉጌታ አለባቸው” (ቃለመጠይቅ)

“ቆይታ ከሙሉጌታ አለባቸው ጋር”

(ቃለመጠይቅ)

.
[ከአንድምታ ጋር የተደረገ ውይይት]

.

[ሙሉጌታ አለባቸውን በርካቶቻችን የምናውቀው በያዝነው ዓመት ባሳተመው “መሐረቤን ያያችሁ” የተሰኘ የልብወለድ መጽሐፉ ነው። አንዳንዶቻችንም በተወዳጁ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣ እና በቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት አጭር ልብወለዶቹን እና ትርጉሞቹን አንብበናል። ምናልባት ጥቂቶቻችን ደግሞ “መቅረዝ የኪነጥበብ አፍቃሪያን ማኅበር” ውስጥ አብረነው ተወያይተን ይሆናል።

ሙሉጌታ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በወልዲያ፣ ከፍተኛ ደረጃውን ደግሞ በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ተከታትሏል። በሥራ በኩልም በጋዜጠኝነት፣ በተርጓሚነት፣ በአርታዒነት እና በሕዝብ ግንኙነት ዘርፎች በማገልገል ላይ ይገኛል። በትርፍ ጊዜውም ሥነጽሑፋዊ መጣጥፎችን እና ድርሰቶችን እያቀረበ ነው። አንድምታ ሙሉጌታን በቅርቡ በሥነጽሑፍ ዙርያ አነጋግራው ነበር።]

በቤታችሁ የነበረው የትረካ ንባብ ባህል ምን ይመስል ነበር?

ልጅነቴ በትረካ የተሞላ ነበር። ያሳደገችኝ አደይ ብዬ የምጠራት አያቴ ናት። የእሷን ሩብ ያክል እንኳን መተረክ ብችል እንደ እኔ ያለ ጸሐፊ አይገኝም ነበር። ከተረከችልኝ ውስጥ “የየዋህ ባልና ሚስቶቹን”፣ እንዲሁም “የአያ ድቡልቡሌን” ታሪክ ሳስታውስ አሁን ራሱ ምናቤ በግልፅ በተሳለ ጣፋጭ ትውስታ ይሞላል። አባቴ እና እናቴ ደሞ አስተማሪዎች ነበሩ። አባቴ ጠዋት የእንግሊዝኛ ተረቶች እያነበበ ይተረጉምልኝ ነበር። “The Axe Porridge” አስታውሳለሁ። ርዕሳቸው የጠፋብኝ ሌሎች ብዙ ተረቶችም አሉ። እሱ ጠዋት በእንግሊዝኛ ተረት የከፈተውን ቀኔን ማታ አደይ በአማርኛ ተረት ትዘጋዋለች።

ፊደል መቁጠር ከጀመርኩ በኋላ የመጀመሪያው ሰፊ የንባብ ጊዜዬ የክረምት ወቅት ነበር። በእርግጥ ሁለቱም ወላጆቼ አስተማሪዎች ስለነበሩ ሳልወድ ከዓመት እስከ ዓመት ወረቀት ላይ ማፍጠጥ ነበረብኝ። አንደኛ ደረጃን እስክጨርስ ልክ ሰኔ ላይ ትምህርት እንደተዘጋ የሚቀጥለው ክፍል መጽሐፎች ቤት ድረስ ይመጡልኛል። ከመደበኛ የትምህርት ጥናት ሸፍቼ ልቦለድ እና ታሪክ ንባብ ውስጥ ሳልሠወር በፊት የክረምት ንባቤ ሳይንስ፤ ኅብረተሰብና ስነ-ሕይወት ነበር።

ቆይቶ ግን ከትምህርት ውጪ ያሉ መጽሐፎች ይመጡልኝ ጀመር። አማርኛ መማሪያ መጽሐፎች ውስጥ ያሉትን ታሪኮችም እወዳቸው ስለነበር የሌሎች የክፍል ደረጃዎችን መጽሐፎች እየተዋስኩ አነባለሁ። “መጀመሪያ የመቀመጫዬ ይውጣ” ያለችው ዝንጀሮ ታሪክ በግጥም ሁሉ ነበር። አሁን ድረስ አልረሳውም። መማሪያ መጽሐፎቻችን ውስጥ ከ“ደማሙ ብዕረኛ” (መንግሥቱ ለማ)፣ ከታደሰ ሊበን፣ ከበአሉ ግርማ ሥራዎች የተቀነጨቡ ታሪኮች ነበሩ።

ተወልጄ ያደግኩባት የወልዲያ ከተማ የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ይመስገንና “ላጠና ነው” በሚል ሰበብ ሄጄ ብዙ አነብ ነበር። ሥራዎቹን በአማርኛ ትርጉም አንብቤ በሼክሲፒር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደመምኩት እዚያ ነው። አሁን የዘነጋኋቸውን ግጥሞች ከመጻሕፍት እየገለበጥኩ ቤት ተመልሼ ለአደይ አነብላት ነበር። የኪራይ መጽሐፍትም ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ሁለት ወር ክረምት ከክፍሌ የምወጣው ሌላ መጽሐፍ ተከራይቼ ለማምጣት ብቻ ነበር ብል ያጋነንኩት ትንሽ ብቻ ነው። በጊዜው መጽሐፍት ማከራያ ቤቱ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ አንብቤያቸው ነበር። ሆኖም እንደ አሁኑ መራጭ አንባቢ አልነበርኩም።

እስቲ ስለትምህርት ቤት እና ልጅነት ትውስታዎችህ አካፍለን።  

አምስተኛ ክፍል ስገባ አባቴ እንግሊዝኛ እናቴ ደሞ አማርኛ አስተማሪዎቼ ነበሩ። ያኔ ይሆናል ሳላስበው በቋንቋ የተመሰጥኩት። ከአማርኛ አስተማሪዎቼ የማስታውሰው የአሥራ ሁለተኛ ክፍል አማርኛ አስተማሪዬ ነው። የታዋቂ ሰዎች የሕይወት ታሪክ እንዲያመጣልኝ እየጠየቅኩት በእንግሊዝኛ የሚያመጣልኝን ጽሑፍ እየተረጎምኩ በሚኒሚዲያ አቀርብ ነበር። በቁም ነገር የሚሠራ ትልቁ የክበብ እንቅስቃሴ ውስጥ የገባሁት ግን “ራዕይ” የተባለ የአማተር የስነ-ጽሑፍ እና የጋዜጠኞች ማሕበርን ስቀላቀል ነው። እዚያ ውስጥ ያሉ ሰዎች በጣም ጠንካራ ናቸው። በሳል ከያኒያን ናቸው። እኔ በዕድሜም ትንሽም ነበርኩ። በእውነት ሳስበው በዚያ ዕድሜዬ እነሱ መካከል መገኘት ባይገባኝም እንድገኝ አድርገውኛልና አመሰግናቸዋለሁ። አስበው ዛሬ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ እንኳን የማይደረገውን ያኔ አንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ ወቅቱን እየጠበቀ የሚወጣ ጋዜጣ ነበረን!

ከእንግሊዝኛ ቋንቋ እና ሥነጽሑፍ ጋር እንዴት ተዋወቅክ?

እንግሊዝኛ አንብቤ መረዳት ስጀምር አባቴ ያነብልኝ የነበረውን የተረት መጽሐፍ በራሴ ማንበብ ጀመርኩ። ከዚያም ወልዲያ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ሄጄ “Short Story International” የተባለ በተከታታይ የሚወጡ የዘመናዊ ጸሐፊዎችን ሥራዎች የያዙ በርካታ መጻሕፍት አገኘሁ። “The Penguin Book of Very Short Stories” የሚልም ነበረ። ከእነዚህ ጥቂቱን ተርጉሜያቸዋለሁ።

ኮስተር ብዬ ማንበብ የጀመርኩት ግን ዘግይቼ ነው። በሀዋሳ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ (አአዩ)። በተለይ በአአዩ ቆይታዬ ሰፊ የማንበቢያ ጊዜ ነበረኝ። ኬኔዲ ቤተ-መጻሕፍት ብዙ መጽሐፎቹ ጠፍተውበት እንኳን ብዙ ሰጥቶኛል። በኋላ ላይ የተወሰኑትን ወደ አማርኛ የተረጎምኳቸውን የጄምስ ጆይስን ሥራዎች፤ ቻርለስ ዲከንስ፤ እና የግሪክ ጸሐፌ ተውኔቶችን ሥራዎች የእነ ሶፎክለስ፣ የእነ አሪስቶፌንስ፣ የሌሎችም። ፈራ ተባ እያልኩ ፍሮይድ እና ያንግን ማንበብ የጀመርኩትም እዚያው ነው። ጸጋዬ ገብረ መድኅን በዋናነት በአማርኛ እንደተጻፉ አድርጎ ያቀረበቸውን የሼክስፒር ተውኔቶች አንብቤ በተአምራዊ ቋንቋው የማለልኩትም በዚህ ጊዜ ነበር።

ዋሳ ኒቨርስቲ ሥነጽሑፍ እንድትማር እን ወሰንክ?

አስቤው አልነበረም። ፍላጎቴ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋዜጠኝነት መማር ነበር። አሁን ሳስበው እዚህ የትምህርት ክፍል ውስጥ ባለመመደቤ ራሴን እንደ ዕድለኛ እቆጥራለሁ። ምክንያቱም የተመደብኩበት የትምህርት ክፍል በዋናነት ሥነ-ጽሑፍ ላይ ቢያተኩርም ከጋዜጠኝነት ጋር ስለሚያያዙ ጉዳዮች ሁሉ በቂ እውቀት ጠቅለል አድርጎ ሰጥቶኛል። ጋዜጠኝነት፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ አርትኦት፣ ማስታወቂያ ወዘተ…

ዋሳ ሳለህ “መቅረዝ የኪነጥበብ አፍቃሪያን ማኅበር ውስጥ ምን አይነት እንቅስቃሴ ደረ ነበር?

ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነበረኝን ቆይታ የማይዘነጋ እንዲሆን ካደረጉልኝ ነገሮች አንዱ መቅረዝ ነው። በየሳምንቱ አንዴ እንገናኝና ሁሉም የጻፈውን ያነባል። ጠንካራ የሂስ ባህል ነበረን። በተማሪነት ዘመኔ እንደዛ ዓይነት ቀጥተኛ እና ክሪቲካል ሂስ መሰጣጠት ለምጄ በኋላ ሰፊው ዓለም ውስጥ ስገባ ግን በተቃራኒው ሆኖብኝ ሁኔታውን ለመረዳት ተቸግሬ ነበር። በአብዛኛው በግል ትውውቅ መረብ እና ካብ ለካብ በመተያየት ደንብ እንደሚዘወር ሲገባኝ እውነታው ይሄ ነው ብዬ ለመቀበል ጥቂት ጊዜ ወስዶብኛል።

መቅረዝ ውስጥ የተመረጡ ሥራዎችን የምናቀርብባቸው ዝግጅቶችም ነበሩን። መቅረዝ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል አቻ ነበር። አብዛኞቹ አባላቱ በአሁኑ ሰዓት ታዋቂ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎች እና ገጣሚዎች ሆነዋል። ራሳቸውን ቢደብቁም ውብ ግጥሞችና አስደማሚ ትረካዎችን የሚጽፉም አሉ።

ዋሳ ሳለህ የአማርኛ ሥነጽሑፍ ንባብህ በምን መልኩ ተቀየረ? የእንግሊዝኛስ?

አንድ የንባብ ቡድን ነበረን፤ በየወሩ ገንዘብ እያዋጣን በአባላቱ ጥቆማ መሠረት መጽሐፍት ገዝተን እሱን በተራ እናነባለን። በአብዛኛው የአማርኛ መጻሕፍት ነበሩ። በዋናነት ታሪክ እና ስነ-ጽሑፍ። መጻሕፍት ከማገኘትም በላይ ጓደኞቼ ምን ዓይነት መጽሐፍ ማንበብ እንዳለብኝ አቅጣጫ ይሰጡኛል። እንደ በፊቱ በአግበስባሽት ማንበብ አይቀጥልም።

የተማርኩት ትምህርት የእንግሊዝኛ ስነጽሑፍ ውስጥ የትኞቹን ግጥሞች፤ የትኞቹን ልቦለዶች እና የትኞቹን ትያትሮች ማንበብ እንዳለብኝ መንገዱን መርቶኛል። አሁን ድረስ አንብቤ ያልጨረስኩት መለሎ የርዕሶች ዝርዝር አለኝ። የምማረው ትምህርት ራሱ ሥነ-ጽሑፍን ማንበብና መረዳት ስለነበር በደስታ ብዙ አነባለሁ። አንብብ ተብዬ በአስተማሪዎቼ ከታዘዝኩት ዘልዬ ሁሉ የዩኒቨርሲቲው ቤተ-መጻሕፍት የደረደራቸውን መጻሕፍት እገላልጣለሁ። የሄሚንግዌይን A Farewell to Arms እና የቼኑ አቼቤን No Longer at Ease በባዶ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተቀምጬ ሳነብ አስታውሳለሁ። የጄኬ ሮውሊንግስ መሳጭ ፋንታሲ Harry Potter Seriesን ከአንድ ወዳጄ ጋር እየተሽቀዳደምን ደጋግመን እናነብ ነበር።

የትርጉም ሥራዎችስ በዚህ እድሜህ ወቅት ሞካክረህ ነበር

ትርጉም መስራት የጀመርኩት በ1998 ዓ.ም. ነው። አስራ ሁለተኛ ክፍል ነበርኩ። ለትምህርት ቤታችን ሚኒ ሚዲያ ከማዘጋጀው ውጪ በጊዜው እሳተፍበት በነበረው የሥነ-ጽሑፍ እና የጋዜጠኞች ማሕበር አቀርብ ነበር።  የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍት ሄጄ ሙሉውን ታሪክ በእጄ ጽፌ ከገለበጥኩ በኋላ የምተረጉመው ቤቴ ሄጄ ነበር። በእንደዚህ ‘ጥንታዊ’ ዘዴ የሠራኋቸው እንደ “Shoboksh and the Hundred Years” (የግብጽ አገር ልቦለድ) ያሉ አጫጭር ልቦለዶች ነበሩ።

ከዚያ በኋላም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ደግሞ የስነ ጽሑፍ ኮርሶች ውስጥ መማሪያ ሆነው የሚመጡ ግጥሞችና አጫጭር ልቦለዶችን መተርጎም ደስ ይለኝ ነበር። እነ ጆን ኪትስ፣ ወርድስወርዝ፣ ሼሊ፣ ቴኒሰን እና የሌሎችም ገጣሚያን ሥራዎች። La Bella Dame Sans Merci (“ምሕረት የለሿ ልዣገረድ”) እና Ode to a Nightingale በተለይ አይረሱኝም። ከአጫጭር ልቦለዶችም የልዩ ልዩ አገራት ጸሐፊዎችን ድርሰቶችን እተረጉም ነበር። የእነ ጆቫኒ ቦካሺዮ እና የእነ አንቶን ቼኮቭ። የቼኮቭን “ቫንካ” ተርጉሜ ዶርም ውስጥ ስናነብ አስታውሳለሁ። ከቼኑ አቼቤ አጫጭር ልቦለዶችም እንደዚሁ ለመቅረዝ አቀርብ ነበር።

በአዲስ አበባ ርስቲ የድኅረ ምረቃ የመመረቂያ ጽሑፍህን ርእስ እን መረጥክ?

ርእሴን (Stream of Consciousness) የመረጥኩበት ምክንያት በቴክኒኩ ፍቅር ስለወደቅኩ ነው። ሆኖም አሁን ላይ ሳየው የመመረቂያ ጽሑፌ በኩራት የማቀርበው ሰነድ አይደለም። የሠራሁት አዳም ረታ “እቴሜቴ ሎሚ ሽታ” ላይ ነበር። ብዙ የተመሰጥኩት በመጽሐፉ ቅርጽ ላይ ነበር፤ ይዘቱን ስቼዋለሁ ሁሉ! ከመጀመሪያ ዲግሪዬ የመመረቂያ ጽሑፍ በተቃራኒ፤ የድኅረ ምረቃ ትምህርት የመመረቂያ ጽሑፌ በአሳዛኝ ሁኔታ እንጭጭ የግብር ይውጣ ሥራ ነበር። ለዚህ በዋናነት ተጠያቂው የግል ስንፍናዬ ቢሆንም ዛሬ ላይ ቆሜ ሳየው ግን ሌሎች ምክንያቶችም ነበሩ።

አሁን ዓለም አቀፍ የሥነ-ጽሑፍ ጆርናሎች ላይ የሚወጡ ጽሑፎችን የማየት ዕድል አግኝቻለሁ። መሥፈርታቸው እና የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ ሳይ ‘ከዚህ ቢፊት የሠራሁት ምንድን ነበር?’ የሚል ማወዳደር ውስጥ እገባለሁ። ተማሪዎች ምርጥ የምርምር ጽሑፎችን ማዘጋጀት የማይችሉት የእኛ ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ምን ቢጎድለው ነው? ብዬ እጠይቃለሁ።

ባለፉት ዓመታት ስቡክ ውስጥ ስለተጀመረው የኪነጥበብ ውይይት ምን ትውስታ አለህ?

አአዩ ውስጥ ሳለሁ በፌስቡክ ኪነ ጥበባዊ ውይይቶችን የሚያደርጉ ጥቂት ግለሰቦችን አይቻለሁ። መጀመሪያ ላይ ጠንካራ ሊባሉ ለሚችሉ ሥነ-ጽሑፋዊ ክርክሮች ምቹ ቦታ ነበር። በደራሲዎቻችን ስሞች በተከፈቱ የፌስቡክ ቡድኖች ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ብዙ መረጃዎችን የሚለዋወጥ፣ ጠባብ ቢሆንም ጠንካራ እንቅስቃሴ ነበር። አሁን ከስሟል።

የሳይበር ግንኙነት በጊዜ እና በቦታ በተራራቁ ሰዎች መካከል እንዲካሄድ ስለሚያስችል በባሕሪው ኀይለ ቃል መለዋወጥና መዘረጣጠጥን ይፈቅዳል። ሥነ-ጽሑፋችን ውስጥ ከጥንት የነበረውን በግል የትውውቅ መረብ የመደናነቅ/የመነቃቀፍ ልማድም አጉልቶቷል። በቃላት ከተደረተ ጽንፈኛ ትችት በስተቀር ውኃ የሚያነሳ ሀሳብ ይዞ የሚሞግት የሥነ-ጽሑፍ ሂስ እና ውይይት ያነበብኩበት ጊዜ እጅግ ጥቂት ነው።

የጋዜጠኝነት ዘመንህ የሥነጽሑፍ ፍቅርህን አደበዘዘው ወይ አጠነከረው?

ጋዜጠኝነት ሥነ-ጽሑፍን ሊተካልኝ አልቻለም። ተርጓሚነትም እንደዛው። ስለዚህ ሥራዬም እረፍቴም ሥነ-ጽሑፍ ነበር ለማለት አልደፍርም። በጋዜጠኝነት ዋና ሥራዬ መረጃ መሰብሰብና አቀናጅቶ ማሰራጨት ነበር። ጋዜጠኝነት ተጨባጭ መረጃን በማነፍነፍ ተጠምዷል። ስለዚህ ሥነ-ጽሑፍን ሊተካልኝ አይችልም። ከጋዜጠኝነት ደረቅ የመረጃ ስርጭት ለማምለጥ የሚረዱኝ ስልቶች ግን ነበሩ … አንደኛው የመጻሕፍት ዳሰሳዎችን መሥራት ሁለተኛው ደሞ ለሌሎች ጋዜጦችና መጽሔቶች መጻፍ። እነ “አዲስ አድማስ” እና “አዲስ ጉዳይ” ማምለጫ ቀዳዳዎቼ ነበሩ።

ሙሉ ጊዜህን ለሥራ ዓለም ብትሰጥም ባለህ ትርፍ ጊዜ ጥበባዊ ድርሰቶችን እየሰራህ ነው። የእንጀራ እና የጥበብ ነገር እንዴት ነው?

የተለመደ አባባል ልጠቀምና “ጥበብ ጠራችኝ” ብልም የእንጀራ ጥሪ ጎልቶ ይሰማኛል። ምንዳ ስለሚከፈለኝ አይደለም። ጽሑፍን እንደምወደው ሁሉ ሥራንም እወዳለሁ። ስለአንድ ፕሮጄክት ዝርዝር ጉዳይ ተጨንቄ ሥራውን በስኬት ማጠናቀቅ አንድ አጭር ልቦለድ ጽፎ ከመጨረስ የማያንስ ደስታ ይሰጠኛል። በአጭሩ ለሥነ-ጽሑፍ ፍቅር ብዬ የእንጀራ ገመዴን አልበጥስም ማለት ነው።

የስብሐት እና የበአሉ ግር ሥራዎች በአንተ ውስጥ ስለተዉት አሻራ የምትለው አለ?

የስብሐት እና የበአሉን ሥራዎች በጣም እወዳለሁ። ከስብሐት ሥራዎች በተለይ “አምስት ስድስት ሰባት” አንጀቴን ያርሰኛል። ፋንታሲው ጠቅልሎ ወደ ሌላ ዓለም ይወስደኛል። ሁልጊዜም ሲጽፍ ሕይወትን ነው። በአሉም እንደዛው። በተለይ “ከአድማስ ባሻገር” ልብ ላይ የሚደርስ ሥራ ነው። ደሞ በሌላ መጽሐፉ ውስጥ ያቺ ውብ የበአሉ ግጥም አለች!

“የኔ ውብ ከተማ የኔ ውብ አገር

የሰው ልጅ ልብ ነው፤

የሌለው ዳርቻ፣ የሌለው ድንበር!”

ከልብወለድ እኩል የግጥም ፍቅር ያለህ ይመስላል።

ቃላትን ወድጄ የግጥም ፍቅር ባይኖረኝ ግዙፍ ምጸት ይሆን ነበር። ሆን ተብለው በተመረጡ ቃላት የተዋቀረች አንዲት ስንኝ ካነበብኩ መጽሐፉን ዘግቼ በሀሳብ ጭልጥ እላለሁ። ግነት አይደለም። አንዳንዱ ቀኔ ጠዋት አንብቤው በምወጣው ነገር ይወሰናልና ምን ማንበብ እንዳለብኝ እጠነቀቃለሁ። እንደ ዮሐንስ አድማሱ “እስኪ ተጠየቁ” ዓይነት ነገር በጠዋት ካነበብኩ ቀኑን ሙሉ ተረብሼ እውላለሁ።

“አዋሽ ማዶ አብረን እንውረድ” ሲል ጸጋዬ፣ ወይም ገብረክርስቶስ “የፍቅር ሰላምታ” ሲል ፍቅር ካልተሰማኝ ቃላት መውደዴን መጠራጠር መጀመር አለብኝ። የደበበንም “ጊዜ በረርክ በረርክ” ሳነብ ልቤን ካልነዘረው። በእውቀቱ ደግሞ ድንቁን ሀሳብ በውብ ቋንቋ አሽሞንሙኖ በልዩ የስንኝ ምጣኔው ሲያስቀምጥ ካልተገረምኩ “በድንቅ አብቃይ ምድር” ሳይገርመኝ እየኖርኩ የማልፍ ትውልድ ሆንኩ ማለት ነው።

እንደመታደል ሆኖ የአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ በዝርው ከሚያቀርብልኝ አማራጮች በላይ በሥነ-ግጥም ሰጥቶኛል። ከምወዳቸው ደራሲያን ቁጥር የምወዳቸው ገጣሚያን ቁጥር ይበልጣል።  ደበበ ሰይፉ፣ ነቢይ መኮንን፣ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣ ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ ዮሐንስ አድማሱ፣ ገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ሰለሞን ዴሬሳ፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣ ጌትነት እንየው፣ የሻው ተሰማ፣ ቴዎድሮስ ፀጋዬ … መአት ናቸው። በመጽሐፍ መልክ ባይሆንም እንኳን የዘፈን ግጥም አለልኝ። በብዛት አለመገኘቱ እንጂ ዝርው ግጥምም አለ!

ከአዳም ረታ ሥራዎች ጋር ስለተዋወቅክበት ኔታ እስቲ ትውስታህን ብታጋራን

በ2000 ዓ.ም ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ማደሪያ ክፍላችን ውስጥ በሚገኘው ሎከር ከተደረደሩት መጻሕፍት መካከል አንድ ወፈር ያለ “ግራጫ ቃጭሎች” የተሰኘ ልቦለድ መዝዤ ማንበብ ስጀምር እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ሁሉም ቦታ ይዤው የምዞረው ጥራዝ ይሆናል ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር።

የቅርጽ እና የይዘት ድንቅ ውሕደቱ ምን ጊዜም አይጠገብም። ከእንጀራ የተቀዳው ቅርጹ ልቦለዱን ከዓይን እስከ ሰበከቱ እየደጋገምኩ እንድበላው/እንዳነበው ያደርገኛል። በገጸ ባሕሪያቱ ተደንቄ ሳልጨርስ በጣፋጭ ቋንቋው እገረማለሁ። ጎልቶ በማይታይ ሤራ መሳጭ ልቦለድ እንደሚጻፍ ሌላ ማሳያ ነው። ይሄው እስከ ዛሬ ድረስ ዋና ገጸ ባሕሪው መዝገቡ ሥጋ እንደለበሰ ሰው እንጂ በመጽሐፍ ገጾች መካከል እንደሚገኝ ምናብ ብቻ አልቆጥረውም።

ግራጫ ቃጭሎችን ደግሜ ባነበብኩት ቁጥር ከዚህ በፊት ያላየሁት ነገር አገኛለሁ። በጥቅሉ በአማርኛ ቋንቋ እንደዚህ ሊታሰብ እና ሊጻፍ መቻሉ አስደመመኝ።

እጅህ ላይ ስላሉት ድርሰቶች እና ውጥኖች ጥቂት ብትነግረንስ?

የአጫጭር ልቦለድ ቢጋሮች አሉኝ። ሆኖም አሁን ትኩረቴ እሱ ላይ አይደለም። አምርሬ ከመጀመሬ በፊት ማንበብ አለብኝ። ከልቦለድ ውጪ ግን የጀማመርኳቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል አንድ ልዩ መጽሐፍ አለበት – ለአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ያልተለመደ ዓይነት መዝገበ ቃላት ነው። በቅርቡ ይታተማል ብዬ ተስፋ አለኝ …

ለቆይታው እናመሰግናለን።

 እኔም አመሰግናለሁ።

.

ሙሉጌታ አለባቸው

(ቆይታ ከአንድምታ ጋር)

ሐምሌ 2009 ዓ.ም

.

የደራስያኑ ጦርነት

የደራስያኑ ጦርነት – መንግሥቱና ጸጋዬ

ከብርሀኑ ዘሪሁን

.

[በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ]

.

ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ እንቅስቃሴ ይልቅ፣ በጥቂቶች ኢትዮጵያውያን የሥነ ጥበብ ቡድኖች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተፋፍሞ ይገኛል። ያልታወጀ ጦርነት ነው። አንዱ ቡድን እግር ይበጥሳል። ሌላው አንገት ለመቁረጥ ይሞክራል።

ሰሎሞን ደሬሣን በ“Addis Reporter”፣ ተቃዋሚውን አንባቢ በ“አዲስ ዘመን”፣ አሁንም ሰሎሞንን በ“African Arts” የሦስት ወር መጽሔት፣ መንግሥቱ ለማን እና ጸጋዬ ደባልቄን በ“የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ያነበበ፣ አልፎ አልፎም የእነ ዓለማየሁ ሞገስን የእነ ዮሐንስ አድማሱን ንግግር ያዳመጠ ሁሉ፣ ከመደነቅ ጋር ምናልባት ግራ ሳይጋባ አልቀረም። ስለምንድን ነው ትንቅንቁና ፍጅቱ?

ከመሠረቱ በሥነጥበብ አካባቢ የአስተያየት ግጭት አዲስ ነገር አይደለም። የመናናቅና የመቀናናት ስሜት አለ። የሥነጥበብ ሰዎችም፣ እንደሌላው ሁሉ ደካማ ፍጡሮች ናቸውና። ከዚህ ጋር ደግሞ፣ የሐሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት ሲታከልበት መጨፋጨፍ ነው። ደግነቱ የሥነጥበብ ሰዎች በሰይፍ አይፋለጡም። በዚያው በብዕር ጫፍ መቦጫጨር ነው።

ቤርናርድ ሾው (Bernard Shaw) ቶልስቶይን “ማጫራ እንጅ ደራሲ አይደለም” ይል ነበር። በሀገራችን (ሁለቱንም በሰማይ ነፍሳቸውን ይማርና) አለቃ ታየ እና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ለገላጋይ አስቸግረው ነበር ይባላል።

ሟቹ ፕሮፌሰር ተአምራት እና ቋሚው አስረስ የኔሰው በ“ኤርትራ ድምፅ” ጋዜጣ ላይ በየሳምንቱ በመቃ ብዕር (እንደዛሬው ጭቃ ቀለም አልመጣም ነበርና) የሚሸቃሸቁበት ዓምድ ነበራቸው። ታዲያ፣ አንዱ እጁን አንስቶ ተማርኮ ወይም ወድቆ ድሉ የማን እንደሆነ በሚገባ ሳይለይ ሁለቱም ተዳክመው ውጊያውን ተዉት።

ምናልባት አቀራረቡ የተለየ ይመስል እንጅ የአሁኑም የሥነጥበብ አካባቢ ጦርነት በመሠረቱ ያለፈው ዓይነት ነው።

እንደጊዜያችን ዓለም ሁሉ፣ የሥነጽሑፍ ጦርነትም አራጋቢዎችና አስታራቂዎች፣ ዝምተኛ ተመልካቾች፣ ሦስተኛ ኀይል ለመሆን የሚፈልጉ ገለልተኞች አሉበት። ከዚያም ሁለቱ ኀያላን ይመጣሉ። ይህ ምናልባት ትንሽ የተጋነነ አገላለጽ ሊመስል ይችላል። ግን ከእውነተኛው በጣም የራቀ አይደለም።

እርግጥ ጸጋዬ ገብረመድኅን፣

“ምን ዓይነቱ ነው! ጦርነት አትበሉት! ለማባባስ ነው!” ይላል።

አቶ መንግሥቱ ለማ ደግሞ በዚያ የለሰለሰ የዲፕሎማሲ አንደበት፣

“ኤዲያ እንዲያው እናንተ ደግሞ ነገር መጐርጐር ትወዳላችሁ! አሁን ምን ያስፈልጋል!” ይላል።

ጸጋዬ ገብረመድኅን ሦስተኛውን፣ መንግሥቱ ለማ አራተኛውን የሥነጽሑፍ ሽልማት ባይወስዱ፣ ሁለቱም ከናካቴው ባይሸለሙ ኖሮ ምናልባት ጦርነታቸው ባልተካረረ ነበር። መንግሥቱ ለማ “ከኔ ቀድሞ ማግኘት አልነበረበትም” ቢል፣ ጸጋዬ ደግሞ “ከኔ መከተል አልነበረበትም” ባይ ነው። አንደኛው ሽልማቱን በተቀበለበት ጊዜ ሌላው ምን ያህል እንዳረረና እንደተከዘ እግዚአብሔር ይወቅ። ምናልባትም ብዙ የአረቄ ጠርሙሶች ተንጠፍጥፈው አድረው ይሆናል። መሳሳብ መገፋተር፣ መቀራረብ መራራቅ፣ መፋቀር መጣላት፣ ይህ ሁሉ በሰው ተፈጥሮ የደካማነትም ባይሆን የተለመደ ባሕርይ ነው። ተፈጥሮ ነው እንበል?

ጸጋዬ ገብረመድኅን እና መንግሥቱ ለማ (ወይም በስም አወሳስ አደላችሁ እንዳንባል) መንግሥቱ ለማ እና ጸጋዬ ገብረመድኅን የመጀመርያ ግንኙነታቸውም ቢሆን እስከዚህም ድረስ የመቀራረብ ወይም የመሳሳብ ኀይል አልነበረበትም።

IMG_4943Menge portraitሁለቱ የሥነጽሑፍ ሰዎች በብዙ ረገድ አይመሳሰሉም። ጸጋዬ ጠይም ረጅም ነው። በበጋውም በክረምቱም ወፍራም ድሪቶ ሹራብ ከማዘውተሩ በቀር፣ ስለ አለባበሱና ስለ አነጋገሩ ጥንቃቄ የለውም። ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ከአፉ የሚወጡት ቃላት የእረኛ ስድቦች ናቸው። ጳውሎስ ኞኞ አንድ ጊዜ “አንደበተ እረኛ” ሲል ጠቅሶት ነበር። ብቻ በክፋት አይደለም። መሳደቡም ማቆላመጡ ሊሆን ይችላል። ንግግር ሲያደርግ ተሞልቶ እንደተለቀቀ ሞላ ይተረተራል። የሚለውን ሁሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ታዲያ “ምን ትንተባተባለህ!” ቢሉት ግድ የለውም።

መንግሥቱ ደግሞ ቀይ፣ ቁመናው ወደ እጥረቱ የሚያደላ፣ በሙያውም በአነጋገሩም በሁናቴውም ዲፕሎማት ነው። ከሚያዜመው ድምፁ ጋር ቀስ ብሎ ሲናገር፣ ሲጫወት፣ ሲተርብ ያውቅበታል። ይራቀቅበታል። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ “ማሽሟጠጡን ያውቁበታል” ነው ያለው? አዎ! እንደ ዜማው፣ እንደ ዘይቤው፣ እንደ ቅኔው ትርጓሜ … የመንግሥቱ ለማ ምስጋና … ነቀፋና ስድብ ሊሆን ይችላል።

ተቃራኒ የማግኔት ጫፎች ይሳሳባሉ እንደሚለው የፊዚክስ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ የሁለቱ ደራስያን ባሕርይ ሁናቴ አለመመሳሰል ሊያወዳጃቸው በተገባ ነበር። ግን ከመጀመርያው አንስቶ፣ በመካከላቸው የመቀራረብ ስሜት የተፈጠረ አይመስልም። የተዋወቁት የጸጋዬ “ቴዎድሮስ” ቴአትር (በእንግሊዝኛ) ስለመታየቱ ዶክተር ካፕላን ባዘጋጀው ግብዣ ላይ ነበር። ከዚያ በፊት አንዱ ስለሌላው ሳይሰማ አልቀረም።

የመንግሥቱ “የግጥም ጉባኤ” ዝነኛ ሆኖ ነበር። ጸጋዬም በመጀመርያ ቴአትሩ አቶ አሐዱ ሣቡሬ በየዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ ካደፋፈሩትና “የሾህ አክሊል”ንም ካቀረበ ወዲህ ስሙ በጋዜጣ ላይ እየተደጋገመ መውጣት ይዞ ነበር። ምናልባት ያን ጊዜ ለወጉ ለማዕረጉ እጅ ተጨባብጠው አንዳንድ መልካም ቃላት ተለዋውጠው ይሆናል። ዛሬ ጸጋዬ፣ “ያን ቀን ‘እንዴ እንዴ ደኅና ሥር የያዝክ ይመስለኛል’ (በእንግሊዝኛ) ሲል መንግሥቱ የተናገረው ትዝ ይለኛል” ይላል። ልዩ ስሜትና ትርጓሜ በማሳደር የታወሰው ከጊዜ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።

ምክንያቱም፣ ከዚያ በኋላ ለአጭር ጊዜ መቀራረብ ጀምረው ነበር። ሁለቱ ብቻ አይደሉም። ሁለቱን ጨምሮ፣ ጥቂቶች ዘመናውያን ደራሲዎች የሥነግጥም ምንባብ ብጤ አቋቁመው ነበር። እንደ ሀገራችን ማኅበር ሁሉ አንድ ቀን ከአንዱ ቤት፣ ሌላ ቀን ከሌላው ቤት ይሰበሰባሉ። ጠላ ባይጠመቅ ዳቦ ባይጋገር ውስኪው፣ አረቄው፣ ቢራው፣ ለስላሣ መጠጡ ፉት እየተባለ አንዱ ቅኔውን ወይም ሥነግጥሙን ያነባል። በኋላም ይተቻቹበታል። የክበቡ ተግባር ይህ ነበር። በኋላም የሥነግጥም ምንባቡ በቀ.ኃ.ሥ ኪነጥበባት ወቲያትር ቤት ውስጥ እንዲደረግ ታስቦ ነበር። በመካከሉ የክበቡ አቋም እንደ በረዶ ሟሸሸ። ጸጋዬ እንደሚለው ለመሟሸሹ ዋናው ምክንያት መንግሥቱ ነው።

በመካከሉ፣ ጦርነቱን ያባባሰው የዳካሩ “የጥቁር ዓለም ሕዝብ የሥነ ጥበብ በዓል” መጣ። ምናልባት ስለ በዓሉ በመጀመርያ ያወቀ እሱ ብቻ ሊሆን ቢችል ባይችል፣ ስለ ተካፋይነቱ ጉዳይ በመጀመርያ ወደ ዳካር ሂዶ ከሴንጎር (Léopold Sédar Senghor) ጋር የተነጋገረው ጸጋዬ ነበር።

Senghorበዚያን ጊዜ ጸጋዬ “Oda Oak Oracle” የተባለውን የእንግሊዝኛ ድራማ አዘጋጅቶ ነበር። ስለ በዓሉ አስቀድሞ ስላወቀ አዘጋጅቶት ለበዓሉ አቅርቦት እንደሆን አስተያየት የማንሰጥበት ሌላ ጥያቄ ነው። ያን ጊዜ መንግሥቱ በውጭ ሀገር ቋንቋ የተጻፈ ድራማ አልነበረውም። በኋላም የአቶ ከበደ ሚካኤል “አኒባል” እንዲሄድ መደረጉ ይታወሳል። ወዲያውም በውጭ ሀገር ቋንቋ ተተርጉሞ ነበር።

ጸጋዬ እንደሚለው “Oda Oak Oracle” እንዳይሄድ በዚህም በዚያም ብሎ ያስቀረው መንግሥቱ ለማ መሆኑ ነው። ያን ሰሞን በሥነጥበብ ሰዎች አካባቢ የሚሰማው ሁሉ ራሱ አንድ ረጅም ሐተታ ይወጣዋል።

አንዱ ወገን፣

“በውጭ ሀገር ቋንቋ ማቅረብ ግድ ከሆነ ‘Oda Oak Oracle’ ግሩም ሥነጽሑፍ ነው። የእንግሊዝ ማሳተሚያ ድርጅት ሳይቀር የተቀበለው። ያም ባይሆን እንግሊዝኛው ‘ቴዎድሮስ’ አለ። የአኒባል ታሪክ ታሪካችን አይደለ። ባህላችን አይደል! ምንድነውኮ የሚሰራው?” ይላል።

የሌላው ወገን ደግሞ ሥራ አልፈታም፣

“እስቲ እግዜር ያሳያችሁ! ዋርካ የሚመለክበት፣ ሕፃን በአምልኮ የሚታረድበት የኢትዮጵያን ባህል፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ይወክላል እንዴ? የምዕራብ አፍሪቃ ታሪክ ከሆነ እነርሱው አሳምረው ያቀርቡታል” ይሉ ነበር።

ከግል የሰብአዊነት ስሜት በቀር በሁለቱ ደራስያን የአማርኛ ሥነጽሑፍ አስተሳሰብና አቀራረብ መካከል ልዩነት አለ።

Shilimat

በመጀመርያ የአስተሳሰብን ጉዳይ እንውሰድ። አስተሳሰባቸውም የወጡበትን አካባቢ የሚጠቅስ ሊሆን ይችላል። መንግሥቱ ለማ፣ አነጋገሩ የአማራ አማርኛ፣ ግዕዝ አዋቂ፣ ባይዘርፍም ቅኔ የቀማመሰ፣ የሰዋስው ሥርዓት አክባሪ ነው። ታዲያ የአማርኛ ሥነጽሑፍ በአማራ ሥነባህል፣ የአማራ ሥነባህል በቤተክህነት ሥነጥበብ፣ የቤተክህነት ሥነጥበብም በግዕዝና በቅኔ በሰዋስውና በአግባቡ የተመሠረተ ስለሆነ መጠበቅ አለበት ቢል ያስኬደዋል ማለት ነው።

በጸጋዬ አስተሳሰብ ደግሞ ቅኔን ለማወቅ መቃብር ቤት ማደር አያስፈልግም፣ “ቅኔ ከግዕዝ የተወለደ ነው። ቅኔና ሥነግጥም ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ደግሞ ዛሬ ጊዜ አማርኛ ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ሆኖ መታየት አለበት። ኢትዮጵያዊኛ ቋንቋ ነው። ኢትዮጵያዊኛም በመሆኑ መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ስሜትና አስተሳሰብ፣ ምኞትና ፍላጎት ህልውናና አኗኗር የሚገልጥ የሚተረጐም መሆን አለበት። ስለኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ስናስብ ከጠባብ አስተያየት መውጣት አለብን” ይላል።

Tsegaye_Gabre-Medhin

ጸጋዬ ስለ ቅኔ ችሎታው እጥረት ሼክስፒርን ይጠቅሳል፣

“ሼክስፒር በዚያን ጊዜ በሥነጽሑፍ ዓለም እንደ ትልቅ ቁምነገር በሚታየው በላቲንና በግሪክ በጣም ደካማ ችሎታ ነበረው። ነገር ግን ቃላት ፈጥሮ፣ ቃላት ከየትም ወርሶና አዋርሶ፣ የሚያፍነውንና የሚያስጨንቀውን የሰዋስው ደንብ ጥሶ፣ የእንግሊዝን ሥነጽሑፍ ከፍተኛ ብቃት ሰጠው።

“ለምሳሌ፣ ‘ጉዲፈቻ’ የሚለው ቃል በአማርኛ ምትክ አይገኝለትም። ‘ማደጎ’ የሩቅ ተመሳሳዩ ነው። ታዲያ ከኦሮምኛ መጣ ከወላይትኛ ለምን አንጠቀምበትም? ዞሮ ዞሮ ሥነጽሑፋችንን ያበለጽግልናል” ይላል ጸጋዬ።

እንደ ዳካሩ በዓል በቅርቡ አልጀርስ ላይ የሚደርገው የፓን አፍሪቃን የሥነጥበብ በዓል ደግሞ ለሁለቱ ደራስያን አንድ ሌላ የጦርነት መስክ ሳይሆን አልቀረም።

ብቻ አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። መንግሥቱ ለማ “ያላቻ ጋብቻ”ን በእንግሊዝኛ ተርጉሞ ተጨዋቾቹን በማሠልጠን ላይ ይገኛል። ካሁን ቀደምም በአንዳንድ የውጭ ዩኒቨርስቲዎች ቴአትሩ ታይቷል አሉ።

“እኔ አቀርባለሁ። መቸም መምረጡ የዳኞች ፈንታ ነው” ካለ በኋላ፣ “ለነገሩ ግን፣ የአቡነ ጴጥሮስ ቴአትር ወደ አልጀርስ መላኩ ለፖለቲካ የሚበጅ ይመስልሃል? ሰማኸኝ ወይ፣ በእኔ ቴአትር ስንኳ አንድ ሐጅ ካለበት” ሲል በቴሌፎን ያጫውታል።

ጸጋዬ ለአልጀርሱ በዓል ያሰበው ቴአትር ደግሞ ገና ለሕዝብ ያልቀረበ፣ “ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት” የሚል ነው። በጸጋዬ ግምት፣ ኢትዮጵያ የምትመካበት ዋና ሥነባህል፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነፃነታቸው ያደረጉት ተጋድሎ ነው። የጴጥሮስ አሟሟት ያኮራናል።

“ግን ቴአትሩን ያዘጋጀሁት ከመንግሥቱ ጋር ለመወዳደር ወይም አልጀርስ ለመሄድ አይደለም” ይላል።

“ ‘የከርሞ ሰው’ን ከፒንተር (Harold Pinter) ወስደህ ነው፤ ሼክስፒርንም በደንብ አልተረጐምክም ይልሃል” አልነው ጸጋዬን።

“ከየትም አምጥቶ፣ ሌላ ‘የከርሞ ሰው’ ይጻፍ እስቲ! እርሱም ይቅር፣ ‘ሐምሌት’ን ይተርጉምና እንይለት። ይተያይ። እንዲሁ ከመንቀፉ የሚያዋጣው ይኸው ነው” ሲል መለሰልን።

Mengistu smiling 2

ለማበላለጥና ለማባለጥ ሳይሆን፣ የጸጋዬ ድርሰት ቁምነገር ሲጫነው፣ የመንግሥቱ ለማ ወደ ቀልድ ያጋድላል። የጸጋዬ ጽሑፍ ስሜትን ይወጋል። ጸጋዬ በድርሰቱ ስሜት ውስጥ ራሱ ገብቶ እየተሰማው የሚጽፍ ይመስላል። በተመልካችና በአንባቢ ላይም ተመሳሳይ ስሜት ያሳድራል።

ለምሳሌ፣ ‘ጴጥሮስ ያችን ሰዓት’ን እንውሰድ። ጸጋዬ የጴጥሮስ ጭንቀት፣ የጴጥሮስ ሰቀቀን የተሰማው ይመስላል። የቴአትሩ ተመልካችም ሳይወድ በግድ ወደ አቡነ ጴጥሮስ የጭንቀትና የሰቀቀን ዓለም ውስጥ መግባት አለበት።

የመንግሥቱ ለማ አቀራረብ ደግሞ የተመልካችና የታዛቢ ዓይነት ነው። ሊያስቅ ሊያስደስት ይችላል። ግን የተካፋይነት ስሜት አያሳድርም። ለምሳሌ፣ ‘መጽሐፈ ትዝታ’ን ስናነብ የማናውቀው ሌላ ዓለም ይታየናል። በስሜት በዚያ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ግን አያደርገንም። ‘ያላቻ ጋብቻ’ም እንዲሁ ነው። ታላቋ እሜቴ ሲቆጡ፣ በለጤ ቡና ስታቀርብ፣ ባሕሩና በለጤ ሲሽኮራመሙ እያየን ከመደሰትና ከመሳቅ በቀር ወደ ስሜት ዓላማቸው ውስጥ አንገባም።

 

ታዲያ የሁለቱም ዓይነት ሥነጽሑፍ ዓለም ውስጥ ቦታ አላቸው። ተፈላጊዎች ናቸው። በየፊናቸው በየተሰጥኦዋቸው መወዳደር ይችላሉ።

የሚበጀው ግን ቀና ውድድር እንጅ አጉል ፉክክር አልነበረም።

.

ብርሃኑ ዘሪሁን

1961 ዓ.ም

.

(በደራሲው ቤተሰብ መልካም ፈቃድ ለአንድምታ የቀረበ)

.

[ምንጭ] – “መነን” መጽሔት። ግንቦት ፲፫፣ ፲፱፻፷፩። ገጽ ፲፮-፲፰።

ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ጋር

“ውሎ ከጋሽ ጸጋዬ ገብረመድኅን ጋር”

ከግርማ መኮንን

.

በአካልም በስሜትም ከሀገሬ በጣም መራራቅ ጀመርኩ መሰለኝ ትዝታዎቼ ከአምስቱም የስሜት ሕዋሳቶቼ መፍለቅ ጀምረዋል።

ሰው ሁሉ አፍንጫውን ዘግቶ መንገድ ለመሻገር እንደመንጋ ሲንጋጋ እኔ እርምጃዬን ገታ አደርግና ፖሊሱ ወደተቀመጠበት ፈረስ አቅራቢያ ስደርስ ደረቴ እስኪወጠር ድረስ አየሩን እስባለሁ። የፋንድያው ሽታ እኔን የሚያስታውሰኝ ሰፈሬን ሽሮሜዳን ነዋ! እሱም ቢሆን እኮ ይናፍቃል። አዘውትሬ የምሄድበት ቡና ቤትም በአንድ ጥግ በኩል ኮርኒሱ ተቦርድሷል … ያደግኩበት ቤትም እንደዚሁ።

ጆሮዬም ቢሆን የሚናፍቀው የራሱ የሆነ ትዝታ አለው።

አሁን አሁን የእግር ኳስ ጨዋታን እምብዛም ባልከታተልም አንዳንዴ የስፖርት ዘጋቢዎቹ “ጎል!” ብለው ሲጮሁ ለመስማት እጓጓለሁ። እሷን በሰማኹ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አባቴ ነው። እኔና ወንድሜ ሕፃን እያለን በሳምንት እንዴ የሚተላለፈው የእንግሊዞች ኳስ ጨዋታ እንዳያመልጠን ተንደርድረን ከሶፋው ላይ ጉብ እንላለን። የኛም ልብ እንደተሰቀለ አይቀርምና አንድ ጎል ይገባል። ደስታችን ገና በጩኸት ሳይመነዘር በፊት አባታችን ጎል ብሎ ይጀምራል …

“… እንዲያ ነው ጎል! …

ከዚያማ ጎል አባ ቁርጡ

ያንን ሁዳድ ሙሉ ጀግና፥ ከገላገለው ከምጡ …

ምኑ ቅጡ! ምኑ ቅጡ!”

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፻፲፩)

አባታችን ዘወትር ቅድሜና እሑድ ጠዋት፣ መኝታ ቤታችን ድረስ እየመጣ ከሚያነብልን ግጥሞች መሐል ተቀንጥባ እንደወጣች እናውቃለን። ሁሌም ጎል በገባ ቁጥር ስለሚላት ጭፈራ ወይ ሐዘን ከመጀመራችን በፊት የሱን አፍ እንጠብቅ ነበር።

Esat wey Abebaተለቅ ስንል ግን እሱን መጠበቅ አቆምን። ታዲያ የሁለት ሳምንቱን ሸመታ ለማካሄድ በሶማሌ ተራ አድርገን፣ የተክለ ሃይማኖትን መንገድ አሳብረን፣ በጠመዝማዛ መንገድ ተጠማዘን፣ ቅቤና ቡላ ከሚቸረቸርበት መደዳ ደርሰን፣ እናቴ ለብቻዋ ከመኪና ስትወርድ እኔ የአባቴን አፍ መከታተል እጀምራለሁ። እንደለመደው ግራና ቀኙን ካየ በኋላ አንድ ቁም ነገር እንዳስታወሰ ሁሉ ወሬ ሊጀምር ሲል እቀድምና፣

“መርካቶ ያገር ድግሱ

የገጠር ስንቅ አግበስብሱ

ለከተሜው ለአባ ከርሱ …” እላለሁ።

(እሳት ወይ አበባ – ገጽ ፴፩)

አባቴም ኮራ እያለ፣

“እሱን ግጥም ምን እንደጻፈው ታውቃለህ?” ብሎ ይጠይቃል ።

“አፍንጮን የጻፈው ሰውዬ ነዋ” ብዬ መሳቅ እጀምራለሁ።

አባቴም “አንበሳ ሲያረጅ…” እንደሚባለው ቀልዱ በሱ ላይ መሆኑ ይገባዋል። የሱም ጥየቃ የዘልማድ ሆኖ እንጂ ጋሽ ጸጋዬን እንደማውቃቸው ያውቃል – ዳዊት ሳልደግም አይደል “እሳት ወይ አበባን” ያስደገመኝ!

IMG_4952እኔም አውቃቸዋለሁ ስል እንደ አሕዛብ ሁሉ አንዳንድ ሥራዎቻቸውን አንብቤ ወይም ሰምቼ እንጂ በቁም አይቻቸውም አላውቅም ነበር። ታዲያ አሜሪካ ከመጣሁ ከደርዘን ዓመታት በኋላ እምግብ ቤት በራፍ ላይ በቁም አገናኘን።

እሳቸው ከምግብ ቤቱ ሲወጡ፣ እኔ ደሞ ሊጐበኘኝ ከመጣው ታናሽ ወንድሜና ከጓደኞቼ ጋራ ርሃባችንን ለማስታገስ ስንቻኮል። በራፍ ላይ ስለነበርን ሁላችንን ሰላም ብለው ሊያልፉ ሲሉ ከኛው መሐል አንዱ ወደኔና ወንድሜ እየጠቆመ፣

“እነዚህ ደሞ ወንድማማቾች ናቸው። አይመሳሰሉም?” ብሎ ሲያዳንቅ፣

“ለመመሳሰልማ አይጦች ሁሉ ይመሳሰሉ የለ እንዴ?” ብለውን አለፉ።

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ አልፎ አልፎ ኢትዮጵያ ነክ የሆኑ ፕሮግራሞች ላይ ለመሳተፍ ስሄድ በኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ አያቸው ነበር። ሦስት ዓመታት ያኽል እንዲህ አለፉና እንደገና እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ ተፈጠረ። “አንድምታ” የመጽሐፍ ክበብን ወክዬ ጋሽ ጸጋዬን እንዳነጋግር ተጠየኩኝ። እኔም በተራዬ በልጃቸው በኩል ቀጠሮ ያዝኩኝ።

IMG_4942ጋሽ ጸጋዬ ጋር ከቡና ቤት እንድንገናኝ ነበርና ቀጠሮ የተያዘው እኔም እንዳይረፍድብኝ በማሰብ ከቤቴ ቀደም ብዬ ወጣሁ። ግና ሌሊቱን ሰማዩ የበረዶ ገለባ ሲበትን አድሮ ኖሮ፣ ጠዋት ከቤት ስወጣ መንገዱና መኪናው ሁሉ ይህንኑ ሦስት አራት ድርብ ጥጥ ለብሷል። ቀጠሮዬ መሰናከሉ ገብቶኝ አጠገቤ ያየሁትን ነገር ሁሉ መስደብ ስጀምር ከቀበቶዬ ያነገብኩት ስልክ ጥሪ እንዳለ አስታወቀኝ።

“ሃሎ፣ የምጽአት ቀን ዛሬ ናት መሰለኝ….” አልኩ ልጃቸውን።

“የቀጠሮውን ሰዓት ብትረሳው ይሻላል። ግን ቤት ድረስ መምጣት ትችላለህ?” አለችኝ።

የተቃጠርነው ከጠዋቱ 4 ሰዓት መሆኑን ሳልዘነጋ እኔም በ6 ሰዓት ከቤታቸው። የጋሽ ጸጋዬን ባለቤት ወይዘሮ ላቀችን ከሳሎን እንደተቀመጡ ሰላም ብዬ የምትመራኝን ልጃቸውን ተከትዬ በስተቀኝ በኩል ወዳለው መኝታ ቤት ዘው ብዬ ገባሁ።

በቀኝ በኩል ጠረጴዛ፣ በላዩ ላይ ደግሞ ኮምፒውተር – በግራ በኩል አመቺ ወንበር፣ በላዩ ላይ ደግሞ ጋሽ ጸጋዬ፣ ከእጃቸው ላይ ደግሞ ስልክ ተቀምጠዋል። አንድ ወንበር ጐተት አደረኩና ከፊታቸው ቁጭ ብዬ የስልክ ጥሪውን እስኪጨርሱ መጠበቅ ጀምርኩ።

TSEGAYE GEBRE-MEDHINየምሽት ልብሳቸውን እንደለበሱ ነው ቁጭ ያሉት። ቤቱ ውስጥ ባይበርድም ጋቢ ደርበዋል። ከጭንቅላታቸው የደፏት የሹራብ ኮፍያ ለአመል እንጂ በአግባቡ የተደረገች አትመስልም። ይህን የመሳሰሉትን የአለባበስ ዘዬዎች ሳስተውል ስልክ ጥሪያቸውን ጨርሰው ኖሮ አተኩረው ተመልክተውኝ፤

“ከዚህ በፊት ተገናኝተን አናውቅም?” አሉኝ

“እናውቃለን እንጂ ቂም ብይዝ እኮ ነው ቤቶ ድረስ የመጣሁ።”

“እንዴት?”

“ከሦስት ዓመታት በፊት ወንድሜንና እኔን ከአይጦች ጋራ አመሳስለው ነበር። ረሱት እንዴ?”

ፈገግ አሉና፣

“እሱማ የኛኑ ቤተሰብ ትመስላለህ ለማለት ነበር … አንዳንዴ ሰው አይቼ እኔን ይመስሉኝና እደነግጣለሁ። እንዲሁ አንድ ጊዜ የሆነ ልጅ ስድስት ኪሎ አካባቢ አይቼ የኛን ቤተሰብ መምሰሉ በጣም ገረመኝና ተጠግቼ ጠየቅኩት” ብለው ዝም አሉ።

ብጠብቅ አሁንም ዝም።

“ምን ብለው ጠየቁት” አልኩኝ መጠበቅ አላስችል ቢለኝ።

“እናትህ ጐረቤት ነበረች ወይ ነዋ!” ብለው በራሳቸው ቀልድ ራሳቸውንም እኔንም አስቀው ወሬያችንን ቀጠልን።

በደንቡ መሠረት ወደ ቁም ነገር ሰተት ተብሎ አይገባምና እኔና እሳቸውም የባጥ የቆጡን ማውራት ቀጠልን – ወቅቱ ስላመጣው ዝናብና በረዶ፤ ስለ ሰፈሬ እንጦጦ ብርድ፣ ከኒው ዮርክ በፊት ስለኖርኩበት ከተማ፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እንደምሰራ ወዘተ… ይኽንንም ያንንም እየዳሰስን ቀስ በቀስ ወደመጣሁበት ጉዳይ ማዘንበላችን አልቀረም።

እኔም ያለመዳዳት “አንድምታ ክበብ” ከሐሳበ ጽንሰት እስከ ጉርምስና እንዴት እንደደረሰ አስረዳሁ። በጥሞና ከሰሙኝ በኋላ፣

“በኛ ቋንቋ ከተጻፉ ሥራዎች በቅርቡ ያነበብከው ጥሩ ነው የምትለው አግኝተሃል?” በማለት ጥያቄ አቀረቡ።

ለአባቴ ድሮ እንደምመልስለት አፍንጮ ልላቸው አሰብኩና ቀልዱን ለማስረዳት ብዙ ጊዜ እንደሚወስድብኝ ገምቼ ተውኩት። ሆኖም የሳቸው ጥያቄ ለ15 ደቂቅ ያኽል ራሱን የቻለ ውይይት ውስጥ ከተተን። ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ መልስ ባልሰጣቸውም የፈላስፋው ዘርአ ያዕቆብን ሥራ ለራሴ አንብቤ መገምገም በመቻሌ ጽሑፉን ተርጉመውና አቀነባብረው ላቀረቡልን ምስጋናዬን እንደማቀርብ ተናገርኩ።

እሳቸውም አጠፋውን ሲመልሱ፣

“አየህ ሼክስፒር ለእንግሊዝ ትልቅ ቅርስ ነው። እንደ ትልቅነቱም ቅርሱ እንዳይበላሽ በመንግሥት ደረጃ ይጠበቃል። የሼክስፒር ሥራዎች ሌላ ሀገር በመድረክ ላይ ሲቀርቡ በትክክል ካልተሰሩ፣ ባህሉን አቃውሰው ካሳዩ፣ ዝግጅታቸው ጥሩ ካልሆነ፣ ጉዳዩ በአምባሳደሩ ደረጃ ተመክሮበት ነገሩ እንዲስተካከል ተብሎ ‘እርዳታ እናድርግላችሁ’ ብለው እንግሊዞች ይጠይቃሉ። ይኽም የሚሆንበት ምክንያት የሼክስፒር ሥራዎች የእንግሊዝን ታሪክና ባህል ስለሚወክሉ እንደ ቅርስ ተቆጥረው ነው። ምነው የኛ ሀገር ቅርሶች ታዲያ እንዲያ አይያዙም? እነ ያሬድን እነ ዘርአ ያዕቆብን ማን እንደዚህ የሚንከባከባቸው አለ?”

ሊሰነዝሩት ያሰቡት ነጥብ አላመለጠኝም። እሳቸው ግን ቀጠሉ፣

IMG_4943

“ትልቅ ዋጋ እንሰጣቸው የነበሩ ነገሮች በጣም ረክሰው ስናያቸው መንስኤው ምን እንደሆነ ለማወቅም ይታክታል። በአፄ ምኒልክ ጊዜ እንግሊዞች ቱርካና ሐይቅ አካባቢ ዝሆን ያድኑ ነበርና አንዴ አደናቸውን ተከትለው ሲገሰግሱ ከኢትዮጵያ ኬላ ደርሰው ኖሮ ድንበር አላሳልፍ ካሉ የኬላ ጠባቂዎች ጋራ ተኩስ ይከፈትና ከአዳኞች አንዱ በዚሁ ምክንያት ይሞታል። እንግሊዞችም አቤቱታ ያሰሙና ነገሩ የጦር የሚስቴር ከነበሩት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ይደረሳል። እንግሊዞቹ ያላግባብ ሰው እንደተገደለባቸው አመልክተው የደም ካሳ እንዲሆናቸው ከኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ መሬት እንዲሰጣቸው ነበር የጠየቁት።

“ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ነገሩን ያጠኑና ችግር እንደሌለው ለእንግሊዞች ይገልጻሉ። ‘ነገሩ ከመፈጸሙ በፊት ግን ይኽ ሕግ እናንተ ሀገርም እንደሚሰራበት ማየት ስለምንሻ በሰነድ መልክ ረቂቁ ካለ እስቲ እንየው። እውነት የእንግሊዝ ሰው የዌልስን ሰው ቢገድል እንግሊዝ ከመሬቷ ለዌልስ የምትሰጥ ከሆነ እኛም እንሰጣለን። እሱም የሚሆነው ለተገደለብን የኬላ ጠባቂ ካሳ የሚሆን ከቱርካና ሐይቅ አካባቢ መሬት ከተረከብን ይሆናል።’ ብለው መለሷቸው” አሉ።

እንዲህ እንዲያ እያልን የተጀመረው ወሬ በኢትዮጵያ ቅርስ ደጃፍ አቋርጦ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ጓሮ ዞሮ፣ የኢትዮጵያ ደራሲያንን ነካ ነካ አድርጎ ከራሴው ቤት ፊት ለፊት ጣለኝ። ወሬያችን ከአንድ ርእስ ወደ ሌላ ሲሸጋገር በተያያዙ ነጥቦች ስለቤተሰቤ ድንገት ሲጠይቁኝ ምን አስመርኩዘው እንደሆነ አልታወቀኝም። አባቴ የሳቸውን ግጥም ያነብልን እንደነበር ተገልጾላቸው ይሆን?

ያም ሆነ ይኽ ስለቤተሰቤ ተናግሬ ስጨርስ እስቲ የኔን ጽዋ ይቅመሱት ብዬ በምትኩ አዲስ የተጻፈች እንዲት አጭር ታሪክ አነበብኩላቸው – ታሪኩ መኸል እሳቸው የጻፏት “ሕይወት ቢራቢሮ” የተሰኘችው ግጥም ቅንጣቢ ነበረች። የራሳቸው ግጥም አንድ ነገር አስታውሷቸው ልክ ታሪኩን አንብቤ ስጨርስ፣

“እሷ ግጥም በጋዜጣ ታትማ በወጣች ማግስት መንግስቱ ለማ ከቢሮዬ መጥቶ ‘ቢራውን እስቲ አምጣው ወይስ ዝም ብለህ ነው ቢራ ቢሮ ያልከው’ ብሎ እንደቀለደብኝ ትዝ ይለኛል” አሉኝ።

ትንሽ ተከዝ አሉና፣

“ምን የመሰለ ደማም ቋንቋ የነበረው ሰው ነበር። አሁን እኮ ደማም ቋንቋ የሚናገር ሰው ሁሉ ጠፋ።” ብለው እንደገና ትክዝ አሉ።

እኔም አዝማሚያው አላማረኝም። ምክንያቱም የመንግስቱ ለማን ሥራዎችም ቢሆን አባቴ ቅዳሜና እሑድ እንደ ዳዊት ይደግምልን ስለነበር በጣም እያደነቅኩት ነው ያደግኩት። ስለዚህ ስለሱ ማውራት ብንጀምር አዳሬም ከሳቸው ቤት እንደሚሆን በመረዳት እዚህ ላይ ልሰናበታቸው ወሰንኩ።

የአንድምታን መሥራች አባላት ይዤ መጥቼ እንደገና በሰፊው እንደምንወያይ ነግሬያቸው ልወጣ ስል ያዝ አረጉኝና ግንባሬ ላይ ሳሙኝ። ብዙ ባላስቀይማቸው ነው ብዬ ገምቼ ነበር።

IMG_4953

ግን ለካ ወደ ፊት ወጣ ያለው ግንባሬ ቀድሞ ከንፈራቸውን አግኝቶት ኖሯል።

… እኛኑ ትመስላለህ ብለውኝ የለ!

.

ግርማ መኰንን

1998 ዓ.ም

.

[ምንጭ] – “አንድምታ” ቅፅ ፫ – መጋቢት-ግንቦት ፲፱፻፺፰። ገጽ 1፣ 4፣ 10።

 

አለቃ ዘነብ (፲፰፻፲፯-፲፰፻፷፱)

አለቃ ዘነብ (1817-1869)

ከብሩክ አብዱ

.

“ቅቤ ለመጽሐፍ ዘመዱ አይደለም … መጽሐፍ ግን ለሰው ቅቤ ነው” (መጽሐፈ ጨዋታ)

በ1924 ዓ.ም “መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” የተባለ አንድ ወግ-አዘል ድርሰት አዲስ አበባ ከተማ ታተመ። የመጽሐፉ አሳታሚ በብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የተቋቋመው ‘ጎሀ ጽባሕ ማተሚያ ቤት’ ነበር። ደራሲው ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጽሑፎቻቸው የታወቁት አለቃ ዘነብ ነበሩ። መቶ ሃምሳ አመት በላይ ያስቆጠረው ይህ የአለቃ ዘነብ ድርሰት እስከዛሬ ድረስ የአማርኛ ሥነጽሑፍ እድገት መነሻ ተደርጎ ይታያል።

ሆኖም፣ ስለኚህ ደራሲ ሕይወት ከምናውቀው የማናውቀው ያመዝናል። በመቀጠል፣ ከተለያዩ የአገር ውስጥ ምንጮች (የዘመኑ ድርሰቶች፣ ደብዳቤዎች) እና ከባሕር ማዶ መረጃዎች (የጐብኚዎች ትረካ እና የሚስዮን መዛግብት) የቃረምኩትን የአለቃ ዘነብን የሕይወት ታሪክ አቀርባለሁ።

.

ከይፋት እስከ ደብረ ታቦር (1817-1847)

Bernatz Ankober
የመንደር ኑሮ በ1820ዎቿ ሸዋ

“አንድ ዓይንና አንድ ዓይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ። ይህ ነገር ምንድር ነው? … አንድ ካባቱ አንዱ ከናቱ ነዋ” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 2 – አንቀጽ 8)

አለቃ ዘነብ በ1810ዎቹ አጋማሽ (እንዳንድ ሰነዶች 1817 ዓ.ም) በሸዋ በይፋት አካባቢ ተወለዱ። በ1820ዎቹ የልጅነታቸውንና የትምህርት ዘመናቸውን በዚያው በሸዋ ይሁን በሌላ የአገሪቱ ማዕከላት እንዳሳለፉ ለጊዜው መረጃው የለንም። ቢሆንም በአካል ያገኟቸው ሰዎች እንደሚመሰክሩት አለቃ ጠለቅ ካለ የማወቅ ጉጉት በተጨማሪ የግእዝ ሰዋስው፣ የአቡሻክር (ቀን አቆጣጠር) እና የጽሕፈት ሙያ ነበራቸው። አለቃ ዘነብን የያዛቸው ይህ የትምህርት እና የቋንቋ እውቀት ጥማትም፣ ወደፊት እንደምናየው፣ በብዙ የድርሰት መስኮች (ታሪክ፣ ወግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ፈር-ቀዳጅ እንዲሆኑ ያገዛቸው ይመስላል።

ደብተራ ዘነብ በ1830ዎቹ ግድም እንደመነኰሱ የተወሰኑ የውጪ ሰነዶች ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ መጠሪያቸው አንድም ከመነኩሴነታቸው፣ አንድም ደግሞ የባሕር ማዶ ሰዎች ያገራችንን የባህልና የማዕረግ ሥርዓት በሚገባ ካለመረዳታቸው የመነጨ ሊሆን ይችላል። ‘አባ’ ዘነብ ባዮቹም በደብረ ታቦር አካባቢ ጋፋት የሰፈሩት ‘መድፍ ሠሪ’ ሚስዮናውያን (St. Chrischona Pilgermission) ነበሩ።

tewodros
አፄ ቴዎድሮስ ከነአጃቢዎቻቸው

በ1840ዎቹ ደብተራ ዘነብ በማናውቀው ሁኔታ እጣቸው ከአባ ታጠቅ ካሳ ጋር መጣመር ይጀምራል። የቋራው ደጃዝማች ካሳም አፄ ቴዎድሮስ ተሰኝተው በ1847 ዓ.ም አገሪቱን ሲገዙ ዜና መዋዕላቸውን እንዲጽፉ የሾሟቸው ደብተራ ዘነብን ነበር። ደብተራ ዘነብም ከልጅነት ጀምሮ እስከ 1852 ዓ.ም ድረስ ያለውን የቴዎድሮስን ታሪክ (በመቅደላ ከመሞታቸው ከስምንት አመት በፊት) ውብ በሆነ አማርኛ ጽፈውታል። ይህም ፈር-ቀዳጅ ድርሰታቸው ቀዳሚው የአማርኛ ዜና መዋዕል ተደርጎ በሰፊው ይጠቀሳል።

.

ከደብረ ታቦር እስከ መቅደላ (1847-1860)

“ዝናም ከዘነመ በኋላ ቡቃያ ያበቅላል። ንጉሥም ከወደደ በኋላ ይሾማል” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 1 – አንቀጽ 10)

አለቃ ዘነብ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ስመጥር የቤተመንግሥት ባለሟል የነበሩ ይመስላሉ። በጸሐፌ ትእዛዝነታቸው እስከ 1850ዎቹ መጀመሪያ ድረስም አገልግለዋል። ከ1852 አጋማሽ እስከ መጋቢት 1860 ዓ.ም ደግሞ የመዝገብ ቤት ሹም ሆነው በመቅደላ ቆይተዋል። የዘመኑን ታሪክ ከጻፉት መሐል አንዱ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም እንደሚሉትም አለቃ ዘነብ የድርሰት ብቻ ሳይሆን ሌላም ሙያ ነበራቸው፣

“በዚህ ዘመን በሰው ሁሉ ብዙ መከራ ነበረበት። በየሀገሩ በመቅደላም ሌሊት እየገባ የቡዳ ጅብ ሲበላ ሰውን ሁሉ አስጨነቀ። በዚህም ጭንቅ ነፍጠኛ ሁሉ መክሮ በየደጁ ሲተኩስ ብዙ ጅብ አለቀ። አለቃ ዘነብ የሚባልም ለአፄ ቴዎድሮስ የተወደደ ጸሐፊ የሸዋ ሰው ነበረ ለብቻው 11 ጅብ ከደጁ ላይ ገደለ።” (የቴዎድሮስ ታሪክ፣ ገጽ ፵፮)

Tewodros house Meqdela 2
የመቅደላ አምባ አፋፍ

ከላይ የሚነበበው ቃልም በተራው “መጽሐፈ ጨዋታ” ላይ አለቃ ዘነብ በነፍጥ ዙርያ ያነሷቸውን ወጎች በመጠኑ ያስታውሰናል፣

“ተጌጥ መልካም ማነው ወርቅና ብር፤ ለሰልፍስ መልካም ባሩድና አረር … ለሰውስ መልካም ማነው አገር፤ ለወገብስ መልካም ማነው ዝናር … ካረህ ማን ይውላል ነፍጠኛ፤ ከሜዳ ማን ይውላል ፈረሰኛ … ፍቅር ዘውድ ነው፤ መልካም ጠባይ ዝናር ነው።” (ክፍል 4፤ አንቀጽ 4-9)

እንዳጋጣሚ ሆኖ ከ1850ዎቹ እስከ 1869 ዓ.ም ላሉት አመታት ስለ አለቃ ዘነብ በርከት ያሉ መረጃዎችን እናገኛለን። ለዚህም ዋናው ምክንያት ከ1850 ዓ.ም መባቻ ጀምሮ አለቃ ዘነብ በሚስዮናውያን ሰነዶች ውስጥ መጠቀስ መጀመራቸው ነው።

captives 2
በ1860 ዓ.ም በመቅደላ የነበሩት ሚስዮናውያን እስረኞች

በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሚስዮኖች በቀላሉ ለመንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። በአንድ በኩል፣ ወንጌልን በአደባባይ መስበክ ስለማይፈቀድላቸው በየቤታቸው ትምህርት በመስጠት እና በአገሪቷ ቋንቋዎች የታተሙ ወንጌሎችን በማከፋፈል ይሰሩ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አዳዲስ አማኞችን ወደ ሚስዮኑ እምነት (ወንጌላዊ ወይም ካቶሊክ) ሳይሆን ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና ማስጠመቅ ይገደዱ ነበር።

እናም፣ ሰነዶቹ እንደሚገልጹት፣ በ1850 ዓ.ም መባቻ አፄ ቴዎድሮስ በጋፋት ያሉትን ባለሙያ ሚስዮናውያን አማርኛ የሚያስጠና አንድ ሊቅ ይመድባሉ። መምህር ሆነው የተመረጡትም የያኔው ደብተራ/አለቃ ዘነብ ነበሩ። እሳቸውም እኒህን ሚስዮናውያን ቋንቋ በማስተማር ሳሉ እግረመንገዳቸውን በቅርቡ ታትሞ የተሰራጨውን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ማንበብ ሳይጀምሩ አይቀርም። በዚህም ምክንያት ብዙ ሳይቆዩ ወንጌልን የመስበክ ጠንካራ ፍላጎት አድሮባቸው ከ1851 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን ተልእኮ የተያያዙት ይመስላል።

በ1852 ዓ.ም አለቃ ዘነብ የአፄ ቴዎድሮስ ጸሐፌ ትእዛዝነታቸው አበቃ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እሳቸው የደረሱት “የቴዎድሮስ ታሪክ” በዚሁ አመት ዘገባ የሚያቋርጠው። አፄ ቴዎድሮስም በተራቸው አለቃ እንግዳን አዲሱ ጸሐፌ ትእዛዛቸው አድርገው ሲሾሙ፣ አለቃ ዘነብን ደግሞ (በግዞት ይሁን በሹመት) የመዝገብ ቤት ሹም አሰኝተው ወደ መቅደላ ላኳቸው። መቅደላም በነበሩባቸው ዓመታት (1852-1860 ዓ.ም) አለቃ ዘነብ ለአምባው ወታደሮች ወንጌልን በአማርኛ መስበክ የጀመሩ ይመስላል።

Zeneb Dawit 2
የአለቃ ዘነብ ዳዊት (መቅደላ፤ ፲፰፻፶፪)

አለቃ ዘነብ መቅደላ ሳሉ ከመዝገብ ቤት ኀላፊነታቸውም ባሻገርም በጸሐፊነት ሙያቸው ቀጥለዋል። በጊዜው ከቀዷቸው በርካታ ብራናዎችም ቢያንስ አንዱ ለትውልድ ተርፏል። ይህንንም የዳዊት ብራና በመቅደላ ሳሉ በእጃቸው የጻፉት አለቃ ዘነብ እና መልአከ ገነት ወልደ መስቀል ሲሆኑ ወቅቱም በ1852 ዓ.ም ነበር። (ወደፊት የአለቃን እና የመልአከ ገነትን እጅ ለይቶ ለማጥናት መሞከር የበለጠ ውጤት ሳይሰጥ አይቀርም።)

ChewataTewodros Tarik

አለቃ ዘነብ መቅደላ ሳሉ በርካታ ድርሰቶችን ለአገራችን ሥነጽሑፍ አበርክተዋል – “የቴዎድሮስ ታሪክ” (1852 ዓ.ም)፣ “መጽሐፈ ጨዋታ” (1856 ዓ.ም)፣ እንዲሁም “የኦሮምኛና አገውኛ መዝገበ ቃላት” (1860 ዓ.ም ግድም)። በዚህም ዘመን አለቃ ዘነብ ከሚስዮናውያኑ (Martin Flad እና Johannes Meyer) እንግሊዝኛን መማር ጀምረው ነበር። በተራቸውም ኦሮምኛን ያስተምሩ ነበር። የዘመኑ ሰነዶች እንደሚሉት አለቃ ወደፊት ወንጌልን በኦሮምኛ ለመስበክ እንዲችሉ እየተዘጋጁ የነበረ ይመስላል።

.

ከመቅደላ እስከ አድዋ (1860-1864)

“በርበሬ ላይን ቀይ ሆኖ ይታያል ምነው ቢሉ በብልሐት ገብቶ ሊለበልብ። ክፉ ሰውም ቀስ ብሎ ገብቶ ኋላ ነገሩን ያመጣል” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 1 – አንቀጽ 9)

ብዙም ሳይቆይ በ1860 ዓ.ም አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አረፉ። አለቃ ዘነብም የደጃች ዓለማየሁ ሞግዚት ሆነው በእንግሊዙ ጦር ተመደቡ። በሞግዚትነት የተመረጡበትንም ሁኔታ በወቅቱ የእንግሊዝን መንግሥት ወክሎ በአስተርጓሚነት ያገለግል የነበረው ሶርያዊው ራሳም (Hormuzd Rassam) ሲገልጽ፣

“በኔው አመልካችነት አለቃ ዘነብ የሚባለው ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ክርስቲያን ያፄ ቴዎድሮስ የመዝገብ ቤት ሀላፊ የነበረው፣ ለዓለማየሁ ሞግዚት ሆኖ አብሮት እንዲሄድ ተፈቀደ። በኋላ ግን በየምክንያቱ አብሮት ሊሄድ አልቻለም።” (ትርጉም – ተክለጻድቅ መኩሪያ)

ምክንያቱም እንዲህ ነበር። አለቃ ዘነብ ከእንግሊዞች ጋር የጌታቸውን ልጅ ደጃች አለማየሁን ተከትለው ሰንአፈ ድረስ ተጓዙ። ሰንአፈም ላይ ከደጃች አለማየሁ ጋራ በመርከብ ተሳፍረው በግብጽ የስዌዝ ካናል ሊደርሱ ሲሉ አንድ ችግር ተፈጠረ። ስለዚህም ሁኔታ አለቃ የጻፉት የብሶት ደብዳቤ ኦርጅናሌው አማርኛ ቢጠፋም እንግሊዝኛ ቅጂው ግን ሊተርፍ ችሏል፣

NPG Ax30351; Prince (Dejatch) Alamayou of Abyssinia (Prince Alemayehu Tewodros of Ethiopia); Tristram Charles Sawyer Speedy by (Cornelius) Jabez Hughes
Capt. Speedy (ባሻ ፈለቀ) እና ደጃች ዓለማየሁ

“… Before we arrived at Suez and when we were still at sea, Captain Speedy told us ‘Alam-Ayahoo does not like you, remove, do not come near him’ … When we said, ‘Why do you separate us from the son of our Lord Theodoros?’ Basha Falaka (Capt. Speedy) replied ‘When man has too much blood, he dislikes his friend … I shall buy a vessel and take you until his heart returns to you and Alam-Ayahoo likes you again.’ And saying this Falaka took his oath by himself saying, ‘May Falaka die!’ …

 

“On the following day … Basha Falaka came and said ‘Give to me the baggage of Dedjadj Alam-Ayahoo’ and when we were delivering it fully we said to him, ‘Why, if we have offended, let us be judged in a judicial way, why do you separate us?’ … We returned without having received from him any money and paper …

Speedy Pose
‘ባሻ ፈለቀ’ አንዱን አሽከሩን አጊጦ ‘ሲማርክ’

“We have been wrong treated with great injustice. Is it then right in your country to oppress a man by subtility? To be sure the face of an Abyssinian is black, but has he not been created in the resemblance of the Trinity and been redeemed by the blood of Christ? … And now, I have written this that the Christians of England might know it.”

 

[“ታላቅ ግፍና ታላቅ በደል ደርሶብናል። በአገራችሁ አንድን ሰው አባብሎ ማታለል ነውር አይደለምን? ምንም እንኳን ሐበሻ ጥቁር ቢሆን መልኩ በአርአያ ሥላሴ አልተፈጠረምን? በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነጻ አልወጣምን? … ይህንንም አሁን የጻፍኩት የእንግሊዝ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲያውቀው ብዬ ነው።” (ትርጉም – ብ.አ)]

አለቃ ዘነብ ለ Krapf፤ ኅዳር 8፣ 1861 ዓ.ም፤ ምጽዋ።

.

በዚህም ምክንያት አለቃ ዘነብ ግብጽ ድረስ ደርሰው ደጃች ዓለማየሁን ሳይሰናበቱ፣ ኢየሩሳሌምንም ሳይሳለሙ በመመለስ ለበርካታ ወራት በምጽዋ ለእንግልት ተዳረጉ። በምጽዋ ቆይታቸውም ወቅት ከፈረንሳይ ምክትል ቆንስሉ ሙንዚገር (Werner Münzinger) ዘንድ አርፈው የተወሰኑ መጻሕፍትን የጻፉ ይመስላል። በሙንዚንገር ገፋፊነትም (እስከዛሬ ድረስ ሊገኝ ያልተቻለ) ሁለተኛውን የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ ያኔ ሳያዘጋጁ አይቀርም።

Dawit 1871
“Farsoota Mottin Daawiid” 1864 ዓ.ም

በመቀጠልም ለሚስዮናዊ ሥራ እንዲሆን አራቱን ወንጌላት ወደ ኦሮምኛ በትጋት ተርጉመው ወደ ጀርመን አገር ላኩ። ለአመት ያህል ምጽዋ ከቆዩም በኋላ በመጋቢት 1861 ዓ.ም ከሁለት ሚስዮናውያን ጋር በመሆን በእንግሊዝ የታተመውን የአማርኛ ወንጌልን ለማሠራጨት British Foreign Bible Society ስር ተቀጥረው ወደ አድዋ አመሩ።

በአድዋ ቆይታቸው ወቅት (1861-1864 ዓ.ም) አለቃ ዘነብ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለአካባቢው ነዋሪዎች በማሰራጨት እና የኦሮምኛ ቋንቋ እውቀታቸውን በጥናት በማዳበር ጊዜያቸውን ያሳለፉ ይመስላል። ብዙም ሳይቆይ እሳቸው ተርጉመው (ወይም የመጽሐፉ ሽፋን እንደሚለው ‘ጽፈው’) የጨረሱት ኦሮምኛው ዳዊት አድዋ ሳሉ ታተመ።

መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የመተርጎሙንም ሥራ በማስፋፋት ከሌሎች የቋንቋው ተናጋሪዎች ጋር (ዋሬ፣ ሩፎ፣ ሾለን፣ ጀገን እና ገብረሚካኤል) በመተባበር ሙሉውን አዲስ ኪዳን ወደ ኦሮምኛ ተርጉመው በሰኔ 1862 ዓ.ም አገባደዱ። ይህም ትርጉማቸው ለኦሮምኛ ሥነጽሑፍ የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን መሆኑ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚስዮኑ ክራጵፍ (J.L. Krapf) በ1869 ዓ.ም በራሱ ስም ያሳተመው ይህንኑ የነአለቃ ዘነብን ሥራ ነበር።

ታዲያ የአለቃ ዘነብ እና የባልደረቦቻቸው ትርጉም እንደ ፈር ቀዳጅነቱ ያህል በአንዳንድ የቋንቋው ምሁራን ግን ብዙውን የተወደደ አይመስልም። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኦሮምኛ የመለሰው ታታሪው ኦነሲሞስ ነሲብ ሥራውን ሲጀምር የነአለቃ ዘነብን ትርጉም መሠረት ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ሆኖም የነአለቃ ዘነብ የአዲስ ኪዳን ትርጉም በርካታ የፊደል ስሕተቶች፣ የቃላት አመራረጥ እና የግስ እርባታ አካሄድ ችግሮች ስለነበሩበት ኦነሲሞስ መጽሐፍ ቅዱሱን ከእንደገና ወደ ኦሮምኛ ለመተርጐም እንደተገደደ ይናገራል።

Menelik and his chiefs
ንጉሥ ምኒልክ ከመኳንንቶቻቸው ጋር

አለቃ ዘነብ አድዋ በገቡ ባመታቸው (በሚያዝያ 1862) ያልጠበቁት ደብዳቤ ከንጉሥ ምኒልክ ደረሳቸው። በመቅደላ በእስረኝነታቸው ዘመን ያውቋቸው የነበሩት የዛሬው “ንጉሠ ሸዋ” ከደብዳቤው ጋር 2,000 ጠገራ ብር ለአለቃ ዘነብ ልከው ነበር። ንጉሥ ምኒልክም በደብዳቤያቸው ውስጥ አለቃ ዘነብ በድጋሚ ግብጽ ድረስ ሄደው (ከዚህ በፊት ከዛ መድረሳቸውን ያውቃሉና) የተለያዩ መሣሪያዎችን እና የእጅ ባለሙያዎችን ቀጥረው ወደ ሸዋ እንዲያመጡ ጠየቋቸው።

.

ከአድዋ እስከ ልቼ (1864-1869)

“መልካምን መብል መልካምን መጠጥ ዓለምንም ሁሉ ቢወዱት ምን ይሆናል?

ሞት ድንገት መጥቶ አስጨንቆ በግድ ይወስዳልና” (መጽሐፈ ጨዋታ፤ ክፍል 4 – አንቀጽ 16)

ከጥቂት አመታትም በኋላ አለቃ ዘነብ በመጋቢት 1864 ዓ.ም በሸዋ ሚስዮን ለማቋቋም አድዋን ለቀው ከሁለት ሚስዮናውያን ጋር ንጉሥ ምኒልክ ዘንድ አመሩ። መንገዳቸው ግን በችግር የተሞላ ነበር። ተከዜን ከመሻገራቸው፣ ሰቈጣ ላይ የወቅቱ የየጁ ባላባት (አሊ ብሩ) ለሁለት ወር ሙሉ አስሮ አገታቸው። ከብዙ እንግልትም በኋላ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ወረኢሉ ተገናኙ።

አለቃ ዘነብ አመጣጣቸው መቅደላ ላይ ሳሉ እንዳቀዱት ወንጌልን በኦሮምኛ ለመስበክ ነበር። ንጉሥ ምኒልክ ለካቶሊኩ አባ ማስያስ እንደፈቀዱት ሁላ፣ አለቃ ዘነብና አብረዋቸው የመጡት ሚስዮናውያንም ተመሳሳይ ወንጌልን የመስበክ ነጻነት እንደሚሰጣቸው ተስፋ አድርገው ነበር። ሆኖም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ያቀዱት ሊሳካላቸው አልቻለም። አለቃም ባላሰቡት መንገድ ቆይታቸው በያኔዋ ሸዋ ዋና ከተማ በነበረችው ልቼ እና በአንኮበር ውስጥ ሊሆን ቻለ።

አለቃ ዘነብ ልቼ ሳሉ ከንጉሥ ምኒልክ አዳራሽ ብዙም አልራቁም ነበር። ሸዋ በገቡ በሦስተኛ አመታቸው የፈረንሳይ ዜጎች ከሸዋ ወደ አፋር ሲጓዙ አንድ አደጋ ተከሰተ። በዚህም ምክንያት የፈረንሳይ መንግሥትን ለማረጋጋት በልቼ ከተማ በታኅሣስ 1867 ዓ.ም በተፈረመው ሰነድ ላይ ከውጭ አገር ነዋሪዎች፣ ከሚስዮናውያን እና ከቤተመንግሥት ባለሟሎች መሐል የምስክርነት ፊርማቸውን አለቃ ዘነብ አውለው ነበር።

አለቃ ዘነብ በሸዋ ተቀምጠው በነበረበት ወቅት “መጽሐፈ ጨዋታ” እና ሌሎች ድርሰቶቻቸው በቤተ መንግሥት እና በመኳንንት መሐል በብዛት ተቀድተው የተሰራጩ ይመስላል። በዛሬም ዘመን በእጃችን የሚገኙት የ“መጽሐፈ ጨዋታ” ቅጂዎች ሊበረክቱ የቻሉት በሸዋ ቆይታቸው ድርሰቱ ተወዳጅነትን አትርፎ ስለነበረ ሳይሆን አይቀርም።

depositphotos_13297287-stock-photo-abyssinian-warriors

ሸዋ በገቡ በአምስተኛ አመታቸው፣ በጥቅምት 1869 ዓ.ም በጉራጌ ምድር ቸሃ አካባቢ የንጉሥ ምኒልክ ጦር ዘምቶ ነበር። በዚህም ዘመቻ አብረው ተጉዘው የነበሩት አለቃ ዘነብ ባልታወቀ ሁኔታ ሕይወታቸው አለፈች። የአለቃ ዘነብን “መጽሐፈ ጨዋታ” ከማሳተማቸው ከአስር አመት በፊት ብላታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በአንዱ መጽሐፋቸው እንዲህ ብለው ነበር፣

“አለቃ ዘነብ የተማሩ ሊቅ ነበሩ … እርሳቸውም በውስጡ እጅግ የረቀቀ ምስጢር ያለበት መጽሐፈ ጨዋታ የሚባል መጽሐፍ ትተው ስለሞቱ ስማቸው አልጠፋም።”

.

ብሩክ አብዱ

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

የመረጃ ምንጮች

.

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“።

ኅሩይ ወልደሥላሴ (ብላታ)። [፲፱፻፲፭]። “የሕይወት ታሪክ”፤ ገጽ ፸፰።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፮]። “ሐፈ ጨዋታ/ መጽሐፈ ጥበብ” አርታዒ፤ ኅሩይ ወልደሥላሴ (፲፱፻፳፬)።

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷]። የኦሮምኛና አገውኛ ግስ” (ያልታተመ)።

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፩]። ደብዳቤ ለክራጵፍ” ውስተ “Acta Aethiopica – Vol II” Rubenson, Sven [Ed.] (1996)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፪]። “ቁልቁሎታ መጣፎታ ከኩ ሐረዋ” (Kaku Harrawaa) አርታዒ፤ Krapf, J.L (1876)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፷፬]። “ፈርሶታ ሞቲን ዳዊድ” (Farsoota Motin Dawid) አርታዒ፤ Krapf, J.L (1872)

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

Aren, Gustav (1978). “Evangelical Pioneers in Ethiopia”

Smidt, Wolbert (2014) “Zännäb” ውስተ Encyclopaedia Aethiopica Vol V ገጽ 140-142 

Rubenson, Sven [Ed.] (2000) “Acta Aethiopica – Vol III”

መሰንቆ እና ብትር (ወግ)

“መሰንቆ እና ብትር”

ከበዕውቀቱ ሥዩም

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ …”

አዝማሪ ጣፋጭ [1845 ዓ.ም]

.

የዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ጎሹ እና የቋራው ፋኖ ደጃዝማች ካሳ በኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም ጉራምባ ላይ ጦርነት ገጠሙ። ካሳ፣ ከጥቂት ታማኝ ጭፍሮቻቸው ፊት ተሰልፈዋል። ጎሹም፣ በተለመደው የጀብድ መንገድ ከሰራዊታቸው ፊት ለፊት ቀድመው፣ ሲዋጉና ሲያዋጉ ውለዋል። ውጊያው እንደተፋፋመ፣ ደጃች ጎሹ በጥይት ተመትተው ወደቁ። የመሪውን መውደቅ እንደተረዳ የዳሞት ጦር ፀንቶ መመከት ተሳነው። ወዲያው የንቧይ ፒራሚድ ሆነ። ያለቀው አልቆ ቀሪው ተማረከ።

ከምርኮኞች አንዱ፣ አዝማሪው ጣፋጭ ነበር።

ጣፋጭ፣ የደጃች ጎሹ አዝማሪ ስለነበር በብዙ ጦር ሜዳ ላይ ውሏል። በጌታው ጠላት እጅ ሲወድቅም የመጀመሪያው አይደለም። በራስ ይማም ዘመንም እንዲሁ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ የተባለ መስፍን ደጃዝማች ጎሹን ድል በነሳ ጊዜ፣ ከጌታው ጋር ተማርኮ ነበር።

ይሁን እንጂ ያኔ ዝንቡን እሽ ያለው አልነበረም። ጣፋጭ፣ የደጃች ማጠንቱ ምርኮኛ ቢሆንም፣ የእግር ብረት አልገባበትም። እንዲያውም፣ በድል አድራጊው አዳራሽ ውስጥ ያሻውን ከማንጎራጎር አልተከለከለም ነበር። በወቅቱም፣ አዝማሪው ጣፋጭ ይህንን ገላጋይ ዝማሬ አቅርቦ ነበር፤

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

ጣፋጭ፣ ደጃዝማች ማጠንቱ በጦር ሜዳ ላይ ስምንት ወታደር መግደሉን አስታውሶ፣ አሁን ተማራኪውን ቢገድል የሚጨመርለት ክብር እንደሌለ አስታወሰው። በሁለት መስመር ግጥም ለድል አድራጊው የሚገባውን መወድስ ሳይነፍግ፣ የጌታውን ሕይወት ለመታደግ ጥሯል። ድል አድራጊው ደጃች ማጠንቱም ጎሹን ሳይገድለው ቀረ።

በዚህ በኅዳር ዕለት ጦርነት ግን፣ አዝማሪው ጣፋጭ በቋረኛው ካሳ ጦር ተማርኳል። ተስፋና ፍርሀት ከፊቱ ተደቅነዋል። ባንድ በኩል፣ አዝማሪን መግደል ነውር የሚያደርገው ባህል ጋሻ ሁኖት ከክፉ እንደሚታደገው ተስፋ ያደርጋል። በሌላ በኩል፣ ደጃዝማች ካሳ ይህን ደምብ ለማክበራቸው ርግጠኛ አይደለም።

እነሆ፣ አዝማሪው በካሳና በጭፍሮቻቸው ፊት ቆሟል። ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ የሚተርኩልን ለዘመኑ ቅርብ የነበሩት አለቃ ወልደማርያም ናቸው፤

“አዝማሪ ጣፋጭ … ተይዞ በቀረበ ጊዜ ባደባባይ አቁመው ደጃች ካሳ ‘እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ’ ቢሉት እጅግ ተጨነቀ፤ እንዴህም አለ፤

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

እንዲህም ቢል ሞት አልቀረለትም፤ በሽመል ገደሉት።”

አለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ከሁለት ትውልድ በኋላ በጣፉት የጎጃም ታሪክ ውስጥ ደግሞ የሚከተለውን ተጨማሪ መስመር እናገኛለን፤

“አወይ ያምላክ ቁጣ አወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ራ ሲያጣ

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

ከመቶ አመት በኋላ ታዋቂው ዘመናይ የታሪክ ጸሐፊ ተክለጻድቅ መኩሪያ በጻፉት ጥናትም “ብትር” የሚለውን “ሽመል” በሚል ቃል ከመተካት በስተቀር ያለቃ ተክለየሱስን ቅጂ ማስተጋባት መርጠዋል፣

“እወይ ያምላክ ቁጣ

ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ

.

ጣፋጭ፣ የደጃች ካሳን ምሕረት አጥብቆ የሚፈልግ ምርኮኛ ሆኖ ሳለ፣ እንዴት ተሽቀዳድሞ በራሱ ይፈርዳል? እንዴት “ሽመል/ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ” ብሎስ ራሱን ለቅጥቀጣ ያቀርባል?

የጣፋጭን ፍርድ በመመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት አለቃ ወልደማርያም ታሪክ ውስጥ መደምደሚያው ስንኝ አለመጠቀሱ አንድ ነገር የሚጠቁም ይመስለኛል። ስንኙ ምናልባት ከጊዜ በኋላ የተጨመረ ይሆናል።

የኔ ግምት እንዲህ ነው … አዝማሪ ጣፋጭ በደጃዝማች ካሳና አጃቢዎቻቸው ፊት ይቀርባል፤

ደጃች ካሳ፤   እንዴት ብለህ ሰደብኸኝ?

ጣፋጭ፣ በጦርነቱ ዋዜማ በደጃች ካሳ ላይ ያወረደውን ዘለፋ እዚህ ቢደግም፣ የድል አድራጊውን ቁጣ ከማቀጣጠል ውጭ የሚፈይድለት ነገር የለም። ስለዚህ የመጨረሻ መሳሪያውን ለመጠቀም ወሰነ። ቧልት! …. ካሳና ጣፋጭ በጎሹ ቤት በሎሌነት ሲኖሩ፣ ካሳ ቀልድና ፈሊጥ እንደሚወድ ያውቃል። ጣፋጭ መሰንቆውን ቃኝቶ ይህን በግለ ሂስ የተሞላ የቧልት ዘፈን ዘፈነ፤

ጣፋጭ፤   ህምም …

እወይ ያምላክ ቁጣ እወይ የግዜር ቁጣ

አፍ ወዳጁን ያማል ሥራ ሲያጣ።

ካሳ አልሳቀም። አዝማሪው የከፈተውን ተውኔት እንዴት መቀጠል እንዳለበት እያሰበ ይሆናል። ደጃዝማች ካሳ፣ ራሱን የመለኮት ተውኔት ፍሬ አድርጎ ስለሚቆጥር ፍርዱን ሳይቀር ተውኔታዊ ማድረግ ይወድ ነበር። የራስ አሊን እናት በማረከም ጊዜ “ገረድ ትሰለጥናለች እመቤት ትፈጫለች” የሚለውን የፍካሬ የሱስ ትንቢት ለማስፈጸም ወይዘሮ መነን ባቄላ እንድትፈጭ ፈርዶባት ነበር። “የኮሶ ሻጭ ልጅ” ብሎ የሰደበው ቀኛዝማች ወንድይራድን ደግሞ “እናቴ ከገበያ ሳይሸጥላት የቀረ ኮሶ ስላለ እሱን ተጋበዝ” ብሎ፣ ከመጠን ያለፈ ኮሶ አስግቶ ለመቅጣት የሆነ የተውኔት ስጦታ ያስፈልጋል። ያገራችን ጸሐፌ ተውኔቶች በፍቅሩ የነሆለሉት ብጤያቸው ስለሆነ መሆን አለበት።

ደጃች ካሳ፤   (ወደ አጃቢዎቹ ዞሮ)

ብትር ይገባዋል ያዝማሪ ቀልባጣ።

.

ጣፋጭ በቧልት የጀመረውን … ካሳ በትራጀዲ ደመደመው።

.

* * *

ጣፋጭን ለድብደባ የዳረገው ዝማሬ ግጥም ይሄ ነበር …

አያችሁት ብያ፥ የኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞ፥ ጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂ፥ መች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት፥ በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ ፥ በነ ጉንጭት ለምዶ።”

* * *

.

አያችሁት ብያ የኛን እብድ” [መስመር ፩]

ብያ” ዛሬ ለመረሳት ከደረሱት ያማርኛ ጥንታዊ ቃላት አንዱ ሲሆን “እኮ፣ አይደል” ማለት ነበር። “አያችሁት ብያ” ሲልም “አይታችሁታል አይደል?” ማለት ነው። ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ራሱን ገድሎ በወደቀ ማግስት ከወረዱ የሙሾ ግጥሞች አንዱ፣ “አያችሁት ብያ ያንበሳውን ሞት” የሚል ስንኝ አለው። ይህም በጊዜው ቃሉ የተለመደ እንደነበር ያመለክታል።

“እብድ” ተብሎ ካሳ በይፋ ሲጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የምንሰማው ከአዝማሪ ጣፋጭ ሳይሆን አይቀርም። ጣፋጭ ይህን ሲል፤ የጊዜውን አስተያየት እያስተጋባ ነው? ወይስ በራሱ ምርመራ የደረሰበት ነበር? አላውቅም። አለቃ ተክለየሱስ ከግማሽ መቶ አመት በኋላ በጐንደር ሲወርድ የነበረውን ግፍ ዘግቦ፣ የሕዝቡን ምላሽ ምን እንደነበር ሲጽፍ፣ “ከዚህ በኋላ፣ የበጌምድር ሰው ‘ይህስ የደህንነትም አይደለ’ እያለ አመል አወጣ … ንጉሡንም ጠላው። ሌሊት በተራራ እየቆመ፣ እንደ ሳሚ ወልደ ጌራ ‘እብዱ ገብረኪዳን’ እያለ ተሳደበ” ይላል። (“ገብረኪዳን” የአፄ ቴዎድሮስ የክርስትና ስም እንደነበረ ባልታወቀ ደራሲ ተጽፎ Fusella ባሳተመው ዜና መዋዕል ተጠቅሷል።)

.

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ [መስመር ፪]

ጋሞች” የሚላቸው ባለ አፍላ እድሜ ላይ ያሉትን ጋሜዎች ነው። ባዝማሪው አይን ሲመዘኑ የደጃዝማች ካሳ አጃቢዎች እድሜያቸው ለጋ፣ ቁጥራቸውም ጥቂት ነው። በርግጥም የካሳ ጭፍሮች ማነስ ለባላጋራዎች ግራ የሚያጋባ ነበር። ባነጋገር ፈሊጣቸው የታወቁት ራስ አሊ የቋራው ካሳን ሰራዊት ከሩቅ አይተው ከገመቱት በታች ቢሆንባቸው፣ “ጦረኛ እንዳንለው አነሰ፤ ሰርገኛ እንዳንለው በዛ” ብለው ነበር።

ጉራምባ” (ጉር አምባ) በዛሬው የደንቢያ ወረዳ፣ ጎርጎራ በተባለው ንኡስ ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ስፍራ ነው። ደጃዝማች ካሳ ይህን ስፍራ የመረጡት ለመከታ የሚያመች አምባ ሆኖ ስላገኙት ሳይሆን አይቀርም። አዝማሪው ጣፋጭ በግጥሙ ውስጥ “ጉር አምባ” የሚለውን ነባር ስም “ጉራምባ” ብሎ አሸጋሽጎታል። ይህን ያደረገው ስፍራውን “ጉራ መንፊያ” ብሎ ለመተርጎም እንዲያመቸው ይመስላል። ጣፋጭም የቋራው ካሳን ለይስሙላ እንጂ የምር መዋጋት የማይሆንለት ጦረኛ አድርጎ ይገምተው እንደነበር ቀጣዩ መስመር ያሳያል።

.

ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋ ካሳ” [መስመር ፫]

ያንጓብባል” የሚለው ቃል “አጊጦ በመልበስ ቄንጥ ባለው አካሄድ ይሄዳል፣ ዳር ዳር ይላል” ማለት ነው። ቃሉን የሚከተለው ከአለቃ ዘነብ “መጽሐፈ ጨዋታ” የተቀነጨበ አንቀጽ የበለጠ ያብራራዋል፣

“ሰማይ ከዚያ ላይ ሆኖ አንጓቦብን የሚኖር ከቶ ምንድር ነው? ቀን ፀሐይን ሌሊት ጨረቃንና ከዋክብትን ተሸልሞ ዘወትር እኔን እኔን እዩኝ እዩኝ እያለ ያደክመናል … እንደዚህ የኮራ እንደ ሰም ለመቅለጥ ነው እንጂ ፊቱን እንዴት ያየው ይሆን? ኩራቱም ምድር አስለቅቆታል። ምን ይሆናል እንደሚያልፍ አያውቅምን?”   [ክፍል 15፤ አንቀጽ 16]

ይህ ዳር ዳር ማለት የቋራው ካሳ ጠላቶቹን የሚያዘናጋበት ልዩ የጦር ስልት ነበር። በጠላቶቹ አይን ግን እንደ ፍርሀት ይቆጠር ነበር። ለአብነት ያክል፣ አለቃ ወልደማርያም በደጃች ካሳና በራስ አሊ መሐል የተደረገውን ውጊያ አስመልክተው ሲጽፉ፤ “ራስ አሊ አይሻል በሚባል ሜዳ ጦርዎን ሰርተው ተቀምጠው ሳሉ ደጃች ካሳም ዳር ዳሩን ይዞሩ ጀመሩ። ሰውም የፍርሀት መስሎት ‘ተመልሶ ሊሄድ ነው’ ይል ጀመረ።”

መች ይዋጋል …” የቋራው ካሳ ደፋርና ጽኑ ተዋጊ ቢሆንም ጉልበቱን መዝኖ መሸሽም ያውቅ ነበር። ደጃዝማች ጎሹ በ1840 ዓ.ም ለፈረንሳዊው ሚካኤል አባዲ በጻፉት ደብዳቤ “ተካሳ ጋራ የተዋጋነ እንደሆነ ጎንደር እገባለሁ እንገናኛለን፤ ወደ ቆላ የሸሸ እንደሆነ …” ያሉት ይህን ስለሚያውቁ ይመስላል። እንደገመቱት፣ ካሳ ወደ ትውልድ ቦታው አፈግፍጎ ከርሟል። አዝማሪው ጣፋጭ “… መች ይዋጋል ካሳ” ያለው ይህን ሁኔታ በማጤን መሆን አለበት። ይሁን እንጂ፣ ካሳ ለጣፋጭ ያልተገለጠለት ጠንካራ ጎን ነበረው። ጠላቶቹ ሽሽቷል ብለው ሲዘናጉ እንደገና አፈር ልሶ ተነስቶ ማጥቃትና ማሸነፍ ይችል ነበር።

.

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ [መስመር ፬]

ወርደህ” የሚለውን ቃል አዝማሪው በዚህ ዝማሬ ውስጥ ሁለቴ ተጠቅሞበታል። መስመር 2 ላይ “ጉራምባ ሲወርድ” ብሎ ካሳን የገለጠውን ያክል “ወርድህ ጥመድበት” ብሎ ጎሹን ይጎተጉተዋል። የመፋለሚያውን ቦታ ቆላነት ያሳስባል፤ ወደ ቆላ ወረደ ይባላልና። “ጥመድ” በአማርኛ ብዙ ትርጉም አለው፤ ከግጥሙ ዐውድ ጋር የሚሄደው “አሽክላን ዘረጋ፣ ወይም የጠፋ ሰውን አጥምዶ ሸምቆ ለመያዝ በጎደጎደ አደባ” የሚለውን ነው። ስለማይዋጋ ካሳን አድብቶ መያዝ እንደሚያዋጣ ጣፋጭ ሀሳብ እያቀረበ ነው።

በሽንብራው ማሳ” ሲል አዝማሪ ጣፋጭ ስለየትኛው ነው የሚያወራው? “ካሳ” ከሚለው ቃል ጋር እንዲገጥመለት ይሆን? የለም፤ እኔ እንደሚመስለኝ ቃሉ ታስቦበት የተመረጠ ነው። ደጃች ጎሹ የቋራውን ደጃች ካሳ አባርረው ደንቢያን በጃቸው ባስገቡበት ዘመን ከምግብ ሁሉ የሚወደውን የሽንብራ አዝመራ አውድመውበታል ይባላል። ጣፋጭ “ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ” ያለው ያንን አስታውሶ ይመስለኛል። አለቃ ዘነብ፣ “ያን ጊዜም ቋራ ሁሉ ጠፍ ሆኖ ነበር። ልጅ ካሳም ለባላገሩ ሁሉ ብዙ ብር ሰጡት። መቆፈርያ ግዛ ብለው … ከወታደሩ ጋር ብዙም ቆፍረው ዘሩ” ያሉት የሚታወስ ነው።

.

ወዶ ወዶ!” [መስመር ፭]

ወዶ ወዶ …” ጣፋጭ ይህን የተጠቀመው ለማሽሟጠጥ ነው፤ “ወድያ ወድያ” እንደማለት ነው። በዛሬ አማርኛ ብንመልሰው “ድንቄም ድንቄም” እንል ነበር።

.

በሴቶቹ በነ ጉንጭት ምዶ” [መስመር ፮]

ጉን” ለጉንጫም ሴት የሚሰጥ ቅጥል ነው። ጣፋጭ “በነ ጉንጭት” ሲል ደጃዝማች ካሳን በዘመኑ ያጅቡ ከነበሩት ቅሬዎች (ጋለሞቶች) አንዷን ጉንጫም አስታውሶ ይሆን?  “በነ ጉንጭት ምዶ …” ካሳ ከሴቶቹ ከነጉንጭት የለመደው ምንድነው? በጣፋጭ እይታ መሽቀርቀር፣ የእዩኝ እዩኝ ማለትን ተግባሮች ሁሉ ድምር የሆነው “ማንጓበብ” መሆኑ ነው።

ጣፋጭም ሆነ ካሳ፣ ወንድን እንደ መለኮት ከፍ ከፍ የሚያደርግ፣ ሴትን እንደ ጉድፍ የሚያጣጥል ማኅበረሰብና ዘመን ፍሬዎች ናቸው። በዚህ አይነቱ ዘመን አንድ ጦረኛ ጀብዱው ከከተሜ ቅሬዎች ተግባር ጋር መነጻጸሩን ሲሰማ ደም ብቻ እንደሚያጸዳው ውርደት አድርጎ ቢቆጥረው አይገርምም።

የጣፋጭን ፍጻሜ የወሰነችውም ይቺ የመጨረሻዋ መስመር ሳትሆን አትቀርም።

.

አዝማሪ ጣፋጭ (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም)

እና ድርሰቶቹ

*

“እወይ ያምላክ ቁጣ፣ እወይ የግዜር ቁጣ፤

አፍ ወዳጁን ያማል፣ ሥራ ሲያጣ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* *

“ክፉ የክፉለት፣ ይሆን የነበረ፤

ብሩን ‘ይሙት’ ብሎ፣ አለ የመከረ።”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * *

አያችሁት ብያየኛን እብድ 

አምስት ጋሞች ይዞጉራምባ ሲወርድ

ያንጓብባል እንጂመች ይዋጋል ካሳ

ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ

ወዶ ወዶ 

በሴቶቹ  በነ ጉንጭት ለምዶ፤

(ሐሩ ቋዱ፣ ለውዙ ገውዙ አለ ቋራ፤

መንገዱ ቢጠፋ፣ እኔ ልምራ።)”

[ኅዳር 19፣ 1845 ዓ.ም – ጉራምባ]

.

* * * *

“አስረህ አንድ አትግደል፣ ደጃዝማች ማጠንቱ፤ 

ለጀብዱ እንደሆነ፣ ይበቃል ስምንቱ።”

[1820 ዓ.ም – ቋሚ ጨርቅ]

.

በዕውቀቱ ሥዩም

ሰኔ 2009 ዓ.ም

.

ምንጮች

ስለ አዝማሪ ጣፋጭ ሕይወት (1790ዎቹ-1845 ዓ.ም) ያሉን ቀጥተኛ ምንጮች ሁለት ብቻ ናቸው። ቀዳሚው፣ በአፄ ዮሐንስ ዘመን (1875 ዓ.ም) የቴዎድሮስ ታሪክን የጻፈው አለቃ ወልደማርያም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በንግሥት ዘውዲቱ ዘመን (1917 ዓ.ም) የጐጃምን ታሪክ የጻፈው አለቃ ተክለየሱስ ነው። ሁለቱም ስለ ጣፋጭ የጻፉት በጣም በጥቂቱ፣ ለዚያውም ባለፍ ገደም ነው። ጣፋጭም ለትውስታ የበቃው፣ አሳዛኝ እጣው ከአፄ ቴዎድሮስ ጋር ስለተቆራኘ መሆን አለበት።

ተሰማ ሀብተ ሚካኤል። (፲፱፻፶፩)። “ከሳቴ ብርሃን የዐማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 266፣ 821።

ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ (አለቃ)። [፲፱፻፲፯]። “የኢትዮጵያ ታሪክ” አርታዒ፤ ስርግው ገላው (2002 ዓ.ም)፤ ገጽ 94-102

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፴፮]። “የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ“፤ (9ኛ እትም፤ ገጽ ፮-፯)

ተክለጻድቅ መኩሪያ። [፲፱፻፹፩]። “ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት“፤ ገጽ 125-127።

ወልደማርያም (አለቃ)። [፲፰፻፸፭]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Mondon-Vidailhet, Cassimir (1904)

ዘነብ (አለቃ)። [፲፰፻፶፪]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Littmann, Enno (1902).

(ያልታወቀ ደራሲ)። [፲፰፻፸ዎቹ]። “የቴዎድሮስ ታሪክ” አርታዒ፤ Fusella, Luigi (1959).

ደስታ ተክለወልድ። (፲፱፻፷፪)። “ዐዲስ አማርኛ መዝገበ ቃላት“፤ ገጽ 169፣ 217።

Blanc, Henry (1868) “A Narrative of Captivity in Abyssinia“, p. 178.

Lejean, Guillaume (1865) “Théodore II: Le Nouvel Empire d’Abyssinie“.